፶፱ ይሰጠዎ
መዝሙር ይሰጠዎ ከሐምሌ ፫ እስከ ሐምሌ ፱
፶፱.፩ (በ፩/ዩ) ይሰጠዎ ወይሰምዖ ጸሎቶ ለኵሉ ለዘሰአሎ እግዚኣ ለሰንበት አምላከ ምሕረት ያርኁ ክረምተ በበዓመት ይሰምዑ ቃሎ ደመናት።
ትርጉም፦
ይመልስለታል የለመነውን ሁሉ ጸሎቱን ይሰማዋል የይቅርታ አምላክ የሰንበት ጌታ በየዓመቱ ክረምትን ይከፍታል (በጋና ክረምትን ያፈራርቃል) ደመናት ቃሉን ይሰማሉ።
፶፱.፪ የዕለቱ ምንባባት፦
ዕብ ፮፥፯ – ፍ፤
፩ጴጥ ፫፥፰ – ፲፭፤
ግብ ፲፬፥፰ – ፲፱፤
ወንጌል፦ ማቴ ፲፫፥፩ – ፴፩
ቅዳሴ፦ ዘእግዚእነ
፶፱.፫ የዕለቱ ምስባክ፦
አርውዮ ለትለሚሃ፤
ወአሥምሮ ለማእረራ፤
ወበነጠብጣብከ ትበቊል ተፈሢሓ። መዝ ፷፬፥፲
ትርጕም፦
ትልሟን አርካው፤
መከሯንም አብጀው፤
በነጠብጣብህም ደስ ብሏት ትበቅላለች።
ምሥጢር፦
የኢየሩሳሌም ትልሟን አርካው፤
መከሯንየ በጀ/የሚጠቅም አድርገው፤
እንዲህ የሆነ እንደሆነ ጠብ ጠብ ብሎ በሚዘንመው ዝናም ደስ ብሏት ተካክላ ትበቅላለች። ብርቱ ዝናም የዘነመ እንደሆነ ከነመሬቱ ድሶት (ጠራርጎት) ይሄዳል፤ ለሰስ ብሎ የወረደ እንደሆነ ደስ ብሏት ተካክላ ትበቅላለችና።
አንድም ልቡናዋን ደስ አሰኘው፤
ሚጠተ ሥጋውን የበጀ አድርግላት፤
በዘሩባቤል ደስ ብሏት ተካክላ ትወጣለች።
አንድም ነፍሷን ደስ አሰኘው፤
ሚጠተ ነፍሷን የበጀ አድርገው፤
ከቀኝ ጎንህ በፈሰሰ ጽሩይ ማይ ተጠምቃ ደስ እያላት ከሲኦል ወደገነት ትወጣለች።
ሐምሌ ፭ በዓለ ጴጥሮስ ወጳውሎስ
ዘነግህ ምስባክ፦
ውስተ ኵሉ ምድር ወጽአ ነገሮሙ፤
ወእስከ አጽናፈ ዓለም በጽሐ ነቢቦሙ፤
ወውስተ ፀሐይ ሤመ ጽላሎቶ። መዝ ፲፰፥፬፤ ትርጒሙንና ምሥጢሩን ከታኅሣሥ ፳፩ ላይ ተመልከት።
ወንጌል፦ ዮሐ ፲፭፥፩ – ፲፯፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
፩ተሰ ፬፥፲፫ – ፍጻሜ፤
፪ጴጥ ፩፥፩ – ፲፪፤
ግብ ፳፫፥፲ – ፲፮፤
ወንጌል፦ ዮሐ ፳፩፥፲፭ – ፳፤
ቅዳሴ፦ ዘሐዋርያት
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
ወበኀቤየሰ ፈድፋደ ክቡራን አዕርክቲከ እግዚኦ፤
ወፈድፋደ ጸንዑ እምቀደምቶሙ፤
እኌልቆሙ እምኆፃ ይበዝኁ። መዝ ፻፴፰፥፲፯፤ ትርጒሙንና ምሥጢሩን ጥር ፬ ላይ ተመልከት።
፷ አሠርገዎሙ
ለእመ ኮነ በዓለ ሐዋርያት በሰንበት መዝሙር አሠርገዎሙ
፷.፩ (በ፬/ኪ) አሠርገዎሙ ለሐዋርያት በሰማያት (አ) ወንጌለ መንግሥት አወፈዮሙ (አ) ሰንበተ ክርስቲያን ለዕረፍት ሠርዐ ሎሙ (አ) ከመ ወርቅ በእሳት ፈተኖሙ (አ) ወከመ ጽንሐሐ መሥዋዕት ተወክፎሙ አሠርገዎሙ ለሐዋርያት በሰማያት።
ትርጕም፦
ሐዋርያትን በሰማያት አስጌጣቸው/ሸልማቸው፤ የመንግሥትን ወንጌል ሰጣቸው፤ ሰንበተ ክርስቲያንን ለዕረፍት አዘጋጀላቸው፤ እንደ ወርቅ በእሳት ፈተናቸው፤ እንደ ተወደደ መሥዋዕት ተቀበላቸው፤ በሰማያት አስጌጣቸው/ሸለማቸው።
፷.፪ የዕለቱ ምንባባት፦
፪ጢሞ ፬፥፩ – ፍጻሜ፤
፩ጴጥ ፩፥፲፪ – ፲፱፤
ግብ ፳፫፥፲ – ፍጻሜ፤
ወንጌል፦ ሉቃ ፮፥፩ – ፳፤
ቅዳሴ፦ ዘአበዊነ ሐዋርያት
፷.፫ የዕለቱ ምስባክ፦
አልቦ ነገር ወአልቦ ነቢብ ዘኢተሰምዐ ቃሎሙ፤
ውስተ ኵሉ ምድር ወጽአ ነገሮሙ፤
ወእስከ አጽናፈ ዓለም በጽሐ ነቢቦሙ። መዝ ፲፰፥፫፤
ትርጕም፦
ነገራቸው ቃላቸው ያልተሰማበት ነገር የለም፤
ቃላቸው ወደምድር ሁሉ ወጣ፤
ነገራቸው እስከ ዓለም ዳርቻ ደረሰ።
ምሥጢር፦
ቃሎሙ ለሰማይ ወምድር ነው የሰማይና የምድር ያልተነገረ ነገር ያልተሰማ ቃል የላቸውም፤ ቦ የመዓልተ እሑድ የመዓልተ ሰኑይ የሌሊተ እሑድ የሌሊተ ሰኑይ ነገራቸው ያልደረሰበት ያልተነገረበት የለም፤ ሥነ ፍጥረት ያልደረሰበት የለምና አንድም መሸ ጠባ/ነጋ የማይል የለምና።
በአራቱ ማዕዘን ሁሉ ተነገረ፤
ጽንፍ እስከ ጽንፍ ደረሰ።
አንድም ቃሎሙ ለነቢያት ወሐዋርያት ነው የነቢያት ትንቢታቸው የሐዋርያት ስብከታቸው ያልደረሰበት ያልተነገረበት የለም። አንድም “በቃሎሙ” ይላል ነቢያት በቃላቸው ያልተናገሩት ትንቢት ሐዋርያት ያላስተማሩት ትምህርት ያልሰበኩት ስብከት የለም።
የነቢያት ትንቢታቸው የሐዋርያት ስብከታቸው በአራቱ ማዕዘን ደረሰ፤ ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል ያሉትን ሐዋርያት ወረደ ተወለደ ብለው አስተምረዋልና፤ “ወየኀብር ቀስም ምስለ ማዕረር” እንዲል፤
የነቢያት ትንቢታቸው የሐዋርያት ስብከታቸው ከሰው ጆሮ ደረሰ፤ ጽንፍ አለው ጆሮን? የአካል ዳርቻ ነውና። አንድም ከምድር ጽንፍ እስከ ምድር ጽንፍ ተነገረ።
ሐምሌ ፯ በዓለ ቅድስት ሥላሴ
ዘነግህ ምስባክ፦
ሣህሉ ለእግዚአብሔር መልዐ ምድረ፤
ወበቃለ እግዚአብሔር ጸንዐ ሰማያት፤
ወእምእስትንፋሰ አፉሁ ኵሉ ኃይሎሙ።
ወንጌል፦ ዮሐ ፩፥፩ – ፮፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
ሮሜ ፱፥፩ – ፲፯፤
፩ዮሐ ፬፥፲፩ – ፍጻሜ፤
ግብ ፲፩፥፲፩ – ፲፱፤
ወንጌል፦ ዮሐ ፰፥፶፩ – ፍጻሜ
ቅዳሴ፦ ዘዲዮስቆሮስ
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
ወኀሠሥኩ ገጸከ፤
ገጸ ዚአከ አኀሥሥ እግዚኦ፤
ወኢትሚጥ ገጸከ እምኔየ። መዝ ፳፮፥፰፤
ትርጒም፦
ፊትህን ፈለግሁ፤
አቤቱ ፊትህን እሻለሁ፤
ፊትህን ከእኔ አትመልስ።
ምሥጢር፦
ገጸ ረድኤትህን ሻሁ፤
ገጸ ረድኤትህን እሻለሁ፤
ገጸ ረድኤትህን ከእኔ አትመልሰው፤ ሦስት ጊዜ መላልሶ ተናገረ ለአጽንኦተ ነገር ቦ ለአጠይቆተ አካላት፤ ወኀሠሥኩ ያለው እግዚብሔር አብን፣ አኀሥሥ ያለው እግዚአብሔር ወልድን፣ ኢትሚጥ ያለው መንፈስ ቅዱስን ነው።
፷፩ ንጉሥ ውእቱ
መዝሙር ንጉሥ ውእቱ ከሐምሌ ፲፩ እስከ ሐምሌ ፲፮
፷፩.፩ (በ፮/ዕ) ንጉሥ ውእቱ ክርስቶስ ንጉሥ ውእቱ ክርስቶስ መሐሪ ውእቱ ይሁብ ዘርዐ ለዘራዒ (ን) ያሠምር እክለ ለሲሳይ ያነሥኦ እምድር ለነዳይ (ን) ዘኢየኃይድዎ ሥልጣኖ ዘይኤዝዝ ትፍሥሕተ ለጻድቃኒሁ (ን) ወሠርዐ ሰንበተ ለሰብእ ዕረፍተ ገባሬ ሕይወት ያርኁ ክረምተ በበዓመት ንጉሥ ውእቱ ክርስቶስ ንጉሥ ውእቱ ክርስቶስ።
ትርጕም፦
ክርስቶስ ንጉሥ ነው ይቅር ባይ ነው ለዘሪ ዘርን ይሰጣል ለምግብ እህልን ያዘጋጃል ድኃውን ከመሬት ያነሣዋል ሥልጣኑን የማይቀሙት ነው ለጻድቃኑ ደስታን ያዛል (ለፍጥረት ፀሐይን ያወጣል) ሰንበትን ለሰው ዕረፍት ሠራ ሕይወትን የሠራ በየዓመቱ ክረምትን ይከፍታል።
፷፩.፪ የዕለቱ ምንባባት፦
፩ጢሞ ፩፥፲፪ -፲፰፤
ራእይ ፲፱፥፲፩ – ፲፯፤
ግብ ፭፥፳፯ – ፴፫፤
ወንጌል፦ ማቴ ፳፪፥፩ – ፲፭፤ ወይም ማቴ ፲፫፥፲፰ – ፳፬
ቅዳሴ፦ ዘኤጲፋንዮስ
፷፩.፫ የዕለቱ ምስባክ፦
ዘያበቊል ሣዕረ ለእንስሳ፤
ወሐመልማለ ለቅኔ እጓለ እመሕያው፤
ከመ ያውጽእ እክለ እምድር። መዝ ፻፫፥፲፬፤
ትርጕም፦
ለእንስሳ ሣርን የሚያበቅል እርሱ ነው፤
ለሰው ልጆች አገልግሎት ለምለሙን የሚያበቅል እርሱ ነው፤
እህልን ከምድር ያወጣ ዘንድ።
ምሥጢር፦
ለእንስሳ ምግብ ይሆን ዘንድ ሣርን የሚያበቅል ዝናም ነው አንድም ጌታ ነው፤
ለሰው ለሚያገለግል እንስሳ ልምላሜ ያለውን የሚያበቅል ዝናም ነው አንድም ጌታ ነው። አንድም ቅኑይ ሲል ነው ለእግዚአብሔር ለሚገዛ ለሰው እህሉን ተክሉን የሚያበቅል ዝናም አንድም ጌታ ነው። ሰው ያንን (እህሉን) እየተመገበ ለእግዚአብሔር ይገዛ ዘንድ ነው።
ከወደኋላ እምፍሬ ተግባርከ ትጸግብ ምድር – ከሥራህ ፍሬ ምድር ትጠግባለች (ምድር ከደመና የተገኘውን ዝናም ረክታ ትጠግባለች አንድም ከደመናው ለይተህ ያወረድኸውን ዝናም ጠጥታ ትጠግባለች ፍሬ አለው? ፍሬ መስሎ የሚወርድ ነውና ሲል ነው) ብሎ ነበርና ዝናም ከምድር እህሉን ያበቅል ዘንድ ነው አለ።
ማሳሰቢያ፦ ንጉሥ ውእቱ ለሚለው መዝሙር ምስባኩ እግዚአብሔርሰ ንጉሥ ውእቱ የሚለው ቢሆን ጥሩ ይመስለኛል። ምክንያቱ ደግሞ አንዳንድ የግጻዌ መጻሕፍት ንጉሥ ውእቱን ከመዝሙር ተራ አስገብተው ስላልጻፉ ነው። በመሆኑም ዘያበቊል ሣዕረ የሚለውን በቀዳሚ ገብረ ለሚለው መዝሙር ይጽፋሉ ምሥጢሩ ለሁለቱም ይስማማል፤ ለንጉሥ ውእቱም ለበቀዳሚ ገብረም።
አንዳንድ የግጻዌ መጻሕፍት ለበቀዳሚ ገብረ እስመ ትቤ ለዓለም የሚለውን ይጽፋሉ። አነ አቀውም ኪዳንየ ዘምስሌከ የሚል ኃይለ ቃል በመዝሙሩ ውስጥ ስላለ ነው። እንዲህ ያለ ነገር ሲያጋጥም መምህራንን መጠየቅና በእነሱ ቃል መመራት አላስፈላጊ ከሆነ ሙግትና የኃይለ ቃል ልውውጥ ይጠብቃል።
ሐምሌ ፲፪ በዓለ ቅዱስ ሚካኤል
ዘነግህ ምስባክ፦
ይትዐየን መልአከ እግዚአብሔር ዐውዶሙ፤
ለእለ ይፈርህዎ ወያድኅኖሙ፤
ጠዐሙ ወታእምሩ ከመ ኄር እግዚአብሔር።
ወንጌል፦ ማቴ ፳፬፥፴ – ፴፮፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
ሮሜ ፱፥፲፯ – ፴፤
ይሁዳ ፩፥፮ ፲፬፤
ግብ ፲፥፫ – ፱፤
ወንጌል፦ ሉቃ ፲፰፥፩ – ፱፤
ቅዳሴ፦ ዘያዕቆብ ዘሥሩግ
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
ኢይድኅን ንጉሥ በብዝኃ ሠራዊቱ፤
ወያርብሕኒ ኢድኅነ በብዝኃ ኃይሉ፤
ወፈረስኒ ሐሰተ ኢያድኅን። መዝ ፴፪፥፲፮፤
ትርጒም፦
ንጉሥ በሠራዊቱ ብዛት አይድንም፤
ኃያልም በኃይሉ ብዛት አይድንም፤
ፈረስም ከንቱ ነው አያድንም።
ምሥጢር፦
በሐልዮ በነቢብ በገቢር በተሠራው ኃጢአት መርምሮ የሚፈርድ ስለሆነ ሰናክሬም በሠራዊቱ ብዛት አይድንም፤
አርበኛም በኃይሉ ብዛት አይድንም፤ ቦ ከዚህ አስቀድሞ ያርብሐዊ ፈርዖን በሠራዊቱ ብዛት አልዳነም፤
ፈረስ ያድናል ማለት ሐሰት ነው አያድንም፤ ቦ በሐሰት ሆኖ ፈረስ አያድንም፤ እስራኤል ባሕረ ኤርትራን ከተሻገሩ በኋላ ግብፃውያን እንሻገራለን ብለው ቢገቡ ጌታ ሙሴን ዝብጣ ለባሕር አለው በትሩን እንደ ትእምርተ መስቀል አድርጎ አመሳቅሎ ቢመታት ፈረሰች የፈረዖን ፈረስ ወደላይ ዘለለ መልአኩ ቢመታው ተመልሷልና እንዲህ አለ።
፷፪ በቀዳሚ ገብረ
መዝሙር በቀዳሚ ገብረ ከሐምሌ ፲፯ እስከ ሐምሌ ፳፫
፷፪.፩ (በ፪/ዩ) በቀዳሚ ገብረ እግዚአብሔር ሰማየ ወምድረ ወኵሎ ፈጺሞ አዕረፈ በሰንበት ወይቤሎ ለኖኅ አመ አይኅ ግበር ታቦተ በዘትድኅን አነ አቀውም ኪዳንየ ዘምስሌከ ለዓለም ከመ ዳግመ ለምድር ኢያማስና በአይኅ ከመ አሀባ ለምድር ሣዕረ ሐመልማለ ክረምተ ወሐጋየ ዘርዐ ወማዕረረ ዝኬ ውእቱ ጸጋሁ ለእግዚአብሔር በአማን ኢይኄሱ ቃሎ ዘነበበ።
ትርጕም፦
በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ፈጠረ ሁሉን ፈጽሞ በሰንበት አረፈ በጥፋት ውኃ ጊዜ ኖኅን የምትድንበትን መርከብ ሥራ አለው እኔ ዳግመኛ ምድርን በጥፋት ውኃ እንዳላጠፋት ለዘለዓለም ኪዳኔን ከአንተ ጋር አቆማለሁ/አጸናለሁ ለምድር ሣርን ልምላሜን ክረምትን በጋን ዘርና መከርን እሰጣት ዘንድ ኪዳኔን ከአንተ ጋር አጸናለሁ የእግዚአብሔር ስጦታው ይህ ነው በእውነት የተናገረውን ቃሉን አይዋሽም።
፷፪.፪ የዕለቱ ምንባባት፦
ቲቶ ፫፥፩ – ፍ፤
፩ጴጥ ፬፥፮ – ፲፰፤
ግብ ፳፰፥፩ – ፲፯፤
ወንጌል፦ ማቴ ፳፬፥፴፮ – ፍጻሜ፤ ወይም ማር ፮፥፵፯ – ፍጻሜ፤
ቅዳሴ – ዘኤጲፋንዮስ
፷፪.፫ የዕለቱ ምስባክ፦
እስመ ትቤ ለዓለም አሐንጽ ምሕረተ፤
በሰማይ ጸንዐ ጽድቅከ፤
ኪዳነ ተካየድኩ ምስለ ኅሩያንየ። መዝ ፹፰፥፪
ትርጕም፦
ምሕረትን ለዘለዓለም አጸናለሁ ብለሃልና፤
ጽድቅህ በሰማይ ጸና፤
ከመረጥኋቸው ጋር ቃል ኪዳን አደረግሁ።
ምሥጢር፦
አሐንጽ ያለውን እገብር ሲል ነው ቸርነትን ለዘለዓለም አደርጋለሁ ማለት አጸናለሁ ብለሃልና “አጽንዐ ምሕረቶ እግዚአብሔር ላዕለ እለ ይፈርህዎ – እግዚአብሔር በሚፈሩት ላይ ምሕረቱን አጸና” እንዲል መዝ ፻፪፥፲፩
ቸርነትህ እንደ ሰማይ ጸንቶ ይኖራል። ይህም በምድር ላይ የቱንም ያህል መናወጥ ቢደረግም ሰማይ እንደማይናወጥ የኃጢአታችን ብዛት በኖኅ ዘመን የገባልልንን ኪዳን እንዲናወጥ የማያደርገው መሆኑን መናገር ነው። በደመና የሚሳለው ምልክት እስካሁን አልተለወጠምና።
አንድም ቸርነትህ በፈጢረ ፀሐይ ጸና። በናቡከደነጾር ያሳይበታል “አነ ዘአሠርቅ ፀሐየ – ፀሐይን የማወጣ እኔ ነኝ” እስከ ማለት ደርሶ ነበርና
አንድም ሊቃነ መላእክትን ሠራዊተ መላእክትን በመፍጠር ጸና። “ገባሬ መላእክት አበ ኵሉ ዓለም – የመላእክት ፈጣሪ የዓለሙ ሁሉ አባት” እንዲል።
ትቤ ያለበት ነው ለአባትነት ከመረጥኋቸው ከወዳጆቼ ከባለሟሎቼ ከአብርሃም ከይስሐቅ ከያዕቆብ ጋር መሐላን ተማማልሁ ብለህ ነበር ማለት ይህንን መሐላ አስብ አስበህ ይቅር በለን ማለት ነው።
ወይም፦
ሐወፅካ ለምድር ወአርወይካ፤
ወአብዛኅኮ ለብዕላ፤
ፈለገ እግዚአብሔር ምሉዕ ማያተ። መዝ ፷፬፥፱
ትርጕም፦
ምድርን ጐበኘኻት አረካሃትም፤
ብልጥግናዋን እጅግ አበዛህ፤
የእግዚአብሔር ወንዝ ውኆችን የተመላ ነው።
ምሥጢር፦
ይህችን ዓለም በረድኤት ጐበኘሃት፤ ቦ ኢየሩሳሌምን ከሰባ ዘመን በኋላ ጐበኘሃት ማለት የዘሩባትን እንድታበቅል የተከሉባትን እንድታጸድቅ አደረግሃት።
የዚችን ዓለም ቦ የኢየሩሳሌምን ብዕለ ሥጋዋን ማለትም አዝርዕቱን አትክልቱን አበዛህላት፤ ቦ ለምእመን ብዙ ጸጋ ክብር የሚገኝበትን ልጅነትን ሰጠሃት።
እግዚአብሔር የፈጠራቸው አራቱ አፍላጋት ኤፌሶን ኤፍራጥስ ግዮን ጤግሮስ ውኃን የተመሉ ናቸው።
ሐምሌ ፲፱ በዓለ ቅዱስ ገብርኤል
ዘነግህ ምስባክ፦
ወአጽዐንከ ሰብአ ዲበ አርእስቲነ፤
አኅለፍከነ ማዕከለ እሳት ወማይ፤
ወአውጻእከነ ውስተ ዕረፍት። መዝ ፷፭፥፲፪፤
ትርጒም፦
በራሳችን ላይ ሰውን አስጫንህ፤
በእሳትና በውኃ መካከል አሳለፍኸን፤
ወደ ዕረፍትም አወጣኸን።
ምሥጢር፦
ግብጻውያንን ባቢሎናውያንን አሠለጠንህብን፤ ቦ አጋንንትን በጠላትነት አስነሣህብን፤ ሰብእ አላቸው በማደሪያቸው፤ ቦ ሰው በባሕርዩ እንዲራባ እነሱም በግብር ይራባሉና፤
በእሳትና በውኃ መካከል አሳለፍኸን፤ በግብፅ ዝናም አይዘንምም ለሐድሶተ ንስር ያህል በአምስት በአምስት መቶ ዘመን ያካፋል እንጂ፤ ያን ጊዜ ቀን ገጥሞት እሳትና በረድ እንደሰምና ፈትል ተጣምቶ ወርዷል፤ “የእንጦጦ መምር አይናገር፣ ቢናገር በዓመት ያውም ሬት” እንዲሉ፤
ከኤርትራ ወደምድረ በዳ አወጣኸን።
ቦ በእሳትና በውኃ መካከል አሳለፍኸን ይላሉ ሠለስቱ ደቂቅ፤ እሳት አለው በቀደመ ግብሩ፤ ውኃ አለው በኋላ ግብሩ፤ ቦ በእሳትና በውኃ መካከል አሳለፍኸን፤ እሳት ያለው የባቢሎንንን ጦር ነው፤ ውኃ ማለቱ ከባቢሎን ሲወጡ ሰባት ወንዝ ተከፍሎላቸዋልና፤
ከፋርስ ከባቢሎን ዕረፍት ወደአለባት ወደ ኢየሩሳሌም አወጣኸን።
ቦ በሲኦልና በገሃነም መካከል አሳልፍኸን፤ ቦ ጥምቀትን ልጅነትን ሰጠኸን፤
ዕረፍተ ነፍስ ወዳለባት ወደ መንግሥተ ሰማያት አገባኸን፤
ወንጌል፦ ማቴ ፲፰፥፩ – ፲፪፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
ዕብ ፲፩፥፴፫ – ፍጻሜ፤
፩ጴጥ ፬፥፲፪ – ፍጻሜ፤
ግብ ፳፫፥፲ – ፲፭፤
ወንጌል፦ ማቴ ፲፩፥፳፭ – ፍጻሜ፤
ቅዳሴ፦ ዘያዕቆብ ዘሥሩግ
ምስባክ ዘቅዳሴ፦
ይትኀፈሩ ኵሎሙ እለ ይሰግዱ ለግልፎ፤
ወእለ ይትሜክሑ በአማልክቲሆሙ፤
ወይሰግዱ ሎቱ ኵሎሙ መላእክቲሁ። መዝ ፺፮፥፯፤
ትርጒም፦
ለተቀረጸ ምስል የሚሰግዱ ሁሉ ይፈሩ፤
በጣዖቶቻቸውም የሚመኩ፤
መላእክት ሁሉ ይሰግዱለታል።
ምሥጢር፦
ለተቀረጸ ለተጐነፈ ጣዖት የሚሰግዱ ሁሉ ይፈሩ ይዋረዱ፤ ቦ አጥብቆ ይትኀፈሩ ይላል ያፍራሉ ይዋረዳሉ፤
ቤል ዳጎን ያድነናል እያሉ በጣዖቶቻቸው የሚመኩ ሁሉ ይፈሩ ይዋረዱ፤
እንዲህ የሚሉ ለራሳቸው ይባሳቸው እንጂ ለእሱስ መላእክት ይሰግዱለታል።
ሐምሌ ፳፩ በዓለ እግዝእትነ ማርያም
ዘነግህ ምስባክ፦
ወትቀውም ንግሥት በየማንከ፤
በአልባሰ ወርቅ ዑፅፍት ወኊብርት፤
ስምዒ ወለትየ ወርእዪ ወአጽምዒ ዕዝነኪ።
ወንጌል፦ ሉቃ ፩፥፴፱ – ፶፯፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
ኤፌ ፮፥፲ – ፲፱፤
፩ዮሐ ፭፥፩ – ፮፤
ግብ ፰፥፳፮ – ፍጻሜ፤
ወንጌል፦ ማቴ ፲፱፥፩ –፲፮፤
ቅዳሴ፦ ዘእግዝእትነ ማርያም
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
ብፁዕ ዘይሌቡ ላዕለ ነዳይ ወምስኪን፤
እምዕለት እኪት ያድኅኖ እግዚአብሔር፤
እግዚአብሔር የዐቅቦ ወያሐይዎ ወያበፅዖ ዲበ ምድር። መዝ ፵፥፩፤
ትርጒም፦
ለድኃና ለምስኪን የሚያስብ ብፁዕ ነው፤
እግዚአብሔር ከክፉ ቀን ያድነዋል፤
እግዚአብሔር ይጠብቀዋል ሕያውም ያደርገዋል።
ምሥጢር፦
ዘላዕለ ነዳይ ነው፤ በድኃው በጦም አዳሪው ላይ ያለውን ችግር የሚመለከት ሰው ንዑድ ክቡር ነው፤ ቦ ድኃውን ጦም አዳሪውን ልብ የሚያደርግ ሰው ንዑድ ክቡር ነው፤ ተመልክቶ ዝም ማለት አይደለም የተራበውን ማብላት የተጠማውን ማጠጣት የታረዘውን ማልበስ ነው፤
እንዲህ የሚያደርገውን ሰው እግዚአብሔር መቅሠፍት ከታዘዘበት ቀን ቦ በዕለተ ምጽአት ከሚሆን መቅሠፍት ያድነዋል፤
እግዚአብሔር ከመከራ ያድነዋል ከደዌውም ይፈውሰዋል በዚህ ዓለም ዕፁብ ዕፁብ ያሰኘዋል።
፷፫ በሰንበት ቦአ
መዝሙር በሰንበት ቦአ ከሐምሌ ፳፬ እስከ ሐምሌ ፴
፷፫.፩ (በ፫/ሙ) በሰንበት ቦአ ኢየሱስ ምኵራቦሙ ለአይሁድ ምህሮሙ ወይቤሎሙ አክብሩ ሰንበትየ (በ) በሰንበት አጋንንተ አውጽአ ወበቃሉ እለ ለምፅ አንጽሐ (በ) በሰንበት ወረቀ ምድረ ወገብረ ፅቡረ ወበምራቁ አሕየወ ዕውረ (በ) ዘይኤዝዞሙ ለደመናት ያውርዱ ዝናመ ውስተ ኵሉ ምድር (በ) ያውርዱ ዝናመ ውስተ ኵሉ ምድር ውስተ ፍና ኀበ ይትፈቀድ መካን (በ) ውስተ ፍና ኀበ ይትፈቀድ መካን ከመ ኅቡረ ይትፈሣሕ ዘይዘርዕ ወየዓርር (በ) ምድርኒ ርእየቶ ወአእኰተቶ ባሕርኒ ሰገደት ሎቱ።
ትርጕም፦
በሰንበት ወደአይሁድ ምኲራብ ገባ ሰንበቴን አክብሩ ብሎ አስተማራቸው በሰንበት አጋንንትን አወጣ በቃሉ ለምፃሞችን አነጻ በሰንበት ምራቁን ወደምድር እንትፍ አለ ጭቃም አደረገ በምራቁ ዕውሩን አዳነ በምድር ሁሉ ላይ ዝናምን ያወርዱ ዘንድ ደመናዎችን የሚያዛቸው እሱ ነው በሚያስፈልግበት ስፍራ ሁሉ። የሚዘራም የሚያጭድም አንድ ላይ ይደሰቱ ዘንድ። ምድር አየችው አመሰገነችው ባሕርም ሰገደችለት።
፷፫.፪ የዕለቱ ምንባባት፦
፪ቆሮ ፲፥፩ – ፍ፤
ያዕ ፫፥፩ – ፱፤
ግብ ፳፰፥፲፯ – ፍጻሜ፤
ወንጌል፦ ማር፮፥፵፯ – ፍ ወይም ማቴ ፰፥፳፫ – ፍጻሜ
ቅዳሴ ፡- ዘኤጲፋንዮስ ወይም ዘእግዚእነ
፷፫.፫ የዕለቱ ምስባክ፦
ያዐርግ ደመናተ እምአጽናፈ ምድር፤
ወገብረ መብረቀ ለጊዜ ዝናም፤
ዘያወጽኦሙ ለነፋሳት እመዛግብቲሆሙ። መዝ ፻፴፬፥፯፤
ትርጕም፦
ከምድር ዳር ደመናትን ያወጣል
ለዝናም ጊዜም መብረቅን አደረገ፤
ነፋሳትን ከመዛግብቱ ያወጣል።
ምሥጢር፦
ደመናትን ከጽንፈ ምድር ፈጠረ።
የደመናትን ተፈጥሮ ከዚህ ይናገሩታል። ከዚህ እስከ ብሩህ ሰማይ ውኃ መልቶ ነበርና ለይትጋባእ ማይ ውስተ ምዕላዲሁ – ውኃ በመከማቻው ይሰብሰብ ብሎ ከሦስት ከፍሎታል ምድርም ደም እንደሰረበው ጉበት ሆና ታየች አሥራ ሁለቱን ነፋሳት አውጥቶ አስመታት ጸጥ አለች (ስምንቱ የመዓት ሲባሉ አራቱ የምሕረት ናቸው) በዚህ ጊዜ ከይቡስ ምድር ይቡስ ጢስ ከርጡብ ባሕር ርጡብ ጢስ ወጥቶ አንድ ደመና ይሆናል ወይመውቁ በፀሐይ ወይከውኑ ክልኤሆሙ አሐደ ደመና – በፀሐይ ይሞቃሉ አንድ ደመና ይሆናሉ እንዲል።
መብረቅን ለዝናም ምልክት አደረገ አንድም ለዝናም ምልክት የሚሆን መብረቅን ፈጠረ። ይኸውም ለከንቱ አይደለም አትክልት አዝርዕት ሊያብቡባቸው ሊያፈሩባቸው ነው። ወይበርቁ መባርቅት ለጽጋብ ወለበረከት – መባርቅት ለጥጋብና ለበረከት ይበርቃሉ/ብልጭ ይላሉ እንዲል።
የመብረቅ ተፈጥሮ እንደምን ነው ቢሉ? ውኃው በደመና አይበት ተቋጥሮ በነፋስ ወደል ጋዝ ተጭኖ ሲመጣ ደመናና ደመና በተጋጨ ጊዜ እንደ አረቄ ከውኃ ይወጣል፤ ወተት ሲገፋ ቅቤ እንዲወጣው።
ነፋሳትን ከየሳጥናቸው የሚያወጣቸው እሱ ነው ለአሥራ ሁለቱ ነፋሳት አሥራ ሁለት መሳክው አሏቸው። በምሥራቅ ስድስት በምዕራብ ስድስት፤ ከዚህ እየመጠነ የሚያወጣቸው እሱ ነው። አንድ ጊዜ የወጡ እንደሆነ አንድም መጥኖ ባያወጣቸው ዓለምን የሚያሳልፉ ናቸውና።
ሐምሌ ፳፱ ተዝካረ ልደቱ ለእግዚእነ
ዘነግህ ምስባክ፦
ምስሌከ ቀዳማዊ በዕለተ ኃይል፤
በብርሃኖሙ ለቅዱሳን፤
ወለድኩከ እምከርሥ እምቅድመ ኮከበ ጽባሕ።
ወንጌል፦ ሉቃ ፪፥፩ – ፰፤
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
ገላ ፫፥፲፭ – ፍጻሜ፤
፩ዮሐ ፬፥፱ – ፲፰፤
ግብ ፱፥፳ – ፴፪፤
ወንጌል፦ ሉቃ ፲፪፥፩ – ፲፫፤
ቅዳሴ፦ ዘዲዮስቆሮስ
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
ወእምኵሉ ያድኅኖሙ እግዚአብሔር፤
እግዚአብሔር የዐቅብ ኵሎ አዕፅምቲሆሙ፤
ወኢይትቀጠቀጥ አሐዱ እምውስቴቶሙ። ትርጒሙንና ምሥጢሩን ጥር ፲፰ ላይ ተመልከት።

