ትንቢተ ኢሳይያስ ትርጓሜ

ምዕራፍ ፩

የትርጓሜ አመጣጥ፦

ቤተ ክርስቲያን ሦስት ዋና መገለጫዎች አሏት

ሐዋርያዊ ክህነት፤ (ከሐዋርያት ጀምሮ ሳይቋረጥ የመጣ ሢመተ ክህነት)

ሐዋርያዊ የአምልኮ ሥርዓት (የምሥጢራት አፈጻጸም)

ሐዋርያዊ ትምህርት ናቸው (እየተረጐሙ፣ ምሳሌ እየመሰሉ፣ እያመሠጠሩና እያብራሩ ማስተማር)

ደቀመዛሙርቱ ተርጉምልን ብለውት ጌታችን ምሳሌ ዘርዕን ተርጕሞላቸዋል። ማቴ ፲፫

ቅዱስ ጳውሎስ አጋርን የኦሪት፣ ሣራን የወንጌል፣ (ገላ ፬፥፳፩ – ፍ) ባሕረ ኤርትራን የጥምቀት፣ መናውን የሥጋ ወደሙ፣ ዐለቱን የክርስቶስ ምሳሌ አድርጎ ተርጕሟል። (፩ቆሮ ፲፥፩ – ፭)

በዕለተ ጰራቅሊጦስ ቅዱስ ጴጥሮስ የነቢዩ የኢዩኤልን ትንቢት ተርጕሞ ያስተማረበት መንገድ ከትርጓሜ ስልቶች አንዱ ነው።

በእስክንድርያና በአንጾኪያ ተከፍተው የነበሩት ትምህርት ቤቶች ትርጓሜን በማስፋፋት ረገድ ታላቅ አስተዋጽኦ ነበራቸው።

በ፫፻፳፭ በኒቅያ በ፫፻፹፩ በቍስጥንጥንያ በ፬፻፴፩ በኤፌሶን የተደረጉ ጉባኤያት ቅዱሳት መጻሕፍትን በመተንተንና ቀኖናዎችን በመደንገግ መሠረት ጥለዋል።

ተስዓቱ ቅዱሳን፤ ካልእ ሰላማ፣ ትርጓሜ እንዲሰፋ ካደረጉቱ ተጠቃሽ ናቸው።

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅና ቅዱስ ያሬድ ትርጓሜን በማስፋፋት ከሚታወቁ ሊቃውንት ትልቁን ቦታ ይይዛሉ።

በሰሙነ ሕማማት የሚነበበው ግብረ ሕማማት የሚሰጠው የትርጓሜ ሐተታ የትርጓሜያችንን አመጣጥና አሁን ያለበትን ሁናቴ ያሳያል።

በዓፄ ኢያሱ አድያም ሰገድ ትእዛዝ ሊቃውንተ ኢትዮጵያ ተሰባስበው ወጥ የሆነ በሁሉም ቤተ ጉባኤ የሚነገር ስልተ ትርጓሜ አዘጋጅተዋል። ምክንያቱም የአማርኛ ቋንቋ እያደገ በመሄዱ ለረጅም ጊዜ የቆየው የግእዝ በግእዝ ትርጓሜ ለሕዝቡ እንዳይከብድ ግእዙን መሠረት አድርጎ መልእክቱ በአማርኛ እንዲተላለፍ ስለተፈለገ ነው።

ዕጨጌ አባ ቃለ ዓዋዲ የግእዝ በግእዝ ትርጓሜና በጎጃም በተለይም በሞጣ አካባቢ ይነገር የነበረውን የላይ ቤት ትርጓሜ በመባል የሚታወቀውን የትርጓሜ ስልት መነሻ አድርገው የታች ቤት ትርጓሜ የሚባለውን መሠረት ጥለዋል።

ጉባኤያቱ አራት እንዲሆኑ ተወስኗል፤ ብሉይ ኪዳን፤ ሐዲስ ኪዳን፤ ሊቃውንት፤ ሕንፃ መነኮሳት።

ዕጨጌ ቃለ ዓዋዲ መምህረ ብሉይ፤

መምህር ሠርዌ ክርስቶስ መምህረ ሐዲስ፤

መምህር ክፍለ ዮሐንስ መምህረ ሊቃውንት፤

መምህር አብራንዮስ ሕንፃ መነኮሳት፤  

የእጨጌ ቃለ ዓዋዲ ደቀ መዝሙር በሆኑት በመምህር ኤስድሮስ ደግሞ ተጨማሪ ፫፻ የሚደርሱ መጻሕፍትን የማመሳከር ሥራ ተሠርቷል፤ ይህንን መነሻ አድርጎ የላይ ቤትና የታች ቤት ትርጓሜ የሚል ስያሜ የትርጓሜ መጠሪያ ሆኗል፤ አሁን አሁን በሰፊው የሚነገረው ለአቋቋም ትምህርት ሆኗል።

መምህር ወልደ ሩፋኤልና አለቃ ገብረ መድኅን የተባሉ ሊቃውንት የወንጌልን የአንድምታ ትርጓሜ መልክ በማስያዝ ስማቸው ተጠቃሽ ነው። መምህር ወልደ አብም በዚህ መስክ ሱታፌ ካደረጉ ሊቃውንት አንዱ ናቸው፤ ከመምህራቸው ዝግጅት በጥዕፍ የሚበልጡ ፮፻ መጻሕፍትን አመሳክረው የትርጓሜውን ስልት አጠናክረዉታልና።

በቅርቡ ደግሞ የኔታ ጥበቡ ከደብረ ሊባኖስ፣ የኔታ መንክር ከጎንደር፣ የኔታ ገብረ ሥላሴ ከአዲስ አበባና ሌሎችም የብሉይ ኪዳኑን ትርጓሜ በሁሉም ቤተ ጉባኤ በአንድ መልክ እንዲነገር ለማድረግ ሥራ ጀምረው እንደነበር ታውቋል።

የትርጓሜ አይነት፦

፩. ነጠላ ትርጓሜ

ምንም ማብራሪያ ሳይደረግበት ከቋንቋ ወደቋንቋ የሚደርግ ትርጓሜ ነጠላ ትርጓሜ ይባላል

“በልዋ ለዛቲ ቍንጽል – ያቺን ቀበሮ እንዲህ በሏት – Go, tell that fox” ሉቃ ፲፫፥፴፪፤

እንደ ኢትዮጵያ ከቋንቋ ወደ ቋንቋ ለተደረገው ነጠላ ትርጓሜ ሁለት ሐሳቦች አሉ፤

አንዱ በቀዳማዊ ምኒልክ ከዕብራይስጥ ወደ ግእዝ የተተረጐመው ትርጉም ሲሆን ሁለተኛው በበጥሊሞስ ዘመነ መንግሥት ከዕብራይስጥ ወደጽርዕ/ግሪክ ቀጥሎ ወደ ግእዝ የተተረጐመው ትርጉም ነው።

ከግእዝ ወደ አማርኛና ወደሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች መተርጐም የተጀመረው ባለፉት ፪፻ ዓመታት ውስጥ ነው፤ የመጀመሪያው የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ከ፲፰፻ እስከ ፲፰፻፲ በአባ አብርሃም ተተርጒሞ በ፲፰፻፴፪ በእንግሊዝ በመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር አሳታሚነት ታትሟል። አባ አብርሃም ጀምስ ብሩስ የተባለውን ተመራማሪ አማርኛ ቋንቋን መስተማራቸው ይነገርላቸዋል።

በ፲፰፻፺፩ በአናሲሞስ ነሲብ ወደ ኦሮምኛ ተተርጒሟል፤ ለጽሑፍ የተጠቀሙትም ፊደል የግእዙን ፊደል ነው። በኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ብዙ ቋንቋዎች እየተተረጐመ ነው።

በቅርብ ዓመታት መጽሐፈ ቅዳሴ ወደ ኦሮምኛ መተርጐሙ ይታወሳል፤ ሌሎችም መጻሕፍት እንዲሁ በተለያዩ ቋንቋዎች እየተተረጐሙ እንደሆነ ይታወቃል።  

፪. ምሥጢራዊ ትርጓሜ

ቍንጽል ማለት ቀበሮ ማለት ነው በምሥጢር ግን ቀበሮ የተባለው ሄሮድስ ነው።

አምላካችን ይህንን የተናገረው “ሄሮድስ ሊገድልህ ይፈልጋልና ከዚህ ውጣና ሂድ” ካሉት በኋላ ነውና።

ንሥትዎ ለዝንቱ ቤተ መቅደስ ወበሠሉስ ዕለት አነሥኦ…ወውእቱሰ በእንተ ቤተ ሥጋሁ ይቤሎሙ – ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት በሦስተኛው ቀን አነሣዋለሁ…እሱ ግን ስለሥጋው ቤት ይላቸው ነበር” የሚለው ገጸ ንባብ ያስከተለው ምሥጢር የጌታችንን ሞትና ትንሣኤ ነው ዮሐ ፪፥፲፱፤

ተስእሎ እምነቢይ ወተሠጥዎ እመንፈስ ቅዱስ የሚለውንም ለዚህ ማስረጃ አድርጎ መጥቀስ ይቻላል። ነቢዩ “እግዚኦ መኑ የኀድር ውስተ ጽላሎትከ ወመኑ ያጸልል ውስተ ደብረ መቅደስከ” ብሎ ሲጠይቅ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ “ዘየሐውር በንጹሕ ወይገብር ጽድቀ” ብሎ ይመልስለታል።

የትርጓሜ አንዱ ዓላማው የረቀቀውን እያጐላ የተሠወረውን እየገለጠ እውቀት ማስፋት፣ ምሥጢር ማጉላት ነውና።

፫ የአንድምታ/የአወራረድ ትርጓሜ

ገጸ ንባቡን መሠረት አድርጎ በማስረጃዎት እያጠናከረ በተለያዩ መጻሕፍት የተመዘገቡ ምሥጢራትን እያመሳከረ ሰፊ ሐተታ የሚሰጥ የትርጓሜ ስልት ነው። “ምሳሌውን ተርጕምልን አለው” እንዲል ማቴ ፲፭፥፲፭

ለምሳሌ፦ ሐመረ ኖኅ የእደ እግዚአብሔር፤ የእመቤታችን፤ የመስቀል፤ የጥምቀት፤ የቤተ ክርስቲያን፤ የሦስቱ ክፍለ ዘመን (የዘመነ አበው፤ የዘመነ ኦሪት፤ የዘመነ ሐዲስ) ምሳሌ ተብሎ ሰፊ ማብራሪያ ይሰጥበታል።  

ሁለት መለያ ምልክቶች አሉት። “አንድም የሚልና ቦ የሚል”።

ከስድስት ሺህ በላይ ገጽ ያለው የአይሁድ ትውፊታዊ ትርጓሜ ተብሎ የሚታወቀውና በሁለት ክፍል የተከፈለው (የኢየሩሳሌም እስትጉቡዕና የባቢሎን እስትጉቡዕ ተብሎ) ታልሙድ ሌላኛው የትርጓሜ አመጣጥና ስልቱ ከመነገርባቸው አንዱ ነው። የኢየሩሳሌም እስትጉቡዕ የሚባለውን አጥኚዎችና ተመራማሪዎች የበለጠ ቦታ ሲሰጡት አይሁድ ደግሞ የባቢሎኑን እስትጉቡዕ የበለጠ ያከብሩታል። ይህም ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ፪፻ ዓመት ጀምሮ ድኅረ ልደተ ክርስቶስ ፭፻ ዓመት ድረስ እንደተጻፈ በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ሊቃውንት አረጋግጠዋል።

ኊልቈ ልደተ አበውን ቀንሶ ቀናንሶ መሲሕ የሚወለድበት ዘመን ገን አንድ ሺህ አራት መቶ ይቀረዋል የሚለውም በዚህ ሊካተት ይችላል። የእኛ መተርጉማን ሊቃውንት ይህንን በተመለከተ የሚከተለውን ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ኦሪት አራት ጊዜ ተጽፏል

፩ ሙሴ የጻፈው፣ ይህ ኦሪት ዘሌዋውያን ተብሏል

፪ ሰባ ሊቃናት የጻፉት፣ ኦሪት ዘሊቃውንት/ዘሊቃናት ተብሏል። ይህም በጥሊሞስ ያጻፈው ነው

፫ ምናሴ ካህነ ሰማርያ የጻፈው፣ ስልምናሶር ፲ሩን ነገድ ማርኮ በሰማርያ አጀም ኮንታን የሚባል ጭፍራ ሠራ መቅሠፍት ይፈጽማቸው ጀመር በዚህ ሀገር ያዕቆብ አቡነ እግዚአብሔር አምላክነ የማይል አይኖርበትም አሉት ምናሴ የሚባል ካህነ ሰማርያን አስተምራቸው ብሎ ሰደደላቸው እሱ አስተምሮ ኦሪት ጻፈላቸው። ኦሪት ዘሳምራውያን ተብሏል።

፬ ኦሪተ አይሁድ ብጡል፣ አቡል ፈህር ይለዋል ምክሐ ዘመድ አበ ዘመድ ማለት ነው ዓመተ ቃይናንን ከዘጠኝ መቶ አራት መቶ ቀንሶ ጽፏል፤ ታልሙድ የሚለውን ሐሳብ ለማጠናከር የሚረዳን ይህ ኦሪተ አይሁድ ብጡል የተባለው ነው።  

ምክንያቱ ደግሞ፦  

እስጢፋኖስ ሱባኤ ትውልድ ዘሄኖክን ሱባኤ ዕለት ዘኤርምያስን አምጥቶ ዘመኑን ከነትውልዱ አስማምቶ ከመጻሕፍተ ነቢያት ምስክር አምጥቶ ስለረታቸው ነው በእስጢፋኖስ ትምህርት ተበሳጭተው እሱን በደንጊያ ወግረው ኊልቈ ልደተ አበውን ወደመቀነስ ሄዱ።

ከላይ እንደተገለጠው ዓመተ ቃይናን አወጡ ቦ ዘጠኝ መቶ የነበረውን ዓመተ ቃይናን አራት መቶ አደረጉ ኦሪተ ሌዋውያንን ለወጡ

ልደተ አበውንም ሲቀናንሱ እንደሚከተለው አድርገው ነው፤  

አዳም ሴትን በሁለት መቶ ሠላሳ ወለደ የሚለውን በመቶ ሠላሳ አሉ

ሴት ሄኖክን በሁለት መቶ አምስት የሚለውን በመቶ አምስት አሉ

እንዲህ እያደረጉ እስከ አብርሃም አምስት መቶ ዘመን አወጡ በአጠቃይ አንድ ሺህ አራት መቶ ዓመት ግድም ቀንሰዋል።

ለዚህ ነው “አይሁድ ገና ይወርዳል ይወለዳል የሚሉት አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም የወረደ የተወለደ፤ ተንባላት አላህ አይወርድም አይወለድም የሚሉት የወረደ የተወለደ የቃልን በሥጋ ሕማሙን እናምናለን” ተብሎ የሚታተተው።

መቅድም፦ ዘኢሳይያስ ነቢይ በረከተ አምላኩ የሃሉ ምስሌነ ለዓለመ ዓለም

ነቢዩ ኢሳይያስ አባቱ አሞጽ እናቱ ሶፍያ ይባላሉ። የነበረበት ዘመን ፰፻፹፰ እስከ ፯፻፵ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ነው። ዕረፍቱ መስከረም ስድስት ነው፤ “ወበዛቲ ዕለት አዕረፈ ዐቢይ ነቢይ ኢሳይያስ ወልደ አሞጽ – በዚች ቀን ታላቁ ነቢይ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ አረፈ” እንዲል መጽሐፈ ስንክሳር፤ በምናሴ ትእዛዝ በመጋዝ ተሰንጥቆ በኵላብ ተሰቅሎ ነው ሰማዕት የሆነው፤ መዋዕለ ትንቢቱ ፸ ዘመን ነው በመጽሐፈ ስንክሳር እንደተገለጠው ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ፱፻፲፫ ዓመት ድረስ ነበር፤ (የዘመን አቈጣጠሩ ላይ የተለያዩ ጸሐፍት የተለያየ ቁጥር ተጠቅመዋል፤ የቀረበውን መጠቀም የአንባቢ ድርሻ ይሆናል፤ ሃይማኖት ስላልሆነ ሊያከራክር አይገባም)

ከአራቱ ዐበይት ነቢያት ከኤርምያስ፣ ከሕዝቅኤልና ከዳንኤል አንዱ ነው፤ ዐቢይ የተባለውም በዕድሜው ሳይሆን በእውቀቱ፣ በድርሰቱና በመዐርጉ ነው።

የትርጓሜ ሊቃውንት “ልዑለ ቃል” የሚል መለያ ስም ሰጥተዉታል፤ ይህም የተገኘው ከቅዱስ ያሬድ ነው፤ “ተነበየ ኢሳይያስ ልዑለ ቃል እምነቢያት – ከነቢያት ልዑለ ቃል ኢሳይያስ ትንቢት ተናገረ” እንዳለ መዋሥዕት በተሰኘው ድርሰቱ።  

መጽሐፈ ትንቢቱ ፷፮ ምዕራፎች አሉት፤ ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ባለረጅም ምዕራፍ መጽሐፍ ነው። በመጽሐፈ ነገሥት ካልዕ ከምዕራፍ ፲፭ እስከ ፳፩ እና በዜና መዋዕል ካልዕ ከምዕራፍ ፳፮ እስከ ፴፫ ድረስ በመጽሐፈ ትንቢቱ ጋር የሚመሳል ተግሣጽ፣ ትምህርትና ታሪክ ይገኛል።

መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” እያለ ሲያስተምር ለማንነቱ ማረጋገጫ አድርጎ የጠቀሰው የነቢዩን የኢሳይያስን ቃለ ትንቢት ነው ማቴ ፫፥፪፤ ዮሐ ፩፥፳፫፤

ጌታችን የኢሳይያስን ትንቢት እየጠቀሰ ያስተምር ነበር ማቴ ፲፫፥፲፬፤ ፲፭፥፯፤

ወንጌላውያን በወንጌላቸው ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክታቱ የነቢዩ የኢሳይያስን መጽሐፈ ትንቢት እየጠቀሱ አስተምረዋል ጽፈዋልም። ለዚህ ብዙ ማስረጃ መጥቀስ ቢቻልም የሚከተሉት ጥቅሶች በቂ ግንዛቤ ይሰጣሉ ማቴ ፲፪፥፲፯፤ ሮሜ ፱፥፳፯፤

ኢሳይያስ ማለት ቅቡዕ እምቅብዐ ትንቢት ማለት ነው፤ ትንቢትን የሚገልጥ ሥጋዌን የሚያስፈጽም መንፈስ ቅዱስ አድሮበታልና ቅቡዕ እምቅብዐ ትንቢት ተባለ።

አንድም መድኃኒት ማለት ነው፤ ኢያሱ፣ ሆሴዕ፣ ኢየሱስ ማለት መድኃኒት ማለት እንደሆነ፤

መድኃኒት መባሉም እንደ ኢያሱ ወልደ ነዌ በአጭር ታጥቆ ዘገር ነቅንቆ ጋሻ ነጥቆ እስራኤልን አድኖ አማሌቃውያንን አጥፍቶ አይደለም፤

እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ ሕማማተ መስቀልን ታግሦ አጋንንትን አጥፍቶ ምእመናንን አድኖ አይደለም፤ አባት እናቱ ደጋጎች ናቸውና በትንቢቱ በትምህርቱ እንዲያድን አውቀው ኢሳይያስ ብለዉታል።

ሲያወጡለትም ዛሬ በአርባ በሰማንያ ቀን እኛ ከቤተ እግዚአብሔር ገብተን አጥምቀን ስም እንድናወጣ በስምንት ቀን ከቤተ ግዝረት ገብተው ነው።

አንድም ደጋግ ሰዎችን ማን እንበለው ብለው ጠይቀው በትንቢቱ በትምህርቱ እንዲያድን አውቀው ኢሳይያስ ብለዉታል።

ይህም ኢሳይያስ በእስራኤል ስለሦስት፣ በአሕዛብ ስለአራት ነገር ተናግሯል፤ በእስራኤል ስለሦት ነገር እንደምን ነው ቢሉ? በደብረ ሲና የተሠራላቸውን ሕግ ቢያፈርሱ፦ በሀገራቸው ሳሉ አባር ቸነፈር እንዲመጣባቸው፤ ጼዋዌ እንዲደረግባቸው፤ ሚጠት እንዲደርግላቸው ተናግሯል። 

ለዚህም ለሦስቱ ሥጋዊ መከራ ሦስት አምሳል መርገፍ ይሰጧል፤ እንደ አባር ቸነፈር ርኂቅ እምእግዚአብሔር አግኝቷቸዋል፤ “ሞታ ለነፍስ ርኂቅ እምእግዚአብሔር – የነፍስ ሞቷ ከእግዚአብሔር መራቅ ነው” እንዲል

በአንጻሩ “ሰብእ ይመውት በመንፈሱ እስመ ሕይወታ ለነፍስ ቀሪብ ኀበ እግዚአብሔር ሕያው – ሰው በመንፈሱ ይሞታል የነፍስ ሕይወቷ ወደ ሕያው እግዚአብሔር መቅረብ ነውና” ይላል ፊልክስዩስ ተስእሎ ፶፬፤

እንደ ጼዋዌ ሥጋ ጼዋዌ ነፍስ ተደርጎባቸዋል፤

እንደ ሚጠተ ሥጋ ሚጠተ ነፍስ ተደርጎላቸዋል፤

አባር፣ ቸነፈርና ጼዋዌስ አንድ ወገን ናቸው ብሎ ሦስተኛ ሥጋዌ ወልደ እግዚአብሔርን ተናግሯል ይወርዳል ይወለዳል ብሎ።

በአሕዛብ ስለ አራት ተናግሯል፤ ይህስ እንደምን ነው ቢሉ

አሕዛብ አምላከ ሕዝብ ነው እንጂ አምላከ አሕዛብ አይደለም ብለዋል፤ ግድ አምላከ አሕዛብ ወሕዝብ እንደሆነ ተናግሯል፤ የናቡከደነጾር ሕልም፤ የነነዌ ስብከትና ድኅነት ማስረጃ ነው።

ቅዱስ ጳውሎስም “ቦኑ ለባሕቲቶሙ ለአይሁድ እግዚአብሔር አኮኑ ለሕዝብኒ ወለአሕዛብኒ – በውኑ እግዚአብሔር ለአይሁድ ለብቻቸው ነውን ለሕዝብም ለአሕዛም አይደለምን” ብሏል ሮሜ ፫፥፳፱፤

ሁለተኛ በደበያት እንዲጠፉ ተናግሮባቸዋል ማለት በፍዳ እንዲጠፉ ተናግሮባቸዋል፤ እስራኤልን እያጋደሙ ኮር ይወጡባቸው ፈረፈር ይሻገሩባቸው ነበርና በዚህ ፍዳ ይጠፋሉ ሲል ነው። “ድንኒ ወንትዐዶኪ – አጐንብሺ እንሻገርብሽ” እንዲል ኢሳ ፶፩፥፳፫፤ ቦ አንድ ሁነው ይጠፋሉ ሲል ነው ደበያት ማለት ደቦ ማለት ነውና። 

ሦስተኛ አፍርሆ ነው እስራኤል በአሕዛብ መከራ ሲያጸናባቸው አይተው በአሕዛብ እንዲህ መከራ ያጸናባቸው በደብረ ሲና የተሠራልንን ሕግ ብናፈርስማ መከራውን እንዴት ያጸናብን ይሆን እያሉ ይፈራሉና።

አራተኛ ትእምርት ነው፤ ነቢይ ሕዝቡም አሕዛቡም ይጠፋሉ ብሎ ይናገራል ኋላ እስራኤል አሕዛብ ሲጠፉ አይተው ነቢይ የተናገረው ነገር አልቀረም አሕዛብ ጠፉ እኛም እንጠፋ ይሆናል ብለው ምልክት ያደርጓቸዋልና።

አፍርሆና ትእምርትስ አንድ ወገን ነው ብሎ በነቢይ በካህን አድሮ ሳያናግር እንዳያጠፈ ተናግሯል “ሠረይነ ሰብአ ወኢያሕየውነ ፈወስናሃ ለባቢሎን ወኢተፈወሰት ባቢሎን -ሰውን አስተማርን ማዳን አልተቻለንም ባቢሎንን ፈወስናት አልተፈወሰችም” ኤር ፶፩፥፱፤ ወኮነ ጽድቅነ ከመ ፀርቀ ትክቶ – ጽድቃችን እንደመርገም ጨርቅ ሆነ” እንዲል ኢሳ ፷፬፥፮፤

ይህም ተጽፎ ሲነበብ ሲተረጐም ከነቢያት እስከ ሐዋርያት ደረሰ ሐዋርያት ለቀሌምንጦስ መጻሕፍትን ቆጥረው ሲያስረክቡ አሐዱ መጽሐፈ ኢሳይያስ ብለው ቆጥረው ሰጥተዉታል። ይህም መጻፉ ለከንቱ አይደለም እኛ ልንመከርበት ልንገሠጽበት ነው “ወኵሉ ዘተጽሕፈ ለተግሣጸ ዚአነ ተጽሕፈ ከመ በትዕግሥትነ ወበተወክሎ መጻሕፍት ንርከብ ተስፋነ – የተጻፈው ሁሉ እኛ ልንመከርበት ልንገሠጽበት ተጻፈ በትዕግሥታችን መጻሕፍትን በማመናችን ተስፋችንን እናገኝ ዘንድ” እንዲል ሮሜ ፲፭፥፬፤

ሠለስቱ ምዕት ለመጻሕፍት ሁሉ አርእስት ሲሰጡ ይህን አርእስት ሰጥተዋል እሱ ነገሩን ራእይ ዘርእየ ብሎ ያመጣዋል።

ራእይ ዘርእየ ኢሳይያስ ወልደ አሞጽ

– ትንቢት ዘተነበየ ነገር ዘተናገረ ሲል ነው፤ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ያየው ራእይ የተናገረው ነገር ያስተማረው ትምህርት ይህ ነው።

ዘርእየ በእንተ ይሁዳ

– ይህ በእንተ ያለስፍራው የገባ ነው የክፉ ነው ሰዎቹ እንዲማረኩ፤

ወበእንተ ኢየሩሳሌም – ሀገሪቱ እንድትጠፋ ቦ ጥቃቅኑ አህጉር መዲናይቱ ኢየሩሳሌም እንድትጠፋ አይቶ የተናገረው ነገር ይህ ነው።  

በመዋዕለ ዖዝያን ወኢዮአታም ወአካዝ ወሕዝቅያስ እለ ነግሡ በይሁዳ

– እለ ነግሡ ለይሁዳ ነገሥታት ዘይሁዳ ነገሥታተ ይሁዳ ይላል፤ በይሁዳ በነገሡ ነገሥታት በእነዚህ ዘመን አይቶ የተናገረው ነገር ይህ ነው፤ እነዚህን ለምን ለይቶ አነሣቸው ቢሉ በእነዚህ ዘመን ብመክራቸው ባስተምራቸው አንሰማም ብለው ጠፉ ለማለት፤ ቦ አሁን ወደፊት እየተረተረ የሚያመጣቸው ነውና እንደ አርእስት አነሣቸው።  

ስማዕ ሰማይ

– እስከዚህ አርእስት ነው፤ ነገሩን ከዚህ ይጀምራል፤ ሰማይ የእስራኤልን ነገር ስማ ማለት ዝናም ለዘር ጠል ለመከር አትስጥ።

ወአጽምዒ ምድር – ምድርም የእስራኤልን ነገር አድምጪ ማለት የዘሩብሽን አታብቅዪ የተከሉብሽን አታጽድቂ።  

ቦ ሰማይ ልዑላኑ ምድር ትሑታኑ የእስራኤልን ነገር ስሙ።

ቦ ሰማይ መላእክት ምድር ደቂቀ አዳም የእስራኤልን ነገር ስሙ፤ እስራኤልን በተጣላበት ወራት በጎ በጎዎችን አትማልዱኝ ይላቸዋልና።

ቦ ሰማይ የእስራኤልን ነገር ስማ ምድርም የሰማይን ምስክርነት አድምጪ፤ በተጣላበት ወራት ሰማይን ዝናም ለዘር ጠል ለመከር አትስጥ ይለዋል ይህን ይነሣል።

ምድርንም የዘሩብሽን አታብቅዪ የተከሉብሽን አታጽድቂ ይላታል ይህን ትነሣለችና እንዲህ አለ።

ቦ ሰማይ የአይሁድን ነገር ስማ፤

ምድርም የአይሁድን ነገር አድምጪ፤ ቦ ሰማይ ልዑላኑ ምድር ትሑታኑ፤ ቦ ሰማይ መላእክት ምድር ደቂቀ አዳም የአይሁድን ነገር ስሙ፤ በተጣላበት ወር ደጋጎቹን አትማልዱ ይላቸዋልና።

ዐይኑ ዐ ነው ቢሉ ስማ፤ አልፋው አ ነው ቢሉ መስክር ማለት ነው፤ አንድም ያዘዋውሩታል ዐይኑ ዐ ነው ቢሉ መስክር አልፋ አ ነው ስማ ማለት ነው።

አንድም ስማዕ ሰማይ – አብ የክርስቶስን ነገር መስክር ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ብለህ፤

ወአጽምዒ ምድር – ዮሐንስ የክርስቶስን ነገር መስክር፤ ወአነ ሰማዕቱ ከመ ዝንቱ ውእቱ ወልደ እግዚብሔር – የእግዚአብሔር ልጁ እንደሆነ ምስክሩ እኔ ነኝ ብለህ ዮሐ ፩፥፴፬፤

እስመ እግዚአብሔር ነበበ ከመዝ – እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናግሯልና፤

ወይቤ ውሉደ ወለድኩ – በሕገ ልቡና ልጅ ወለድሁ ብሏልና።

ወአልሐቁ – በሕግ መጽሐፋዊ አሳደግሁ ብሏልና።

አንድም በፍቅር በሃይማኖት ልጅ ወለድሁ ብሏልና፤ በመና በደመና አሳደግሁ ብሏልና።

አንድም በትንቢት ልጅ ወለድሁ፤ በሱባኤ አሳደግሁ ማለት ትንቢት እያናገርሁ ሱባኤ እያስቆጠርሁ አሳደግሁ።

እሙንቱሰ ዐለዉኒ – እነሱ ካዱኝ ከዱኝ ወነጀሉኝ፤ ቦ ኃጢአት ሠርትው ጣዖት አምልከው ወነጀሉኝ።

አንድም እሩቅ ብእሲ ወልደ ዮሴፍ አሉኝ።

ላህምኒ አእመረ ዘአጥረዮ – ዘቀነዮ ዘኰነኖ ሲል ነው ላም ስንኳ የገዛውን ጌታውን ያውቃል።

ወአድግኒ ምቅማሖ ወቤተ እግዚኡ – አህያም ገፈራ/ገለባ የሚቅምበት የጌታውን ቤት ያውቃል፤ አንድ ገዝ የሆነ እንደሆነ ከዋለበት ሲመጣ ከብዙ መንጋ ተለይቶ ወደጌታው ቤት ይሄዳልና።

ቦ ላህምኒ አእመረ፤ ዘአጥረዮ ዘፈጠሮ ሲል ነው ላም ስንኳ የፈጠረውን ጌታውን ያውቃል ቦ ለሰው ጥሪት አድርጎ የሰጠውን ያውቃል፤ አህያም ገፈራ የሚቅምበትን የጊታውን ቤት ያውቃል፤ ቤተ እግዚኡ ያለው ባለቤት የሌለው ዝርዝር ነው ሀገሩ እንዲህ ሆነ ጌታው እንዲህ አደረጉ እንደ ማለት ያለ ነው።

እመቤታችን ለመቈጠር በወጣች ጊዜ ከባለላሙ ከባለአህያው ቤት ደርሳ ጌታን ወለደች ከዚያ አግኝተው አሟሙቀዉታል ወአስተማቅዎ እስትንፋሰ አድግ ወላህም እንዲል።

አንድም ቤት ያለው አምቦውን ነው እመቤታችን ለመቈጠር በወጣች ጊዜ ከዚህ ደረሰች ዮሴፍ ጎጆ ቢሉ ሠርቶላት ዳስ ቢሉ ጥሎላት ከዚያ ወለደችው አምቦውን ሲሉ መጥተው አሟሙቀዉታል።

አንድም ቤት ያለው የነዳዊት የነሰሎሞን የነኢዮስያስን ቤት ነው የቀድሞ ነገሥታት ቤታቸውን በጨው ማሸጊያ/መሽጋ ይሠሩት ነበር በጼዋዌ ፈርሶ እንስሳት እየጋጡ አጐድጉደዉታል እመቤታችን ለመቈጠር በወጣች ጊዜ ከዚያ ደረሰች ዮሴፍ ጎጆ ቢሉ ሠርቶላት ዳስ ቢሉ ጥሎላት ከዚያ ወለደችው ከዚያ አግኝተው አሟሙቀዉታል።

አንድም ቤት ያለው ጎልን ነው የጌታውን ቤት ጎልን አወቀ።

እስራኤልሰ ኢያእመሩኒ ወሕዝብየኒ ኢጠየቁኒ – ዐሥሩ ነገድ ሁለቱ ነገድ ግን አላወቁኝም አልተረዱኝም፤ እነሱ ከላሙ ከአህያው ብሰው እኔን ከባለላሙ ከባለአህያው አሣንሰው።

አንድም ሐና ቀያፋ አልተረዱኝም አላወቁኝም።  

አለማወቃቸው ብቻ ሳይሆን ሌላውም ሰው እንዳያምንበት ለማድረግ የሄዱበት ርቀት የክፋታቸውን ዳርቻ ያሳያል “እስመ አዘዙ አይሁድ ለእመቦ ዘአምነ ቦቱ ከመ ውእቱ ክርስቶስ ይሰደድ እምኵራብ – እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ ያመነበት ቢኖር ከምኵራብ እንዲሰደድ አዘው ነበርና” የሚለው ቃለ ወንጌል ይህንን በግልጽ ያስረዳል ዮሐ ፱፥፳፪፤

አሌ ሎ ለሕዝብ ኃጥእ ዘምሉዕ ዓመፃ – ዓመፅን ለተመላ ለኃጥእ ወገን ወዮለት። “እንተ አፍአክሙ ትጼደቁ ለዐይነ ሰብእ ወእንተ ውስጥክሙሰ ምሉዓን አንትሙ ዓመፃ ወሀዪደ ወአድልዎ – በውጭ ለሰው ጻድቃን ትመስላላችሁ በውስጣችሁ ግን ዓመፅን ግብዝነትን ቅሚያንም የተመላችሁ ናችሁ” ማቴ ፳፫፥፳፰፤  

ዘርዕ እኩያን – አዝርዕተ እኩያን ሲል ነው ለክፉዎች ልጆች ወዮላቸው፤ ቦ እንዳለ ይሆናል ክፉ ለሆኑ ልጆች ወዮላቸው። “ለሊክሙ ተአምኑ ከመ ደቂቆሙ አንትሙ ለቀተልተ ነቢያት – የነቢያት ገዳዮች ልጆች መሆናችሁን እናንተ ራሳችሁ ትመሰክራላችሁ” ማቴ ፳፫፥፴፩፤

ወውሉድ ጽልሕዋን – ውሉደ ጽልሕዋን ሲል ነው ለከዳተኞች ልጆች ወዮላቸው፤ አንድም እንዳለ ይሆናል ከዳተኛ ለሆኑ ልጆች ወዮላቸው። “ትውልድ ዕሉት ዓማፂት ወዘማዊት ትእምርተ ተኀሥሥ ወትእምርትሰ ኢይትወሀባ ዘእንበለ ትእምርተ ዮናስ ነቢይ – ከዳተኛ ዓመፀኛና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ትሻለች ከነቢዩ ከዮናስ ምልክት በቀር ሌላ ምልክት አይሰጣትም” ማቴ ፲፪፥፴፱፤

እፎ ኀደግምዎ ለእግዚአብሔር – እግዚአብሔርን በሕግ በአምልኮት እንዴት ተዋችሁት ተዋችሁት እንዴት ትተዉት?

ወአመዐዕክምዎ ለቅዱሰ እስራኤል – ጽንዐ እስራኤል ክብረ እስራኤል እግዚአብሔርን እንዴት አሳዘናችሁት ታሳዝኑት እንዴት ታሳዝኑት?

እፎ እንከ ትቈስሉ እንዘ ትዌስኩ ኃጢአተ በዲበ ኃጢአት – በኃጢአት ላይ ኃጢአት እየጨመራችሁ በመከራ ላይ መከራ እንዴት ትቀበላላችሁ?

ምንተ እንከ ንብል ንግበርኑ ኃጢአተ ከመ ይፈድፍድ ጸጋሁ ለእግዚአብሔር ሐሰ አኮኑ ወዳእነ ሞትነ እምኃጢአትነ እፎ እንከ ንክል ሐዪወ ባቲ – እንግዲህ ምን እንላለን የእግዚአብሔር ጸጋ እንዲበዛ ኃጢአት እንሥራን? አይደለም ከኃጢአታችን የተለየን እኛ ዳግመኛ በእርሷ ጸንተን መኖር እንችላለን?” ሮሜ ፮፥፩፤

ኵሉ ርእስ ለሕማም – ይከውን ያለበት ነው ካልተመለሳችሁ የሰው ሁሉ ራስ ለመገጠብ ይሆናል ትብትብ ምንጣፍ በመሸከም፤

ወኵሉ ልብ ለኀዘን – የሰው ሁሉ ልብ ለኀዘን ይሆናል፤

ቦ ኵሉ ርእስ – ንጉሡ ለመከራ ይሆናል ርእስ አለው ከሁሉ በላይ ነውና ቦ ራስ በጠጉር ተከቦ እንዲኖር ንጉሡም በሠራዊት ተከቦ ይኖራልና። የጥበብ ሰው ሰሎሞንም “ኃይሉ ወክብሩ ለንጉሥ ብዝኀ ሠራዊት – የንጉሥ ኃይሉና ክብሩ የሠራዊት ብዛት ነው” ብሏል ምሳ ፲፬፥፳፰።

ወኵሉ ልብ – ሊቀ ካህናቱ ለኀዘን ይሆናል ልብ አለው አለባዊ ነውና ቦ የልቡን ምሥጢር አውጥቶ ይናገራልና። ልብ ዕረፍት የለውም የደም የሐሳብ ይርፈቃድ የእውቀት ምንጭ ነው። “ተዘከሩ ከመ ሠለስተ ዓመተ ኢነትገ አንብዕየ ሌሊተ ወመዓልተ እንዘ እሜህረክሙ – ሳስተምራችሁ ሦስት ዓመት ዕንባየ እንዳልተቋረጠ አስቡ” እንዲል ግብ ፳፥፴፩፤

የጥበብ ሰው ሰሎሞንም “ሀበኒ ወልድየ ልበከ – ልጄ ልብህን ስጠኝ” ያለው ልብ የሁሉም ነገር ማዕከል ስለሆነ ነው። ምሳ ፳፫፥፳፭፤

ካህናት አዕይንት ይባላሉ፤ ልብ፣ ልቡና፣ አእምሮ እነዚህ ሦስቱ በዐይን ይመሰላሉ፤ ልብ በጥቁሩ፣ ልቡና በብሌኑ፣ አእምሮ በብርሃኑ፤ ቦ አዛውሮ ልብ በነጩ፣ ልቡና በጥቁሩ፣ አእምሮ በብሌኑ ይመሰላል። ቦ ልዑላኑ ትሑታኑ ለኀዘን ይሆናሉ።

በተመሳሳይ ሁኔታ “ልብ እምከመ ትትፌሣሕ ትበርህ ገጽ ወእመሰ ተኀዝን ትዴምን – ልብ ደስ ካላት ፊት ትበራለች ብታዝን ግን ትጠቊራለች” ተብሎ ተገልጧል ምሳ ፲፭፥፲፫፤ ይህም የካህናት መንፈሳዊ ደስታ የሕዝብ ደስታ ኀዘናቸውም የሕዝብ መሆኑን ያሳያል።

ቦ ኵሉ ርእስ – ክርስቶስ ለሕማም ይሆናል ንሕነ አባል ወውእቱ ርእስ – እኛ ሕዋስ ነን እሱ ደግሞ ራስ እንዲል ድርሳን ዘዮሐስን አፈወርቅ ፮፥፹፱፤  

ቅዱስ ጳውሎስም “እስመ ብእሲ ርእሳ ለብእሲት ከመ ክርስቶስ ርእሳ ለቤተ ክርስቲያን – ክርስቶስ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደሆነ ባል የሚስቱ ራስ ነውና” ብሏል ኤፌ ፭፥፳፫፤

ወኵሉ ልብ – የሰው ሁሉ ልብ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ለኀዘን ይሆናል፤ በመንጸፈ ደይን ወድቆ በእግረ አጋንንት ተጠቅጥቆ ይኖር ነበርና።

እምእግር እስከ ርእስ ዘኢኮነ ቊስለ – ከእግር ጀምሮ እስከ ራስ ድረስ ያልቈሰለ የለም፤ ራሳቸው ትብትብ ምንጣፍ በመሸከም ይመለጣል እግራቸውን እሾሁ እንቅፋቱ ያቈስለዋል የቀረ ሰውነታቸውን ለፈለማ እያሉ ይወጓቸዋልና።

ወኢኮነ ፍቅዐተ – ያልተገመሰ የለም። 

ወኢኮነ ጽልዐ ዘይመግል – የሚመግል ቊስል ባይደለ ቊስል ያልቈሰለ የለም።

ወአልቦ ከመ ይጠይዕዎ ሥራየ ወኢይፀምምዎ[1] ወኢይቀብዕዎ – “ወ” ን “ዘ” አልቦን አኮ ሲል ነው፤ ይቀብዕዎ ወይፀምምዎ ይላል መድኃኒት ቀብቶ የሚያሽሩት ቊስል ባይደለ ቊስል ያልቈሰለ የለም አለ ማርከው ወስደው አያሳርፏቸውምና።

ቦ እንዳለ ይሆናል ቊስሉ ሲሽር ለምፅ ይሆናል ያንን የሚያድን መድኃኒት ይቀቡታልና።

ቦ ከእግር እስከ ራስ የዘመድ ቊስል ባይደለ በባዕድ ቊስል ያልቆሰለ የለም።

የዘመድ ግምሳት ባይደለ በባዕድ ግምሳት ያልተገመሰ የለም።

የሚመግል የዘመድ ቊስል ባይደለ ቊስል ያልቈሰለ የለም።

የዘመድ ቊስል የሆነ እንደሆነ ቀቅ[2] ተፍቶ አካክሶ ያሽሩታል ለእስራኤል ግን ይህን ሁሉ የሚያደርግላቸው የለምና። ቦ የዘመድ ቊስል የሆነ እንደሆነ ፀቡን አስክሰው ያስታርቁታል ቊስሉን መድኃኒት ቀብተው ያድኑታል እነዚህን ግን ወግተው ገምሰው ጥለዋቸው ይሄዳሉ ይህን ሁሉ አያደርጉላቸውምና።

ቦ ከቋሚ ከለጓሚ ጀምሮ እስከ ንጉሡ ድረስ አፍአዊ ባይደለ በውስጣዊ ቊስል ያልቈሰለ የለም። ምሥጢሩ ኀዘን ጼዋዌ ነው።

ቦ ከሰባ ዘመን አስቀድሞ መድኃኒት ሚጠትን ሰጥቶ የሚያሽሩት አፍአዊ ቊስል ያይደለ በውሳጣዊ ቊልስ ያልቈሰለ የለም።

ቦ ከምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን አስቀድሞ በማያድኑት ቊስለ ነፍስ ያልቈሰለ የለም።

ምድርክሙኒ በድወ – ትከውን ያለበት ነው ሀገራችሁ ምድረ በዳ ትሆናለች ቦ እንዳለ ይሆናል ሀገራችሁ ምድረ በዳ ሆነ።

ወአህጉሪክሙኒ ውእያ በእሳት – ሀገራችሁ በእሳት ተቃጠለ።

ለበሐውርቲክሙኒ ፀር ይበልዖ በቅድሜክሙ – ሀገራችሁን እያያችሁ ስልምናሶር ናቡከደነፆር ያጠፉታል ሀገር እያዩት ሲጠፋ ያሳዝናልና በቅድሜክሙ አለ።

ቦ ዘበቅድሜክሙ ይላል ስልምናሶር በፊታችሁ ያጠፋዋል።

ያማስኖ ወያመዘብሮ ፀር – ስልምናሶር ናቡከደነፆር ፈጽሞ ያጠፋዋል ቦ ያማስኖ ወያመዘብሮ ነኪር ልዩ ጠላት ስልምናሶር ናቡከደነፆር ያጠፋዋል። ቦ ባዕድ ጠላት ያጠፋዋል የዘመድ ጠላት የሆነ እንደሆነ የዓመት ልብስ የዕለት ጉርስ ይተዋል የባዕድ ጠላት ግን አይተውምና።

ወትትኀደግ ወለተ ጽዮን ከመ ልገተ ዐቃቤ ቀምሕ – የጽዮን ልጅ እንደ ፍሬ ጠባቂ ጎጆ ትጠፋለች፤ ፍሬ ጠባቂ ፍሬውን ለቅሞ ጎጆውን አፍርሶ እንዲሄድ ሰዎቹን ማርከው ገንዘባቸውን ዘርፈው ሀገራቸውን ተኩሰው ሄደዋልና።  

ወለተ ጽዮን ያላት መላ ቤተ እስራኤልን ነው፤ ልጅ አምሐራ ልጅ ጎጃም ልጅ ትግሬ እንዲሉ። ቦ ጽዮን ያላት የዳዊትን ከተማ ነው፤ ትቀድማለችና። ወለት ያላት የሰሎሞንን ከተማ ነው፤ በኋላ ናትና። ቦ ጽዮን ያላት የሰሎሞን ከተማ ናት፤ ትበልጣለችና። ወለት ያላት የዳዊት ከተማ ናት፤ ታንሳለችና። ቦ ወለተ ጽዮን ባለው ወለተ ሕግ ይላል ሕግ የምትጠብቅ ምዕመን ሲል።

ወከመ ዳሕሰ[3] ዐቃቤ ወይን – እንደ ወይን ጠባቂ ጎጆ ትጠፋለች፤ ቦ ወይኑን ከመውደቅ እንደሚጠብቀው እንደዳሱ ትጠፋለች፤ በክረምት ግዘፍ እንዲነሣ ብለው ከመሬት ጥለዉት ይከርማል ኋላ በበጋ ያነሡታልና። ቦ ፍሬውን ከመርገፍ እንደሚጠብቀው እንደዘለላው ትሆናለች።  

ወከመ ሀገር ኅፅርት – በጦር ታጥራ እንደነበረች፤

ቅትልት – እስራኤል እንደወጓት፤

ቅጽርት – ሰባት ቅጽር እንደነበራት፤

ንሕልት – እንደፈረች እንደ ኢያሪኮ ትሆናለች።  

ወሶበ አኮ እግዚአብሔር እግዚእ ፀባዖት ዘአትረፈ ለነ ዘርዐ – አሸናፊ እግዚአብሔር ዐሥሩን ሁለቱን ነገድ አስማርኮ ትሩፋንን ያስቀረልን ባይሆን፤

ከመ ሰዶም እምኮነ – እንደ ሰዶም በሆን፤

ወከመ ገሞራ እመሰልነ – ገሞራንም በመሰልን ነበር፤ እነዚያ ምክንያት አጥተው እንደጠፉ እኛም ዘር ምክንያት አጥተን በጠፋን ነበር።

ቦ አሸናፊ እግዚአብሔር ዐበይትን ነቢያትን አሳልፎ ደቂቅ ነቢያትን፣ ደቂቅ ነቢያትን አሳልፎ ካህናት መምህራንን ያስቀረልን ባይሆን እንደሰዶም በሆን ገሞራንም በመሰልን ነበር፤ እነዚያ የሚመክራቸው የሚያስተምራቸው አጥተው እንደጠፉ እኛም የሚመክረን የሚያስተምረን አጥተን በጠፋን ነበር።

ቦ አሸናፊ እግዚአብሔር ዐበይትን ነቢያትን ደቂቅ ነቢያትን ካህናት መምህራን አሳልፎ ሐውርያትን ሰባ አርድእትን ቅዱሳት አንስትን ከክሕደት ከእምቢታ ያስቀረልን ባይሆን እንደሰዶም በሆን ገሞራንም በመሰልን ነበር፤ እነዚያ መምር አብነት አጥተው እንደጠፉ እኛም መምር አብነት አጥተን በጠፋን ነበር።

ቦ አሸናፊ እግዚአብሔር እመቤታችንን ከመርገመ ሥጋ ከመርገመ ነፍስ የጠበቀልን ባይሆን እንደሰዶም በሆንን ገሞራንም በመሰልን ነበር፤ እነዚያ የነፍስ አማላጅ አጥተው በነፍስ እንደተጎዱ እኛም የነፍስ አማላጅ አጥተን በነፍስ በተጎዳን ነበር።

ስምዑ ቃለ እግዚአብሔር መላእክተ ሰዶም – የሰዶም አለቆች የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ ከመ ሰዶም እምኮነ ብሎ ነበርና።

ወአጽምዑ ሕገ እግዚአብሔር ሕዝበ ገሞራ – የገሞራ ወገኖች የእግዚአብሔርን ሕግ ስሙ፤ ወከመ ገሞራ እመሰልነ ብሎ ነበርና። መላእክተ ሰዶም ሕበ ገሞራ ማለቱ የትውልድ አይደለም የግብር ነው።

ለምንት ሊተ ብዝኀ መሥዋዕቲክሙ ይቤ እግዚአብሔር – መሥዋዕት እያቀረብንልህ መላእክተ ሰዶም ሕዝበ ገሞራ ትለናለህን ትሉኝ እንደሆነ በኃጢአት ሳላችሁ የምታቀርቡት የመሥዋዕቱ ብዛት ለእኔ ምኔ ነው?

ጽጉብ አነ እመሥዋዕተ ሐራጊት ወስብሐ አባግዕ – የጊደሩን የበጉን መሥዋዕት የጠገብሁ ነኝ ማለት የበጎ የበጎዎችን ሰዎች መሥዋዕት የጠገብሁ ነኝ።

ቦ ሐራጊት የሙሴ የአሮንን

አልሕምት የዳዊት የሰሎሞንን

አባግዕ የኢዮአስን መሥዋዕት የጠገብሁ ነኝ፤ ኢዮስያስ ለፋሲካ እልፍ አባግዕ ሠውቷልና።

ዘይኄይስ ያለበት ነው ከዚህ ሁሉ የሚበልጥ ቅዳሴ መላእክትን የጠገብሁ ነኝ።

ቦ የልጄን መሥዋዕትነት የጠገብሁ ነኝ።

ኢይፈቅድ ደመ ላህም ወጠሊ – የላሙን የፍየሉን መሥዋዕት አልሻም፤ ምነው ሠዉልኝ ብሏቸው የለምን ቢሉ በግብጽ ሳሉ ላም ያመልኩ ነበርና በለመዱት ለመሳብ እንጂ ለእሱ የሚረባው የሚጠቅመው ሆኖ አይደለም። ቦ ጥንቱንም አልሻም ሲል ነው። ቦ የልጄን መሥዋዕትነት እንጂ የላሙን የበጉን መሥዋዕት አልሻም ሲል ነው።

እመኒ አምጻእክሙ ኢታስተርእዩኒ – መሥዋዕቱን ብታመጡም በባለሟልነት አትታዩኝም ቦ ዛሬ አምጥታችሁ እንደሆነ ነገ አታሳዩኝም አለ ወደ ቤተ ጣዖት ትወስዱታላችሁ፤ ቦ ኢታርእዩኒ ይላል የቁጣ አነጋገር አታሳዩኝ።

መኑ ኀሠሦ ለዝንቱ እምእዴክሙ – እንዲህ ያለውን መሥዋዕት ከእጃችሁ ማን ፈለገው የሚፈልገው ማነው? ኢይፈቅድ ደመ ላህም ወጠሊ ላለው፤

ወኢትድግሙ እንከ ከይደ ዐፀድየ – ዳግመኛ የቤተ መቅደሴን አትረግጡም ተማርካችሁ ትሄዳላችሁ ሲል፤ ቦ ዛሬ መጥታችሁ እንደሆነ ነገ ወደ ቤተ ጣዖት ትሄዳላችሁ ሲል ነው፤ ቦ ኢትድግሙ ይላል የቁጣ አነጋገር ዳግመኛ የቤተ መቅደሴን ደጃፍ እንዳትረግጡ።  

ወእመኒ አምጻእክሙ ስንዳሌ ከንቱ – ልጦ ጉርዶ የወጣለትን ስንዴ ብታመጡም በኃጢአት ሳላችሁ ከንቱ ነው አለ አልቀበለውም።

ወዕጣንክሙኒ ርኵስ – ዕጣናችሁም ርኵስ ነው አልቀበለውም።

አስሕርቲክሙኒ – ሠርቀ ወርኃችሁንም አልቀበለውም አስርሕቲክሙኒ ቢል እሸት ነዷችሁ ርኵስ ነው አልቀበለውም።

ወሰንበታቲክሙኒ – ሰንበታችሁንም አልቀበለውም የዓመቱን ቅዳሜ ጨምሮ ቆጥሮ ሰንበታት ብሎ አበዛ ቦ እሑድን በትንቢት ጨምሮ ቆጦሮ።

ወዕለተክሙኒ ዐባየ ኢይፈቅድ – በዓለ ፋሲካንም አልሻም።

ወጾመክሙኒ – ጾማችሁንም አልሻም፤ ምን ጾም ነበራቸውና እንዲህ አለ ቢሉ እኛ ዓርብና ረቡዕን እንድንጾም ማክሰኞና ሐሙስን ይጾሙ ነበርና፤ ቦ ጥቅምት ዐሥር ቀን ዕለተ ዮሴፍን ይጾሙ ነበርና፤ አባቶቻቸው በግፍ ሸጠው እኩይ አርዌ በልዖ ብለው ነበርና እዳ አታድርግባቸው ሲሉ ይጾሙ ነበርና።

ዕረፍተክሙኒ ወጽርዓተክሙኒ – አንድ ወገን ዓመተ ኅድገትን አልሻም ቦ ዕረፍተክሙኒ ዓመተ ኅድገትን ወጽርዓተክሙኒ በኢዮቤልዩ በአርባ ዘጠኝ ዘመን የሚያከብሯት ሃምሳይቱን ዘመን ወቀድስዋ ለይእቲ ዓመት ዘሃምሳ ኵላ ክረምታ – ሃምሳይቱን ዓመት አክብሯት የሚላትን አልሻም ዘሌ ፳፭፥፲፤

ወሠርቀ ወርኅክሙኒ – የላይኛውን እሸት ነዶ ቢሉ ይህንን የዐሥራ ሁለቱን ሠርቀ ወርኅ አልሻም ቦ የሚያዝያን ሠርቀ ወርኅ አልሻም። ዝንቱ ወርኅ ቀዳማየ አውራኅ ይኩንክሙ – ይህ የወራት መጀመሪያ ይሁናችሁ ብሏቸዋለና ዘጸ ፲፪፥፪፤

ወበዓላቲክሙኒ ጸልዐት ነፍስየ – በዓለ ሰዊትን በዓለ መጸለትን ሰውነቴ ጠላች።

ሰቈራረ ኮንክሙኒ – የምታጸይፉ ሆናችሁብኝ ማለት ርኂቅ እምእግዚአብሔር አገኛችሁ።

ወጠለቁክሙ – ሰለቸኋችሁ ፈታኋችሁ ጌታን በመርዓዊ ቤተ እስራኤልን በመርዓት ይመስላቸዋልና ፈታኋችሁ አለ።   

ወኢይሠሪ ለክሙ ኃጢአተክሙ – ኃጢአታችሁን ይቅር አልላችሁም ንስሐ ከገቡ ይቅር የማይላቸው ሆኖ አይደለም አይገቡም ሲል ነው።

ወሶበ ታነሥኡ እደዊክሙ ኀቤየ እመይጥ ገጽየ እምኔክሙ – እጃችሁን ለመሥዋዕት ቃላችሁን ለጸሎት ብታነሡ ገጸ ረድኤቴን ከእናንተ እመልሳለሁ።     

ወእመኒ አብዛኅክሙ ምህላክሙ ኢይሰምዐክሙ – ምህላ ብታበዙም አልሰማችሁም፤ ብቻ ለብቻ ሆኖ የሚጸልዩት ጸሎት ተሰብስቦ የሚጸልዩት ምህላ ይባላል።

እስመ ደመ ምሉዕ እደዊክሙ – እጃችሁ ደምን ተመልቷልና ቦ እስመ ደም ምሉዕ ውስተ እደዊክሙ በእጃችሁ ደም መልቷልና።

ተሐጸቡ ወንጹሐነ ኩኑ – ይስማንስ ካላችሁ ታጠቡ ንጹሐን ሁኑ ማለት ንስሐ ግቡ። “ወባሕቱ አኮ ኵልክሙ ንጹሐን እስመ የአምር እግዚእ ዘያገብኦ ወበእንተ ዝንቱ ይቤ አኮ ኵልክሙ ንጹሐን” ዮሐ ፲፫፥፲ 

ጲላጦስ “ንጹሕ አነ እምደሙ ለዝ ብእሲ ጻድቅ” ብሏል ማቴ ፳፯፥፳፬፤ 

ወአዕትቱ እከየ እምነፍስክሙ – ቂም በቀልን ክፋት ተንኰልን ከልቡናችሁ አርቁ።

እከይ የሚለው ሲተረጐም ቂም የሚለውንም አካቶ ተተርጒሟል “ዔሳው በያዕቆብ ቂም ይዞ ነበር” ዘፍ ፳፯፥፵፩፤ 

ወንድምህን በልብህ አትጥላው የተባለው የልብ ጥላቻ ወደሌላ በደል ስለሚያደርስ ነው ዘጸ ፲፱፥፲፯፤ 

እምቅድመ አዕይንትየ ኅድጉ እከየክሙ – ክፋታችሁን ሁሉ ከፊቴ አርቁ አለ ኃጢአት እየሠሩ አያይብንም አያውቅብንም ብለዋልና እምቅድመ አዕይንትየ አለ። 

ይሁዳ ከአይሁድ ጋር ሲመክር ቆይቶ ጌታችንን ሰላምታ ለመስጠት በመጣ ጊዜ “የሰውን ልጅ በመሳም አሳልፈህ ትሰጣለህን” በማለት ከአይሁድ ጋር በድብቅ የመከረበትን ጉዳይ በግልጥ ነግሮታል ሉቃ ፳፪፥፵፰

ወተመሀሩ ገቢረ ሠናይ – በጎ ሥራ መሥራትን ተማሩ።  

ኅሥዋ ለጽድቅ – ዐሠርቱ ቃላትን ሿት ቦ እውነት ፍርድን ሿት ቦ ሕገ ወንጌልን ሿት።

ወአድኅኑ ግፉዐ – የተበደለውን እውነት ፈርዳችሁ አድኑት።

ፍትሑ ለዕጓለ ማውታ – እናት አባቱ ጥለዉት ለሞቱ ፍረዱለት ማለት ችግረኛ መሆኑን አይታችሁ እርዱት ሲል ነው።  

ወአጽድቁ ዕቤረ – ባልቴቲቱን እውነተኛ ነሽ በሏት ሐሰት ይዛ ብትመጣ አይደለም እውነት ይዛ ብትመጣ ነው እንጂ።  

ንዑ ንትዋቀስ ይቤ እግዚአብሔር – ጌታና ሎሌ ተጣልቶ ደንጊያና ቅል ተማቶ አይሆንምና ኑ እንዋቅስ ይላል እግዚአብሔር፤ ሰውና እግዚአብሔርማ ተዋቅሶ ይሆናልን ብሎ ኑ እንታረቅ ሲል ነው ሲታረቁ ከሆድ ሲታጠቡ ከክንድ እንዲሉ።  

እመኒ ኮነ ኃጢአትክሙ ከመ ኳኳ አፀዐድዎ ከመ በረድ – ኃጢአታችሁ እንደ ሱፋላ[4] እንደ በርኖስ ቢጠቁር እንደ በረዶ ነጭ አደርገዋለሁ።

ወእመኒ ቄሐ ከመ ለይ አነጽሖ ከመ ፀምር – እንደ ጁኽ[5] ግምጃ ቀይ ቢሆን እንደ ብዝት አነጻዋለሁ፤ ኃጢአቱን አነጻዋለሁ ማለቱ አይደለም ከኃጢአታችሁ አነጻችኋለሁ አከብራችኋለሁ ሲል ነው።

ቦ እንደ ቁራ ቢጠቁር እንደ በረድ ነጭ አደርገዋለሁ እንደ ግምጃ ቀይ ቢሆን እንደ ብዝት አነጻዋለሁ፤ ከመ ኳኳ ባለው ከመ ቀርመዝ[6] ይላል ትርጓሜው አይለወጥም። 

ወእመሰ ፈቀድክሙ ወሰማዕክሙኒ በረከተ ምድር ትበልዑ – የምመክራችሁን ምክር የማስተምራችሁን ትምህርት ወዳችሁ ፈቅዳችሁ ብትሰሙኝ የኢየሩሳሌምን ድልብ ትበላላችሁ።

ወእመሰ አበይክሙ ሰሚዖትየ መጥባሕትየ ትበልዐክሙ – መስማቱን እንቢ ብትሉ ሰይፌ ትበላኋለች አለ ሥልጣኔ ታጠፋችኋለች፤ መጥባሕትየ አለ በአርበኛ ግስ ተናግሮታል።

አንድም ሾተሌ ታጠፋችኋለች፤ የስልምናሶር የናቡከደነጾር ሾተል በተፈጥሮ ገንዘቡ ናትና የእነርሱን ለእርሱ ሰጥቶ ተናገረ።  

እስመ ከማሁ ነበበ አፉሁ ለእግዚአብሔር – እግዚአብሔር ይጥፉ ብሎ አዟልና።

ለዚህ ነው ነቢዩ ኤርምያስ “ፍሬዋንና በረከቷን ትበሉ ዘንድ ወደ ፍሬያማ ምድር አገባኋችሁ ነገር ግን በገባችሁ ጊዜ ምድሬን አረከሳችሁ ርስቴንም አጐሰቈላችሁ” ያለው ኤር ፪፥፯፤ 

ዝቅ ብሎ በዚሁ ቁጥር ፲፩ “ሕዝቤ ክብሩን ለማይረባ ነገር ለወጠ” የሚል ቃል ተመዝግቧል፤ እግዚአብሔርን ከሰጠን ውጭ ሌላ ነገር ፍለጋ መሄድ ክብርን ለማይረባ ነገር መለወጥ ነው።  

እፎ ኮነት ዘማ ሀገረ ጽዮን ማእምንት – የታመነች የጽዮን መዲና ኢየሩሳሌም እንዴት ዘማ ሆነች? ዝሙት የሴትና የወንድ ብቻ አይደለም እግዚአብሔር ያላዘዘውን ሁሉ መሥራት ዝሙት ነውና እንዲህ አለ። “እስመ ዘማዊ ዲያብሎስ ዘአኀዘክሙ ኢክህለ ይዕቀብክሙ – የያዛችሁ ዘማዊ ዲያብሎስ ይጠብቃችሁ ዘንድ አልቻለም” እንዲል፤

እንተ ምልዕት ፍትሐ – እውነተኛ ፍርድ ይፈረድባት የነበረች፤

ወኀደረ ውስቴታ ጽቅድ – ምግባር ትሩፋት ይሠራባት የነበረች ቦ ዐሠርቱ ቃላት ይነገሩባት የነበረች የጽዮን መዲና ኢየሩሳሌም እንዴት ዘማ ሆነች?

ወይእዜሰ ፈያት ወቀተልት – መልዕዋ ያለበት ነው ዛሬ ግን ነፍሰ ገዳዮች ወንበዴዎች መሉባት።

ወርቅኪኒ ወብሩርኪኒ ተምያን – ወርቅሽ ብርሽ ግብዝ ነው፤ በወርቁ ናስ በብሩ ቆርቆሮ ይጨምሩበታልና።

ቦ ሕግሽ ሕገ ኦሪት ግብዝ ነው አለ ሕገ ጣዖት የተቀላቀለበት ነው፤ ሕጉ ሕገ ጣዖት ተቀላቅሎበት ሳይሆን እነሱ ሕገ ኦሪትንና ሕገ ጣዖት ይቀላቅሉ ስለነበረ ነው። 

ቦ ሕግሽ ሕገ ኦሪት ግብዝ ነው አለ ድኅነተ ነፍስ አያሰጥም፤ እለፊ ካላት በኋላ ሲሠሯት ቢገኙ ግብዝ የምታሰኝ ስለሆነ።

ወመያስያንኪኒ ይቶስሑ ማየ በውስተ ወይን – መሸተኞችም በወይኑ ውኃ ይቀላቅሉበታል፤ ባለወይን/ባለዋጋ ባለ ጊዜ ሸሌውን በርዳዴውን ታቀምሰዋለች ዘወር ሲል አንድ ዋንጫ ሁለት ዋንጫ ውኃ ቀድታ ትቀላቅልበታለች።  

ቦ ነቢያተ ሐሰት ካህናተ ጣዖት በነቢያት በካህናት ትምህርት ላይ ሐሰተኛ ትምህርት ይቀላቅላሉ ማለት ነቢያት ምግባር ትሩፋት ሥሩ ሃይማኖት ያዙ ያለዚያ ትማረካላችሁ ብለው ያስተምራሉ ነቢያተ ሐሰት ሰላም ሰላም ጼዋዌ የለም እያሉ ያስተምራሉና።

ቦ መምራኖችሽ ጸሐፍት ፈሪሳውያን በሕገ ወንጌል ላይ ሐሰተኛ ትምህርትን ይቀላቅላሉ ወንጌል እንበለ ኦሪት ጥምቀት እንበለ ግዝረት አይረባም አይጠቅምም እያሉ ያስተምራሉና።

መላእክትኪኒ ሐያድያን – አለቆሽ ቀማኞች ናቸው ቦ ዳኞችሽ ቀማኞች ናቸው፤ ቀማኞች የሚሆኑ እሊህ

ሱቱፋነ ሰረቅት –  ከሌቦች ጋር የሚተባበሩ ናቸው፤ ከሌቦች ጋር የሚተባበሩ እሊህ

መስተናድአን – አንዱ በፊት አንዱ በኋላ እየሆኑ የሚሄዱ ናቸው።

ቦ መስተንዕንዳን ይላል ዛሬማ እንጂ ከእገሌ ቤት ሄጄ ውሻ ስይጮኽብኝ ሰው ሳይነቃብኝ እንዲህ ያለ ገንዘብ አመጣሁ ባለ ጊዜ ምናቦ ጎልማሳ እናትህ ትውለድ መልሳ መልሳ እያሉ የሚያደንቁ ናቸው።

መስተፋጥናን ይላል ሰውን የሚያፋጥኑ ናቸው፤ አንተ ስረቅ እኔ ላጥልቅ (ልጠብቅ) እያሉ።

ቦ መስተናስአን ይላል የሚያነሳሱ ናቸው አንገቱን ደፍቶ ባዩት ጊዜ ምን ሆነህ አንገትህን ደፍተሃል ይሉታል ቢርበኝ ይላቸዋል ምነው እንደእኛ ሰርቀህ ቀምተህ አትበላም እያሉ ሰውን ያነሳሳሉና።

ወያፈቅሩ ሕልያነ ወይፈቅዱ ይሚጡ ፍትሐ – መማለጃ ተቀብለው ፍርድ ሊለውጡ ይወዳሉ።

ወኢያጸምዑ ዕቤረ ብእሲተ – ባልቴቱቱን አይሰሟትም።

ወኢይፈትሑ ለዕጓለ ማውታ – እናት አባቱ ጥለዉት ለሞቱ አይፈርዱለትም ማለት ችግረኛ መሆኑን አይተው አይረዱትም።

በእንተዝ ከመዝ ይቤ እግዚአብሔር ጸባዖት – ወያፈቅሩ ሕልያነ ወይፈቅዱ ይሚጡ ፍትሐ ብሎ ነበርና መማለጃ ተቀብለው ፍርድ ሊለውጡ ስለሚወዱ አሸናፊ እግዚአብሔር እንዲህ አለ። 

አሌ ሎሙ ለኃያላነ እስራኤል – ለመኳንንተ እስራኤል ሲል ነው ለኃያላነ ፈርዖን እንዲል ለእስራኤል አለቆች ወዮላቸው።

ኢይቈርር መዓትየ እምላዕለ ፀርየ – መዓት መቅሠፍቴ ከጠላቶቼ አይርቅም። ቦ ኢያቈርር ይላል መዓት መቅሠፍቴን ከጠላቶቼ አላርቅም።

ወእትቤቀሎሙ ለጸላእትየ – ጠላቶቼን ተበቅዬ አጠፋቸዋለሁ።

ወአመጽእ እዴየ ላዕሌኪ – እደ መዓቴን በአንቺ ላይ አመጣለሁ።

ወአረስነኪ – በመከራው አግልሻለሁ።

ወእፈትን ዛኅለኪ በከውር – ዝገትሽን በከውር እፈትነዋለሁ ማለት ክፉ ክፉውን ለይቼ አተፋዋለሁ።  

ወአሴስል ኵሎ ናዕከኪ – ቅልቅሉን ኃጢአትሽን ቦ ናሕከኪ ይላል ጽኑዕ ኃጢአትሽን አርቃለሁ።

ወአውዕዮሙ ለከሀድያን – ከሀድያንን አጠፋቸዋለሁ። 

ወአዐትቶሙ እምኔኪ ለኵሎሙ ዓማፅያን – ዓመፀኞችን ሁሉ ከአንቺ አርቃቸዋለሁ።

ወእሠይም ለኪ መኳንንተኪ ከመ ትካት – አለቆችሽን እንደ ዳዊት እንደ ሰሎሞን ጊዜ እሾማቸዋለሁ።

ወመማክርተኪ ከመ ቀዲሙ – መማክርቶችሽንም እንደ ሙሴ እንደ አሮን ጊዜ እሾማቸዋለሁ።

ቦ ስለዓበይት ነቢያት ፈንታ ሐዋርያትን ሰለደቂቅ ነቢያት ፈንታ ሰባ አርድእትን እሾምልሻለሁ።

ወእምዝ ትሰምዪ ሀገረ ጽድቅ ደብረ አህጉረ ጽዮን ማእምንት – ከሚጠት በኋላ የታመንሽ የጽዮን መዲና ኢየሩሳሌም ዐሠርቱ ቃላት የሚነገሩባት ሀገር ትባያለሽ።

ቦ የታመንሽ የምእመናን መዲና ወንጌል የሚነገርባት ሀገር ቤተ ክርስቲያን ትባያለሽ።

እስመ በጽድቅ ይድኅኑ ጺውዋንኪ – ምርኮኞችሽ እስራኤል በእውነት ይድናሉና። ወኀሊቆ ሰብዓ ዐመት ባለው፤ ወእምድኅረ ሰብዓ ዓመት ይሔውፀክሙ እግዚአብሔር በሣህል ባለው ይድናሉና።

ቦ ምርኮኞችሽ ነፍሳት በሐሙስ ዕለት ወበመንፈቃ ለዕለት ባለው ይድናሉና።

ወበምጽዋት – ቸርነቱን ምጽዋት አድርጎ ሰጥቷቸው፤ ቦ በጽድቅ በሃይማኖት ወበምጽዋት በምግባር ይድናሉ።

ቦ ሥጋውን ደሙን ምጽዋት አድርጎ ሰጥቷቸው።

ወይትቀጠቀጡ ኃጥአን ወዓማፅያን ኅቡረ – ኃጥአን ዓማፅያን አንድ ሆነው ይጠፋሉ፤ ኃጥአን የሚላቸው ሃይማኖት ያላቸው ምግባር የሌላቸውን እንደእኛ ያሉ ናቸው፤ ዓማፅያን ያላቸው ሃይማኖትም ምግባርም የሌላቸው ናቸው።

ወይጠፍዑ ኵሎሙ እለ ኀደግዎ ለእግዚአብሔር – እግዚአብሔርን በሕግ በአምልኮት የተዉት ሁሉ ይጠፋሉ።

ወይትኀፈሩ በአማልክቲሆሙ በዘመከሩ ለሊሆሙ – ራሳቸው በሠሯቸው በጣዖታቱ ያፍራሉ።

ወይትኀፈሩ በምሕራማቲሆሙ ዘፈተዉ – በወደዱት በመስገጃቸው ያፍራሉ።

ወይከውኑ ከመ ዕፀ ጠርቤንቶስ እንተ ነገፈት ቈጽላ – ቅጠሏ እንደ ረገፈ እንደ ቡጥም (ደረቅ) እንጨት ይሆናሉ፤ ቅጠሉ ረግፎ ግንዱ እንዲቀር ገንዘባቸው አልቆ ያለ ገንዘብ ባዷቸውን ቀርተዋልና።

ወከመ ገነት እንተ አልባቲ ማይ – ውኃ እንደሌለባት ተክል ይሆናሉ፤ ያቺ ከሥሯ ተነቃቅላ እንድትወድቅ ሥር መሠረታቸው ይጠፋልና።

ወይከውን ኃይሎሙ ከመ ብርዐ ባሕሩስ – የእስራኤል ኃይላቸው እንደ መቃ መስዬ ገለባ ይሆናል ማለት ያ ደካማ እንደሆነ ኃይላቸው ይደክማል ሲል ነው። ቦ መቃ እንዲሰበር ድል ይነሣሉ ሲል ነው።

ወምግባራቲሆሙ ከመ አፍሐመ እሳት – ኃጢአታቸው እንደ እሳት ይሆናል ማለት ያ እንዲያጠፋ የሚያጠፋ ይሆናል። እሳት ቢቆሙበት እንዲጎዳ ኃጢአት ይጎዳልና።

ቦ የነስልምናሶር የነናቡከደነጾር ነፍጣቸው መርቡጣቸው እንደ እሳት አጥፊ ይሆናል ቦ ሠራዊታቸው እንደ መቃ ይሆናል።

ወይውዕዩ ኃጥአን ወዓማፅያን ኅቡረ – ኃጥአን ዓማፅያን አንድ ሆነው ይጠፋሉ።

ወየኃጥኡ ዘያጠፍእ ሎሙ እሳቶሙ – መዓቱን መቅሠፍቱን የሚያርቅላቸው ያጣሉ መዓት መቅሠፍት በብዙ ወገን ይርቃልና፤ እንደ ሙሴ ያለ ነቢይ የተገኘ እንደሆነ መዓት መቅሠፍት ይርቃል ጠስየኒ እመጽሐፈ ሕይወት ዘጸሐፍከኒ እምትጥስዮሙ ለእሉ ብሎ መዓት መቅሠፍቱን አርቋልና፤

እንደ ኢያሱ ያለ መስፍን የተገኘ እንደሆነ መዓት መቅሠፍት ይርቃል፤ ለምንት አዕድዎ አዕድውኮ ለገብርከ ናሁ ሜጠ እስራኤል ዘባኖ ቅድመ ፀሩ ብሎ መዓት መቅሠፍቱን እንደመለሰ፤

እንደ ዳዊት ያለ ንጉሥ የተገኘ እንደሆነ መዐት መቅሠፍት ይርቃል ምንተ ገብሩ እሉ አባግዕ እንዘ አነ ኖላዊሆሙ ዘአበስኩ ዛቲ ኃጢአት ትኩን ላዕሌየ ወላዕለ ቤተ አቡየ ብሎ መዓት መቅሠፍቱን እንደመለሰ፤

እንደ ሕዝቅያስ ያለ ንጉሥ የተገኘ እንደሆነ መዓት መቅሠፍት ይርቃል ርኢ ትዕይቶ ለሰናክሬም ብሎ መዓት መቅሠፍቱን እንደመለሰ፤

እንደ ሰብአ ነነዌ ያለ የተገኘ እንደሆነ መዓት መቅሠፍት ይርቃል፤ ንስሐ ገብተው መዓት መቅሠፍቱን እንደመለሱ።

ምዕራፍ ፪

ቃል ዘኮነ ኀበ ኢሳይያስ ወልደ አሞፅ   – ዘመጽአ ዘተነግረ ሲል ነው፤ ከአሞጽ ልጅ ከኢሳይያስ ዘንድ የመጣ የተነገረ የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው። 

ዘርእየ በእንተ ይሁዳ – ይህ በእንተ በስፍራው የገባ ነው የበጎ ነው ሰዎቹ እንዲመለሱ፤ 

ወበእንተ ኢየሩሳሌም – ሀገሪቱ እንድትቀና አይቶ የተናገረው ነገር ይህ ነው፤ ቦ ዐሥሩ ነገድ ዐሥራ ሁለቱ ነገድ እንዲመለሱ ቦ ጥቃቅኑ አህጉር መዲናይቱ ኢየሩሳሌም እንዲቀኑ አይቶ የተናገረው ነገር ይህ ነው። 

በዚሁ አንጻር ቃሉን ሰምተው በንስሐ ሕይወት ተመላልሰው ሥጋውን ደሙን ተቀብለው የእግዚአብሔርን መንግሥት በመጠባበቅ የሚኖሩ ኃይላቸውን እንደ ንስር እያደሱ እረኛው በጎቹን በቀኝ በሚያቆባት ሰዓት ቃለ በረከቱን ሰምተው ቅድመ ዓለም የተዘጋጀላቸውን መንግሥት ይወርሱ ዘንድ ወደዘለዓለም ሕይወት ይሄዳሉ። ከዚህ በተቃራኒው መኖርን ምርጫቸው ያደረጉ ደግሞ ለሰይጣንና ለሠራዊቱ ወደተዘጋጀ የዘለዓለም እሳት ይጣላሉ። 

ወይከውን በደኃሪ መዋዕል – በኋላ ዘመን እንዲህ ይሆናል አለ በሕዝቅያስ በዘሩባቤል ዘመን እንዲህ ይሆናል። 

ያስተርኢ ቤተ እግዚአብሔር ውስተ አርእስተ አድባር ወይትሌዐል መልዕልተ አውግር – ይከውን ያለበት ነው በሕዝቅያስ ዘመን ያሉ እንደሆነ ቤተ መቅደስ በኪዳነ አብርሃም በኪዳነ ይስሐቅ በኪዳነ ያዕቆብ ጸንቶ ይኖራል። “ብዙኃን ይመጽኡ እምሥራቅ ወእምዕራብ ወይረፍቁ ውስተ ሕፅነ አብርሃም ይስሐቅ ወያዕቆብ በመንግሥተ ሰማያት – ብዙዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ ይመጣሉ በመንግሥተ ሰማያት በአብርሃም በይስሐቅ በያዕቆብ አጠገብ ይቀመጣሉ” እንዲል ማቴ ፰፥፲፩፤  

ይህም ማለት በእነዚህ ቅዱሳን ቃል ኪዳን በምትወረስ መንግሥተ ሰማያት ይኖራሉ ማለት ነው። የነሣውን ሥጋ የነሣው ከአብርሃም ዘር ነውና “እስመ አኮ እመላእክት ዘነሥኦ ለዘነሥኦ ዘእንበለ ዳእሙ እምዘርዐ አብርሃም – የነሣውን ሥጋ የነሣው ከመላእክት አይደለም ከአብርሃም ዘር እንጂ” እንዲል ዕብ ፪፥፲፮፤ 

ትንሣኤ ሙታንን አስረግጦ በተናገረበት አንቀጽም ማስረጃ አድርጎ የጠቀሳቸው እኒህን ቅዱሳን ነው ማቴ ፳፪፥፴፪፤ ቅዱስ ጳውሎስም “እለ የአምኑ ይትባረኩ ምስለ አብርሃም ምእመን – ያመኑ ከታመነ አብርሃም ጋር ይባረካሉ” በማለት በአብርሃም በኩል የምናገኘውን በረከት በግልጥ ይነግረናል ገላ ፪፥፲፤

ኦሪትም የምትነግረን ይህንኑ ነው “በዘርዕከ ይትባረኩ ኵሎሙ አሕዛበ ምድር – በዘርህ የምድር ወገኖች ሁሉ ይባረካሉ” ብላ ዘፍ ፳፪፥፲፰፤ 

ከዚህ ንባብ ቀጥሎ “እስመ ሰማዕከ ቃልየ – ቃሌን ሰምተሃልና” የሚል አስረጂ ቃል ተገልጧል፤ አብርሃም የሰማው ቃል ልጁን መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብ በእግዚአብሔር የታዘዘው ቃል ነው፤ ይህ ደግሞ በቅዱስ ወንጌል “አብርሃም አቡክሙ ተመነየ ከመ ይርአይ ዕለትየ ርእየሂ ወተፈሥሐ – አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ተመኘ አየ ደስም አለው” ተብሎ የተገለጠው ነው ዮሐ ፰፥፶፮፤

ይህንኑ ቃል ቅዱስ ቄርሎስ በተረፈ ቄርሎስ በሃያ አምስተኛው ምዕራፍ እንደሚከተለው አብራርቶ ገልጦታል፤ ትፌኑሁ ቃለከ ውስተ ምድር በመዋዕለ ዚአየ ወእሬኢኑ እንጋ ኪያሃ ዕለተ – ልጅህን በዘመኔ ወደምድር ትልካለህን ያቺንስ ዕለት አያለሁን? 

ወይቤሎ አልቦ አላ አርዕየከ አምሳላ ለይእቲ ዕለት ረድኬ ዕድዎ ለዮርዳኖስ ወትሬኢ ዕለተ ስብሐተ ዚአየ – የለም የዕለት ዓርብ ምሳሌዋን ታያለህ ፈጥነህ ዮርዳኖስን ተሻገር የጌትነቴን ቀን ታያለህ

ወዐደዎ አብርሃም ለዮርዳኖስ ምስለ ኵሉ ኃይሉ ወዝ ትእምርተ ጥምቀት – አብርሃም ከሠራዊቱ ጋር ዮርዳኖስን ተሻገረ ይህም የጥምቀት አምሳል ነው በማለት።  

ይህንኑ ምሥጢር ከዕለተ ልደቱ ጋር አያይዞ ሲገለጠውም “ወበዝ አእመሩ ከመ ውእቱ ወልደ እግዚአብሔር ተመሲሎ አሐደ እምኔሆሙ ኤጲስ ቆጶሰ አወፈዮሙ ርትዕተ ሃይማኖተ እንተ በኵሉ ክብርት ጌና ዘይእቲ ልደቱ በሥጋሁ ለእግዚእነ እንተ ባቲ ተወልደ – ከእነሱ አንዱን መስሎ ርትዕት ሃይማኖትን ያስተማራቸው ወልደ እግዚአብሔር እንደሆነ በዚህ አወቁ ይህችውም ጌታችን በሥጋ የተወለደባት በሁሉ ዘንድ የከበረች ጌና ናት” ብሎ ያጎላዋል። 

በዘሩባቤል ዘመን ያሉ እንደሆነ በአምስቱ በስድስቱ ቆመ ብእሲ ተሠርቶ ይታያል። “በአርብዓ ወስድስቱ ዓመት ተሐንጸ ዝንቱ ቤተ መቅደስ ወአንተሰ ታነሥኦ በሠሉስ መዋዕል – ይህ ቤተ መቅደስ በአርባ ስድስት ዓመት ታነጸ አንተ ግን በሦስት ቀን ታነሣዋለህ” እንዲል ዮሐ ፪፥፳፤

አባቶቻችን ይህ ሁሉ መከራ የደረሰባቸው ቤተ መቅደስን ባይሠሩ ነው እኛ ሚጠቱ ይደረግልን እንጂ ቤተ መቅደስን ሳንሠራ ዘር አንዘራም ቤት አንሠራም ብለው ስለት ተሳሉ ሚጠቱ ተደረገላቸው ዘር ሲዘሩ ቤት ሲሠሩ ሁለት ዓመት ኖሩ በሦስተኛው ጀምረው በአርባ ስድስት ዓመት ፈጽመዉታልና።    

ቦ ከአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን በኋላ በዘመነ ሐዲስ እንዲህ ይሆናል በወርቅ በዕንቊ ከተሠራ ከነገሥታቱ ቤት ይልቅ በጭቃ በጨፈቃ የተሠራች የቤተ ክርስቲያን ክብር በልጦ ይታያል። “አንተ ኰኵሕ ወዲበ ዛቲ ኰኵሕ አሐንጻ ለቤተ ክርስቲያንየ ወአናቅጸ ሲኦል ኢይኄይልዋ – አንተ ዓለት ነህ በዚች ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን እሠራታለሁ የሲኦል ደጆችም አይችሏትም” እንዲል ማቴ ፲፮፥፲፰፤

ቅዱስ ጴጥሮስ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብሎ በሰጠው የሃይማኖት ምስክርነት ላይ ተመሥርተን እኛም ይህን ምስክርነት እንሰጣለንና። “እስመ ተሐነጽክሙ ዲበ መሠረተ ሐዋርያት ወነቢያት – በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ታንጻችኋልና” እንዲል ኤፌ ፪፥፳፤

ወየሐውሩ ኀቤሁ ኵሎሙ አሕዛብ – በሚጠት በኦሪት ያመኑ አሕዛብ ሁሉ ወደቤተ መቅደስ ይሄዳሉ። 

ቦ በዘመነ ሐዲስ በወንጌል ያመኑ አሕዛብ ወደቤተ ክርስቲያን ይሄዳሉ። 

ወይመጽኡ ብዙኃን አሕዛብ – ብዙ አሕዛብ ወደቤተ መቅደስ ቦ ወደቤተ ክርስቲያን ይመጣሉ። 

የሰብአ ሰገልን ጉዞ፣ በቅዱስ ጴጥሮስ ስብከት ያመኑ ሦስት ሺህ ያህል ምእመናንን፣ በቅዱስ ጴጥሮስና በቅዱስ ዮሐንስ እስራት ያመኑ አምስት ሺህ ያህል ምእመናንን በማስተዋል ስንመለከት ሰው ሁሉ ወደቤተ ክርስቲያን ለመሄድና በቤተ ክርስቲያን ለመጽናት የሚያደርገውን ፍጥነትና ትጋት ከነቢዩ ትንቢት ጋር አነጻጽረን ስንረዳው “ጌታም የሚድኑትን ዕለት ዕለት በእነርሱ ላይ ይጨምር ነበር” በሚለው ቃል እንመሰጣለን። ግብ ፪፥፵፯፤

ወይብሉ ንዑ ንዕርግ ውስተ ደብረ እግዚአብሔር – ከመሄዳቸው አስቀድመው ኑ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንውጣ እንሂድ ይላሉ። 

ወውስተ ቤተ አምላከ ያዕቆብ – ወደያዕቆብ ፈጣሪ ማደሪያ ወደ ቤተ መቅደስ እንሂድ ይላሉ። 

ቦ ወደ ቤተ ክርስቲያን ከመሄዳቸው አስቀድመው ኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን እንሂድ ይላሉ፤ ዐሠርቱ ቃላትን ያስተምሩን ዘንድ፤ በስድስቱ ቃላተ ወንጌልም ጸንተን እንኖር ዘንድ፤ 

ይንግሩነ ፍኖቶ ወንሑር በአሠሩ –  ዘጠኙን ቃላት ያስተምሩን ዘንድ በኢታምልክም ጸንተን እንኖር ዘንድ፤ 

ኢታምልክን አሠር አላት ነገር ከነገር ፍለጋ ከመንደር እንዲያደርስ ኢታምልክም ከዘጠኙ ታደርሳለችና። 

እስመ እምጽዮን ይወጽእ ሕግ ወቃለ እግዚአብሔር እምኢየሩሳሌም – ከነቢያት ትንቢት ከካህናት ትምህርት ይገኛልና ንዑ ንሑር፤

ቦ ሕግ ጌታ ከእመቤታችን ይወለዳልና፤ አንሶሰወት ሕግ ወአስተርአየት ውስተ ዓለም ሕግ በዓለም ስትመላለስ ታየች እንዲል። 

ቦ ሐጋጌ ሕግ ጌታ ከእመቤታችን ይወለዳልና፤ ጽዮን አላት ጸወነ ሥጋ ወነፍስ ናትና፤ አካላዊ ቃል ከርሷ ይወለዳልና፤ ኢየሩሳሌም እንጂ ማለት መካነ ሰላም ሀገረ ሰላም ማለት ነው እሷንም ብኪ ድኅነ ዓለም ወበወልድኪ ኮነ ሰላም ይላታልና። 

ቦ ሕገ ወንጌል በቤተ ክርስቲያን ይነገራልና፤ አካላዊ ቃል በሥጋነት በደምነት ይሰጣልና ንዑ ንሑር። 

ወይኴንን በማዕከለ አሕዛብ – ሕዝቅያስ ዘሩባቤል በአሕዛብ መካከል ሆኖ ይፈርዳል። 

ቦ ጌታችን በአሕዛብ መካከል ሆኖ ያስተምራል ይፈርዳል ተኀድገ ለከ ተኀድከ ለኪ እፈቅድ ንጻሕ ተንሥእ ንሣእ ዓራተከ እያለ፤  

ወይዛለፎሙ ለብዙኃን አሕዛብ – ብዙ አሕዛብን ይዘልፋቸዋል ብትገብሩ ገብሩ ብትቀቅሉ ቀቅሉ ያለዚያ እወጋችኋለሁ እያለ፤ 

ቦ ጸሐፍት ፈሪሳውያንን ያዋትታቸዋል አሌ ለክሙ ጸሐፍት ፈሪሳውያን መደልዋን እለ ትበልዑ አብያተ መበለታት እያለ፤ 

ወይመትሩ መጣብሒሆሙ ለምሳር – ሾተላቸውን ምሳር አድርገው ያሠሩታል፤ ቦ ሰይፋቸውን መቆፈሪያ አድርገው ያሠሩታል። 

ወኵያንዊሆሙ ለማዕፀድ – ጦራቸውን ማጭድ አድርገው ያሠሩታል ቦ ጦራቸውን ሠቅ መስቀል አድርገው ያሠሩታል። 

ወኢያነሥእ እንከ ሕዝብ ዲበ ሕዝብ መጥባሕተ – ከእንግዲህ ወዲህ አንዱ በአንዱ ላይ ጠብ አያነሣም፤ 

ወኢይትሜሀሩ እንከ ቀትለ – ከእንግዲህ ወዲህ ሰልፍ አይማሩም፤ በሀገራቸው ወርኃ ጸብእ ሆኖ ሰልፍ መማር፣ በፈረስ እየጋለቡ የአንዱን እግር ሰናፊል በአንድ እግር ማግባት፣ በአረቄ መርፌ ፈትል ማግባት፣ ዘንግ ወርውሮ መቅለብ፣ አለንጋ ማንሣት አለና። 

በሕዝቅያስ በዘሩባቤል ጊዜ ዘመኑ ዘመነ ሰላም ሆኖ እስራኤል ጠላት ጠፍቶላቸው በወይኑ በበለሱ ሥር ድንኳናቸውን ተክለው ጃንጥላቸውን ጥለው ሲበሉ ሲጠጡ ይውሉ ነበርና፤ ይበልዑ ወይሰትዩ ታሕተ ወይኖሙ ወበለሶሙ ወይነብሩ ተአሚኖሙ እንዲል ፩ነገ ፬፥፳፯

ቦ በጌታ ዘመን ሥጋዊ ጠላት ቅሉ ጠፍቶላቸዋልና፤ ወያጠፍእ ሠረገላ እምኤፍሬም ወአፍራሰ እምይሁዳ ወይከውን ሰላም በመዋዕሊሁ እንዲል ዘካ ፱፥፲፤

ወይእዜኒ ቤተ ያዕቆብ ንዑ ንሑር በብርሃነ እግዚአብሔር – አሁንም የያዕቆብ ወገኖች በብርሃነ ረድኤቱ ጸንተን እንኖር ዘንድ ኑ፤ ቦ በብርሃነ ረድኤቱ ጸንተን እንኑር፤ ቦ በብርሃነ ረድኤቱ ጸንተን የምንኖርበትን ሥራ እንሥራ ቦ ጸንተን እንድንኖር እንሁን፤ 

ቦ ያዕቆብ ዘነፍስ በብርሃን ጸንተን እንኖር ዘንድ ኑ። 

እስመ ተረስዐ ሕዝበቶሙ ለእስራኤል – ሕዝብናሆሙ ሲል ነው የዐሥሩ ነገድ ወገንነታቸው ተዘንግቷልና፤ እንደእነዚያ እንዳንዘነጋ ንዑ ንሑር፤  

እስመ መልዐ በሐውርቲሆሙ ከመ ትካት ዘያሰግሉ ከመ ኢሎፍሊ – መልዐ ከመ ኢሎፍሊ ዘያሰግሉ ከመ ኢሎፍሊ ብለህ ግጠም፤ ሀገራቸው ኢሎፍላውያን ቀድሞ ይጠነቁሉት እንደ ነበረ ያለ ጥንቈላ መልቷልና። 

ወከመ ትውልደ ነኪር ኮኑ – የከነዓን ልጆች ያመልኩት እንደ ነበረ ያለ ጣዖት ሀገራቸው ስለመላ እንደ እነዚያ እንዳንዘነጋ በብርሃነ ረድኤቱ ጸንተን እንኖር ዘንድ ንዑ ንሑር። 

ወተወልዱ ሎሙ ብዙኅ ደቂቅ ካልዕ ሕዝብ – ለእናት ለአባታቸው ሁለተኛ የሚሆኑ ብዙ ልጆች ተወለዱላቸው፤ ቦ የልጅ ልጆች ተወለዱላቸው፤ ቦ እምካልዕ ሕዝብ ከራቀ ወገን ከአሕዛብ ብዙ ልጆች ተወለዱላቸው።  

ወመልዐ ብሔሮሙ ወርቀ ወብሩረ – ሀገራቸው ወርቁን ብሩን መላ። 

ወአልቦ ኊልቊ ለመዛግብቲሆሙ – ለገንዘባቸው ስፍር ቁጥር የለውም።  

ወመልዐት ምድሮሙ አፍራሰ – ምድራቸው ፈረሶችን ተመላች። 

ወመልዐት ምድሮሙ ጣዖተ ዘገብሩ በእደዊሆሙ ወሰገዱ ለዘገብሩ በአጻብኢሆሙ – ወርቁ ብሩ በዛባቸው ምን እናውለው ብለው ጣዖት አድርገው ሠርተዉት ሀገራቸው በእጃቸው ሠሩት ጣዖትን ተመላ፤ በእጃቸው ለሠሩት ለጣዖቱ ሰገዱ። 

ወተቀጽአ ሰብእ ወኀሥረ ዕጓለ እመሕያው – ሰው ሁሉ በመከራው ጐበጠ ሰው ሁሉ ጐሰቈለ ቦ መከራ ተቀበለ።  

ወኢይስሕቶሙ ሞት – የተወረወረ ጦር አይስታቸውም ቦ ኢያሴሕቶሙ ሞት ሞት አያሳርፋቸው ዛሬም ነገም ይሞታሉ። 

ወይእዜኒ ባኡ ውስተ ኰኵሕ – አሁንም ይሆንላችሁ እንደሆነ ወደዋሻው ግቡ ይላቸዋል፤ ፍና ተሣልቆ፤ ቦ መከራ እንዳለባቸው መናገር ነው። 

ወተኀብዑ ውስተ ግበበ ምድር እምፍርሃተ እግዚአብሔር – የእግዚአብሔር ገጸ መዓቱን ከመፍራታቸው የተነሣ በጒድጓድ ውስጥ ተሰወሩ። 

ወእምግርማ መዓቱ ወእምስብሐተ ኃይሉ – ከግርማ መዓቱ የተነሣ ከሃሊነቱን ከሚገልጥበት ከተአምራቱ የተነሣ። 

አመ ተንሥአ ይቀጥቅጣ ለምድር – ኢየሩሳሊምን ያጠፋት ዘንድ በተነሣ ጊዜ፤ ቦ እንደ ሰም ያቀልጣት እንደ ገል ይቀጠቅጣት ዘንድ በመዓት በተነሣ ጊዜ፤ ቦ እስመ ተንሥአ በመዓት ተነሥቷልና፤  

እስመ አዕይንተ ልዑላን ሰብእ የኀሥራ ወየኀሥር ልዕልናሁ ለእጓለ እመሕያው – የልዑላን ሰዎች ዐይን በሞት ይፈሳልና፤ የሰው ክብሩ ይዋረዳልና ተኀብዑ፤ 

ወይትሌዓል እግዚአብሔር ባሕቲቱ ይእተ አሚረ – ያንጊዜ እግዚአብሔር ብቻውን እነሱን አጥፍቶ ልዕልናውን ይገልጣል። 

እስመ ዕለተ እግዚአብሔር ፀባዖት ላዕለ ኵሉ ፀር ወጸላኢ ወዝኁር ወላዕለ ኵሉ ዕፀ ሊባኖስ ወዲበ ኵሉ ወግር ልዑላት ወላዕለ ኵሉ ማኅፈድ ነዋህ ወልዑል ወላዕለ ኵሉ አረፍት ቀዋም ወላዕለ ኵሉ አሕማር ወላዕለ ኵሉ ጣዖተ አማልክት – አሸናፊ እግዚአብሔር የሚፈርድባት ዕለተ ጼዋዌ በጠላቶች ላይ በትዕቢተኛው ላይ በባለጠጋው ላይ በመካንንቱ ላይ ልዑል ክቡር በሚሆን በንጉሡ ላይ በአርበኛው ላይ በደሴት በሚኖሩ ነጋድያን ላይ ቦ ነጋድያኑን በሚገዙ በነገሥታቱ ላይ አማልክት በሚባሉ በጣዖታቱ ላይ ቦ ካህናት ባሏቸው ጣዖታት ላይ ቦ ጣዖታቱን በሚያመልኩ በካህናቱ ላይ ትመጣለችና፤ ፀር የዕለት ጠላት፤ ጸላኢ ጥንተ ጠላት ነው ዝኩ ጸላኢነ ሐማ – ይህ ጥንተ ጠላታችን ሐማ እንዲል አስቴር ፯፥፮፤ 

ወይቴሐት ኵሉ ሰብእ ወአዕይንተ ዕቡያን ሰብእ ይቴሐታ ወየኀሥር ልዕልናሁ ለጓለ እመሕያው – ሰው ሁሉ ይዋረዳል የክፉዎች ሰዎች ዐይን ይፈሳል የሰው ሁሉ ልዕልናው ክብሩ ይዋረዳል። 

ወይትሌዓል ይእተ አሚረ እግዚአብሔር ባሕቲቱ – ያንጊዜ እግዚአብሔር ብቻውን ልዕልናውን ይገልጣል።  

ወየኀብዑ ኵሎ ጣዖቶሙ ዘገብሩ በእደዊሆሙ ወያበውእዎሙ ውስተ በአታት ወውስተ ንቅዓታተ ኰኵሕ ወውስተ ግበበ ምድር – በእጃቸው የሠሩትን ጣዖታቸውን ሁሉ ይሠውራሉ፤ የወርቅ የብር ነውና ይወስዱብናል ብለው፤ ወደዋሻ ያገቧቸዋል ወደተከፈለው ደንጊያ ያገቧቸዋል ወደ ጒድጓድ ያገቧቸዋል። 

ወእምስብሐተ ኃይሉ – በከሃሊነቱ ከሚያደርገው ከተአምራቱ የተነሣ፤ 

አመ ተንሥአ ይቀጥቅጣ ለምድር – ኢየሩሳሌምን ያጠፋት ዘንድ በተነሣ ጊዜ፤ ሦስት ጊዜ ይቀጥቅጣ አለ? ሦስት ጊዜ ተማርከዋክና፤ በኢኮንያን፣ በኤልያቂምና በሴዴቅያስ።

ወኀደጉ ኵሉ ዕጓለ እመሕያው ዘነፍስ ውስተ ገጹ – ሥጋዊ ደማዊ የሆኑ ሰዎች ሁሉ በጣዖቱ ግንባር ጉድፉን ትቢያውን ጣሉ፤ የሠወርን መስሏቸው፤ 

ምንተ ይሄሊ ውእቱ – አያድናቸው አይረዳቸው አይታደጋቸውም ምን ያደርግላቸዋል ይላል ነቢዩ፤ 

ቦ ዕጓለ እመሕያው ዘነፍስ፤ ባለአእምሮ ሰዎች በሚጠት ጊዜ ጣዖቱን በግንባሩ ደፍተው ጥለዉት ይሄዳሉ አያዳን አይረዳ አይራዳ አይታደግ ብለው። 

፲፩

፲፪

፲፫

፲፬

፲፭

፲፮

፲፯

፲፰

፲፱

፳፩

፳፪

፳፫

፳፬

፳፭

፳፮

፳፯

፳፰

፳፱

፴፩