ከትንሣኤ እስከ ጰራቅሊጦስ
ሚያዝያ ፲፪ በዓለ ቅዱስ ሚካኤል
ዘነግህ ምስባክ፦
ይትዐየን መልአከ እግዚአብሔር ዐውዶሙ፤
ለእለ ይፈርህዎ ወያድኅኖሙ፤
ጠዐሙ ወታእምሩ ከመ ኄር እግዚአብሔር።
ወንጌል፦ ማቴ ፳፬፥፴ – ፴፮፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
፩ጢሞ ፬፥፱ – ፍጻሜ፤
፩ጴጥ ፪፥፲፫ – ፲፯፤
ግብ ፳፬፥፲፬ – ፳፪፤
ወንጌል፦ ማቴ ፲፮፥፲፫ – ፳፤
ቅዳሴ፦ ዘያዕቆብ ዘሥሩግ
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
አድኅነኒ እምእለ ሮዱኒ እስመ ይኄይሉኒ፤
ወአውጽኣ እሞቅሕ ለነፍስየ፤
ከመ እግነይ ለስምከ እግዚኦ። ትርጒሙንና ምሥጢሩን መስከረም ፩ ላይ ተመልከት።
ሥርዓተ ትንሣኤ
ህየንተ ዋዜማ የዮሐንስ ራእይ ይነበባል፤ ቀጥሎ ላሐ ማርያም ይነበባል፤ ከመቅደስ ወንጌለ ዮሐንስ ይደገማል፤ በማኅሌት ፲፭ቱን ነቢያት ድገም። ይ.ካ አቡነ ዘበሰማያት።
አያይዞ ሰላም ለኪ በዜማ ይበል መሪና ተመሪ ተሰመይኪ ፍቅርተን እየተቀባበሉ ይበሉ በኅብረት ወበእንተዝ ይበሉ።
ተመሪ ለብቻው ታቦትን ይበል። ከመቅደስ እስከ በትረ አሮን አድል ለኪ ይደሉን መሪ ለብቻው በዜማ ይበል።
ወበእንተዝን በኅበረት ዝመም፦ ወበእንተዝ ናዓብየኪ ኲልነ ኦ እግዝእትነ ወላዲተ አምላክ ንጽሕት ኲሎ ጊዜ ንስእል ወናንቀዓዱ ኀቤኪ ከመ ንርከብ ሣህለ በኀበ መፍቀሬ ሰብእ – ሁል ጊዜ ንጽሕት የሆንሽ አምላክን የወለድሽ እመቤታችን እናከብርሻለን እናገንሻለን ሰውን ከሚወድ ልጅሽ ይቅርታን እናገኝ ዘንድ ወደ አንቺ እናጋጥጣለን/እንለምናለን። አያይዘህ ጸሎታ በል ቀጥሎ ተፈሥሒ ማርያም ለአዳም ፋሲካሁ፣ ኦ ፍጡነ ረድኤት ብሎ ሦስት ተአምረ ማርያም አንድ ተአምረ ኢየሱስ ማንበብ ነው፤ መልክአ ሥዕል አልቦ። የትንሣኤ ተአምር መቅድም የለውም፤ ከተአምር ቀጥሎ ሥርዐተ ቅዳሴ ይደርሳል፤ ከሥርዐተ ቅዳሴው ላይ ዘጠኝ ኪዳን ይደርሳል፤
ከኪዳን ቀጥሎ ምስባክ፦
ወተንሥአ እግዚአብሔር ከመ ዘንቃሕ እምንዋም፤
ወከመ ኃያል ወኅዳገ ወይን፤
ወቀተለ ፀሮ በድኅሬሁ። መዝ ፸፯፥፷፭
ትርጉም፦
እግዚአብሔር ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ፤
የወይን ስካር እንደ ተወው እንደ ኃያልም ሰው፤
ጠላቶቹንም በኋላው ገደለ።
ምሥጢር፦
የተኛ ሰው ፈጥኖ እንዲነሣ እግዚአብሔር ከሰባ ዘመን በኋላ በረድኤት ተነሣ አንድም በአሕዛብ ላይ በመዓት ተነሣ፤
ከመ ዘኀደጎ ስካረ ወይን – የወይን ስካር እንደተወው ሲል ነው። የወይን ስካር እንዳለፈለት አርበኛ ሰው። አንድም ከመ ኅዱግ ወይን ይላል እንደተጣለ ወይን። በሀገራቸው ጽኑ መጠጥ አለ ሰው የጠጣው እንደሆነ ሦስት ቀን ወድቆ ይሰነብታል በሦስተኛው ቀን ጤና አግኝቶ ኃይል ተሰምቶት ይነሣል። አንድም ወይን በተተከለ በሦስት ዓመት ዳስ ጥለውለት ያፈራል። አንድም ይህን ወይን በሐምሌ በነሐሴ ከምድር ይጥሉታል፤ ገዝፎ እንዲነሣ፤ በመስከረም በጥቅምት ፈጥኖ ይነሣልና። አንድም ወይን በክረምት ወድቆ ይከርማል በበጋ ዳስ ጥለው በዚያ ላይ ያደርጉታል ይለመልማል ያብባል ያፈራል ጌታም ትሩፋንን ከባቢሎን አውጥቷቸዋልና።
ለእስራኤል ከፈረደ በኋላ በአሕዛብ ፈረደባቸው። አንድም እስራኤልን ተከትለው የመጡ ግብጻውያንን አሰጠመ። አንድም በዘድኅሬሁ ይላል ወደኋላው በተመለሰ ውኃ ግብጻውያንን አጠፋ።
አንድም ወተንሥአ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር አድሮ ተነሣ የወይን ስካር እንዳለፈለት ሰው። ያ ፈጥኖ እንዲነሣ ጌታችንም ሦስት መዓልትና ሌሊት በከርሠ መቃብር አድሮ ተነሣ አንድም በርትቶ እንደተጣለ ወይን። ያንን ወይን የጠጣ አርበኛ በሦስተኛው ቀን ፈጥኖ እንዲነሣ ጌታችንም በሦስተኛው ቀን ተነሥቷልና።
ለአዳምና ለሔዋን ከፈረደላቸው በኋላ በአጋንንት ፈረደባቸው። አንድም በዘድኅሬሁ ይላል በኋለው በተተከለ መስቀል ዲያብሎስን ድል ነሣው። አንድም ተከታይ ጠላት ዲያብሎስን አንድም ታናሽ ጠላት ዲያብሎስን ድል ነሣው።
ከምስባክ ቀጥለህ ሦስት ወንጌል አንብብ፤ ማቴዎስን ማርቆስንና ሉቃስን። ዮሐንስን ለቅዳሴ አቆይ።
አያይዘህ መስቀል ይዘህ አርያም ምራ፤ ሃሌ ሉያ ለአብ ሃሌ ሉያ ለወልድ ሃሌ ሉያ ወለመንፈስ ቅዱስ ቀዳሚ ዜማ ግበሩ በዓለ በትፍሥሕት እስከ አቅርንቲሁ ለምሥዋዕ ዛቲ ፋሲካ ቀዳሚት ሕግ
– ቅድመ ዓለም ለነበረ ዓለምን አሳልፎ ለሚኖር ለአብ ምስጋና ይገባል ቅድመ ዓለም ለነበረ ዓለምን አሳልፎ ለሚኖር ለወልድ ምስጋና ይገባል ቅድመ ዓለም ለነበረ ዓለምን አሳልፎ ለሚኖር ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይገባል ዜማ መጀመሪያ ነው ቤተ ክርስቲያንን እስከመምላት ደርሳችሁ በደስታ በዓልን አድርጉ ይህች ፋሲካ ቀዳሚት ሕግ ናት።
ይህንን በመሪ በኩል ዝመም።
በአንሽ በኩል ያለምራት ሁለተኛውን አርያም ዝመም ሃሌ ሉያ ለአብ ሃሌ ሉያ ለወልድ ሃሌ ሃሌ ሉያ ወለመንፈስ ቅዱስ ይገብሩ በዓለ ሰማያት ይገብሩ በዓለ ደመናት ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ ተሐጺባ በደመ ክርስቶስ
– ሰማያት በዓልን ያደርጋሉ ደመናት በዓልን ያደርጋሉ ምድርም በክርስቶስ ደም ታጥባ ፋሲካን ታደርጋለች።
አያይዘህ ዮም ፍሥሐ ኮነ በል።
ምልጣን/አንገርጋሪ፦ ዮም ፍሥሐ ኮነ በሰንበተ ክርስቲያን እስመ ተንሥአ ክርስቶስ እሙታን ቀደሳ ወአክበራ እምኵሎን መዋዕል አልዓላ አማን (አማን በአማን) ተንሥአ እምነ ሙታን – ዛሬ በክርስቲያን ሰንበት ደስታ ሆነ ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቷልና ከዕለታት ሁሉ ለይቶ ቀደሳት አከበራት ከፍ ከፍ አደረጋት በእውነት ከሙታን ተለይቶ ተነሣ።
የምልጣኑን ሥርዓት ከፈጸምህ በኋላ አያይዘህ እስመ ለዓለም በል።
እስመ ለዓለም፦ ትንሣኤከ ለእለ አመነ ብርሃነከ ፈኑ ዲቤነ – ትንሣኤህን ለምናምን ብርሃንህን ወደኛ ላክ። የእስመ ለዓለሙን ሙሉ ሥርዐት ከአደረስህ በኋላ አያይዘህ የኪዳን ሰላም ይእቲ ማርያም በል።
ይ.ካ ሰላመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ብሎ እግዚኦ ይበል ቀጥሎ ኪዳን አድርስ ከኪዳን ቀጥሎ እንደ ሰዓቱ ስብሐተ ነግሁን ማድረስ ነው፤ በመጨረሻም ወደቅዳሴ መሄድ ነው።
፵፭ ይትፌሣሕ ሰማይ መዝሙር ዘትንሣኤ
፵፭.፩ (በ፩/ዩ) ይትፌሣሕ ሰማይ ወትትሐሠይ ምድር ወይንፍሑ ቀርነ መሠረታተ ሕምዝ ወይወውዑ አድባር ወአውግር ወኵሉ ዕፀወ ገዳም ወዮምሰ ዓባይ ፍሥሐ በሰማያት ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ ተሐጺባ በደመ ክርስቶስ።
ትርጕም፦
ሰማይ ደስ ይለዋል ምድርም ደስ ይላታል የምድር መሠረቶች መለከትን ይነፋሉ ተራራዎቹ ኮርብታዎቹ የምድረ በዳ እንጨቶች ሁሉ ይጮሃሉ ዛሬ በሰማያት ታላቅ ደስታ ነው ምድርም በክርስቶስ ደም ታጥባ ፋሲካን ታደርጋለች።
ምሥጢር፦
በዕለተ ትንሣኤ መላእክት ደስ ይላቸዋል አዝነው የነበሩ ሐዋርያት ደስ ይላቸዋል የኃጢአት መርዝ ያላቸው አጋንንት ያመሰግናሉ “አእመርናከ ከመ አንተ ቅዱሱ ለእግዚአብሔር – የእግዚአብሔር ቅዱስ ሆይ አንተ ማን እንደሆንህ አውቅናል” ብለው አመስግነዋልና ማር ፩፥፳፭፤ ሊቃነ ጳጳሳት ጳጳሳት ኤጲስ ቆጶሳት ቀሳውስት ዲያቆናት ምእመናን ሁሉ በትንሣኤ ደስ ብሏቸው ያመሰግናሉ።
፵፭.፪ ምንባብ ዘቅዳሴ፦
፩ቆሮ ፲፭፥፳ – ፵፩፤
፩ጴጥ ፩፥፩ – ፲፫፤
ግብ ፪፥፳፪ – ፴፯፤
ወንጌል፦ ዮሐ ፳፥፩ – ፲፱፤
ቅዳሴ፦ ዘዲዮስቆሮስ
ዳግም ትንሣኤ፦ ሁሉም ሥርዓት እንደ ትንሣኤ ነው። ከቅዳሴ በኋላ ምስባክ ተሰብኮ የዮሐንስ ወንጌል ዐሥራ ሰባተኛው ምዕራፍ ይነበባል፤ ሁለት አቡኖች ይባላሉ፤ እነሱም በከመ ይቤ እግዚእነ የሚለውና ይቤ ክርስቶስ የሚሉት ናቸው፤ ሁለቱን አቡኖች የሚገልጡት በወንጌሉ የተነበበውን ነው፤ ሁለት የሆኑበትም ምክንያት በመቃብሩ ራስጌና ግርጌ የነበሩት የሁለቱ መላእክት ምሳሌ ስለሆነ ነው። ይቤ ክርስቶስ የሚለው አቡን ተመርቶ ሥርዐተ መዋሥዕት ይደርሳል፤
፵፮ ወበእሑድ ሰንበት
መዝሙር ወበእሑድ ሰንበት በግእዝ አው በዓራራይ (ከትንሣኤ ሦስተኛው ሰንበት)
፵፮.፩ (በ፩/ፌ/፭/ር) ወበእሑድ ሰንበት ጌሠት ማርያም መግደላዊት በጽባሕ ኀበ መቃብር እንዘ ዓዲ ጽልመት ወረከበት ዕብነ ዕቱተ እምአፈ መቃብር ወበጽሐት ኀበ ስምዖን ጴጥሮስ ወኀበ ካልዕ ረድእ ዘያፈቅሮ ኢየሱስ ወትቤሎሙ ነሥእዎ ለእግዚእየ እምውስተ መቃብር ወኢየአምር ኀበ ወሰድዎ እንዘ ይረውጹ ክልኤሆሙ ኅቡረ በደሮ ለጴጥሮስ ዝኩ ካልዕ ረድእ ዘያፈቅሮ ኢየሱስ።
ትርጕም፦
በእሑድ ሰንበት መግደላዊት ማርያም በማለዳ ገና ጨለማ ሳለ ወደ መቃብር ገሠገሠች ደንጊያው ከመቃብሩ አፍ ተወግዶ አገኘች ወደ ስምዖን ጴጥሮስና ኢየሱስ ወደሚወደው ወደሁለተኛው ደቀመዝሙር ደረሰች እንዲህም አለቻቸው ጌታዬን ከመቃብር ወስደዉታል ወዴት እንደወሰዱትም አላውቅም ሁለቱ በአንድ ላይ ሲሮጡ ኢየሱስ የሚወደው ሌላው ደቀመዝሙር ጴጥሮስን ቀደመው።
፵፮.፪ የዕለቱ ምንባባት፦
፪ቆሮ ፭፥፲፩ – ፍጻሜ፤
፪ጴጥ ፫፥፲፬ – ፍጻሜ፤
ግብ ፳፩፥፴፩ – ፍጻሜ፤
ወንጌል፦ ሉቃ ፳፬፥፲፫ – ፴፫፤
ቅዳሴ፦ ዘዲዮስቆሮስ
፵፮.፫ የዕለቱ ምስባክ፦
ይእዜ እትነሣእ ይቤ እግዚአብሔር፤
እሬሲ መድኃኒተ ወአግህድ ቦቱ፤
ቃለ እግዚአብሔር ቃል ንጹሕ። መዝ ፲፩፥፭
ትርጕም፦
ዛሬ እነሣለሁ ይላል እግዚአብሔር፤
መድኃኒትን አደርጋለሁ በእርሱም እገለጣለሁ፤
የእግዚአብሔር ቃል ንጹሕ ቃል ነው።
ምሥጢር፦
አሜሃ ሲል ነው ያን ጊዜ እግዚአብሔር በረድኤት እነሣለሁ አለ፤
ድኅነቴን አደርጋለሁ በትድግናዬ ኃይሌን እገልጣለሁ አለ፤
አግህድ ሎቱ – ለድኃው ትድግናዬን እገልጥለታለሁ።
አግህድ ቦቱ – በባለጠጋው መዓቴን እገልጥበታለሁ አንድም በመዓት እገለጥበታለሁ (ባለጠጋ መሆን ክፋት አለው ማለት አይደለም ለድኃው የማይራራውን ባለጠጋ እቀጣለሁ ሲል ነው)
መድኃኒትን አደርጋለሁ ያለ እግዚአብሔር ከሐሰት ከዝርውነት ንጹሕ ነው። አንድም ይህን የተናገረበት ቃሉ ንጹሕ ነው ሐሰት የለበትም።
አንድም (ይእዜ እትነሣእ) ያን ጊዜ ሰው እሆናለሁ አለ እግዚአብሔር፤
አንድም ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር አድሬ እነሣለሁ አለ እግዚአብሔር፤
ትንሣኤዬን አደርጋለሁ ኃይሌን በትንሣኤዬ እገልጣለሁ፤
እትገሃድ ሎቱ – ለአዳም እገለጥለታለሁ። እትገሃድ ቦቱ – በዲያብሎስ እገለጥበታለሁ፤
አደርጋለሁ እገለጣለሁ ያለ እግዚአብሔር ከዕሩቅ ብእሲነት ንጹሕ ነው። (አምላክ ወልደ አምላክ ነው ሲል ነው)
ሚያዝያ ፳፩ በዓለ እግዝእትነ ማርያም
ዘነግህ ምስባክ፦
ወትቀውም ንግሥት በየማንከ፤
በአልባሰ ወርቅ ዑፅፍት ወኊብርት፤
ስምዒ ወለትየ ወርእዪ ወአጽምዒ ዕዝነኪ።
ወንጌል፦ ሉቃ ፩፥፴፱ – ፶፯፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
ኤፌ ፩፥፭ – ፳፩፤
፩ጴጥ ፪፥፬ – ፲፩፤
ግብ ፲፯፥፴ – ፍጻሜ፤
ወንጌል፦ ሉቃ ፲፯፥፩ – ፲፩፤
ቅዳሴ፦ ዘእግዝእትነ ማርያም
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
ወለገጽኪ ይትመሐለሉ ኵሎሙ አሕዛብ ብዑላነ ምድር፤
ኵሉ ክብራ ለወለተ ንጉሠ ሐሴቦን፤
በአዝጽፋረ ወርቅ ዑፅፍት ወኊብርት። መዝ ፵፬፥፲፪፤
ትርጒም፦
የምድር ባለጠጎች አሕዛብ ሁሉ በፊትሽ ይማለላሉ፤
ለሐሴቦን ንጉሥ ሴት ልጅ ሁሉ ክብሯ ነው፤
በወርቀ ዘቦ የተጐናጸፈችና የተሸፋፈነች ናት።
ምሥጢር፦
በዚህ ዓለም ከብረው ገነው የሚኖሩ ምእመናን ፊትሽን ለማየት ይማልዳሉ፤ ሐቤ ምዕት ቆርነሌዎስ የጴጥሮስን ፊት፣ ጢባርዮስ ቄሣር የዮሐንስን ፊት ለማየት እንደማለዱ፤
የባለአእምሮ ንጉሥ ልጅ ምእመን ሁሉ ክብሯ ነው፤ አልቦው ድሪው ድኮቱ ቀለበቱ፤ ቦ ዘእምውስጥ ይላል ለባለ አእምሮ ንጉሥ ልጅ ለምእመን ክብሯ ውሳጣዊ ነው፤ ከሰው ተለይታ ከአዳራሽ ገብታ እልፍኝ ተከታ ደጇን ዘግታ ነውና ሥራዋን የምትሠራ፤
በወርቀ ዘቦ ግምጃ አሸብርቃ ታጥቃ አለ ምግባር ሃይማኖትን አስተባብራ ይዛ፤
ቦ በዚህ ዓለም ከብረው ገነው የሚኖሩ ምእመናን የእመቤታችንን ፊት ለማየት ይማልዳሉ፤ ይስሐቅ መነኮስ ኦ እግዚኦ አርእየኒ እመከ እያለ ሰባት ለምኗል፤
የንጉሥ ልጅ እመቤታችን ክብሯ ውሳጣዊ ነው አይመረመርም፤ እንበለ ዘርዕ መውለዷ፤
ንጽሐ ሥጋን ንጽሐ ነፍስን ንጽሐ ልቡናን አስተባብራ ይዛ።
ሚያዝያ ፳፫ በዓለ ቅዱስ ጊዮርጊስ
ዘነግህ ምስባክ፦
ይቀጠቅጦሙ ለነገሥት በዕለተ መዓቱ፤
ወይኴንኖሙ ለአሕዛብ ወያበዝኅ አብድንተ፤
ወይሰብር አርእስተ ብዙኃን በዲበ ምድር። መዝ ፻፱፥፭፤
ትርጒም፦
ነገሥታትን በቊጣው ቀን ይቀጠቅጣቸዋል፤
በአሕዛብ መካከል ይፈርዳል፤ ሬሳዎችንም ያበዛል፤
በምድር ላይ የብዙዎችን ራሶች ይሰብራል።
ምሥጢር፦
በአብ እሪና ሆኖ በሚፈርድበት ቀን በዕለተ ምጽአት ቦ በማንኛውም ጊዜ ነገሥታቱን ቀጥቅጦ ያጠፋቸዋል፤
አሕዛብን እውነት ፈርዶ ያጠፋቸዋል ሬሳቸው ይበዛል፤ አንዱን ከሁለት ከሦስት ይከፍለዋል ማለት አይደለም የሚፈርድባቸው ብዙ ስለሆኑ ነው፤ ቦ የኃጥአንን ብዛት የጻድቃንን ማነስ መናገር ነው፤
በዚህ ዓለም የብዙዎችን ቸብቸቦ ሰብሮ ያጠፋል፤ ቦ የብዙዎቹን ሥልጣን ያጠፋል።
ወንጌል፦ ሉቃ ፲፪፥፩ – ፲፫፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
፪ቆሮ ፩፥፩ – ፲፪፤
፩ጴጥ ፩፥፮ – ፲፤
ግብ ፲፬፥፩ – ፳፫፤
ወንጌል፦ ማቴ ፲፥፲፮ – ፴፬፤
ቅዳሴ፦ ዘወልደ ነጐድጓድ ወይም ዘዲዮስቆሮስ
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
ወይርአዩ አሕዛብ በቅድመ አዕይንቲነ፤
በቀለ ደሞሙ ለአግብርቲከ ዘተክዕወ፤
ይባዕ ቅድሜከ ገዐሮሙ ለሙቁሐን። ትርጒምና ምሥጢሩን መስከረም ፲፩ ላይ ተመልከት።
ሚያዝያ ፳፱ ተዝካረ ልደቱ ለእግዚእነ
ዘነግህ ምስባክ፦
ምስሌከ ቀዳማዊ በዕለተ ኃይል፤
በብርሃኖሙ ለቅዱሳን፤
ወለድኩከ እምከርሥ እምቅድመ ኮከበ ጽባሕ።
ወንጌል፦ ሉቃ ፪፥፩ – ፰፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
ቈላ ፬፥፲ – ፲፬፤
፩ዮሐ ፬፥፱ – ፲፰፤
ግብ ፲፫፥፬ – ፲፮፤
ወንጌል፦ ሉቃ ፲፥፩ – ፲፪፤
ቅዳሴ፦ ዘዲዮስቆሮስ
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
አልቦ ነገር ወአልቦ ነቢብ ዘኢተሰምዐ ቃሎሙ፤
ውስተ ኵሉ ምድር ወጽአ ነገሮሙ፤
ወእስከ አጽናፈ ዓለም በጽሐ ነቢቦሙ። ትርጒምና ምሥጢሩን መዝሙር አሠርገዎሙ ላይ ተመልከት።
ግንቦት ፩ በዓለ ልደታ ለማርያም
ዘነግህ ምስባክ፦
ወለገጽኪ ይትመሐለሉ ኵሎሙ አሕዛብ ብዑላነ ምድር፤
ኵሉ ክብራ ለወለተ ንጉሠ ሐሴቦን፤
በአዝጽፋረ ወርቅ ዑፅፍት ወኊብርት። መዝ ፵፬፥፲፪፤
ወንጌል፦ ማቴ ፩፥፩ – ፲፰፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
ገላ ፬፥፩ – ፲፫፤
፩ጴጥ ፩፥፰ – ፲፫፤
ግብ ፯፥፵፬ – ፶፩፤
ወንጌል፦ ሉቃ ፩፥፴፱ – ፶፯፤
ቅዳሴ፦ ዘእግዝእትነ ማርያም
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
መሠረታቲሃ ውስተ አድባር ቅዱሳን፤
ያበድሮን እግዚአብሔር ለአናቅጸ ጽዮን፤
እምኵሉ ተዐይኒሁ ለያዕቆብ። መዝ ፹፮፥፩፤ ትርጉሙንና ምሥጢሩን ኅዳር ፲፩ ላይ ተመልከት።
፵፯ ተንሥአ ወአንሥአ
መዝሙር ተንሥአ ወአንሥአ (ከትንሣኤ አራተኛው ሰንበት)
፵፯.፩ (በ፫/ሙ) ተንሥአ ወአንሥአ ኵሎ ሙታነ ተንሥአ ወአንሥአ ወፈትሖሙ ለሙቁሐን (ተ) በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን ወአግዓዘ ነፍሰ ጻድቃን (ተ) ለአልዓዛር ተንሥእ ዘይቤሎ ወለዕውርኒ ዘፈወሶ በቃሉ (ተ) ትንሣኤሁ ገብረ በሰንበት በሣልስት ዕለት ተንሥአ ወአንሥአ ኵሎ ሙታነ ተንሥአ ወፈትሖሙ ለሙቁሐን።
ትርጉም፦
ተነሣ ሙታንን አነሣ የታሰሩትን ፈታ በታላቅ ኃይልና ሥልጣን ተነሣ የጻድቃንን ነፍስ ነጻ አወጣ አልዓዛርን ተነሥ ያለው ዐይነ ስውሩንም በቃሉ የፈወሰው ተነሣ ትንሣኤውን በሦስተኛው ቀን በሰንበት አደረገ።
፵፯.፪ የዕለቱ ምንባባት፦
ቈላ ፫፥፩ – ፍ፤
፩ጴጥ ፫፥፲፭ – ፍ፤
ግብ ፲፩፥፩ – ፲፱፤
ወንጌል፦ ሉቃ ፳፬፥፴፫ – ፵፭
ቅዳሴ፦ ዘዲዮስቆሮስ
፵፯.፫ የዕለቱ ምስባክ፦
አንሰ ሰከብኩ ወኖምኩ፤
ወተንሣእኩ እስመ እግዚአብሔር አንሥአኒ፤
ኢይፈርህ እምአዕላፍ አሕዛብ። መዝ፫፥፭
ትርጉም፦
እኔተኛሁ አንቀላፋሁም፤
እግዚአብሔር አንሥቶኛልና ተነሣሁ፤
ከአዕላፍ አሕዛብ የተነሣ አልፈራም።
ምሥጢር፦
ኖምኩ ወሰከብኩ ብለህ አዛውር እኔስ ሞትሁ ተቀበርሁ ብዬ ነበር፤
እግዚአብሔር እንዳልሞት እንዳልቀበር አድርጎኛልና ዳንሁ እንጂ።
የብዙ ብዙ ከሚሆኑ ከነአቤሴሎም ብዛት አልፈራም።
ስለምን እነአቤሴሎምን አሕዛብ አላቸው ቢሉ ስለብዛታቸው ነው አንድም በጸያፍ የገባ ነው ግብረ አሕዛብ ይሠሩ ነበርና፤ አንድም አቤሴሎም በእናቱ ከአሕዛብ ወገን ይወለዳልና።
አንድም (አንሰ ሰከብኩ) ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር አደርሁ
እግዚአብሔር አንሥቶኛልና ተነሣሁ አብ አንሥኦ መንፈስ ቅዱስ አንሥኦ ቢል አንድ ነው እሪናቸውን መናገር ነው። አንድም እግዚአብሔርነቴ አነሣኝ። ወተንሣእኩ በሥልጣነ ባሕቲትየ – በራሴ ሥልጣን ተነሣሁ እንዲል።
ከአቀብተ መቃብር ብዛት የተነሣ አልፈራም።
ግንቦት ፲፪ በዓለ ቅዱስ ሚካኤል ወፍልሰተ ዐፅሙ ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት
ዘነግህ ምስባክ፦
እስመ መምህረ ሕግ ይሁብ በረከተ፤
ወየሐውር እምኃይል ውስተ ኃይል፤
ወያስተርኢ አምላከ አማልክት በጽዮን።
ወንጌል፦ ማቴ ፭፥፩ – ፲፯፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
፩ቆሮ ፮፥፩ – ፱፤
ይሁዳ ፩፥፱ – ፲፬፤
ግብ ፲፫፥፲፮ – ፳፤
ወንጌል ሉቃ ፲፥፳፱ – ፴፰፤
ቅዳሴ፦ ዘዮሐንስ አፈወርቅ
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
በዐመፃ ሰደዱኒ ርድአኒ፤
ሕቀ ክመ ዘእምደምሰሱኒ ውስተ ምድር፤
ወአንሰ ኢኀደጉ ትእዛዘከ። መዝ ፻፲፰፥፹፮፤
ትርጒም፦
በዐመፃ አሳደዉኛል እርዳኝ፤
ከምድር ሊያጠፉኝ ጥቂት ቀርቷቸው ነበር፤
እኔ ግን ትእዛዝህን አልተውሁም።
ምሥጢር፦
በዐመፅ በግፍ ሀገር አስጥለው ሰደዉኛልና እርዳኝ፤
ከባቢሎን ቦ ከዚህ ዓለም ሊያጠፉኝ ጥቂት ቀርቷቸው ነበር፤ ቦ ወደ መቃብር ሊያወርዱኝ ጥቂት ቀን ብቻ ቀርቶኝ ነበር፤
እኔ ግን ሕግህን አልረሳሁም አላፈረስሁም።
አማራጭ ምስባክ፦
ወእምኲሉ ያድኅኖሙ እግዚአብሔር፤
እግዚአብሔር የዐቅብ ኲሎ አዕፅምቲሆሙ፤
ወኢይትቀጠቀጥ አሐዱ እምውስቴቶሙ፤ መዝ ፴፫፡፲፱፤
ትርጒም፦
እግዚአብሔር ካገኛቸው መከራ ሁሉ ያድናቸዋል፤
እግዚአብሔር አጥንቶቻቸውን ሁሉ ይጠብቃል፤
ከአጥንቶቻቸው አንዱ ስንኳ አይጎዳም።
ምሥጢር፦
እግዚአብሔር ከልዩ ልዩ መከራ ያድናቸዋል፤
ዐፅመ ኤልሳዕን እንደ ጠበቀ ዐፅማቸውን ይጠብቃል፤
ከወገናቸው ቦ በቃል ኪዳናቸው ከታመነ አንዱ ስንኳ አይጐዳም።
፵፰ አርአየ ሥልጣኖ
መዝሙር አርአየ ሥልጣኖ (ከትንሣኤ አምስተኛው ሰንበት)
፵፰.፩ (በ፮/ፋኝ) አርአየ ሥልጣኖ ላዕለ ሞት አርአየ ሥልጣኖ ላዕለ ሞት ንጉሠ ነገሥት እግዚአ አጋዕዝት (አ) ዘይሴብሕዎ ሊቃነ መላእክት ይሰግዱ ሎቱ ቅድሜሁ በፍርሃት (አ) ይቤሎሙ ኢየሱስ ለአይሁድ አመ ይእኅዝዎ በይእቲ ሌሊት (አ) ተናገሮሙ ወይቤሎሙ ከመ ሰራቂ መጻእክሙ ተአኀዙኒ በመጥባሕት (አ) ኦ ትዕግሥት ወአርምሞት በፍቅረ ዚአነ በጽሐ እስከለሞት (አ) ወንሕነኒ ንግበር በዓለነ ቅድስተ ፋሲካ በሐሤት አርአየ ሥልጣኖ ላዕለ ሞት ገባሬ ሕይወት ክርስቶስ።
ትርጉም፦
ሥልጣኑን በሞት ላይ ገለጠ የነገሥታት ንጉሥ የጌቶች ጌታ ነው። የመላእክት አለቆች ያመሰግኑታል በፊቱ በፍርሃት ይሰግዱለታል። በዚያች ሌሊት አይሁድ በያዙት ጊዜ ኢየሱስ አላቸው። ተናገራቸው እንዲህም አላቸው በሰይፍ እንደሌባ ልትይዙኝ መጣችሁን አላቸው። ምን ዐይነት ትዕግሥት ምን ዐይነት ዝምታ ነው በእኛ ፍቅር እስከሞት ደረሰ። እኛም የተቀደሰች ፋሲካን በደስታ በዓልን እናድርግ ሕይወትን የሠራ ክርስቶስ ሥልጣኑን በሞት ላይ ገለጠ።
፵፰.፪ የዕለቱ ምንባባት፦
ሮሜ ፮፥፩ – ፲፭፤
፩ጴጥ ፬፥፬ – ፲፪፤
ግብ ፳፫፥፲፭ – ፳፪፤
ወንጌል፦ ዮሐ ፳፩፥፲፭ – ፍጻሜ፤
ቅዳሴ፦ ዘዲዮስቆሮስ
፵፰.፫ የዕለቱ ምስባክ፦
እስመ ሰበረ ኆኃተ ብርት፤
ወቀጥቀጠ መናሥግተ ዘሐፂን፤
ወተወክፎሙ እምፍኖተ ጌጋዮሙ። መዝ ፻፮፥፲፯
ትርጕም፦
የናሱን ደጆች ሰብሯልና፤
የብረቱንም መወርወሪያ ቀጥቅጧልና፤
ከበደላቸው ጎዳና ተቀበላቸው።
ምሥጢር፦
ኃያላኑን አጥፍቷልና አንድም መርገመ ሥጋን መርገመ ነፍስን ሠራዊተ አጋንንትን አጥፍቷልና።
ነገሥታቱን መኳንንቱን ኃያላኑን አንድም ሊቃነ አጋንንትን አጠፋ።
በድለው ከሄዱበት ሀገር ከባቢሎን በረድኤት አንድም ከመከራ በንስሐ ተቀበላቸው። አንድም ኃጢአት ሠርተው ከሄዱበት ሀገር ከሲኦል በልጅነት ተቀበላቸው።
፵፱ ፋሲካ
መዝሙር ፋሲካ (ከትንሣኤ ስድስተኛው ሰንበት)
፵፱.፩ (በ፫/ሙ) ፋሲካ ዛቲ ዕለት ቅድስት ይእቲ ፋሲካ ዛቲ ዕለት ንትፈሣሕ ባቲ (ፋ) ንትፈሣሕ ባቲ ወንትሐሠይ ባቲ (ፋ) ዛቲ ዕለት ናኅይ ወዕረፍት (ፋ) ሰማይ ወምድር ይትፌሥሑ ባቲ ፋሲካ ፋሲካ ፋሲካ ፋሲካ ተዝካረ ትንሣኤሁ ለመድኃኒነ።
ትርጉም፦
ፋሲካ! ይህች ዕለት ቅድስት ናት ይህች ቀን ፈጽመን የምንደሰትባት ቀን ናት ይህች ዕለት ፍጹም የዕረፍት ቀን ናት ሰማይና ምድር ይደሰቱባታል ፋሲካ የመድኃኒታችን የትንሣኤው መታሰቢያ ናት።
፵፱.፪ የዕለቱ ምንባባት፦
ሮሜ ፬፥፲፬ – ፍ፤
ራእይ ፳፥፩ – ፍ፤
ግብ ፲፥፴፱ – ፵፬፤
ወንጌል፦ ዮሐ ፳፩፥፩ – ፲፭
ቅዳሴ፦ ዘዲዮስቆሮስ
፵፱.፫ የዕለቱ ምስባክ፦
በልዑ ወጸግቡ ጥቀ፤
ወወሀቦሙ ለፍትወቶሙ፤
ወኢያኅጥኦሙ እምዘፈቀዱ። መዝ ፸፯፥፳፱
ትርጕም፦
በሉ እጅግም ጠገቡ፤
ለምኞታቸውም ሰጣቸው፤
ከወደዱት አላሳጣቸውም።
ምሥጢር፦
በልተው ፈጽመው ጠገቡ። ምግቡም የባሕር ዶሮ ዓሣ ድርጭት ነው። ሲያዩት አሸዋ ሲበሉት ስብ ይመስላል።
አንድም ጥጋቡ ምንድነው ቢሉ መናውን ሰለቹት ተጠየፉት ሲል ነው። “ሕዝቡም… እንጀራ የለም ውኃ የለም ሰውነታችንም ይህንን ቀላል እንጀራ ተጸየፈ ብለው ተናገሩ” እንዲል ዘኊ ፳፩፥፭
(ወወሀቦሙ) ፈቃዳቸውን ለመፈጸም የሚሹትን ሁሉ ሰጣቸው። አንድም ፈቃዳቸውን ሊፈጽሙበት ሰጣቸው።
(ወኢያኅጥኦሙ) ከሚሹት ነገር ሁሉ አላሳጣቸውም ሥጋ ቢሉ ሥጋ መና ቢሉ መና ሰጣቸው።
ግንቦት ፳፩ ተዝካረ በዓላ ለእግዝእትነ ማርያም
ዘነግህ ምስባክ፦
ወለገጽኪ ይትመሐለሉ ኵሎሙ አሕዛብ ብዑላነ ምድር፤
ኵሉ ክብራ ለወለተ ንጉሠ ሐሴቦን፤
በአዝጽፋረ ወርቅ ዑፅፍት ወኊብርት። መዝ ፵፬፥፲፪፤
ወንጌል፦ ሉቃ ፩፥፴፱ – ፶፯፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
፩ቆሮ ፮፥፱ – ፍጻሜ፤
ራእይ ፲፪፥፩ – ፭፤
ግብ ፯፥፵፬ – ፶፩፤
ወንጌል፦ ማቴ ፲፰፥፮ – ፲፪
ቅዳሴ፦ ዘእግዝእትነ ማርያም
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
ሠወርከኒ በዕለተ ቀትል መልዕልተ ርእስየ፤
ኢትመጥወኒ እግዚኦ እምፍትወትየ ለኃጥአን፤
ተማከሩ ላዕሌየ ኢትኅድገኒ ከመ ኢይዘኀሩ። መዝ ፻፴፱፥፯፤
ትርጒም፦
በጦርነት ቀን በራሴ ላይ ሆነህ ሰወርኸኝ፤
አቤቱ ከምኞቴ የተነሣ ለኃጢአተኞች አትስጠኝ፤
በላዬ ተማከሩ እንዳይታበዩ አትተወኝ።
ምሥጢር፦
በሰልፍ ቀን በእኔ አድረህ አዳንኸኝ፤ ቦ በራሴ ላይ እንደ ድባብ ሆነህ ጠበቅኸኝ፤ ያ ከዋዕየ ፀሐይ እንዲያድን ከተጣለ ጠጠር ከተወረወረ ጦር አዳንኸኝ፤
ወድጄ በሠራሁት ኃጢአቴ ለኃጥአን ለነሳኦል አሳልፈህ አትስጠኝ፤
እኔን ገድለው ሊታበዩ መክረዋልና በረድኤት አትለየኝ።
፶ በሰንበት ዐርገ ሐመረ
መዝሙር ዘዕርገት
፶.፩ (በ፫/ፈ) በሰንበት ዐርገ ሐመረ ገሠፀ ባሕረ ወገሠፆሙ ለነፋሳት ወይቤሎሙ ኢትናፍቁ ወኢይምጻእ ኑፋቄ ውስተ ልብክሙ በከመ ፈነወኒ አቡየ አነኒ እፌንወክሙ ውስተ ቤተ አቡየ ብዙኅ ማኅደር ቦቱ ካዕበ እመጽእ ወእነሥአክሙ ከመ ተሀልዉ ምስሌየ በመንግሥተ አቡየ ዘበሰማያት።
ትርጕም፦
በሰንበት ወደመርከብ ወጣ ባሕርን ጸጥ አደረገ ነፋሳትንም ገሠፀ አትጠራጠሩ ወደልባችሁ ጥርጥር አይግባ አባቴ እኔን እንደላከኝ እኔም እልካችኋለሁ በአባቴ ቤት ብዙ ማደሪያ አለ አላቸው በሰማያት ባለ በአባቴ መንግሥት ትኖሩ ዘንድ ዳግመኛ መጥቼ እወስዳችኋለሁ።
፶.፪ የዕለቱ ምንባባት፦
ሮሜ ፲፥፩ – ፍጻሜ፤
፩ጴጥ ፫፥፲፭ – ፍጻሜ፤
ግብ ፩፥፩ – ፍጻሜ፤
ወንጌል፦ ሉቃ ፳፬፥፵፭ -ፍጻሜ፤
ቅዳሴ፦ ዘዲዮስቆሮስ
፶.፫ የዕለቱ ምስባክ፦
ዐርገ እግዚአብሔር በይባቤ፤
ወእግዚእነ በቃለ ቀርን፤
ዘምሩ ለአምላክነ ዘምሩ። መዝ ፵፮፥፭
ትርጕም፦
እግዚአብሔር በዕልልታ ዐረገ፤
ጌታችን በመለከት ድምፅ ዐረገ፤
ዘምሩ ለአምላክችን ዘምሩ።
ምሥጢር፦
ዐርገ እግዚአብሔር እግዚእነ በይባቤ ወበቃለ ቀርን ብለህ ግጠም።
ጌታችን እግዚአብሔር ከሰባ ዘመን በኋላ በዘሩባቤል አድሮ ትሩፋንን ይዞ ነጋሪት እያስመታ ሳንቲ ዛንጉፍ መለከት እያስነፋ ድብ አንበሳ እያሳበ ከባቢሎን ወደኢየሩሳሌም ወጣ። የዘሩባቤል መንግሥት የጌታ ፈቃድ ስለሆነ የዘሩባቤልን ለጌታ ሰጥቶ ዐርገ አለ።
አንድም በይባቤ መላእክት በቅዳሴ በብርሃን በሥልጣን ዐረገ።
ለአምላካችን ምስጋና አቅርቡ አንድም ፈጽማችሁ አመስግኑ።
፶፩ ወረደ መንፈስ
መዝሙር ወረደ መንፈስ ቅዱስ (ከጰራቅሊጦስ የመጀመሪያው ሰንበት)
፶፩.፩ (በ፪/ዘዮ) ወረደ መንፈስ ቅዱስ ላዕለ ሐዋርያት ከመ ዘእሳት ወተናገሩ በነገረ ኵሉ በሐውርት።
ትርጕም፦
መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ እንደ እሳት ሆኖ ወረደ በሀገሩ ሁሉ ቋንቋ ተናገሩ።
፶፩.፪ የዕለቱ ምንባባት፦
ኤፌ ፬፥፩ – ፲፯፤
፩ዮሐ ፪፥፩ – ፲፰፤
ግብ ፪፥፩ – ፲፬፤
ወንጌል፦ ዮሐ ፲፬፥፳፪ – ፍጻሜ
ቅዳሴ፦ ዘዲዮስቆሮስ
፶፩.፫ የዕለቱ ምስባክ፦
ልበ ንጹሐ ፍጥር ሊተ እግዚኦ፤
መንፈሰ ርቱዐ ሐድስ ውስተ ከርሥየ፤
ኢትግድፈኒ እምቅድመ ገጽከ። መዝ ፶፥፲
ትርጕም፦
አቤቱ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፤
የቀናውን መንፈስ በውስጤ አድስ፤
ከፊትህ አትጣለኝ።
ምሥጢር፦
አቤቱ ንጹሕ ልቡናን ፍጠርልኝ ሌላ ልብ ፍጠርልኝ ማለቱ አይደለም ያንኑ ከኃጢአት ንጹሕ አድርግልኝ ሲል ነው። አንድም እንደገናማ ሲፈጥር ይኖራልን ብሎ ይግለጠው።
ልበ ያለውን መንፈሰ፤ ንጹሐ ያለውን ርቱዐ፤ ፍጥር ያለውን ሐድስ ብሎ ገለጠው ልቡናየን በእውቀት አድስልኝ።
ከገጸ መዓትህ የተነሣ በመከራው አትጣለኝ። አንድም ከባለሟልነት እንዳወጣኸኝ አትቅር።
መልእክት፦
ንጹሕ ልብ ነቅዐ አንብዕ፣ ነቅዐ ርኅራኄ፣ ነቅዐ ትዕግሥት፣ ነቅዐ ተአምኖ፣ ነቅዐ ስምዕ፣ ነቅዐ ምሕረት፣ ነቅዐ ትሕትና ነው። ማር ይስሐቅ “ንጹሕ ልብ በጸሎት ጊዜ እየጮኸ ዕንባን ያጎርፋል” ብሏል ማር ይስሐቅ አንቀጽ ፪ ምዕራፍ ፲፩፤ ሌላውን የንጹሕ ልብ መገለጫ ሲናገር ደግሞ እንዲህ አለ “ንጽሕናን የምትወድ ከሆንህ የጐሰቈሉ ሐሳቦችን ዘወትር መጻሕፍትን በማንበብና በጸሎት አስወግዳቸው” ማር ይስሐቅ አንቀጽ ፫ ምዕራፍ ፭፤
እግዚአብሔርን የማየት መሠረቱ ንጹሕ ልቡና መሆኑ በተራራው ስብከት ተነግሯል “ልበ ንጹሐን ብፁዓን ናቸው እግዚአብሔርን ያዩታልና” እንዲል ማቴ ፭፡፰፤
ንጹሕ ልብ እግዚአብሔርን የማየት መሠረት ነው ስንል ለእግዚአብሔር አልቦ ዘርእዮ ግሙራ የሚለውን ዘንግተን አይደለም በዘፈቀደ ተገልጦ ነው እንደሚታይ በባሕርዩ ግን ያየው የየው እንደሌለ እናውቃለን እናምናለን። ለሙሴ “ፊቴን አይቶ መዳን የሚችል የለም” ተብሎ እንደተነገረውም ከመጻሕፍት እናነባለን ዘጸ ፴፫፡፳፤ በደብረ ታቦርም መለኮታዊ ክብሩን በገለጠ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ በግንባራቸው ወደምድር ወድቀዋል ማቴ ፲፯፡፮፤ ምሥጢሩ ከዚያ ማዶ ቤት አየሁ ዱር አየሁ ገደል አየሁ ባሕር አየሁ እንደ ማለት ነው፤ በውስጡ ያለው ተመርምሮ እንዳይታወቅ።
ስለሆነም እግዚአብሔርን ማየት ማለት እንደ እግዚአብሔርነቱ አውቆ ማመን ማምለክ መገዛት ማመስገን ማለት ነው። “ወአወጽእ ልበ እብን እምሥጋክሙ ወእሁበክሙ ልበ ዘሥጋ – የድንጋዩን ልብ ከሥጋችሁ አወጣለሁ የሥጋን ልብን እሰጣችኋለሁ” ተብሎ የተነገረው እግዚአብሔርን የማያውቀው ልብ እግዚአብሔርን ወደማወቅ መምጣቱን ለማስረዳት ነው። ሕዝ ፴፮፡፳፮፤
አለባበሳችንን አሳምረን ልባችንን አሳድፈን የምንሰጠው አገልግሎት በውኃ ውስጥ እንደሚናገር ግን ሰሚ እንደማያገኝ ሰው መሆን ነው፤ “ወትከውኒ ከመ ዘይትናገር በታሕተ ማይ ወትደክሚ ወይቴሐት ቃልኪ በውስተ ማይ – በውኃ ውስጥ እንደሚናገር ሰው ትሆኛለሽ ትደክሚያለሽ ቃልሽ በውኃ ውስጥ እንዳለ ድምፅ ዝቅ ይላል” እንዲል ኢሳ ፳፰፡፬፤
ልቡ ንጹሕ ያልሆነ ሰው ሰነፍ ነው፤ ሰነፍ ደግሞ እግዚአብሔር የለም ወደማለት ይደርሳል፤ መዝ ፲፫፡፩፤ የክፋት መዝገብ ስለሚሆን መልካም ነገር አውጥቶ መናገር አይችልም ማቴ ፲፪፡፴፬፤
ልቡ ንጹሕ የሆነለት ሰው የሚጸልየው ጸሎት በአምላኩ ዘንድ ያለው ተሰሚነት ከአፍ እስከ ጆሮ እንደሚሰ’ማው ነው፤ “ጸሎቱ ለትሑተ ልብ እምአፍ እስከ ዕዝን – የትሑት ሰው ጸሎት ከአፍ እስከ ጆሮ ነው” እንዲል ማር ይስሐቅ አንቀጽ ፫ ምዕራፍ ፲፩፤ ብዝኀ ትሕትና ባለበት የእግዚአብሔር ክብር በዝቶ ይገለጣል፤ ትሑትና የዋህ ልብ ያለውን ሰው እግዚአብሔር አይንቅምና መዝ ፶፡፲፯፤ በወንጌል የተመዘገበውም “ከእኔ ተማሩ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና” ተብሎ ነውና ማቴ ፲፩፡፳፱፤
አረጋዊ መንፈሳዊ ልቡናችን ንጹሕ የሚሆንበት ጊዜ፣ ቦታና ምክንያት ሲገልጥ እንዲህ አለ፤ “ወአመ ትትሜጦ ምሥጢራተ ቅድሳት አእትት ግዘፈ ልብከ – ሥጋውን ደሙን በምትቀበልበት ጊዜ የልብህን ድንዳኔ አርቅ” አረጋዊ መንፈሳዊ ድርሳን ፲፬፤
ይሁዳ ማኅደረ ሰይጣን የሆነውና ከሐዋርያት አንድነት የተለየው በልቡ ደንዳናነት ነው፤ በአካሉ ከሐዋርያት ጋር ተቀምጧል በልቡ ከአይሁድ ጋር እየመከረ እንዴት አሳልፎ እንደሚሰጠው ምቹ ጊዜ ይሻ ነበር። በከንፈር እያከበሩ በአፍ እየቀረቡ በልብ መራቅ ይሁዳዊነት ነው ኢሳ ፳፱፡፲፫፤ ለዚህ ነው ነቢዩ “አቤቱ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ” ያለው። በንጹሕ ልብ እናመልከው ዘንድ ልባችንን በቃሉ ንጹሕ ያድርግልን።
የወንጌሉ መልእክት፦
ክፍለ ንባቡ የሚጀምረው በጥያቄ ነው፤ የአስቆሮቱ ይሁዳ ያይደለ ታዴዎስ በመባል የሚታወቀው ይሁዳ ለዓለሙ ያይደለ ለእኛ ራስህን ትገልጥ ዘንድ ያለህ እንዴት ነው ብሎ ይጠይቃል፤ ጌታችን ኢየሱስም ሲመልስ “የሚወደኝ ቃሌን ይጠብቅ” ብሎታል። እግዚአብሔር ፍቅር ነው፤ ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡና እግዚአብሔር የተገለጠላቸው ሁሉ በፍቅር ይኖራሉ፤ መለያቸው መገለጫቸው ፍቅር ነው። እርስ በእርሳችሁ የምትፋቀሩ ከሆነ የእኔ ደቀ መዛሙርት መሆናችሁን ሁሉም ያውቃል ዮሐ ፲፫፡፴፭፤ ስለዚህ የማዛችሁ ትእዛዝ እርስ በእርሳችሁ ትፋቀሩ ዘንድ ነው ብሏቸዋል ለደቀ መዛሙርቱ ዮሐ ፲፭፡፲፰፤
ቃሉን በሚጠብቁ ሁሉ ላይ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ያድሩባቸዋል አብ በወልድ ስም የሚልከው ጰራቅሊጦስ መንፈስ ቅዱስ ሁሉን ያስተምራቸዋል የተማሩትን እንዲያስታውሱት እንዳይዘነጉት ያደርጋቸዋል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚሰጠው ዓለም እንደሚሰጠው ያለውን አይደለም፤ ምክንያቱም ዓለም ሊሰጥ የሚችለው ግዙፉን ነው፤ እሱ ግን የሚሰጠው ረቂቁን ነውና። ዓለም የሚሰጠው ቁም ነገር አልባ ለሆነ ነው፤ እሱ ግን የሚሰጠው አምነው ለለመኑት ሁሉ ነውና። ዓለም የሚሰጠው የአንዱን ነጥቆ ለአንዱ ነው፤ እሱ ግን ለእያንዳንዱ የሚያስፈልገውን ሁሉ ነውና። ዓለሙ ከሰጠ በኋላ ይጸጸታል፤ እሱ ግን ከሰጠ በኋላ ጸጸት የለበትምና። ዓለም ከሰጠ በኋላ እንደገና ሊነጥቅ ይችላል፤ እሱ እንደዚህ አያደርግምና የሚሰጠን ዓለሙ እንደሚሰጠን አይደለም።
የአባቱን ሰላም ስለሰጠን ልባችን አይደነግጥም ፍርሃት አይሰማንም እንደሚያር’ግ እንደሰማን ዳግም እንደሚመጣ ሰምተናል ወደ አብ በመሄዱ ደስታ እንጂ ኀዘን አይሰማንም፤ የሌለበት ቦታ የለምና፤ ሁል ጊዜ ከእኛ አይለይምና። ልባችንን መስታወት አድርገን ሁል ጊዜ እናየዋለንና። አረጋዊ መንፈሳዊ በሃያ ሰባተኛው ድርሳኑ “በመጽሔተ ልቡ ኅቱም አንተ ዘእንበለ ፈሊስ – ያለመንቀሳቀስ አንተ በልቡ መጽሔት ታትመሃል” እንዳለ። በዐይነ ነፍስ የጌትነቱን መልክ ያያሉ፤ አይተው አይሰለቹም፤ የእይታቸው ሁሉ ማረፊያ መደምደሚያ እሱ ነውና፤ “ዘበኀቤከ የዐርፍ ነጽሮተ ነባብያን – የተናጋሪዎች እይታ የሚያርፍብህ አንተ ነህ” እንዲል አረጋዊ መንፈሳዊ ድርሳን ፫፤ በንጽሐ ሥጋ ግዙፋኑን ፍጥረታት እነብሔሞትን እነሌዋታንን አድማስን ያያሉ በንጽሐ ነፍስ ረቂቃን ፍጥረታት ነፋሳትን ነፍሳትን መላእክትን ያያሉ በንጽሐ ልቡና ሥላሴን ያያሉ ከዚህ በኋላ ሌላ እንይ አይሉም እሱን ዘወትር እያዩ እያመሰገኑ ይኖራሉ።
በንባቡ ውስጥ “አብ ይበልጠኛል” የሚል ኃይለ ቃል አለ፤ ይህም በአብና በወልድ መካከል መበላለጥ አለ ማለት አይደለም፤ “እኔና አብ አንድ ነን” ዮሐ ፲፡፴፤ “እኔን ያየ አብን አየ…እኔ በአብ እንዳለሁ አብ በእኔ እንዳለ እመኑ” ዮሐ ፲፬፡፱፤ ተነግሯልና።
“ይበልጠኛል” ሲል ሦስት ምክንያቶችን ሊያስረዳን ነው፤ ፩. ሥግው ቃል ግዙፍ ሥጋን ተዋሕዷል፤ ፪. ብዙ ጸዋትወ መከራ ተቀብሏል፤ ፫. ሞትን ቀምሶ በመቃብር ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት አድሯል። እነዚህ ሦስት ምክንያቶች በአብ ዘንድ ስለሌሉ አብ ይበጠኛል አለ። በመዝሙር ስምንት “ከመላእክት ጥቂት አሳነስኸው” የተባለው መላእክትን ሕያዋን አድርጎ የፈጠረ እሱ በለበሰው ሥጋ ሞትን ስለቀመሰ ነው እንጂ ከመላእክት አንሶ አይደለም የመላእክት ጌታ ነው እንጂ።
በተደረገ ጊዜ የበለጠ በሃይማኖት ይጸኑ ዘንድ ወደፊት የሚሆነውን ሳይሆን አስቀድሞ ይነግራቸዋል የሚሰቀልበት ጊዜ እየተቃረበ ስለሆነ ከእንግዲህ ወዲህ ከእናንተ ጋር ብዙ አልነጋገርም የዚህ ዓለም ገዥ የሆነው ዲያብሎስ ይመጣል ማለት በአይሁድ አድሮ ይከሰኛል ነገር ግን በእኔ ላይ ምንም አያገኝም ይላቸዋል፤ ንጹሐ ባሕርይ ነውና፤ በሐልዮ በነቢብ በገቢር ምንም ምን ነውር የለበትምና። ለዚህም ነው የሐሰት ምስክር ፍለጋ የሄዱት፤ ለዚህ ነው ትንሣኤውንም በገንዘብ ኃይል ለማስተባበል ዋጋ የከፈሉት።
አባቴን እንደምወደው ዓለም ያውቅ ዘንድ የሰጠኝን ትእዛዝ እፈጽማለሁ እንደዚሁም ሁሉ እናንተንም ወደ ዓለም እልካችኋለሁ የምልካችሁም ትሰ’ቀሉና ትሞቱ ዘንድ ልዩ ልዩ መከራ ትቀበሉ ዘንድ ነው ብሎ ወደፊት የሚጠብቃቸውን ይነግራቸዋል።
ግንቦት ፳፱ ተዝካረ ልደቱ ለእግዚእነ
ዘነግህ ምስባክ፦
ምስሌከ ቀዳማዊ በዕለተ ኃይል፤
በብርሃኖሙ ለቅዱሳን፤
ወለድኩከ እምከርሥ እምቅድመ ኮከበ ጽባሕ።
ወንጌል፦ ፪፥፩ – ፰፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
ገላ ፬፥፩ – ፲፪፤
፩ዮሐ ፬፥፱ – ፲፰፤
ግብ ፲፪፥፯ – ፲፪፤
ወንጌል፦ ማቴ ፭፥፩ – ፲፯፤
ቅዳሴ፦ ዘሠለስቱ ምዕት
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
ወተግሣጽከ ውእቱ ዘይሜህረኒ፤
ወአርኀብከ መከየድየ በመትሕቴየ፤
ወኢደክመ ሰኰናየ። መዝ ፲፯፥፴፰፤
ትርጒም፦
የሚያስተምረኝ ተግሣጽህ ነው፤
አረማመዴን በታች አሰፋህ፤
ሰኰናዬም አልደከመም።
ምሥጢር፦
ሕግህ መምህሬ ነው፤
ከእግሬ በታች ጫማዬን አሰፋኸው፤ ብሮጥ ብገሠግሥ አንዳልደክም አደረግኸኝ፤ ቦ የጫማ መስፋት አያስመሰግንም ብሎ ጫማዬን መልቼ እንድሄድ አደረግኸኝ፤ ጠላት ያለበት ሰው አዩኝ አላዩኝ እያለ ይሄዳል እንጂ ጫማውን መልቶ አይረግጥምና፤
እግሬ አልደከመም፤ ቦ እግረ ልቡናየ ሰኰና ሕሊናየ በአምልኮ ጣዖት በገቢረ ኃጢአት አልተሰነካከለም።
፶፪ ዐርገ እግዚአብሔር
መዝሙር ዐርገ እግዚአብሔር
፶፪.፩ (በ፫/ሙ) ዐርገ እግዚአብሔር በቃለ ቀርን በይባቤ ዐርገ ወበቃለ ቀርን ወነበረ በየማነ አቡሁ (ዐ) ዐርገ በስብሐት ውስተ ሰማያት ተኰነኑ ሎቱ መላእክት (ዐ) ተኰነኑ ሎቱ መላእክት ኵሉ ኃይል ወኵሉ ፍጥረት (ዐ) ዘምሩ ለአምላክነ ዘምሩ ዘምሩ ለንጉሥነ ዘምሩ።
ትርጕም፦
እግዚአብሔር በመለከት ድምፅና በዕልልታ ዐረገ በአባቱ ቀኝ ተቀመጠ በምስጋና ወደሰማይ ዐረገ መላእክት፣ ኃይላትና ፍጥረት ሁሉ ተገዙለት ለአምላካችን ዘምሩ ለንጉሣችን ዘምሩ።
፶፪.፪ የዕለቱ ምንባባት፦
፩ቆሮ ፲፬፥፩ – ፳፯፤
፩ዮሐ ፬፥፩ – ፱፤
ግብ ፲፥፵፬ – ፍጻሜ፤
ወንጌል፦ ዮሐ ፲፭፥፲፯ – ፍጻሜ፤
ቅዳሴ፦ ዘዲዮስቆሮስ
፶፪.፫ የዕለቱ ምስባክ፦
ኢትግድፈኒ እምቅድመ ገጽከ፤
ወመንፈሰከ ቅዱሰ ኢታውጽእ እምላዕሌየ፤
ዕሥየኒ ፍሥሐ ወአድኅኖተከ። መዝ ፶፥፲፩
ትርጕም፦
ከፊትህ አትጣለኝ፤
ቅዱስ መንፈስህን ከእኔ ላይ አትውሰድ፤
ደስታንና ማዳንህን ስጠኝ።
ምሥጢር፦
ከገጸ መዓትህ የተነሣ በመከራው አትጣለኝ። አንድም ከባለሟልነት እንዳወጣኸኝ አትቅር። ዳዊት ነው ቢሉ ጽኑ ረድኤትህን ምእመን ነው ቢሉ ልጅነትን ከእኔ አትውሰድ/አታርቅ።
በማዳንህ ደስ አሰኘኝ ዳዊት ነው ቢሉ የንስሐ ደጅ ጥናቴን ተዐደዋ እግዚአብሔር ለኃጢአትከ – እግዚአብሔር ኃጢአትህን ተወልህ የሚለውን ቃል አሰማኝ። ትሩፍ ነው ቢሉ የሰባ ዘመን ደጅ ጥናቴን ሚጠተ ሥጋውን አድርግልኝ። ምእመን ነው ቢሉ የአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ደጅ ጥናቴን በሐሙስ ዕለት ያለውን አድርግልኝ ይላል። አንድም በትድግናህ ልጅነትን ስጠኝ።
፶፫ ዘምሩ
መዝሙር ዘምሩ
፶፫.፩ (በ፫/ሙ) ዘምሩ ለእግዚአሔር ጻድቃኑ እስመ ተንሥአ ክርስቶስ እሙታን (ዘ) በህየ ሰበረ ኆኃተ ብርት ወበህየ አውጽአ ዘቀዳሚ ልሕኵቶ (ዘ) አርአዮ ለቶማስ ርግዘተ ገቦሁ ወለእንድርያስ ቅንዋተ እደዊሁ (ዘ) ዐርገ በስብሐት ውስተ ሰማያት በአርብዓ ዕለት ምስለ መላእክት ዘምሩ ለእግዚአብሔር ጻድቃኑ ወግነዩ ለዝክረ ቅድሳቱ።
ትርጕም፦
ጻድቃን ለእግዚአብሔር ዘምሩ ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቷልና በዚያ የብረት ደጅን ሰበረ በዚያ የመጀመሪያ ሥራውን አወጣ ለቶማስ የጎኑን መወጋት አሳየው ለእንድርያስም የእጆቹን ችንካሮች አሳየው በአርባኛው ቀን ከመላእክት ጋር በምስጋና ወደሰማይ ዐረገ።
፶፫.፪ የዕለቱ ምንባባት፦
፩ቆሮ ፲፪፥፩ – ፲፪፤
፩ዮሐ ፪፥፳ – ፍ፤
ግብ ፪፥፲፬ – ፳፪፤
ወንጌል፦ ዮሐ ፲፮፥፩ – ፲፯
ቅዳሴ፦ ዘዲዮስቆሮስ
፶፫.፫ የዕለቱ ምስባክ፦
ወበመንፈስ አዚዝ አጽንዐኒ፤
ከመ እምሐሮሙ ለኃጥአን ፍኖተከ፤
ወረሲዓን ይትመየጡ ኀቤከ። መዝ ፶፥፲፪
ትርጕም፦
በጽኑ መንፈስ አጽናኝ፤
መንገድህን ለኃጥአን አስተምራቸው ዘንድ፤
ዝንጉዎች ወደ አንተ ይመለሱ ዘንድ።
ምሥጢር፦
በመንፈሰ ረድኤት አንድም በልጅነት አጽናኝ።
እኔ ተምሬ ኃጥአንን አስተምራቸው ዘንድ ረሲዓንም ተምረው ወዳንተ ይመለሱ ዘንድ።
አንድም ከመ እምሐሮሙ ለኃጥአን ረሲዓን ወይትመየጡ ኀቤከ ብሎ ይገጥሟል። ሕግህን ለዘነጉ ለኃጥአን ሕግህን አስተምራቸው ዘንድ ወዳንተም ይመለሱ ዘንድ።

