ታኅሣሥ ፫ በአታ ለማርያም ውስተ ቤተ መቅደስ
ዘነግህ ምስባክ፦
እበውእ ቤተከ ምስለ መባዕየ፤
ወእሁብ ብፅዓትየ ዘነበብኩ በአፉየ፤
ዘእቤ በከናፍርየ አመ ምንዳቤየ። መዝ ፷፭፥፲፫፤
ትርጒም፦
ከመባዬ ጋር ወደቤትህ እገባለሁ፤
በአፌ የተናገርሁትን ስለቴን እሰጣለሁ፤
በመከራዬ ጊዜ በከንፈሮቼ የተናገርሁትን።
ምሥጢር፦
መባዬን ይዤ ወደቤትህ ወደ መቅደስህ እገባለሁ፤
ከፋርስ ከባቢሎን ብታወጣኝ ይህን እሰጣለሁ ብዬ የተሳልሁትን ስለቴን እሰጣለሁ፤
በአፉየ ያለውን ዘእቤ በከናፍርየ ብሎ ደገመው፤
ወንጌል፦ ማቴ ፩፥፩ ߺ ፲፯፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
ዕብ ፱፥፩ ߺ ፲፩፤
፪ዮሐ ፩፥፭ ߺ ፰፤
ግብ ፩፥፲፪ ߺ ፲፭፤
ወንጌል፦ ሉቃ ፩፥፴፱ ߺ ፶፯፤
ቅዳሴ፦ ዘእግዝእትነ ማርያም
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
ስምዒ ወለትየ ወርእዪ ወአጽምዒ ዕዝነኪ፤
ርስዒ ሕዝበኪ ወቤተ አቡኪ፤
እስመ ፈተወ ንጉሥ ሥነኪ። መዝ ፵፬፥፲፤
ትርጒም፦
ልጄ ሆይ ስሚ እዪ ጆሮሽንም አዘንብዪ፤
ወገንሽን የአባትሽንም ወገን እርሺ፤
ንጉሥ ውበትሽ ወዷልና።
ምሥጢር፦
ልጄ ምእመን ምክሬን ትምህርቴን ስሚ እዪ ተመልከቺ ጆሮሽን አዘንብለሽ አድምጪ፤ ነቢይ ነውና ሁሉን ልጄ ይላል፤
ልማደ ናኮርን ልማደ ራግውን እርሺ አለ አምልኮ ጣዖትን ገቢረ ኃጢአትን ተዪ፤ “አኮ በረሲዐ ሕዝባ አላ በእንተ ኃጢአታ – ወገኗን በመርሳቷ አይደለም ስለኃጢአቷ ነው” እንዲል፤
ንጉሥ ክርስቶስ ሥነ ሃይማኖትሽን ሥነ ምግባርሽን ወዷልና።
ቦ ልጄ ድንግል ማርያም ስሚኝ ወደእኔ ተመልከቺ ቃለ መልእክቴን አድምጪ ይላል ቅዱስ ገብርኤል፤ አይወልዳትምና ኢትፍርሂ ይላል ቅዱስ ገብርኤል፤ ይወልዳታልና ስምዒ ይላታል ዳዊት፤
በዘር በሩካቤ እወልዳለሁ ማለትን እርሺ፤ አሁን እመቤታችን ነገሩን ሽታው አይደለም፤
“ዘንተ ትቤ ድንግል በእንተ ዘኢዐርገ ውስተ ልባ ሕሊና ዕጓለ እመሕያው – የሰው ሐሳብ በልቧ ስለሌለ ድንግል ይህን አለች ” እንዲል፤ ቦ እሱ መክሮ አስተምሮ የሚያስተዋት ሆኖ አይደለም በቅታ መገኘቷን መናገር ነው፤
ንጉሥ ክርስቶስ ሥነ ሥጋሽን ለተዋሕዶ ወዶታልና።
፳፪ ሠርዐ ሰንበተ
መዝሙር ሠርዐ ሰንበተ ከታኅሣሥ ፬ – ፮
፳፪.፩ (በ፭/ሴ) ሠርዐ ሰንበተ ለሰብእ ዕረፍተ ለእለ በሰማይ ወለእለ በምድር ለእለ በባሕር ወለእለ በየብስ (ሠ) ለአበዊነ ለነቢያት ወለሐዋርያት (ሠ) ለጳጳሳት ወለቀሳውስት ለዲያቆናት ወለመነኮሳት (ሠ) ለጻድቃን ወለኃጥአን ለሙታን ወለሕያዋን ሠርዐ ሰንበተ ለሰብእ ዕረፍተ ሰንበቱሰ ለክርስቶስ ይእቲ ወማኅደረ ስሙ ለልዑል።
ትርጕም፦
ለሰው ዕረፍት ሰንበትን ሠራ፤ በሰማይና በምድር በባሕርና በየብስ ላሉት ሁሉ። ለአባቶቻችን ለነቢያትና ለሐዋርያት፤ ለጳጳሳትና ለቀሳውስት ለዲያቆናትና ለመነኮሳት፤ ለጻድቃንና ለኃጥአን ለሙታንና ለሕያዋን፤ ለሰው ዕረፍት ትሆን ዘንድ ሰንበትን ሠራ ይህች የክርስቶስ ሰንበት ናት የልዑል የስሙ መጠሪያም ናት።
፳፪.፪ የዕለቱ ምንባባት፦
፩ቆሮ ፲፭፥፲፪ – ፴፫፤
፪ጴጥ ፫፥፲ – ፍጻሜ፤
ግብ ፳፥፳፰ – ፍጻሜ፤
ወንጌል፦ ሉቃ ፲፪፥፴፪ – ፵፩፤
ቅዳሴ፦ ዘአትናቴዎስ
፳፪.፫ የዕለቱ ምስባክ፦
ለነዳያኒሃኒ አጸግቦሙ እክለ፤
ወለካህናቲሃኒ አለብሶሙ ሕይወተ፤
ወጻድቃኒሃኒ ትፍሥሕተ ይትፌሥሑ። መዝ ፻፴፩፥፲፭፤
ትርጕም፦
ድኆችዋን እህልን አጠግባቸዋለሁ፤
ለካህናቶቿም ሕይወትን አለብሳቸዋለሁ፤
ጻድቃኖቿም እጅግ ደስ ያቸዋል።
ምሥጢር፦
ነዳያነ ነፍስን እክለ ጸጋን ብዕለ ጸጋን አንድም ሥጋ ወደሙን ልጅነትን ሰጥቼ ደስ አሰኛቸዋለሁ።
ካህናቱንም ሐይው ከመ መላእክትን እሰጣቸዋለሁ።
ትሩፋን ፈጽሞ ደስ ይላቸዋል አንድም ጻድቃን መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው ደስ ይላቸዋል።
፳፫ ወልዶ መድኅነ
መዝሙር ዘስብከት ከታኅሣሥ ፯ – ፲፫
፳፫.፩ (በ፪/ዩ) ወልዶ መድኅነ ንሰብክ ዘእምቅድመ ዓለም ሀሎ፤ አክሊለ ሰማዕት ሠያሜ ካህናት ወተስፋ መነኮሳት ወልዶ መድኅነ ንሰብክ ወልዶ መድኅነ ንሰብክ።
ትርጕም፦
ቅድመ ዓለም የነበረ መድኃኒት ልጁን እንሰብካለን፤ የሰማዕታት አክሊል፣ ካህናትን የሚሾም፣ የመነኮሳት ተስፋ የሆነ መድኃኒት ልጁን እንሰብካለን።
፳፫.፪ የዕለቱ ምንባባት፦
ዕብ ፩፥፩ – ፍጻሜ፤
፪ጴጥ ፫፥፩ – ፲፤
ግብ ፫፥፲፯ – ፍጻሜ፤
ወንጌል፦ ዮሐ ፩፥፵፬ – ፍጻሜ፤
ቅዳሴ፦ ዘእግዚእነ
፳፫.፫ የዕለቱ ምስባክ፦
ፈኑ እዴከ እምአርያም፤
አድኅነኒ ወባልሐኒ እማይ ብዙኅ፤
ወእምእዴሆሙ ለደቂቀ ነኪር። መዝ ፻፵፫፥፯፤
ትርጉም፦
እጅህን ከአርያም ላክ፤
ከብዙ ውኃም አድነኝ፤
ከባዕድ ልጆችም አድነኝ።
ምሥጢር፦
ረድኤትህን ከአርያም ላክ አንድም ልጅህን በሥጋ ላክ፤
ከብዙ ጦር/ሠራዊት አድነኝ አንድም ከፍትወታት እኩያት ከኃጣውእ ርኵሳት ከፍዳ ከመከራ ነፍስ ፈጽመህ አድነኝ።
ከነናምሩድ ከነሳኦል ልጆች እጅ አድነኝ አንድም ከዲያብሎስ ወገኖች ሥልጣን አድነኝ።
ክንድ ከአካል ተገኝቶ ከአካል ሳይለይ ይኖራል፤ እሱም ከአብ ተገኝቶ ከአብ ሳይለይ ይኖራልና። ቦ የሰው ኃይሉ በክንዱ እንዲታወቅ የአብም ኃይሉ በወልድ ታውቋልና። ቦ ክንድ ከአካል ሳይለይ የወደቀ አንሥቶ ይመለሳል፤ እሱም ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ አንድነት ሳይለይ የወደቀ አዳምን አንሥቶ ተመልሷልና። ቦ በክንድ የራቀ ያቀርቡበታል የቀረበ ያርቁበታል፤ የራቀ አዳምን አቅርቦበታል የቀረበ ዲያብሎስን አርቆበታልና። ቦ በክንድ አሥረው ያጠብቁበታል ወርውረው ያርቁበታል፤ ዲያብሎስን በእሳት ዛንጅር ይዞ በነፋስ አውታር አሥሮ ከሰው ሕይወት አርቆበታልና። ቦ በክንድ የታሠረ ይፈቱበታል የተፈታ ያሥሩበታል፤ የታሠረ አዳምን ፈትቶበታል የተፈታ ዲያብሎስን አሥሮበታልና። ኋላም ሑሩ እምኔየ ብሎ ያርቅበታል ንዑ ኀቤየ ብሎ ያቀርብበታልና እጅህን ላክ አለ።
፳፫.፬ መልእክት፦
ዛፍ ከሥሩ ሳይነቀል ጫፉ መሬት ነክቶ ይመለሳል የአምላክ ሰው የመሆን ምሥጢርም እንዲሁ ነው። ምሥጢሩ የዚህን ያህል ጥልቅና ረቂቅ ከሆነ በምሥጢረ ሥጋዌ ዙሪያ አምላክ እንዴት ሰው እንደሆነ ሰውም እንዴት አምላክ እንደሆነ ተመራምሬ እደርሳለሁ ማለት የውቅያኖስን ውኃ በእንቁላል ቅርፊት ቀድቶ ለመጨረስ እንደመሞከር ነው።
ታኅሣሥ ፲፪ በዓለ ቅዱስ ሚካኤል ወበዓለ ቅዱስ አቡነ ሳሙኤል
ዘነግህ ምስባክ፦
ጻድቅሰ ከመ በቀልት ይፈሪ፤
ወይበዝኅ ከመ ዘግባ ዘሊባኖስ፤
ትኩላን እሙንቱ ውስተ ቤተ እግዚአብሔር። መዝ ፺፩፥፲፪፤
ትርጒም፦
ጻድቅ እንደ ዘንባባ ያፈራል፤
እንደ ሊባኖስ ዝግባም ያድጋል፤
በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ የተተከሉ ናቸው።
ምሥጢር፦
ጻድቅ ሰው እንደ ዘንባባ ነው ያ ብዙ እንዲያፈራ ብዙ ይከብዳል ይወልዳል፤ ቦ ጻድቅ ሕዝቅያስ እንደ ዘንባባ ነው፤ ያ ብዙ እንዲያፈራ እሱም ብዙ ይሰጣል ይመጸውታል፤
ልጁ የልጅ ልጁ እንደ ደጋ ዛፍ ከብሮ ገኖ ይኖራል፤
በእግዚአብሔር ቤት ጸንተው ይኖራሉ።
ወንጌል፦ ማቴ ፮፥፲፱ ߺፍጻሜ፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
ዕብ ፮፥፩ ߺ ፲፫፤
ይሁዳ ፩፥፱ ߺ ፲፬፤
ግብ ፲፥፪ ߺ ፱፤
ወንጌል፦ ፲፰፥፲፪ ߺ ፳፫፤
ቅዳሴ፦ ዘሠለስቱ ምዕት
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
ወሳሙኤልኒ ምስለ እለ ይጼውዑ ስሞ፤
ይጼውዕዎ ለእግዚአብሔር ውእቱኒ ይሰጠዎሙ፤
ወይትናገሮሙ በዓምደ ደመና። መዝ ፺፰፥፮፤
ትርጒም፦
ሳሙኤልም ስሙን ከሚጠሩት ጋር፤
እግዚአብሔርን ይጠሩታል እሱም ይመልስላቸዋል፤
በደመና ዐምድም ይናገራቸዋል።
ምሥጢር፦
ሳሙኤል ስሙን በአምልኮት በጸሎት ከሚጠሩት ጋር ቅዱስ ነው፤
እግዚአብሔርን በአምልኮት በጸሎት ይጠሩታል፤ ቦ ሳሙኤል ወእለ ይጼውዑ ስሞ ሳሙኤልና ስሙን የሚጠሩ ይሰግዱለታል፤
እሱም እሽ በጎ ብሎ በረድኤት ይመልስላቸዋል፤ ቦ ልመናቸውን ይሰማቸዋል ማለት የለመኑትን ያደርግላቸዋል፤
በዐምደ ደመና ይናገራቸዋል። አሮንንስ ይሁን ሳሙኤልን መቼ ተነጋገረው ቢሉ እሱንም ተናግሮታል አሕዛብ በእስራኤል ላይ በጠላትነት በተነሱባቸው ጊዜ ከሳሙኤል ዘንድ ሄደው ሳሙኤል ጸሊ በእንቲአነ ወኢታርምም አሉት መሐስዐ ጠሊ ሠውቶ ወደ እግዚአብሔር ቢያመለክት መብረቅ ነጐድጓድ ደመና ሆኗልና።
፳፬ አቅዲሙ ነገረ በኦሪት
መዝሙር ዘብርሃን ከታኅሣሥ ፲፬ – ፳
፳፬.፩ (በ፮/ሁ) አቅዲሙ ነገረ በኦሪት ከመ ይመጽእ ወልድ በስብሐት ዘይዜንዋ ለጽዮን ቃለ ትፍሥሕት ወካዕበ ይቤ በአፈ ዳዊት ቡሩክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር ብርሃን ዘመጽአ ውስተ ዓለም ዘያበርህ ላዕለ ጻድቃን መርዓዊሃ ለቤተ ክርስቲያን ይርዳእ ዘተኀጒለ ያስተጋብእ ዝርዋነ መጽአ ኀቤነ።
ትርጕም፦
ለጽዮን የደስታ ቃልን የሚያበሥራት ወልድ በምስጋና እንደሚመጣ አስቀድሞ በኦሪት ተነገረ ዳግመኛ በዳዊት አንደበት በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው አለ ወደ ዓለም የመጣው ብርሃን ለጻድቃን የሚያበራ የቤተ ክርስቲያን ሙሽራ ነው የጠፋውን ይረዳ/ይፈልግ ዘንድ የተበተኑትን ይሰበስብ ዘንድ ወደእኛ መጣ።
አጭርመግለጫ፦
፩. በኦሪት ዘፍጥረት ፫፥፳፪ “አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንዳንዱ ሆነ” ተብሎ የተነገረው፤
፪. በዘፍጥረት ፱፥፳፯ “እግዚአብሔር በሴም ድንኳን ይደር” ተብሎ የተነገረው፤
፫. በኦሪት ዘጸአት ፫፥፪ ጀምሮ በምሳሌ የተገለጠው፤
፬. በዘጸአት ፴፫፥፳፫ “ጀርባዬን ታያለህ ፊቴ ግን ለአንተ አይታይም” ተብሎ በምሥጢር የተነገረው
፭. በኦሪት ዘኊልቊ ፳፬፥፲፯ “ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል ከእስራኤል ሰው ይነሣል” ተብሎ በምሳሌ የተገለጠው፤
፮. በኦሪት ዘዳግም ፲፰፥፲፭ “አምላክህ እግዚአብሔር ከወንድሞችህ እንደእኔ ያለ ነቢይ ያስነሣልሃል እሱን ስሙት” ብሎ ሊቀ ነቢያት ሙሴ የተናገረው
፯. በትንቢተ ኤርምያስ ፴፩፥፲ “አሕዛብ ሆይ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ በሩቅም ላሉ ደሴቶች አውሩና እስራኤልን የበተነ እርሱ ይሰበስበዋል እረኛም መንጋውን እንደሚጠብቅ ይጠብቀዋል በሉ እግዚአብሔር ያዕቆብን ተቤዥቶታል ከበረቱበትም እጅ አድኖታል” ተብሎ የተነገረው የማጽናኛ ትምህርትና ሌሎችም አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው እንደሚሆንና እኛን እንደሚያድነን አስቀድመው በኦሪትና በነቢያት መጻሕፍት የተመዘገቡ ናቸው። ሊቁም የዘመረው ይህንን እያነጻጸረ ነው።
፳፬.፪ የዕለቱ ምንባባት፦
ሮሜ ፲፫፥፲፩ – ፍ፤
፩ዮሐ ፩፥፩ – ፍ፤
ግብ ፳፮፥፲፪ – ፲፱፤
ወንጌል፦ ዮሐ ፩፥፩ – ፲፱፤
ቅዳሴ፦ ዘአትናቴዎስ
፳፬.፫ የዕለቱ ምስባክ፦
ፈኑ ብርሃነከ ወጽድቅከ፤
እማንቱ ይምርሓኒ ወይሰዳኒ ደብረ መቅደስከ፤
ወውስተ አብያቲከ እግዚኦ። መዝ ፵፪፥፫
ትርጕም፦
ብርሃንህንና ጽድቅህን ላክ፤
እነሱ ይምሩኝ፤
አቤቱ ወደመቅደስህ ተራራና ወደማደሪያህ ይውሰዱኝ።
ምሥጢር፦
ብርሃነ ረድኤትህን አንድም ቂሮስ ዳርዮስን ዮሴዕ ዘሩባቤልን ላክልኝ።
እነሱ መመስገኛህ ወደምትሆን ወደኢየሩሳሌም መርተው ይውሰዱኝ።
አንድም ብርሃን ልጅህን ላክልኝ። አንድም ብርሃነ ጽድቅ ክርስቶስ ሆይ ሥጋህን ደምህን ስጠኝ።
አንድም ሐዋርያትን ሰባ አርድእትን ላክልኝ።
እነሱ መርተው ወደገነት ወደመንግሥተ ሰማያት ያግቡኝ።
ታኅሣሥ ፲፱ በዓለ ቅዱስ ገብርኤል
ዘነግህ ምስባክ፦
ባርክዎ ለእግዚአብሔር ኵልክሙ መላእክቲሁ፤
ጽኑዓን ወኃያላን እለ ትገብሩ ቃሎ፤
ወእለ ትሰምዑ ቃለ ነገሩ። ትርጒምና ምሥጢር ኅዳር ፳፬ ተመልከት።
ወንጌል፦ ዮሐ ፲፪፥፳፱ ߺ ፴፬፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
፪ተሰ ፩፥፮ ߺ ፍጻሜ፤
ይሁዳ ፩፥፳ ߺ ፍጻሜ፤
ግብ ፯፥፴ ߺ ፴፭፤
ወንጌል፦ ሉቃ ፩፥፲፩ ߺ ፳፩፤
ቅዳሴ፦ ዘእግዝእትነ ማርያም
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
በቅድመ መላእክቲከ እዜምር ለከ፤
ወእሰግድ ውስተ ጽርሐ መቅደስከ፤
ወእገኒ ለስምከ። መዝ ፻፴፯፥፩፤
ትርጒም፦
በመላእክት ፊት እዘምርልሃለሁ፤
በቤተ መቅደስህም ውስጥ እሰግዳለሁ፤
ለስምህ እገዛለሁ።
ምሥጢር፦
በአለቆቹ ፊት ምስጋና አቀርባለሁ፤
በአምስቱ በስድስቱ ቆመ ብእሲ ለአንተ እሰግዳለሁ፤
ለስምህም ምስጋና አቀርባለሁ።
፳፭ ኖላዊ ዘመጽአ
መዝሙር ዘኖላዊ ከታኅሣሥ ፳፩ ߺ ፳፯
፳፭.፩ (በ፪/ሩ) ኖላዊ ዘመጽአ ውስተ ዓለም ወልዱ ወቃሉ ለእግዚአብሔር ዘወረደ እምላዕሉ በአቅሙ ክርስቶስ እስመ ውእቱ እግዚኣ ለሰንበት ይቤሎ አብ ለወልዱ ወልድየ ንበር በየማንየ።
ትርጉም፦
ወደ ዓለም የመጣው እረኛ የእግዚአብሔር አብ ቃሉና ልጁ ነው ከላይ የወረደውም ክርስቶስ ተብሎ ይጠራ ዘንድ ነው የሰንበት ጌታ እሱ ነውና አብ ልጁን ልጄ በቀኜ ተቀመጥ አለው።
፳፭.፪ የዕለቱ ምንባባት፦
ዕብ ፲፫፥፲፮ – ፍ፤
፩ጴጥ ፪፥፳፩ – ፍ፤
ግብ ፲፩፥፳፪ -ፍ፤
የዕለቱ ወንጌል፦ ዮሐ ፲፥፩ – ፳፪
ቅዳሴ ዘእግዚእነ
፳፭.፫ የዕለቱ ምስባክ፦
ኖላዊሆሙ ለእስራኤል አጽምዕ፤
ዘይርዕዮሙ ከመ አባግዐ ዮሴፍ፤
ዘይነብር ላዕለ ኪሩቤል አስተርአየ። መዝ ፸፱፥፩
ትርጕም፦
ዮሴፍን እንደ መንጋ የምትመራ የእስራኤል ጠባቂ አድምጥ፤
በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ ተገለጥ።
ምሥጢር፦
የዮሴፍ በጎች እንዲጠበቁ እስራኤል ዘነፍስን የምትጠብቅ ሆይ ጸሎታችንን አድምጥ ስማ።
በዘባነ ኪሩቤል ተቀምጠህ በአንድነት በሦስትነት የምትመሰገን አቤቱ በሥጋ ማርያም ተገለጥ አንድም በመምርነት ተገለጥ።
፳፭.፬ የወንጌሉ አጠቃላይ መልእክት፦
፩. በበሩ የማይገባ በሌላ የሚገባ ሌባ ነው።
ዛሬም በበሩ የማይገቡና በትክክለኛው በር መግባትን የሚከለክሉ በሰፊው መንገድ የሚሄዱና የሚወስዱ ብዙ ናቸው። እኛን የሚጠቅመን ግን በጠበበው ደጅ መግባቱ ነው እሱ ወደዘለዓለም ሕይወት ያደርሰናልና።
፪. በጎቹ የእረኛቸውን ድምጽ ሰምተው ለይተው ያውቃሉ።
የቤተ ክርስቲያን ድምጽ የሚመስሉ ግን ያልሆኑ ብዙ ድምጾች አሉ እውነተኛውን ድምጽ መስማትና እውነተኛውን እረኛ መከተል ለሕይወታችን ይጠቅመናል።
፫. ከእውነተኛው እረኛ በፊት የመጡ ሌቦች ነበሩ።
በግብረ ሐዋርያት ፭ እንደተገለጠው ይሁዳ ዘገሊላና ቴዎዳስ ዘግብጽ ክርስቶስ ነን ብለው ተነሥተው ነበር እነሱም ጠፉ የተከተሏቸውም ጠፍተዋል። የምንከተላቸው የሚያድኑን እንጂ የሚያጠፉን መሆን የለባቸውም። እንዴት እናውቃቸዋለን ብለን እንዳንጨነቅ አምላካችን ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ ብሎናል።
፬. በበሩ የሚገባ መውጣት መግባት ይችላል መሰማሪያም ያገኛል።
ይህ የሚያሳየን በአባታችን ቤት ያለንን ነጻነትና የዘለዓለም ዕረፍት ነው። የልጅነት መብትና መንፈስ ስላለን የአባታችንን መንግሥት የመውረስ ሥልጣን አለን።
፭. ሌባው ሊሰርቅ ሊያርድ ሊያጠፋ ሲመጣ እውነተኛው እረኛ ግን ዘለዓለማዊ ሕይወት እንዲበዛልን መጣ።
ነፍሳችንን የሚሰርቁ ለዘላማዊ ሞት በሚዳርግ በኑፋቄ በክህደት ሊያጠፉን የሚተጉ አሉና ከእነዚህ እንራቅ።
፮. በጎቹ የእሱ ያልሆኑ ምንድኛ ወይም ሙያተኛ ተኵላ ሲመጣ በጎቹን ትቶ ይሸሻል።
በዘመናችን በተኵላዊ ግብር ውስጥ ሆነው የእረኝነት ሥራ የሠሩ እየመሰሉ ትቶ መሸሽ ብቻ ሳይሆን አስመስለው በያዙት የእረኝነት ሥልጣን በጎችን ቆመው የሚያስበሉና ለዚህ ዓላማ እየሠሩ ያሉ ብዙዎች እየሆኑ ስለመጡ ማነው እረኛችን የሚለውን ጠይቆ ምላሽ ማግኘት አስፈላጊ ነው።
፯. እረኛው አንድ ነው መንጋውም አንድ ነው።
በመጽሐፍ ያለው እውነት ይህ ሆኖ እያለ በተለያየ ምክንያት በልዩነት መንገድ እየሄድን አለመስማማትን መጨቃጨቅን መካሰስን ስም መጠፋፋትን መለያችን ወደማድረግ ከፍ እያልን መጥናተናል አይጠቅመንምና ከእንዲህ ዐይነቱ አካሄድ ራሳችንን በቃሉ ልጓምነት ልንገታ ግድ ነው።
ታኅሣሥ ፳፩ ተዝካረ በዓላ ለእግዝእትነ ማርያም ወበርናባስ ዘእምሰብዐ ወክልኤቱ አርድእት
ዘነግህ ምስባክ፦
ውስተ ኵሉ ምድር ወጽአ ነገሮሙ፤
ወእስከ አጽናፈ ዓለም በጽሐ ነቢቦሙ፤
ወውስተ ፀሐይ ሤመ ጽላሎቶ። መዝ ፲፰፥፬፤
ትርጉም፦
ቃላቸው ወደምድር ሁሉ ወጣ፤
ነገራቸው እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ፤
በጨለማ ውስጥ ፀሐይን አደረገ።
ምሥጢር፦
የነቢያት ትንቢታቸው የሐዋርያት ስብከታቸው በአራቱ ማዕዘን ደረሰ፤
የነቢያት ትንቢታቸው የሐዋርያትስብከታቸው ከሰው ጆሮ ደረሰ፤ ጽንፍ አለው ጆሮን? የአካል ዳርቻ ነውና። አንድም ከምድር ጽንፍ እስከ ምድር ጽንፍ ተነገረ።
ፀዳሉን በክበቡ አኖረ፤ አሁን ፀዳሉ በኋላ ክበቡ በፊት የተገኘ ሆኖ አይደለም ሁሉም አንድ ጊዜ መገኘቱን መናገር ነው፤ ቦ ጽላሎቱ ለሰብእ ነው፤ የሰውን አምሳል መርገፍ በፀሐይ አደረገ፤ ፀሐይ እንዲወጣ እንወለዳለን ሲያበራ እንዲውል ቤት ንብረት እንይዛለን እንዲገባ እንሞታለን ተመልሶ እንዲወጣ በትንሣኤ ዘጉባኤ እንነሣለን።
ቦ የአንድነቱን የሦስትነቱን አምሳል መርገፍ ፀሐይን አደረገ፤ አብ ፀሐይ ወልድ ፀሐይ ወመንፈስ ቅዱስ ፀሐይ እንዲል።
ወንጌል፦ ሉቃ ፲፥፩ ߺ ፲፪፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
ገላ ፪፥፩ ߺ ፲፬፤
ቈላ ፬፥፩ ߺ ፍጻሜ፤
ግብ ፲፩፥፳፫ ߺ ፍጻሜ፤
ወንጌል፦ ሉቃ ፩፥፲፯ – ፴፬፤
ቅዳሴ፦ ዘእግዝእትነ ማርያም
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
ወትቀውም ንግሥት በየማንከ፤
በአልባሰ ወርቅ ዑፅፍት ወኊብርት፤
ስምዒ ወለትየ ወርእዪ ወአጽምዒ ዕዝነኪ።
ታኅሣሥ ፳፪ በዓለ ቅዱስ ደቅስዮስ
ዘነግህ ምስባክ፦
በቅድመ መላእክቲከ እዜምር ለከ፤
ወእሰግድ ውስተ ጽርሐ መቅደስከ፤
ወእገኒ ለስምከ።
ወንጌል፦ ሉቃ ፩፥፳፮ ߺ ፴፱፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
፪ጢሞ ፩፥፰ ߺ ፍጻሜ፤
፩ዮሐ ፬፥፱ ߺ ፲፰፤
ግብ ፲፪፥፯ ߺ ፲፪፤
ወንጌል፦ ሉቃ ፩፥፴፱ ߺ ፶፯፤
ቅዳሴ፦ ዘእግዝእትነ ማርያም
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
ህየንተ አበውኪ ተወልዱ ለኪ ደቂቅ፤
ወትሠይሚዮሙ መላእክተ ለኵሉ ምድር፤
ወይዘክሩ ስመኪ በኵሉ ትውልደ ትውልድ።
ታኅሣሥ ፳፬ በዓለ ልደቱ ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት
ዘነግህ ምስባክ፦
አድኅነኒ እምደም እግዚአብሔር አምላከ መድኃኒትየ፤
ይትፌሣሕ ልሳንየ በጽድቀ ዚአከ እግዚኦ፤
ትከሥት ከናፍርየ ወአፉየ ያየድዓ ስብሐቲከ። መዝ ፶፥፲፬፤
ትርጒም፦
የመድኃኒቴ አምላክ እግዚአብሔር ሆይ ከደም አድነኝ፤
አቤቱ አንደበቴ በአንተ ጽድቅ ደስ ይሰኛል፤
ከንፈሮቼን ትከፍታለህ አንደበቴም ምስጋናህን ይናገራል።
ምሥጢር፦
የኦርዮን ደም ከማፍሰሴ የተነሣ ከፍዳው አድነኝ፤ ቦ በደም ከመጣብኝ ቊራኝነት የተነሣ ከቊራኝነት አድነኝ፤ “እለ ይዴምሩ ደመ ምስለ ደም ኰነኖሙ ሞት እምአዳም እስከ ሙሴ በእንተ ኃጢአቱ ለአዳም – ደምን ከደም ጋር የሚቀላቅሉትን በአዳም ኃጢአት ምክንያት ከአዳም እስከ ሙሴ ሞት ገዛቸው” እንዲል፤ ዲያብሎስ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን የላሜ ልጅ የአውራዬ ውላጅ ብሎ ይገዛቸው ነበርና፤ ቦ ደመ በግዕን ለጣዖት ከማፍሰሴ የተነሣ ከሚመጣብኝ ፍዳ አድነኝ ይላል ትሩፍ፤ ቦ ደመ በለስን አፍስሼ ከመጣብኝ መርገመ ነፍስ አድነኝ ይላል ምእመን፤ ቦ ደመ ወልደ እግዚአብሔርን አፍስሰን ከሚመጣብን ፍዳ አድነን ይላሉ ተነሳሕያን አይሁድ፤
ይቅርታህን ቸርነትህን ስናገር አንደበቴን ደስ ይለዋል፤ ቦ አንደበቴን መልቼ አመሰግንህ ዘንድ ምሥጢር ግለጥልኝ፤
አንደበቶቼን ትገልጣቸዋለህ ምስጋናህን ተአምራትህን ይናገራሉ።
ወንጌል፦ ማቴ ፲፩፥፳፭ – ፍጻሜ፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
ኤፌ ፬፥፲፩ – ፲፯፤
፩ጴጥ ፩፥፲፫ – ፍጻሜ፤
ግብ ፲፱፥፲፩ – ፳፩፤
ወንጌል፦ ፲፰፥፩ – ፲፪፤
ቅዳሴ፦ ዘሐዋርያት
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
እምአፈ ደቂቅ ወሕፃናት አስተዳሎከ ስብሐተ፤
በእንተ ጸላኢ፤
ከመ ትንሥቶ ለጸላኢ ወለገፋዒ። መዝ ፰፥፪፤
ትርጒም፦
ከሕፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ፤
ስለ ጠላት፤
ጠላትንና ግፈኛን ታጠፋው ዘንድ።
ምሥጢር፦
እምአፈ ደቂቅ ቢል ተወከፍከ፤ በአፈ ደቂቅ ቢል አስተዳሎከ ይላል፤ ከሕፃናት አንደበት ምስጋናን ተቀበልህ፤
ደቂቅ የሚላቸው የዓመት የሁለት ዓመት፣ ሕፃናት የሚላቸው የአርባ የሰማንያ ቀን ናቸው፤ ይህስ ተሐፅነ ካለው የወጣ ነው ብሎ ደቂቅ የአርባ የሰማንያ፣ ሕፃናት የዓመት የሁለት ዓመት ልጆች ናቸው፤
ጠላት ዲያብሎስን ደስ አይበለው ብለህ ደስ አይበለው ስትል፤ ቢጽ ሐሳዊን ደስ አይበለው ብለህ ደስ አይበለው ስትል፤
ጸላኢ ዲያብሎስን ገፋዒ ይሁዳን ታጠፋው ዘንድ፤ ቦ ከመ ትንሥት ምክሮ ይላል የጸላኢ የዲያብሎስ ምክሩን ታጠፋበት ዘንድ፤ ሥጋትን በመቃብር ነፍሳትን በሲኦል ተቆራኝቼ እኖራለሁ ብሎ መክሮ ነበር የመከረባቸውን ነፍስና ሥጋ ተዋሕዶ አድኖበታልና።
፳፮ ወእንዘ ሀለዉ
መዝሙር ወእንዘ ሀለዉ ታኅሣሥ ፳፰ እሑድ ሲሆን
፳፮.፩ (በ፫/ሐ) ወእንዘ ሀለዉ ህየ በጽሐ ዕለተ ወሊዶታ ወወለድት ወልደ ዘበኲራ ወአንቲኒ ቤተ ልሔም ምድረ ሳይዳ እምኔኪ ይወጽእ ንጉሠ ይሁዳ አዋልደ ጢሮስ አሜሃ ይሰግዳ ክቡራት ዕንቊ መሠረታ ብእሲ ተወልደ በውስቴታ ይሰግዱ ሎቱ ኵሎሙ ነገሥተ ምድር አምኃሁኒ ወርቀ ከርቤ ወስኂነ ወነዋ ተወልደ መድኃኔ ዓለም ፍሥሐ ለኵሉ ዘየአምን።
ትርጕም፦
በዚያ ሳሉ የምትወልድበት ቀን ደረሰ የበኵር ልጇን ወለደች የይቅርታ ስፍራ የምትሆኚ አንቺ ቤተ ልሔም የይሁዳ ንጉሥ ከአንቺ ይወጣል ያን ጊዜ የጢሮስ ልጆች ይሰግዳሉ መሠረቷ የከበሩ ዕንቊዎች ናቸው በውስጧ ሰው ተወለደ የምድር ነገሥታት ሁሉ ይሰግዱለታል እጅ መንሻውን ወርቁን ከርቤውንና ዕጣኑን ያመጡለታል ለሚያምን ሁሉ ደስታ የሚሆን መድኃኔ ዓለም እነሆ ተወለደ።
፳፮.፪ የዕለቱ ምንባባት፦
ሮሜ ፰፥፫ – ፲፰፤
፩ዮሐ ፬፥፩ – ፱፤
ግብ ፫፥፳፪ – ፍጻሜ፤
ወንጌል፦ ማቴ ፩፥፩ – ፲፰
ቅዳሴ፦ ዘእግዝእትነ ማርያም
፳፮.፫ የዕለቱ ምስባክ፦
ምስሌከ ቀዳማዊ በዕለተ ኃይል፤
በብርሃኖሙ ለቅዱሳን፤
ወለድኩከ እምከርሥ እምቅድመ ኮከበ ጽባሕ። መዝ ፻፱፥፫
ትርጉም፦
ቀዳማዊ በኃይል ቀን፤
በቅዱሳን ብርሃን ከአንተ ጋር ነበር፤
ከአጥቢያ ኮከብ አስቀድሞ ከሆድ ወለድሁህ።
ምሥጢር፦
ቀዳማዊ አብ! ወልድ ከአንተ ጋር በዕለተ ፍጥረት ነበረ ይህስ አይደለም ሰሚው እግዚአብሔር ወልድ ነው ብሎ ቀዳማዊ ወልድ አብ በዕለተ ፍጥረት ከአንተ ጋር ነበር። ይህን ዓለም ካለመኖር ወደመኖር አምጥቶ መፍጠር ኃይል ነውና ዕለተ ኃይል አለ።
በቅዳሴሆሙ ለመላእክት ሲል ነው መላእክት ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ብለው ባመሰገኑበት ቀን። ዝንቱ ብርሃን ኮኖሙ ጥበበ ወአእምሮ – ይህ ብርሃን ጥበብና እውቀት ሆናቸው እንዲል።
ዓለም ሳይፈጠር አስቀድሞ አካል ዘእምአካል ባሕርይ ዘእምባሕርይ ወለድሁህ።
አንድም (ምስሌከ) ቀዳማዊ ወልድ አብ በዕለተ ፅንስ ካንተ ጋር ነበር እንበለ ዘርዕ መፀነስ ኃይል ነውና እንበለ ዘርዕ ተፀንሶበታልና ዕለተ ኃይል አለው።
(በብርሃኖሙ) በትንቢቶሙ ለነቢያት ሲል ነው የነቢያት ትንቢት በተፈጸመበት ቀን። አንድም የመላእክት እውቀት በሚሆን በግብረ መንፈስ ቅዱስ በተፀነስህበት በዕለተ ፅንስ።
(ወለድኩከ) ከዲያብሎስ መፈጠር አስቀድሞ ወለድሁህ እፎ ወድቀ ኮከበ ጽባሕ – የአጥቢያ ኮከብ እንዴት ወደቀ እንዲል።
አንድም (ምስሌከ) ቀዳማዊ ወልድ አብ በዕለተ ልደት ከአንተ ጋር ነበር በኅቱም ድንግልና ተወልዶበታልና ዕለተ ኃይል አለው።
(በብርሃኖሙ) በአእምሮቶሙ ለመላእክት ሲል ነው ሰው መሆንህን ሥጋ መልበስህን ባወቁበት ቀን። አንድም በቅዳሴሆሙ ለመላእክት ሲል ነው በጎል ተጥሎ በጨርቅ ተጠቅልሎ አይተዉት ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ብለው ባመሰገኑበት ቀን።
(ወለድኩከ) አጥቢያ ኮከብ ከመውጣቱ አስቀድሞ በምትወለደው ልደት በማኅፀን አዋሓድሁህ።
አንድም (ምስሌከ) ቀዳማዊ ወልድ አብ በዕለተ ስብከት ካንተ ጋር ነበረ ተአምራት አድርጎበታል ድውይ ፈውሶበታል ሙት አንሥቶበታል ጋኔን አውጥቶበታል ኅብስት አበርክቶበታልና ዕለተ ኃይል አለው።
(በብርሃኖሙ) ለሐዋርያት እውቀት በተሰጠበት ቀን።
አንድም (ምስሌከ) ቀዳማዊ ወልድ አብ በዕለተ አርብ ከአንተ ጋር ነበረ ሰባት ተአምራት አድርጎበታልና ዕለተ ኃይል አለው።
(በብርሃኖሙ) ፀሐይ ጨረቃ ከዋክብት ብርሃናቸውን ባጡበት ቀን። ወርኢኩ ረሲአነ እንዘ ይወርዱ ውስተ መቃብር ቅዱስ – ዝንጉዎችን ወደጽኑ መቃብር ሲወርዱ አየኋቸው እንዲል።
አንድም ነፍሳት ብርሃንን ባገኙበት ቀን። እለ ውስተ ሲኦል ፃዑ ወእለ ውስተ ጽልመት ተከሠቱ ወርእዩ ብርሃነ ዓቢየ – በሲኦል ያላችሁ ውጡ በጨለማ ያላችሁ ተገለጡ ደገኛ ብርሃንን እዩ እንዲል።
አንድም (ምስሌከ) በዕለተ ትንሣኤ ካንተ ጋር ነበረ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት አድሮ ተነሥቶበታልና ዕለተ ኃይል አለው።
(በብርሃኖሙ) ለሐርያት እውቀት በተሰጠበት ቀን። ወኮኑ ከመ ሰብል ይላል እንደተራመመ ብራና ሆነዋልና።
(ወለድኩከ) ከአጥቢያ ኮከብ አስቀድሞ ከዶሮ ጩኸት በኋላ በትንሣኤ ወለድሁህ።
አንድም (ምስሌከ) በስብከተ ሐዋርያት ከአንተ ጋር ነበረ፤ ተአምራት ተደርጎበታልና ዕለተ ኃይል ይለዋል።
(በብርሃኖሙ) ለምእመናን እውቀት በተሰጠበት ቀን።
አንድም (ምስሌከ) በዕለተ ዕርገት ከአንተ ጋር ነበረ፤ በይባቤ መላእክት ዐርጎበታልና ዕለተ ኃይል አለው።
(በብርሃኖሙ) መላእክት ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ብለው ባመሰገኑበት ቀን።
አንድም (ምስሌከ) ቀዳማዊ ወልድ አብ በዕለተ ምጽአት በህልውና ከአንተ ጋር ይመጣል፤ ይህን ዓለም ከመኖር ወዳለመኖር ያሳልፍበታልና ዕለተ ኃይል አለው።
(በብርሃኖሙ) በዕሤቶሙ ለጻድቃን ሲል ነው ጻድቃን ዋጋቸውን በሚያገኙበት ቀን።
አው ዓዲ ምስባክ፦
የሐዩ ወይሁብዎ እምወርቀ ዓረብ፤
ወዘልፈ ይጼልዩ በእንቲአሁ፤
ወኵሎ አሚረ ይድኅርዎ። መዝ ፸፩፥፲፭፤
ትርጕም፦
ይኖራል ከዓረብም ወርቅን ይሰጡታል፤
ሁልጊዜም ስለ እርሱ ይጸልያሉ፤
ዘወትርም ይመርቁታል።
ምሥጢር፦
አርባ ዘመን በሕይወት ይኖራል ከግብጽ የተገኘውን ወርቅ ይገብሩለታል፤ አንድም እንዘ ይሁብዎ ሲል ነው ከምዕራብ ጽሩይ ወርቅ ሲገብሩለት ይኖራሉ አንድም ለጌታ ጽሩይ ምግባር ሃይማኖት ሲያቀርቡለት ይኖራሉ።
ዘመነ መንግሥቱን አብዛለት እድሜውን አርዝምለት ጠላቱን አጥፋለት እያሉ ይጸልዩለታል፤ ጸልዩ በእንተ ናቡከደነፆር ወብልጣሶር ወልዱ – ስለ ናቡከደነፆርና ስለ ልጁ ብልጣሶር ጸልዩ እንዲል። ስንኳን ለምእመናን ንጉሥ ለአሕዛብም ንጉሥ ሊጸልዩለት ይገባልና። አንድም በቅንው ወልድከ በስቁል ወልድከ እያሉ በሱ ለራሳቸው ስለሚያገኙት ድኅነት ይጸልያሉ።
ዕለት ዕለት ሺህ ዓመት ያንግሥህ እያሉ ይመርቁታል አንድም ጌታን ዕለት ዕለት ያመሰግኑታል በየሰዓቱ አያቋርጡም።
ታኅሣሥ ፳፱ በዓለ ልደቱ ለእግዚእነ
ዘነግህ ምስባክ፦
ነገሥተ ተርሴስ ወደሰያት አምኃ ያበውዑ፤
ነገሥተ ሳባ ወዓረብ ጋዳ ያመጽኡ፤
ወይሰግዱ ሎቱ ኵሎሙ ነገሥተ ምድር። መዝ ፸፩፥፲፤
ትርጒም፦
የተርሴስና የደሴቶች ነገሥታት ስጦታን ያገባሉ፤
የሳባና የዓረብ ነገሥታት እጅ መንሻን ያመጣሉ፤
የምድር ነገሥታት ሁሉ ይሰግዱለታል።
ምሥጢር፦
የተርሴስ የደሰያት ነገሥታት ግብር ይገብራሉ፤
የግብፅ የፋስቆሎ ነገሥታት እጅ መንሻ ያመጣሉ፤
በዚህ ዓለም ያሉ ነገሥታት ለሰሎሞን ይሰግዳሉ።
ቦ የፋርስ የባቢሎን ነገሥታት ለጌታ ግብር ይገብራሉ፤ ወርቁን፣ ዕጣኑን፣ ከርቤውን።
ምእመናን ምግባር ሃይማኖት ያቀርባሉ።
ነገሥታቱ ማንቱሲማር፣ በዲዳስፋ፣ ሜልኩ እልፍ እልፍ ሠራዊት አስከትለው መጥተው ይሰግዱለታል።
ወንጌል፦ ማቴ ፩፥፲፰ – ፍጻሜ፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
ገላ ፬፥፩ – ፲፪፤
፩ዮሐ ፬፥፱ – ፍጻሜ፤
ግብ ፲፫፥፲፮ – ፳፪፤
ወንጌል፦ ሉቃ ፪፥፩ – ፳፩፤
ቅዳሴ፦ ዘጎርጎርዮስ ካልዕ
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
የሐዩ ወይሁብዎ እምወርቀ ዓረብ፤
ወዘልፈ ይጼልዩ በእንቲአሁ፤
ወኵሎ አሚረ ይድኅርዎ።
፳፯ ይሠርቅ ኮከብ
መዝሙር ይሠርቅ ኮከብ ከታኅሣሥ ፳፱ – ጥር ፭
፳፯.፩ (በ፪/ኒ) ይሠርቅ ኮከብ እምያዕቆብ ወየአትት ኃጢአተ እምእስራኤል ወአነሂ በኵርየ እሬስዮ ልዑል ውእቱ እምነገሥተ ምድር (ወ) ወይከውን ምስማከ ለኵሉ ምድር (ወ) ውስተ አርእስተ አድባር (ወ) ዮምሰ በሰማያት ይትፌሥሑ ሠራዊተ መላእክት ወአነሂ በኵርየ እሬስዮ ወአነሂ በኵርየ እሬስዮ።
ትርጉም፦
ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል ከእስራኤል ኃጢአትን ያስወግዳል እኔም በኵር አደርገዋለሁ ከነገሥታት ይልቅ ልዑል ነው ከተራራዎችም በላይ ነው ዛሬ በሰማያት የመላእክት ሠራዊት ደስ ይሰኛሉ።
፳፯.፪ የዕለቱ ምንባባት፦
ሮሜ ፲፩፥፳፭ – ፍ፤
፩ዮሐ ፬፥፩ – ፱፤
ግብ ፯፥፲፯ – ፳፫፤
ወንጌል፦ ማቴ ፪፥፩ – ፲፫፤
ቅዳሴ፦ ዘዲዮስቆሮስ
፳፯.፫ የዕለቱ ምስባክ፦
ወአነሂ በኵርየ እሬስዮ፤
ወልዑል ውእቱ እምነገሥተ ምድር፤
ወለዓለም አአቅብ ሎቱ ሣህልየ። መዝ ፹፰፥፳፯
ትርጉም፦
እኔም በኵሬ አደርገዋለሁ፤
ከምድር ነገሥታት ይልቅ ከፍ ያለ ነው፤
ይቅርታዬን ለዘለዓለም እጠብቅለታለሁ።
ምሥጢር፦
በኵረ ምእመናን በኵረ መንግሥት አደርገዋለሁ።
በአራቱ ማዕዘን ከነገሡ ነገሥታት ይልቅ ልዑል ንጉሥ አደርገዋለሁ።
መሐላዬን ለዘለዓለም አጸናለታለሁ።
፳፯.፬ መልእክት፦
በኵር አደርገዋለሁ የሚለው በገጸ ንባቡ ሰጪና ተቀባይ ያለ ይመስላል። ቅድምና ያልነበረው ሥጋ ቀዳማዊ አምላክ መባሉ፣ ደኃራዊነት የሌለው መለኮት ደኃራዊ ሥጋን ተዋሕዶ ዘመን የሚቆጠርለት መሆኑ፤ በገዥነት ታይቶ የማይታወቅ ሥጋ በገዥነት መታየቱ፣ በተገዥነት ታይቶ የማይታወቅ መለኮት በተገዢ ሥጋ ተገልጦ መታየቱ የሚነገርበት ምሥጢር ነው።
በኵር የሚለው ቃል የሚከተሉትን ዋና ነጥቦችን በግልጽ የሚያስረዳ ቃል ነው።
፩. በኵረ አብ – የአብ በኵር፤
“ወአመ ፈነዎ ለበኵሩ ውስተ ዓለም ይቤ ይሰግዱ ሎቱ ኵሎሙ መላእክተ እግዚአብሔር – በኵሩን ወደዓለም በላከው ጊዜ የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉ ይሰግዱለታል አለ” እንዲል ዕብ ፩፥፮፤ ይህም ማለት ቃል ሥጋ በሆነ ጊዜ የቃል ገንዘብ ለሥጋ የሥጋ ገንዘብ ለቃል ስለሆነ መላእክት የሚሰግዱት በተዋሕዶ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ለሆነው ነው ማለት ነው።
ዘሰገደ ለሥጋ ሰገደ ለቃል ወከማሁ አበዊነ ሐዋርያት ሶበ ሰገዱ ለሥጋ ቅዱስ ሰገዱ ለእግዚአብሔር ቃል ወከማሁ መላእክትኒ ኮኑ ይትለአኩ ለአርአያ ሥጋ ወየአምሩ ከመ ውእቱ እግዚኦሙ ወይሰግዱ ሎቱ – ለሥጋ የሰገደ ለቃል ሰገደ ዳግመኛ አባቶቻችን ሐዋርያት በተዋሕዶ ለከበረ ሥጋ በሰገዱ ጊዜ ለእግዚአብሔር ቃል ሰገዱ መላእክትም እንዲሁ ሥጋን አይተው ያገለግሉ ነበር ጌታቸው እንደሆነ አውቀው ይሰግዱለታል እንዲል። አቡሊዲስ ፵፩፥፪
ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅም በድርሳኑ፦ “እስመ ብሂሎቱ አመ አብኦ (ፈነዎ) ለበኵሩ ውስተ ዓለም ዝ ብሂል አመ አኰነኖ በዲበ ዓለም ወእምዝ ሶበ አእመርዎ ይእተ ጊዜ መለከ ኵለንታሁ – ወደዓለም በላከው ጊዜ ማለቱ በዓለም ላይ አሠለነጠው/እንዲፈርድ አደረገው ማለቱ ነውና ያን ጊዜ ካወቁት በኋላ ሁሉን ገዛ አንድም ኵለንታ አካሉ ኵለንታ ባሕርዩ ኵለንታ ትስብእቱ ኵለንታ መለኮቱ ሁሉን ገዛ” ብሎ አመሥጥሮታል።
ይህ ማለት ደግሞ ምን ማለት እንደሆነ ሲያብራራ፦ “ወኢይቤ ዘንተ በእንተ እግዚአብሔር ቃል አላ በእንተ ሥጋሁ – አሠለነጠው ማለትን ስለ እግዚአብሔር ቃል አንድም ስለ ቃልነቱ አልተናገረም ስለ ሥጋ አንድም ሰው ስለ መሆኑ ነው እንጂ” ብሏል። ድር. ዘዮሐንስ አፈወርቅ ፫፥፳፬፤ ወደስሕተት መውደቅ የሚመጣው እንዲህ ያለውን ድንቅና ጥልቅ ምሥጢር በዚህ መንገድ አለመረዳት ሲኖር ነው።
ማነጻጸሪያ ጥቅሶች፦
“እስመ ኢፈነዎ እግዚአብሔር ለወልዱ ውስተ ዓለም ከመ ይኰንኖ ለዓለም ዘእንበለ ከመ ያሕይዎ ለዓለም በእንቲአሁ – በዓለሙ ይፈርድፈበት ዘንድ እግዚአብሔር ልጁን አላከውም በእሱ ዓለሙን ሊያድን ነው እንጂ” ዮሐ፫፥፲፯፤ “እስመ አብሰ ኢይኴንን ወኢመነሂ አላ ኵሎ ኵነኔሁ አፈወዮ ለወልዱ – አብ በማንም ላይ አይፈርድም ፍርድን ሁሉ ለልጁ ሰጠው እንጂ” ዮሐ ፭፥፳፪፤ ይህም ከላይ እንዳልነው ነገረ ተዋሕዶን አጉልቶ የሚያሳይ ነው።
፪. በኵረ ድንግል – የድንግል በኵር፤
ከአብ ያለእናት በመወለድ በኵር እንደተባለ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ያለአባት በመወለድ በኵር ተብሏል። ቅዱስ ያሬድም “ከመዝ ነአምን ዘአልቦቱ እም በሰማያት ወአብ በዲበ ምድር – በሰማያት እናት የሌለችው በምድርም አባት የሌለው እንደሆነ እናምናለን” ብሎ እንደዘመረ።
ቅዱስ ሳዊሮስም፦ “ወዘሀሎ በሕፅነ አቡሁ ኮነ በሕፅነ ማርያም ወዘወለዶ እግዚአብሔር አብ በምሥጢር ዘኢይትረከብ እንበለ መንጸፈ አንስት ወለደቶ ማርያም በሥጋ በምሥጢር ዘኢይትረከብ እንበለ ሩካቤ ተባዕት – በአብ ዕሪና ያለ እርሱ በማርያም እቅፍ ተይዞ ታየ እግዚአብሔር አብ በማይመረመር ምሥጢር ያለእናት የወለደውን ማርያም በማይመረመር ምሥጢር ያለዘርዐ ብእሲ በሥጋ ወለደችው” ብሏል ሃይ አበው ፹፭፥፴፯፤
፫. በኵረ ምእመናን – የምእመናን በኵር፤
ይህንንም ቅዱስ ጳውሎስ “ከመ ይኩን ውእቱ በኵረ በላዕለ ብዙኃን አኃው – በብዙ ወንድሞች ላይ በኵር ይባል ዘንድ ማለትም በኵረ ምእመናን ይባል ዘንድ የጠራቸውን አጸደቀ” ብሎ በግልጽ አስቀምጦታል ሮሜ ፰፥፳፱፤
፬. በኵረ ትንሣኤ – የትንሣኤ በኵር፤
“ወይእዜኒ ክርስቶስ ቀደመ ተንሥኦ እምኵሎሙ ሰብእ ሙታን – አሁንም ክርስቶስ ከሙታን አስቀድሞ ተነሥቷል” እንዳለ ብፁዕ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ በኵረ ትንሣኤ ይባላል ፩ቆሮ ፲፭፥፳፤ በተመሳሳይ ምሥጢር አሁንም ብፁዕ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል፤ “እስመ ውእቱ በኵር ቀደመ ተንሥኦ ከመ ይኩን ርእሰ ለኵሉ – በኵር እሱ ለሁሉ ራስ ይሆን ዘንድ ከሙታን ሁሉ አስቀድሞ ተነሥቷልና” ቈላ ፩፥፲፰፤

