ወርኃ መስከረም

፩ መዝሙር ዮሐንስ አኅድዐ

፩.፩ መዝሙር ዮሐንስ አኅድዐ ከመስከረም ፩ – መስከረም ፯

(በ፭/ን) ዮሐንስ አኅድዐ እምካልአኒሁ አንሐ ወክሐ እንዘ ይብል እምላዕሉ ወረደ ቃለ አብ ወተሐውከ ማየ ዮርዳኖስ እምግርማ መለኮት ወደንገጹ ኵሉ ኃይለ ሰማያት ወምድር ከማሁ ኮነ በቢታንያ በቤተ ራማ በማዕዶተ ዮርዳኖስ ወሶበ ርእዮ ዮሐንስ ለኢየሱስ ከልሐ ወይቤ ነዋ በግዑ ለእግዚአብሔር ይቤሎ ኢየሱስ ለዮሐንስ አጥምቀኒ በማይ ከመ ይትቀደስ ማይ በማዕተበ ሰማይ አጥመቆ ዮሐንስ ለኢየሱስ በፈለገ ዮርዳኖስ እምድኅረ አጥመቀ ለሊሁ ተጠምቀ ምህሮሙ ለሕዝብ ወይቤሎሙ አክብሩ ሰንበተ ተገበሩ ጽድቀ።

ትርጕም፦

ዮሐንስ ከወንድሞቹ ይልቅ ጸጥ አሰኘ ከሌሎቹ ተለይቶ አብዝቶና አሰምቶ ተናገረ እንዲህ ብሎ አስተማረ የአብ አካላዊ ቃል ከሰማያት ወረደ፤ ከመለኮታዊ ግርማው የተነሣ የዮርዳኖስ ውኃ ታወከ ብሎ። በቢታንያ፣ በቤተ ራባና በዮርዳኖስ ማዶ ሁሉ እንዲሁ አሰምቶ ተናገረ። ዮሐንስ ጌታ ኢየሱስን ባየው ጊዜ የእግዚአብሔር በግ እነሆ ብሎ ጮኾ ተናገረ። ጌታ ኢየሱስም ዮሐንስን በሰማያዊ በረከት/በመለኮታዊ ሥልጣን ይባረክ/ይከብር ዘንድ በውኃ አጥምቀኝ አለው። ዮሐንስ ጌታችንን በዮርዳኖስ ወንዝ አጠመቀው። ከአጠመቀ በኋላ ራሱ ተጠመቀ። ሕዝቡን ሰንበትን አክብሩ የጽቅድንም ሥራን ሥሩ ብሎ አስተማራቸው። 

፩.፪ የዕለቱ ምንባባት፦ 

፩ቆሮ ፲፩፥፲፯ -ፍጻሜ፤ 

ያዕ ፪፥፩ – ፲፬፤ 

ግብ ፲፰፥፳፬ – ፍጻሜ፤ 

ወንጌል፦ ዮሐ ፩፥፲፭ – ፴፰፤

ቅዳሴ፦ ዘአትናቴዎስ 

፩.፫ የዕለቱ ምስባክ፦

ሣህል ወርትዕ ተራከባ፤

ጽድቅ ወሰላም ተሰዓማ፤

ርዕትሰ እምድር ሠረፀት። መዝ ፹፬፥፲፤

ትርጉም፦

ይቅርታና እውነት ተገናኙ፤

ጽድቅና ሰላም ተስማሙ፤

ቅንነት ከምድር በቀለች።

ምሥጢር፦

ሊቀ ካህናቱ በግብረ ክህነት ንጉሡ በግብረ መንግሥት ተገናኙ፤ ንጉሡ ይፈርዳል ይተቻል፤ ሊቀ ካህናቱ መንፈሳዊ ትምህርት ያስተምራል።

አንድም ጌታችን ለመጠመቅ ዮሐንስ ለማጥመቅ በዮርዳኖስ ተገናኙ፤ ዮሐንስ ምድራዊ ልደቱንና ምድራዊ ቤተ ሰቡን ይናገራል፤ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ ይበረታል እኔ በውኃ አጠምቃችኋለሁ እያለ ያስተምራል፤ ጌታ ግን ከሰማይ መጣሁ ከሰማይ የወረደ የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ እያለ ያስተምራል። 

አንድም መለኮትና ትስብእት በማኅፀነ ማርያም ተገናኙ ማለት ምሥጢረ ተዋሕዶ ተከናወነ፤ ኤልሳቤጥና እመቤታችን በቤተ ዘካርያስ ተገናኙ፤ “ወቦአት ቤተ ዘካርያስ ወአምኃታ ለኤልሳቤጥ – ወደዘካርያስ ቤት ገብታ እልሳቤጥን እጅ ነሣቻት” እንዲል። ሉቃ ፩፥፵፤ 

መስከረም ርእሰ ዐውደ ዓመት

ምስባክ ዘነግህ፦ 

ወትባርክ አክሊለ ዓመተ ምሕረትከ፤ 

ወይጸግቡ ጠላተ ገዳም፤ 

ወይረውዩ አድባረ በድው። መዝ ፷፬፥፲፩፤ 

ትርጒም፦ 

የምሕረትህን ዓመት አክሊል ትባርካለህ፤ 

ምድረ በዳዎች ጠልን ይጠግባሉ፤ 

የምድረ በዳ ተራሮች ይረካሉ። 

ምሥጢር፦ 

ይቅርታህ ቸርነትህ በተሰጠበት ወራት የተገኘ መከሯን ባርከህ አበዛህላት፤ አክሊል አለው? ምርቱን አክሊል አስመስሎ ያመርተዋልና፤ አክሊላቲሃ ለምድር – የምድር አክሊል እንዲል። ቦ የዘሩባቤልን ዘውድ ታከብረዋለህ፤ ቦ ወንጌልን ታከብራለህ፤ አክሊል አላት ወንጌልን መንግሥተ ሰማያትን ታወርሳለችና። ቦ ልጅነትን ታከብራለህ ማለት ልጅነት በሃይማኖት እንዲሰጥ ታደርጋለህ። 

ይጸግቡ ካለ ገዳማት፣ ገዳም ካለ ይጸግብ ቢል በቀና ነበር ልማደ መጽሐፍ ነው፤ ገዳማት ልምላሜውን ይጠግባሉ አለ ደስ ይላቸዋል፤ ቦ አሕዛብ ሕገ ኦሪትን ይማራሉ፤ ቦ ሕዝበ እስራኤል በወንጌል ያምናሉ። 

በበረኃ ያሉ ተራራዎች ዝናሙን ይረካሉ፤ ቦ ነገሥተ አሕዛብ ቂሮስ ዳርዮስ በኦሪት ያምናሉ፤ ቦ ነገሥተ እስራኤል ምእመናነ እስራኤል በወንጌል ያምናሉ። 

ወንጌል፦ ሉቃ ፬፥፲፮–፳፫፤ 

ምንባብ ዘቅዳሴ፦  

፪ቆሮ ፮፥፩ – ፲፩፤ 

ያዕ ፭፥፰ – ፲፫፤ 

ግብ ፭፥፲፪ – ፲፯፤

ወንጌል፦ ማቴ ፲፩፥፩ – ፳፤

ቅዳሴ፦ ዘሐዋርያት 

ምስባክ ዘቅዳሴ፦ 

አድኅነኒ እምእለ ሮዱኒ እስመ ይኄይሉኒ፤ 

ወአውጽኣ እሞቅሕ ለነፍስየ፤ 

ከመ እግነይ ለስምከ እግዚኦ፤ መዝ ፻፵፩፥፮፤

ትርጒም፦

 ከከበቡኝ አድነኝ፤ ይበረቱብኛልና። 

ነፍሴን ከእስራት አውጣት፤ 

አቤቱ ለስምህ እገዛልህ ዘንድ። 

ምሥጢር፦ 

በነፍስ በሥጋ ከከበቡኝ አጋንንት አድነኝ፤ እነሱ ከእኔ ይበረታሉና፤ 

ሰውነቴን ከግዞት ቤት ቦ ከእቶነ እሳት ቦ ነፍሴን ከፍዳ ከቊራኝነት ከሲኦል ከገሃነም አድናት። 

ኢየሩሳሌም ገብቼ ለስምህ እገዛ ዘንድ፤ ቦ ከእቶነ እሳት ድኜ በገነት በመንግሥተ ሰማያት ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያልሁ አመሰግን ዘንድ፤ 

መስከረም በዓለ ምትረተ ርእሱ ለቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ

ዘነግህ ምስባክ፦ 

እመኒ ነሣእኩ ክንፈ ከመ ንስር፤ 

ወሠረርኩ እስከ ማኅለቅተ ባሕር፤ 

ህየኒ እዴከ ትመርሐኒ። መዝ ፻፴፰፥፱፤

ትርጒም፦ 

እንደ ንስር ክንፍን ብወስድ፤ 

እስከ ባሕር መጨረሻ ብበርም፤ 

በዚያ እጅህ ትመራኛለች። 

ምሥጢር፦ 

በራሴ ሥልጣን ክንፍ ማብቀል አይቻለኝም እንጂ ቢቻለኝ ክንፍ አውጥቼ እስከ አድማስ ድረስ ብሄድ ሥልጣንህ በዚያ ትመራኛለች።  አባ ሕርያቆስ “ይህንን ባሰብሁ ጊዜ ሕሊናየ በነፋሳት ትከሻ ተጭኖ በምሥራቁ በምዕራቡ በሰሜኑ በደቡቡ በአራቱም ማዕዘን ይበር ዘንድ ይወዳል፤ የፍጡራንን አኗኗር ያይ ዘንድ፣ የአብሕርትን ጥልቀታቸውን ይለካ ዘንድ፣ የሰማይን ርዝመት ያውቅ ዘንድ፤ በሁሉም ቦታ ይዞራል ይደክማል ወደቀደመ ቦታው ይገባል” እንዳለ።  

ወንጌል፦ ፲፬፥፩ – ፲፫፤ 

ዘቅዳሴ ምንባብ፦ 

፩ቆሮ ፮፥፩ – ፲፩፤

፩ዮሐ ፫፥፲ – ፲፮፤

ግብ ፲፫፥፳፬ – ፳፰፤

ወንጌል፦ ማር ፮፥፲፬ – ፴፤ 

ቅዳሴ፦ ዘወልደ ነጐድጓድ 

ዘቅዳሴ ምስባክ፦ 

ወይርአዩ አሕዛብ በቅድመ አዕይንቲነ፤ 

በቀለ ደሞሙ ለአግብርቲከ ዘተክዕወ፤ 

ይባዕ ቅድሜከ ገዐሮሙ ለሙቁሐን።

መዝሙር አጥመቆ ዮሐንስ

ለእመ ኮነ በዓለ ዘካርያስ በሰንበት (መስከረም ፰) መዝሙር አጥመቆ ዮሐንስ (በላይ ቤት በ፪/ዩ በቀዳሚ ገብረ እግዚአብሔር )

፪.፩ (በ፫/ሙ) አጥመቆ ዮሐንስ ለኢየሱስ አጥመቆ ዮሐንስ ለኢየሱስ ወገሠሦ እንተ ኢትትገሠሥ ርእሶ (አ) ወገሠሦ እንተ ኢትትገሠሥ ርእሶ ተቀደሰት ማይ በጥምቀቱ (አ) ተቀደሰት ማይ በጥምቀቱ ፈልሑ ማያት ዲበ ርእሱ (አ) ኢየሱስ ክርስቶስ ቀደሳ ወአክበራ ወአልዓላ ለዕለተ ሰንበት።

ትርጕም፦

ዮሐንስ ኢየሱስን አጠመቀው የማትዳሰስ ራሱን ዳሰሰ በጥምቀቱ ውኃ ተቀደሰች ውኃዎች በራሱ ላይ ፈሉ ኢየሱስ ክርስቶስ ዕለተ ሰንበትን ቀደሳት አከበራት ከፍ ከፍ አደረጋት።

፪.፪ የዕለቱ ምንባባት፦

ዕብ ፲፩፥፴፪ – ፍጻሜ፤ 

ራእይ ፮፥፱ – ፲፪፤ 

ግብ ፲፱፥፩ – ፮፤ 

ወንጌል፦ ማቴ ፳፫፥፳፫ – ፍጻሜ፤

ቅዳሴ፦ ዘኤጲፋንዮስ አው ዘወልደ ነጐድጓድ

፪.፫ የዕለቱ ምስባክ፦

ወንግርዎሙ ለአሕዛብ ምግባሮ፤

እስመ ተዘከረ ዘይትኀሠሥ ደሞሙ፤

ወኢረስዐ አውያቶሙ ለነዳያን። መዝ ፱፥፲፩ 

ትርጕም፦ 

ለአሕዛብ ሥራውን ንገሯቸው፤

ደማቸውን የሚመራመር እሱ አስቧልና፤

የድኆችን ጩኸት አይረሳምና።

ምሥጢር፦ 

ሥራውን ለአሕዛብ ንገሩ አስተምሩ፤

እንደፈሰሰ ይቅር የማይባል ደማቸውን አስቧልና፤ አስቦ ጠላቶቻቸውን አጥፍቷልና። አንድም ደማቸውን የሚመራመር እግዚአብሔር አስቧልና፤ አስቦ ጠላቶቻቸውን አጥፍቷልና። አንድም ደማቸውን የሚፈላለግ እግዚአብሔር አስቦ ጠላቶቻቸውን አጥፍቷልና። አንድም ጠላቱን በፍዳ የሚመረምር እግዚአብሔር ደማቸውን አስቦ ጠላቶቻቸውን አጥፍቷልና። እንደ ደመ አቤል፤ እንደ ደመ ዘካርያስ። 

ደመ አቤል፦ መልአኩ ለሄኖክ መካነ ነፍሳትን እያዞረ ሲያሳየው አንዲት ነፍስ ስትካሰስ ስትንጸረጸር አየ ዛ መንፈስ ዘመኑ – ያቺ ነፍስ የማን ነፍስ ናት? አለው ዘአቤል ዘቀተሎ እኁሁ – ወንድሙ የገደለው የአቤል ነፍስ ናት ኪያሁ ትሰኪ እስከ አመ ይትኀጐሉ ደቂቁ በማየ አይኅ – የቃኤል ልጆች በማየ አይኅ እስኪጠፉ ድረስ ስትካሰስ ትኖራለች ብሎታል። ሄኖክ ፮፥፳፯፤

ደመ ዘካርያስ፦ በቤተ መቅደሱና በዕቃ ቤቱ መካከል ሰባ ዘመን ሲፈላ ኖሯል ጥጦስ ቤተ መቅደስን ሲያፈርስ ደሙ ሲፈላ አይቶ ይህ ምንድን ነው? ብሎ ጠየቀ የደግ ሰው ደም ነው አይሁድ በግፍ አስገድለዉት እንዲህ ሲፈላ ይኖራል አሉት ከገዳዮቹ ወገን ሰባት ሰዎች አስመጥቶ ቢያሳርዳቸው ይፈላ የነበረው ደም ጸጥ ብሏል። 

መዝሙር እኲት አንተ

ከመስከረም ፱ – ፲፭

፫.፩ (በ፭/ር) እኵት አንተ ወስቡሕ ስምከ ወዐቢይ ኃይልከ ዘተአርፍ በአርያም ወትሴባሕ በትሑታን ዘአንተ ሠራዕከ ሰንበተ ለዕረፍት ወወሀብከ ሲሳየ ዘበጽድቅ ለኵሉ እግዚኦ ባርክ ፍሬሃ ለምድር መሐሪ ወጻድቅ መኑ ከማከ ዘታርኁ ክረምተ በጸጋከ ነፍስ ድኅንት ወነፍስ ርኅብት እንተ ጸግበት ተአኵተከ

ትርጕም፦

አንተ ምስጉን ነህ ስምህም የተመሰገነ ነው ኃይልህም ደገኛ/ታላቅ ነው በአርያም ትኖራለህ ትሕትናን ገንዘብ ባደረጉ ትመሰገናለህ ዕረፍት ይሆን ዘንድ ሰንበትን የሠራህ አንተ ነህ በእውነት ለሁሉ ምግብን የምትሰጥ አንተ ነህ አቤቱ የምድርን ፍሬ ባርክ መሐሪ እውነተኛ የምትሆን አቤቱ እንዳንተ ያለ ማነው በቸርነትህ ክረምትን የምታገባና የምታወጣ አንተ ነህ ተርባ የጠገበች ነፍስ ድና ታመሰግንሃለች። 

የዕለቱ ምንባባት፦

፪ቆሮ ፱፥፩ – ፍ፤ 

ያዕ ፭፥፩ – ፲፤ 

ግብ ፲፱፥፳፩ – ፍጻሜ፤ 

ወንጌል ማር ፬፥፳፬ – ፴፱

ቅዳሴ፦ ዘወልደ ነጐድጓድ 

፫.፫ የዕለቱ ምስባክ፦

ምድርኒ ወሀበት ፍሬሃ፤

ወይባርከነ እግዚአብሔር አምላክነ፤

ወይባርከነ እግዚአብሔር። መዝ ፷፮፥፮

ትርጕም፦ 

ምድር ፍሬዋን ሰጠች፤

እግዚአብሔር አምላካችን ይባርከናል፤

እግዚአብሔር ይባርከናል። 

ምሥጢር፦

ትሩፍ ሥርዓተ አምልኮን ፍሬ አድርጋ አቀረበች።

አንድም ምእመን ሃይማኖትን ፍሬ አድርጋ ሰጠች።

አንድም እመቤታችን አካሏን ለተዋሕዶ ፍሬ አድርጋ ሰጠች።

መስከረም በዓለ ጼዴንያ

ምስባክ ዘነግህ፦ 

ወትቀውም ንግሥት በየማንከ፤ 

በአልባሰ ወርቅ ዑፅፍት ወኁብርት፤ 

ስምዒ ወለትየ ወርእዪ ወአጽምዒ ዕዝነኪ። 

ወንጌል፦ ሉቃ ፩፥፵፮ – ፶፯፤ 

ዘቅዳሴ ምንባብ፦ 

ሮሜ ፫፥፩ – ፍጻሜ፤ 

ያዕ ፫፥፲፫ – ፍጻሜ፤ 

ግብ ፩፥፲፪ – ፲፭፤ 

ወንጌል፦ ማቴ ፳፭፥፩ – ፲፬፤

ቅዳሴ፦ ዘእግዝእትነ ማርያም 

ምስባክ ዘቅዳሴ፦  

አዋልደ ንግሥት ለክብርከ፤ 

ወትቀውም ንግሥት በየማንከ፤ 

በአልባሰ ወርቅ ዑፅፍት ወኊብርት።  

መስከረም ፲፩ በዓለ ቅዱስ ፋሲለደስ

ምስባክ ዘነግህ፦ 

ተንሥኡ ላዕሌየ ሰማዕተ ዓመፃ፤ 

ወዘኢየአምር ነበቡ ላዕሌየ፤ 

ፈደዩኒ እኪተ ህየንተ ሠናይት። መዝ ፴፬፥፲፩፤ 

ትርጒም፦ 

የዐመፃ ምስክሮች ተነሡብኝ፤ 

የማላውቀውን በእኔ ላይ ተናገሩ፤ 

ስለበጎ ፈንታ ክፉ መለሱልኝ። 

ምሥጢር፦ 

የሐሰት የዐመፅ መሳክርት እስራኤል በጠላትነት ተነሡብኝ፤ 

የማላውቀውን ተናገሩብኝ አለ ነቢየ ሐሰት አሉኝ፤ ኤርምያስ የጼዋዌን ነገር ቢናገር ሕዝቡ አንሰማውም አሉ በእነሱ ዳፋ እኔ ልዳፋ ብሎ ሲሄድ ቦ ከተማ ተርቦበት ወደእናቱ ሀገር ወደ አናቶት ሲሄድ ሱራህ ሱራህያ ይለዋል ወተራከቦ በአንቀጸ ብንያሚን ይላል አገኘው ይህ ነቢየ ሐሰት የተናገረው ትንቢት ባይደርስለት ከለዳውያንን አባብሎ ሊያመጣ ሲሄድ አገኘሁት ብሎ አሳስሮ በአዘቅተ ኵስሕ አስግዞታልና እንዲህ አለ።  

ቦ የሐሰት መሳክርት አይሁድ በጠላትነት ተነሡብኝ፤ 

የማላውቀውን ተናገሩብኝ ማለት እሩቅ ብእሲ ወልደ ዮሴፍ አሉኝ፤  

በጎ ስላደረግሁላቸው ፈንታ ክፉ መለሱልኝ፤ ቦ ድውይ ስለፈወስሁላቸው ሙት ስላነሣሁላቸው ይሙት በቃ ፈረዱብኝ።    

አንባቢ ሆይ! የሐሰት ምስክሮች አይሁድ በጠላትነት ተነሥተው በአምላካችን ላይ የጠላትነት ንግግር ተናግረዋል፤ ይህንን የጠላትነትና የስሕተት ንግግር ይዘው በጥልቅ የክደት ጒድጓድ ውስጥ እየወደቁ ያሉ ብዙ ናቸው፤ ይህ የስሕተት ትምህርት እስርዎን አይሁድ ወደ ወደቁበት አዘቅተ ፍትሕ እንዳይጥልዎ ምን ያህል በማስተዋል ይጓዛሉ? የረቀቀ ምሥጢር ቢያጋጥምዎ ከራስዎ እውቀት ተነሥተው በራስዎ ይወስናሉ? ወይስ ወደ መምህራን ቀርበው የረቀቀው እንዲጐላልዎ የተሠወረው እንዲገለጥልዎ ይጠይቃሉ? 

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳ የእውቀት ሁሉ ባለቤት ሆኖ ሳለ በመቅደስ ተገኝቶ ይሰማም ይጠይቅም ነበር፤ “ከሦስት ቀን በኋላ በመምህራን መካከል ተቀምጦ ሲሰማቸውም ሲጠይቃቸውም በመቀደስ አገኙት የሰሙትም ሁሉ በማስተዋሉና በመልሱ ተገረሙ” እንዲል ሉቃ ፪፡፵፮፤ 

ወንጌል፦  ማቴ ፲፮፥፳፬ – ፍጻሜ፤ 

ዘቅዳሴ ምንባብ፦ 

ዕብ ፲፪፥፩ –፲፪፤

ያዕ ፫፥፩ – ፲፫፤

ግብ ፲፥፩ – ፱፤ 

ወንጌል፦ ፳፩፥፲፪ – ፳፩፤ 

ቅዳሴ፦ ዘባስልዮስ 

ምስባክ ዘቅዳሴ፦ 

ወይርአዩ አሕዛብ በቅድመ አዕይንቲነ፤ 

በቀለ ደሞሙ ለአግብርቲከ ዘተክዕወ፤ 

ይባዕ ቅድሜከ ገዐሮሙ ለሙቁሐን። መዝ ፸፰፥፲፤

ትርጒም፦ 

አሕዛብ በዐይኖቻችን ፊት ይዩ፤ 

የፈሰሰውን የባርያዎችህን የደማቸውን በቀል፤ 

የእስረኞች ጩኸት ወደ ፊትህ ይግባ። 

ምሥጢር፦ 

የባርያዎችህ የፈሰሰ የደማቸው በቀል ሲመለስ አሕዛብ በዐይኖቻችን ፊት ይዩ፤ ቦ እኛ እኩሌቶቻችን ሞተን የእኩሌቶቻችንን ሞት በዐይናችን እንዳየን እነሱም እኩሌቶቹ ሞተው የእኩሌቶቹን ሞት በዐይናቸው ይዩ።

የታሰሩት ሰዎች ጩኸት/ልመና ከፊትህ ይግባ/ይድረስ። 

መስከረም ፲፪ በዓለ ቅዱስ ሚካኤል

ዘነግህ ምስባክ፦ 

ሐለዩ ወነበቡ ከንቶ፤ 

ወነበቡ ዓመፃ ውስተ አርያም፤ 

ወአንበሩ ውስተ ሰማይ አፉሆሙ። መዝ ፸፪፥፰፤ 

ትርጒም፦ 

አስበው ከንቱ ነገርን ተናገሩ፤ 

በአርያምም ዓመፃን ተናገሩ፤ 

አፋቸውንም በሰማይ አኖሩ። 

ምሥጢር፦ 

ሐለዩ ከንቶ ወነበቡ ከንቶ ሲል ነው፤ ከንቱ ነገርን አስበው ከንቱ ነገርን ተናገሩ፤

በአርያም ባለ በእግዚአብሔር ላይ ዐመፅን ተናገሩ፤ 

አንደበታቸውን በሰማይ አኖሩ አለ በሰማይ እግዚአብሔር የለም አሉ፤ ዐመፅ ያለው ይህንን ነው። 

ወንጌል፦ ማቴ ፲፫፥፳፬ – ፵፬፤

ዘቅዳሴ ምንባብ፦ 

፩ቆሮ ፭፥፫ – ፲፩፤

ይሁዳ ፩፥፱ – ፳፤

ግብ ፳፥፳፰ – ፴፩፤

ወንጌል፦ ማቴ ፲፰፥፲፭ – ፲፱፤

ቅዳሴ፦ ዘቄርሎስ 

ዘቅዳሴ ምስባክ፦ 

ይትዐየን መልአከ እግዚአብሔር ዐውዶሙ፤ 

ለእለ ይፈርህዎ ወያድኅኖሙ፤ 

ጠዐሙ ወታእምሩ ከመ ኄር እግዚአብሔር። መዝ ፴፫፥፯፤ 

ትርጒም፦ 

የእግዚአብሔር መልአክ በዙሪያቸው ይሰፍራል፤ 

የሚፈሩትን ያድናቸውማል፤ 

እግዚአብሔር ቸር እንደሆነ ታውቁ ዘንድ ቅመሱ። 

ምሥጢር፦ 

መልአከ እግዚአብሔር በሚፈሩት በሚያመልኩት ዙሪያ ቆሞ ከመከራ ያድናቸዋል፤ ማንን እንደ አዳነ ቢሉ ያዕቆብን ከላባ፣ ኤልሳዕን ከንጉሠ ሶርያ ከወልደ አዴር እንደ አዳነ፤  

ያዕቆብን ከላባ ኤልሳዕን ከወልደ አዴር ማዳኑ እንደምን ነው ቢሉ? ያዕቆብ ከላባ የጌታ አደረ እሱም ከገንዘቡ ከፍሎ ሰጠው የያዕቆብ እየበዛ የላባ እያነሰ ሄደ ላባ እሱን ገድየ ገንዘቡን ወርሼ እኖራለሁ ብሎ አሰበ ከዕለታት በአንድ ቀን በጎቹን ሊያሸልት ወደቀርሜሎስ ሄዶ ሳለ መልአኩ ይህ ሰው ሊገድልህ አስቧልና ልጆችህን ከብቶችህን ሚስቶችህን ይዘህ ሂድ ብሎታል ልጆቹን ከብቶቹን ሚስቶቹን ይዞ ሄዷል ላባ በሦስተኛው ቀን ቢመጣ አጣው ያዕቆብሳ ብሎ ጠየቀ እሱማ ልጆቹን ከብቶቹን ሚስቶቹን ይዞ ወደሀገሩ ሄዶ አሉት ያዕቆብ ሦስት ቀን የሄደውን እሱ በአንድ ቀን ገሥግሦ ደርሶበታል ስለምን ቢሉ ሴት ልጅ ከብት ይዟልና። 

ሌሊት መልአኩ በአጠገቡ ያለውን ቅጠል በሰይፉ እያረገፈ እንዲህ አረግፍሃለሁ እያለ ሲገሥጸው አድሯል ኢትግበር እኩየ ላዕለ ያዕቆብ ቊልዔየ በወዳጄ በያዕቆብ ላይ ክፉ ነገር እንዳታደርግ ብሎታል፤ ሲነጋ ለምንት ትሰርቀኒ ደቂቅየ ወአዋልድየ ከመ ዘበኲናት ተፄወዉ ወሚመ ኢይደልወኒኑ እስዐም ደቂቅየ ወአዋልድየ ለምን ሳትሰናበተኝ መጣህ አለው ትገድለኛለህ ብዬ አለው መልአኩ ሲዘልፈኝ አድሮ ነው እንጂ ልገድልህ ነበር አሁንም የእኔ ልጆች ያንተ፣ ያንተ ልጆች የእኔ ናቸው የአንተ ልጆች የእኔን ልጆች የእኔ ልጆች የአንተን ልጆች እንዳይጣሏቸው እንማማል ብሎት ፍሪዳ አርደው ተማምለዋል ያቺንም ቦታ ቤርሳቤህ ብለዋታል አዘቅተ መሐላ ማለት ነው ከዚህ በኋላ ላባ ወደሀገሩ ተመልሷል ያዕቆብ ከዚያ እልፍ ሲል ተዐይነ እግዚእ አግኝቶ ዝኒ ተዐይኒሁ ለእግዚአብሔር ብሏል ዛሬ ከላባ እንደ አዳንሁ ከዔሳው የማድንህ እኔ ነኝ ብሎታልና እንዲህ አለ። 

ኤልሳዕን ከወልደ አዴር ማዳኑ እንደምን ነው ቢሉ? የሶርያ ንጉሥ ወልደ አዴር የሰማርያ ንጉሥ ኢዮርብዓም ይባላሉ ኢዮርብዓም ከሰው ተለይቶ የሚጸልይባት ምግላል ቦታ አለችው ይህንን ወልደ አዴር ያውቃል ይዛችሁ አምጡልኝ ብሎ በፈረስ በሠረገላ የተጫኑ ሰዎችን ሰደደ ኤልሳዕ በጸጋ አውቆ ዛሬ ከምትጸልይበት ቦታ አትሂድ ጠላት ይይዝሃል አለው እሱም እውነትና ሐሰት መሆኑን ለማወቅ ሰልሉ ብሎ ሰው ሰዷል አዎ ከበዉታል አሉት ሳይሄድ ቀረ እነዚያም አጥተዉት ተመልሰው ሄደዋል ወልደ አዴር እንደምን ሆናችሁ መጣችሁ አላቸው አጣነው/አላገኘውም አሉት ለዚህ ብዬ ሰው አስመልሼ አዳራሽ ገብቼ እልፍኝ ተከትቼ እመክራለሁ ከእናንተ አንዱ ነግሮት ይሆናል እንጂ ከሚጸልይበት ቦታ እንደምን ይቀራል? ብሎ ወርህፀት ነፍሱ ለወልደ አዴር ይላል ተበሳጨ 

ስንኳን የተናገርኸውን ያሰብኸውን የሚያውቅ ነቢይ አለ እሱ ነግሮት ይሆናል አሉት ማነው አለ ኤልሳዕ ነው አሉት ሀገሩ ወዴት ነው አለ ዶታይን አሉት ይዛችሁ አምጡልኝ ብሎ በፈረስ በሠረገላ ሰዎችን ሰደደ፤ የኤልሳዕ ብላቴና ግያዝ ይባላል ልባም ለማፍሰስ ቢሉ ሌላም ሥራ ሊሠራ ቢሉ ቢወጣ በፈረስ በሠረገላ የተጫኑ ሰዎች ከበዋቸው አየ ኧረ አባቴ እንዲህ ያሉ ሰዎች ከበውናል አለው አይዞህ አትፍራ አለው ፈራ እግዚኦ ክሥት ሎቱ ምሥጢረ ለዝንቱ ወልድ ብሎ አመለከተ ሁለተኛ ቢወጣ መላእክት በእሳት ፈረስ በእሳት ሠረገላ ተጭነው የእነዚያን ፊት ወደዚያ መልሰው እነሱ ፊታቸውን ወደዚህ መልሰው ቁመው አይቷል አባቴ አሁንስ እንዲህ ያሉ ሰዎች ከበውናል ብሎታል አይዞህ በወዲያ ያሉ አጥፊዎቻችን በወዲህ ያሉ ጠባቂዎቻችን ናቸው ብሎታል አዑሮሙ ብሎ ወደ እግዚአብሔር ቢያመለክት ሲያዩ እንዳያዩ ሲያውቁ እንዳያውቁ ሆነዋል ወጥቶ መነሃ ተኀሥሡ አላቸው ኤልሳዕሃ ነቢየ አሉ ለኤልሳዕ አኮ ዝየ ማኅደሩ የኤልሳዕ ቤቱ እዚህ አይደለም ብሎ እየመራ ሰማርያ አውርዶ ምግብ መግቦ ምሕረት አድርጎ ሸኝቷቸዋልና እንዲህ አለ።   

ይትዐየን መልአክ እንደምን ይመቻል ቢሉ? አንድ ነውና መልአክ አለ፤ አለቃው ካለበት ጭፍራው አይለይምና ይትዐየን አለ። 

ለአንተ ቢደረግልህ ለእኛ ይደረግልናልን ትሉኝ እንደሆነ አዎና! ይደረግላችኋልና በልመና ቅመሱት፤ የባሕርይ ቸር እንደሆነ ታውቁ ትረዱ ዘንድ፤ 

መዝሙር ሐነጽዋ ለቤተ ክርስቲያን

ለእመ ኮነ ሕንጸተ ቤተ መቅደስ በሰንበት (መስከረም ፲፮) መዝሙር ሐነጽዋ

፬.፩ (በ፮/ሥ) ሐነጽዋ ለቤተ ክርስቲያን ወሣረርዋ በመንፈስ ቅዱስ እንተ ተሐንጸት በእደ ካህናት ወተቀደሰት በአፈ ጳጳሳት ወተዓተበት በማይ ዘውኅዘ እምገቦሁ አመ ሕማማቲሁ ለሰማይ አቅዲሙ ፈጠሮ ወበምድር ተከለ ደብተራ ቀደሳ አብ ወማኅደሮ ረሰያ።

ትርጕም፦

ቤተ ክርስቲያንን በመንፈስ ቅዱስ ሠሯት አነጿት በካህናት እጅ ታንጻለችና በጳጳሳት አፍ ተቀድሳለችና በሕማሙ ጊዜ ከጎኑ በፈሰሰ ውኃ ከብራለችና። አስቀድሞ ሰማይን ፈጠረ በምድርም ድንኳንን ተከለ አብ ቀደሳት ማደሪያውም አደረጋት።

፬.፪ የዕለቱ ምንባባት

፩ቆሮ ፫፥፩ – ፲፰፤

ራእይ ፳፩፥፲ – ፍጻሜ፤

ግብ ፯፥፵፬ – ፶፩፤

ወንጌል፦ ዮሐ ፲፥፳፪ – ፍጻሜ፤

ቅዳሴ፦ ዘእግዚእነ

፬.፫ የዕለቱ ምስባክ፦

ደብረ ጽዮን ዘአፍቀረ፤

ሐነጸ መቅደሶ በአርያም፤

ወሣረራ ውስተ ምድር ዘለዓለም። መዝ ፸፯፥፷፰፤ 

ትርጕም፦

የወደደውን የጽዮንን ተራራ፤

መቅደሱን በአርያም ሠራ፤

ለዘለዓለም በምድር ውስጥ መሠረታት።

ምሥጢር፦

የጽዮንን ተራራ የወደደ እሱ ነው አንድም የእመቤታችንን ሥነ ውበት ለተዋሕዶ የወደደ እሱ ነው፤

መመስገኛው የምትሆን ቤተ መቅደስን በልዕልና ሠራት አንድም ማደሪያው የምትሆን እመቤታችንን በልዕልና ፈጠራት፤

በዚህ ዓለም ለዘለዓለም አጽንቶ ሠራት አንድም እመቤታችንን በንጽሕና በቅድስና አጸናት። 

መስከረም ፲፯ በዓለ ቅዱስ መስቀል

ዘነግህ ምስባክ፦ 

ወወሀብኮሙ ትእምርተ ለእለ ይፈርሁከ፤ 

ከመ ያምሥጡ እምገጸ ቅስት፤ 

ወይድኃኑ ፍቁራኒከ። 

ወንጌል፦ ዮሐ ፫፥፲፬ – ፳፪፤ 

ዘቅዳሴ ምንባብ፦ 

፩ጢሞ ፭፥፱ – ፲፮፤

ያዕ ፫፥፲፩ – ፍጻሜ፤

ግብ ፭፥፳፮ – ፴፫፤

ወንጌል፦ ዮሐ ፲፱፥፳፭ – ፳፰፤

ቅዳሴ፦ ዘዮሐንስ አፈወርቅ 

ዘቅዳሴ ምስባክ፦ 

ወረከብናሁ ውስተ ዖመ ገዳም፤ 

ንበውእ እንከሰ ውስተ አብያቲሁ ለእግዚአብሔር፤ 

ወንሰግድ ውስተ መካን ኀበ ቆመ እግረ እግዚእነ።

መዝሙር ዝንቱ ውእቱ መስቀል

ከመስከረም ፲፯ – መስከረም ፳፫

፭.፩ (በ፫/ደ) ዝንቱ ውእቱ መስቀል በአማን ዕፁበ ያቀልል በጽንዐ ኃይል ወበሠናይ ምግባር በዕፀ መስቀሉ ኃጢአተ ይሠሪ (ዝ) ጸርሑ ጻድቃን እምደብር ልዑል ወኃጥአነ ምድር በማዕከለ ደይን (ዝ) ለእምነ ጽዮን ቆመ ማዕበል በዕለተ ሰንበት ገሠፃ ለባሕር (ዝ) በዕለተ ሰንበት ገሠፃ ለባሕር ደቂቀ እስራኤል ዐደዉ በእግር (ዝ) ደቂቀ እስራኤል ዐደዉ በእግር ንሕነ ነአምን ረድኤተ ወኃይለ (ዝ) ንሕነ ነአምን ረድኤተ ወኃይለ ጽንዕነ ቤዛነ በማዕከለ ፀር (ዝ) ኃይልነ ወፀወንነ ወሞገስነ ዝንቱ ውእቱ መስቀል። 

ትርጕም፦

መስቀል ይህ ነው በእውነት የጨነቀ ነገርን ያቀላል በኃይል ጽናት በበጎ ምግባር በዕፀ መስቀሉ ኃጢአትን ያስተሠርያል። ጻድቃን ከልዑል ተራራ ላይ ሆነው ጮኹ ኃጥአንም በሥቃይ መካከል ሆነው ጮኹ። ለእናታችን ጽዮን ማዕበል ቆመ በዕለተ ሰንበት ባሕርን ገሠፃት የእስራኤል ልጆች በእግር ተሻገሩ እኛም ረድኤቱንና ኃይሉን እናምናለን። መስቀል በጠላት መካከል ጽናችን ቤዛችን ነው። ይህ መስቀል ኃይላችን ፀወናችን ሞገሳችን ነው።

፭.፪ የዕለቱ ምንባባት፦

፩ቆሮ ፩፥፲ – ፍጻሜ፤

፩ጴጥ ፬፥፩ – ፲፪፤

ግብ ፪፥፳፪ – ፴፯፤

ወንጌል፦ ማር ፰፥፳፯ – ፍጻሜ፤  

ቅዳሴ፦  ዘአትናቴዎስ አው ዘዮሐንስ አፈወርቅ፤ 

፭.፫ የዕለቱ ምስባክ፦

ወወሀብኮሙ ትእምርተ ለእለ ይፈርሁከ፤

ከመ ያምስጡ እምገጸ ቅስት፤

ወይድኀኑ ፍቁራኒከ። መዝ ፶፱፥፬ 

ትርጉም፦

ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው፤

ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ፤

ወዳጆችህም እንዲድኑ።

ምሥጢር፦

ለሚፈሩህና ለሚያመልኩህ ለሚጠተ ሥጋ ምልክት የሚሆን ሞተ ብልጣሶርን ሰጠሃቸው።

ከመከራ ሥጋ ይድኑ ዘንድ፤

በሕግ በአምልኮት የሚወዱህ ከመከራ ሥጋ ይድኑ ዘንድ፤

አንድም፦ ለሚያመልኩህ ለሚፈሩህ ለሠለስቱ ደቂቅ ለድኅነተ ነፍስ ምልክት የሚሆን ተአምራትን አደረግህላቸው፤

የሚወዱህ የሚያመልኩህ ሠለስቱ ደቂቅ ከእቶነ እሳት ይድኑ ዘንድ፤

አንድም፦ ለባህታውያን የተመውዖ አጋንንት (የአጋንንት ድል መነሣ’ት / አጋንንትን የማሸነፍ ምልክት) ምልክት የሚሆን ግራ ቀኝ ማማተብን ስመ ሥላሴን መጥራትን ሰጠሃቸው፤

ከፀብዐ አጋንንት/ከአጋንንት ፈተና ይድኑ ይጠበቁ ዘንድ። 

መስከረም ፲፰ በዓለ ኤዎስጣቴዎስ ከፋሌ ባሕር

ዘነግህ ምስባክ፦   

  እስመ መምህረ ሕግ ይሁብ በረከተ፤ 

ወየሐውር እምኃይል ውስተ ኃይል፤ 

ወያስተርኢ አምላከ አማልክት በጽዮን። 

ወንጌል፦ ማቴ ፭፥፩ – ፲፯፤ 

ዘቅዳሴ ምንባብ፦ 

ሮሜ ፲፥፲፩ – ፍጻሜ፤

፪ጴጥ ፫፥፲፬ – ፍጻሜ፤

ግብ ፲፬፥፳፮ – ፍጻሜ፤ 

ወንጌል፦ ሉቃ ፲፭፥፰ – ፲፤

ቅዳሴ፦  ዘሠለስቱ ምዕት 

ዘቅዳሴ ምስባክ፦ 

አንተ ትኴንን ኃይለ ባሕር፤ 

ወአንተ ታረምሞ ለድምፀ ማዕበላ፤ 

አንተ አኅሠርኮ ለዕቡይ ከመ ቅቱል። መዝ ፹፰፥፱፤

ትርጒም፦ 

አንተ የባሕርን ኃይል ትገዛለህ፤ 

የሞገዱንም መናወጥ አንተ ዝም ታሰኘዋለህ፤  

አንተ ትዕቢተኛውን እንደተገደለ አዋረድኸው። 

ምሥጢር፦ 

በውቅያኖስ ያሉ ፍጥረታትን የምትገዛ አንተ ነህ፤ 

የውቅያኖስን ማዕበል ሞገድ ጸጥ የምታደርግ አንተ ነህ፤ እስከ ዝየ ብጽሒ ወኢትትዐደዊ እምወሰንኪ ብለህ፤ ኢዮ ፴፰፥፰፤

ብሔሞትን በውቅያኖስ የወሰንኸው አንተ ነህ፤ ሌዋታንን ሲያይ ለብሔሞት ሰጥቶ ተናገረ።  

ቦ በባሕረ ኤርትራ ያሉ ፍጥረታትን የምትገዛ አንተ ነህ፤ 

የኤርትራን ማዕበል ሞገድ ጸጥ ያደረግኸውን አንተ ነህ፤ እንዲህ አድርገህ ከሦስት ከአራት የከፈልኸው አንተ ነህ፤ 

ዕቡይ ፈርዖንን በባሕረ ኤርትራ ያሰጠምኸው አንተ ነህ።

ቦ በባቢሎን ያሉ ፍጥረታትን የምትገዛ አንተ ነህ፤

ድምፀ ኃያላኒሃ ሲል ነው የአርበኞቹን ድንፋታ ጸጥ ያደረግኸው አንተ ነህ፤ 

ዕቡይ ብልጣሶርን በባቢሎን የወሰንኸው አንተ ነህ።

ቦ በሲኦል በገሃነም ያሉ ነፍሳትን የምትገዛ አንተ ነህ፤ 

የሲኦል የገሃነምን ማዕበል ሞገድ ጸጥ ያደረግህ አንተ ነህ፤ አብ ቢሉ ልጅህን ሰደህ፤ ወልድ ቢሉ ሰው ሆነህ ሥጋ ለብሰህ፤

ዕቡይ ዲያብሎስን አዳምን እንደማሳቱ መጠን በገሃነም የወሰንኸው አንተ ነህ።   

መስከረም ፳፩ በዓለ እግዝእትነ ማርያም

ዘነግህ ምስባክ፦ 

አድኅነኒ እግዚኦ ወተሣሃለኒ፤ 

እስመ በርቱዕ ቆማ እገርየ፤ 

በማኅበር እባርከከ እግዚኦ። መዝ ፳፭፥፲፩፤ 

ትርጒም፦

አቤቱ አድነኝ ይቅርም በለኝ፤ 

እግሮቼ በቅንነት ቆመዋልና፤ 

አቤቱ በማኅበር አመሰግንሃለሁ። 

ምሥጢር፦

አቤቱ ኃጢአቴን ይቅር ብለህ ከመከራው አድነኝ፤ 

እግሬ ቦ ወገኔ በተስፋ በመርህበ ኢየሩሳሌም ቆሟልና፤ ቦ እግረ ልቡናየ በዐሥሩ ቃላት ጸንቷልና፤ 

ይቅር ብትለኝ ብታድነኝ በጉባኤ ቦ በብዙ ወገን አመሰግንሃለሁ። 

ወንጌል፦ ሉቃ ፲፥፲፭ – ፳፭፤ 

ዘቅዳሴ ምንባብ፦ 

፩ቆሮ ፭፥፫ – ፍጻሜ፤

፪ዮሐ ፩፥፬ – ፍጻሜ፤

ግብ ፲፱፥፲፯ – ፳፩፤

ወንጌል፦ ሉቃ ፩፥፴፱፤

ቅዳሴ፦ ዘሠለስቱ ምዕቱ፤

ዘቅዳሴ ምስባክ፦ 

ወትቀውም ንግሥት በል።  

ካልዕ ምስባክ፦ 

አስተጋብኦሙ እምበሐውርት፤ 

እምጽባሕ ወእምዓረብ ወመስዕ ወባሕር፤ 

አስተጋብኦሙ እምበሐውርት። መዝ ፻፮፥፫፤

ትርጒም፦

ከየሀገሩ ሰበሰባቸው፤ 

ከምሥራቅና ከምዕራብ፣ ከመስዕና ከባሕር፤ 

ከየሀገሩ ሰበሰባቸው።

ምሥጢር፦ 

ከአራቱ ማዕዘን ሰበሰባቸው፤ 

በሐውርት ያለውን ይዘረዝራል፤ እምጽባሕ – ከፋርስ፤ እምዓረብ – ከግብፅ፤ ወመስዕ – ከባቢሎን፤ ወባሕር – ከህንድ ሰበሰባቸው።  

መዝሙር መስቀልከ እግዚኦ

አመ ፳ወ፬ ለመስከረም

፮.፩ (በ፪/ዶ) መስቀልከ እግዚኦ ተሰብሐ ኃይለ መስቀልከ ሙቁሐነ ፈትሐ (መ) ኃይለ መስቀልከ እለ ለምጽ አንጽሐ (መ) ኃይለ መስቀልከ አጋንንተ አውጽአ (መ) ኃይለ መስቀልከ ሙታነ አንሥአ (መ) ወሠርዐ ሰንበተ ለሰብእ ዕረፍተ መስቀልከ እግዚኦ ተሰብሐ ወቃልከ እሙን ፈድፋደ።

ትርጕም፦

አቤቱ መስቀልህ ከበረ የመስቀልህ ኃይል የታሰሩትን ፈታ ለምጻሞችን አነጻ አጋንንትን አወጣ ሙታንን አነሣ ለሰው ዕረፍት ይሆን ዘንድ ሰንበትን ሠራህ አቤቱ መስቀልህ ከበረ ቃልህም ፈጽሞ የታመነ ነው።

የዕለቱ ምንባባት፦

፩ቆሮ ፪፥፩ – ፲፪፤

፩ጴጥ ፪፥፳ – ፍጻሜ፤

ግብ ፬፥፲፱ – ፴፩፤

ወንጌል፦ ሉቃ ፱፥፲፰ – ፳፰፤  

ቅዳሴ፦ ዘእግዚእነ

፮.፪ የዕለቱ ምስባክ፦

ወአጽንኦ እግዚኦ ለዝንቱ ዘሠራዕከ ለነ፤ 

ውስተ ጽርሕከ ዘኢየሩሳሌም፤

ለከ ያመጽኡ ነገሥት አምኃ። መዝ ፷፯፥፳፰፤

ትርጕም፦ 

አቤቱ የሠራኽልንን አጽናልን፤

በኢየሩሳሌም ባለው በመቅደስህ፤

ነገሥታት እጅ መንሻ ያመጡልሃል። 

ምሥጢር፦

ይደረግላችኋል ብለህ በነቢያት ያናገርኸውን ወኀሊቆ ሰባ ዓም እትቤቀሎ ለንጉሠ ባቢሎን – ሰባው ዘመን ሲፈጸም የባቢሎንን ንጉሥ እበቀለዋለሁ ያልኸውን ሚጠተ ሥጋውን አንድም ሚጠተ ነፍሱን አጽናልን፤

እንዲህ የሆነ እንደሆነ በኢየሩሳሌም ወደተሠራች ወደ ቤተ መቅደስህ ነገሥታቱ እጅ መንሻውን ይዘው ይመጣሉ አንድም ሰብአ ሰገል ወርቁን ዕጣኑን ከርቤውን ይዘው ይመጣሉ።

መዝሙር ትብሎ መርዓት

አመ ፳ወ፭ ለመስከረም ጸዐተ ክረምት (መዝሙር ትብሎ መርዓት)

፯.፩ (በ፫/የ) ትብሎ መርዓት ለመርዓዊሃ ወልድ እኁየ ነዓ ኀቤየ ወሪደ ኢታጐንዲ ዬ መስቀል ጸገየ ዘጋዲ ምስለ ጴጥሮስ ዓዋዲ ወጳውሎስ ሰዳዲ (ዬ) ማርያም መስቀሎ ለበዓል ኀበ ትወዲ ዬ መስቀል ጸገየ ዘጋዲ ዬ መስቀል ጸገየ ዘጋዲ።

ትርጉም፦ 

መርዓት መርዓዊን ትለዋለች፤ ልጅ ወንድሜ ወደእኔ ና ለመውረድ/ለመምጣት አትዘግይ፤ እሰይ የጋዲ መስቀል አበበ፤ ከአዋጅ ነጋሪው ከጴጥሮስ ጋር አሳዳጅ ከነበረው ከጳውሎስ ጋር ና፤ ማርያም የመስቀሉን በዓል ወደምታደርግበት ና እሰይ የጋዲ መስቀል አበበ።

፯.፪ የዕለቱ ምንባባት፦

ኤፌ ፭፥፳፩ – ፍ፤

ራእይ ፳፩፥፩ – ፱፤ 

ግብ ፳፩፥፴፩ – ፍጻሜ፤

ወንጌል፦ ማቴ ፱፥፲፬ – ፲፰፤

ቅዳሴ፦ ዘአበዊነ ሐዋርያት አው ዘወልደ ነጐድጓድ 

፯.፫ የዕለቱ ምስባክ፦

ውእቱሰ ከመ መርዓዊ ዘይወጽእ እምጽርሑ፤

ይትፌሣሕ ከመ ያርብህ ዘይሜርድ ፍኖቶ፤

እምአጽናፈ ሰማይ ሙጻኡ። መዝ ፲፰፥፭፤

ትርጕም፦ 

እርሱ እንደ ሙሽራ ከእልፍኙ ይወጣል፤

በመንገዱ እንደሚራመድ አርበኛ ደስ ይለዋል፤ 

አወጣጡ ከሰማይ ዳርቻዎች ነው።

ምሥጢር፦

ፀሐይ ከጫጉላው የወጣ ሙሽራን ይመስላል፤ ምነው ሙሽራው ፀሐይ ይመስላል ይባላል እንጂ ፀሐዩ ሙሽራ ይመስላል ይባላልን? ቢሉ መመሳሰል የጋራ ከሆነ ብሎ እንዲህ አለ፤

ከመ ይርባሕ ሲል ነው ይረባ ይጠቅም ዘንድ ፀሐይ በወጣ ጊዜ ጎዳናውን የሚጠበጥብ ሰው ደስ ይለዋል፤

ከፀሐይ መውጫ እስከ ፀሐይ መግቢያ። አንድም ከፀሐይ ብርሃን የሚሠወር የለም፤ ፀሐይ ከመስኮቱ በወጣ ጊዜ ከቆጡ የተሰቀለው ከግድግዳው የተንጠለጠለው ይገለጣልና። 

መስከረም ፳፱ በዓለ ልደቱ ለእግዚእነ

ዘነግህ ምስባክ፦

ይትፌሥሓ አድባረ ጽዮን፤ 

ወይትሐሠያ አዋልደ ይሁዳ፤ 

በእንተ ፍትሕከ እግዚኦ። መዝ ፵፯፥፲፩፤

ትርጒም፦  

 የጽዮን ተራሮች ደስ ይሰኛሉ፤ 

የይሁዳ ሴቶች ልጆች ሐሤት ያደርጋሉ፤ 

አቤቱ ስለፍርድህ። 

ምሥጢር፦ 

የጽዮን ነገሥታት ደስ ይላቸዋል፤ 

የይሁዳ ንግሥታትም ሐሤት ያደርጋሉ፤ 

ሰናክሬምን አጥፍተህ ሕዝቅያስን ስለ አዳንህላቸው። 

ወንጌል፦ ማቴ ፳፭፥፩ – ፲፬፤

ዘቅዳሴ ምንባብ፦ 

ገላ ፬፥፩ – ፲፪፤

፩ዮሐ ፩፥፩ – ፍጻሜ፤

ግብ ፫፥፩ – ፲፪፤

ወንጌል፦ ፳፩፥፳፩ – ፍጻሜ፤

ቅዳሴ፦ ዘእግዚእነ 

ዘቅዳሴ ምስባክ፦ 

እግዚአብሔር ይቤለኒ ወልድየ አንተ፤ 

ወአነ ዮም ወለድኩከ፤ 

ሰአል እምኔየ እሁበከ አሕዛበ ለርስትከ። መዝ ፪፥፯፤

ትርጉም፦

እግዚአብሔር አለኝ አንተ ልጄ ነህ፤ 

እኔም ዛሬ ወለድሁህ፤ 

ለምነኝ አሕዛብን ለርስትህ እሰጥሃለሁ። 

ምሥጢር፦ 

ቅድመ ዓለም አካል ዘእምካል የወለድሁህ ልጄ ነህ ይለኛል፤ ቃል በሥጋ ተገብቶ፤ 

አነን አይሻውም ወዮም ወለድኩከ ነው ዛሬም አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም አካል ዘእምአካል የወለድሁህ ልጄ ነህ ይለኛል፤ ሥጋ በቃል ርስት ተገብቶ፤

ቦ እግዚአብሔር ይቤለኒ፦ በተዋሕዶ የወለድሁህ ልጄ ነህ ይለኛል፤ 

ወዮም ዛሬም በግብረ መንፈስ ቅዱስ የወለድሁህ ልጄ ነህ፤ 

ቦ እግዚአብሔር ይቤለኒ፦ በግብረ መንፈስ ቅዱስ የወለድሁህ ልጄ ነህ ይለኛል፤

ወዮም ዛሬም በትንሣኤ የወለድሁህ የባሕርይ ልጄ ነህ አለ ሁለተኛ የሚወልደው ሆኖ አይደለም የምሳሌ አነጋገር ነው፤ አባት ዘምቶ ያረጃል በልቶ ያፈጃል ርስቱን ጉልቱን ተቀምቶ ሲኖር ልጄ ዘምቶ ያረጀ በልቶ ያፈጀ ይሉሃል እኔ ነኝ በርስቴ ውጣበት ውረድበት ብሎ ይሰጠዋል 

ልጁም ወጣሁ ልጅ ነኝ ፈላሁ ጠጅ ነኝ ብሎ ደርሶለት ግንባሩን ለጦር እግሩን ለጠጠር ሰጥቶ ወጥቶ ወርዶ ርስቱን ጉልቱን ያስመለሰለት እንደሆነ ቀድሞም ልጄ ዛሬም ልጄ ይልቁንም ዛሬ ወለድሁህ ይለዋል፤ ጌታም አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን በግብርናተ ዲያብሎስ ተይዘው የነበሩ ነፍሳትን እለ ውስተ ሲኦል ፃዑ ወእለ ውስተ ጽልመት ተከሠቱ ወርእዩ ብርሃነ ዐቢየ – በሲኦል ያላችሁ ውጡ በጨለማ ያላችሁ ተገለጡ ብርሃንን እዩ ብሎ በገነት ባደረገ ጊዜ ዛሬም ልጄ ነህ አለው እንጂ። 

ርስት ትሆናቸው ዘንድ አሕዛብን ለምነኝና እሰጥሃለሁ “ለሊሁ ዓለሞሙ ወለሊሁ ውእቱ ርስቶሙ – ዓለማቸው እርሱ ነው ርስታቸው እርሱ ነው” እንዲል፤ ቦ ሰአል፦ ርስት ሊሆኑህ አሕዛብን ለምን እሰጥሃለሁ “ንሕነ አባል ወውእቱ ርእስ – እኛ ሕዋስ እርሱ ራስ ነው” እንዲል፤ ቦ ርስት መንግሥተ ሰማያትን ልታወርሳቸው አሕዛብን ለምን እሰጥሃለሁ። አሁን ድኅረ ተዋሕዶ በአብ መለመን በወልድ መለመን ኑሮ አይደለም ቅድመ ተዋሕዶ ንዴት ስኢል ይስማማው የነበረ ሥጋን እንደተዋሐደ ለማጠየቅ ነው። አይቴ ቀበርክምዎ ለአልዓዛር እንዳለው ያለ ነው። 

ይህንንም ሊቁ፦ አኮ በኢያእምሮቱ ኅቡዓተ አላ ከመ የሀብ መካነ ለጥንተ ትስብእቱ ዘኢየአምር ኅቡዓተ – የተሠወረውን ባለማወቁ አይደለም የተሠወረውን ለማያውቅ ትስብእቱ ቦታ ይሰጥ ዘንድ ነው እንጂ” ብሎ ወስዶታል።

መዝሙር ትዌድሶ መርዓት

ከመስከረም ፳፮ – ጥቅምት ፪

፰.፩ (በ፬/ኵ) ትዌድሶ መርዓት እንዘ ትብል ነዓ ወልድ እኁየ ንጻእ ሐቅለ(ት) ንርዓይ ለእመ ጸገየ ወይን ወለእመ ፈረየ ሮማን(ት) አሠርገወ ሰማየ በከዋክብት ወምድረኒ በሥነ ጽጌያት(ት) እስመ ውእቱ ወልድ ዋሕድ እግዚኣ ለሰንበት ትዌድሶ መርዓት ወትብሎ ወልድ እኁየ ቃልከ አዳም።

ትርጉም፦

መርዓት ልጅ ወንድሜ ና ወደመስክ እንውጣ እያለች ታመሰግነዋለች። ወይን አብቦ እንደሆነ ሮማንም አፍርቶ እንደሆነ እንይ። ሰማይን በከዋክብት ምድርንም በአበቦች አስጌጠ። የሰንበት ጌታ ወልድ ዋሕድ ነውና። ልጅ ወንድሜ ቃልህ ያማረ ነው እያለች ታመሰግነዋለች። 

ምሥጢር፦

መርዓት የተባለች ቤተ ክርስቲያን ናት እሷ አካሉ ስትሆን እሱ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ራስ ነውና፤ 

ወደመስክ እንውጣ ማለት፦ 

ለጊዜው ኢየሩሳሌም ጠፍታ ነበርና መስክ/ሐቅል አላት፤ ፍጻሜው ግን የሰው ልጅ ከጸጋ እግዚአብሔር ተራቁቶ የነበረ መሆኑን ያሳያል “በእርሱ ድህነት እናንተ ባለጠጎች ትሆኑ ዘንድ ስለእናንተ ድሀ ሆነ” እንዳለ ሐዋርያው ፪ቆሮ ፰፥፱

ወይኑ አብቦ ሮማኑ አፍርቶ እንደሆነ ማለት፦ የጸና ሃይማኖት የቀና ሥነ ምግባር ቢኖራቸው በዓይነ ምሕረት ተመልከታቸው ማለት ነው።

፰.፪ የዕለቱ ምንባብ፦ 

ኤፌ ፭፥፳፩ – ፍ፤

ራእይ ፳፩፥፩ – ፱፤ 

ግብ ፳፩፥፴፩ – ፍ፤

ወንጌል፦ ዮሐ ፫፥፳፭

ቅዳሴ፦ ዘእግዝእትነ ማርያም

፰.፫ የዕለቱ ምስባክ፦

ፍሬ ፃማከ ተሴሰይ፤

ብፁዕ አንተ ወሠናይ ለከ፤

ብእሲትከ ከመ ወይን ሥሙር ውስተ ጽርሐ ቤትከ። መዝ ፻፳፯፥፪

ትርጕም፦

የድካምህን ዋጋ ተመገብ፤

ብፁዕ ነህ መልካምም ይሆንልሃል፤

ሚስትህ በቤት ከእልፍኝ ውስጥ እንደሚያፈራ ወይን ትሆናለች።

ምሥጢር፦ 

በጾም በጸሎት በፍጹም ሃይማኖትና በፈሪሃ እግዚአብሔር ሆነህ ሥጋውን ደሙን ተቀበል።

እንዲህ ያደርግህ እንደሆነ ድኅነተ ሥጋ ድኅነተ ነፍስ ታገኛለህና ለአንተ መልካም ነው።

በሰውነትህ ተዋሕዳ ያለች ነፍስህም እንደተወደደ ወይን ፍሬ በረከትን ታገኛለች።