፲፯ በሰንበት አጋንንተ አውጽአ
ለእመ ኮነ በዓለ ዕንባቆም በሰንበት ኅዳር ፫ መዝሙር በሰንበት አጋንንተ አውጽአ
፲፯.፩ (በ፪/ብ) በሰንበት አጋንንተ አውጽአ እለ ለምጽ አንጽሐ ተአምረ ገብረ ዕንባቆምኒ ይቤ እግዚኦ ሰማዕኩ ድምፀከ ወፈራህኩ ርኢኩ ግብረከ ወአንከርኩ ለሊሁሰ ይቤ ስምዑ ቃልየ ወዕቀቡ ሕግየ ወአእትቱ እከየ እምአልባቢክሙ ይቤ እግዚአብሔር ኢሳይያስኒ ይቤ ጽገዪ ገዳም ተፈሥሒ ገዳም ቀንሞስ ፈረየ ናሁ ናርዶስ ወሀበ መዓዛሁ።
ትርጕም፦
በስንበት አጋንንትን አወጣ ለምጻምን አነጻ ተአምርን አደረገ ዕንባቆምም አቤቱ ድምፅህን ሰምቼ ፈራሁ ሥራህን አይቼ አደነቅሁ አለ እርሱ እራሱ እግዚአብሔር ቃሌን ስሙ ሕጌን ጠብቁ ከልባችሁ ክፋትን አስወግዱ አለ ኢሳይያስም ገዳም አብቢ ገዳም ደስ ይበልሽ አለ ቀንሞስ አፈራ እነሆ ናርዶስ መዓዛውን ሰጠ።
ምንባብና ምስባክ የክርስቶስ ሠርዐን በል።
፲፰ ኢተዘኪሮ አበሳነ
መዝሙር ኢተዘኪሮ አበሳነ ከኅዳር ፮ – ፲፪
፲፰.፩ (በ፰/ዩ) ኢተዘኪሮ አበሳ ዚአነ ኢኀደገነ ፍጹመ ንማስን ኄር እግዚአብሔር አዘዞሙ ሙሴ ለሕዝብ ያክብሩ ሰንበተ በጽድቅ።
ትርጕም፦
የቀደመ በደላችንን አስቦ ፈጽመን እንድንጠፋ ቸር እግዚአብሔር አልተወንም ሰንበትን በእውነት ያከብሩ ዘንድ ሙሴ ሕዝቡን አዘዛቸው።
፲፰.፪ የዕለቱ ምንባባት፦
ሮሜ ፭፥፲ – ፍ፤
፩ዮሐ ፪፥፩ – ፲፰፤
ግብ ፳፪፥፩ – ፲፪፤
ወንጌል፦ ማቴ ፮፥፭
ቅዳሴ፦ ዘእግዚእነ
፲፰.፫ የዕለቱ ምስባክ፦
ኢትዝክር ለነ አበሳነ ዘትካት፤
ፍጡነ ይርከበነ ሣህልከ እግዚኦ፤
እስመ ተመደብነ ፈድፋደ። መዝ ፸፰፥፰፤
ትርጕም፦
የቀደመ በደላችንን አታስብን፤
አቤቱ ይቅርታህ ፈጥኖ ይደረግልን፤
እጅግ ተቸግረናልና።
ምሥጢር፦
ሕፃናተ አእምሮ ሆነን የሠራውን ኃጢአታችንን አታስብብን፤ ለሥርየተ ኃጢአት የሚፈሰው ደምህ ሕይወት ይሆነን ዘንድ ይሰጠን፤ በአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን መከራ ሥጋ መከራ ነፍስ ተቸግረናልና።
ኅዳር ፮ በዓለ ቊስቋም
ዘነግህ ምስባክ፦
ዖፍኒ ረከበት ላቲ ቤተ፤
ወማዕነቅኒ ኀበ ታነብር ዕጐሊሃ፤
ምሥዋዒከ እግዚኦ እግዚአ ኃያላን። መዝ ፹፫፥፫፤
ትርጒም፦
ወፍ ለእርሷ ቤትን አገኘች፤
ዋኖስም ጫጩቶቿን የምታኖርበት ቤት አገኘች፤
የኃያላን ጌታ አቤቱ እርሱ መሠዊያህ ነው።
ምሥጢር፦
ወፍ ስንኳ ቤትን አገኘች፤
ዋኖስም ገላግልቶቿን የምታኖርበት ቤትን አገኘች፤
አገኘች ማለቴም ምሥዋዐ ቅዳሴን ነው፤ ኢየሩሳሌም ሰባ ዘመን የዋኖስ የዋሊያ መኖሪያ ሆናለችና፤ ቦ ምሥዋዒከሰ ነው፤ የምስጋናህ ማደሪያ የሚሆኑ እስራኤል ማደሪያ አጥተው ፋርስ ለፋርስ ባቢሎን ለባቢሎን ይንከራተታሉ።
ቦ ዖፍኒ፤ ካህናት ትምህርት የሚያስተምሩበት ቦታን አገኙ፤
ነቢያትም ትንቢት የሚናገሩበት ቦታን አገኙ፤ ትንቢት ተናገሩ፤ ልጅ አለው ትንቢቱን ልጅ ከአብራክ እንዲገኝ ትንቢትም የሚገኝ ከልቡና ነውና፤ አገኙ ያልኩትም የምስጋናህ ማደሪያ እስራኤልን ነው፤ ሰባ ዘመን ትምህርት ተከልክሎባቸው ነበርና።
ቦ ርግብና ዋኖስ ማደሪያ ሲያገኙ የአብርሃም የይስሐቅ የያዕቆብ ጌታ አቤቱ እናትህ ድንግል ማርያም ግን ማደሪያ አጥታ ግብፅ ለግብፅ ትዞራለች።
ቦ ዖፍኒ፤ እመቤታችን ማደሪያ አገኘች፤ ዮሴፍ ሰሎሜን የምታኖርበት አገኘች፤ አገኘች ማለቴም የምስጋናህ ማደሪያ እስክንድርያን ደብረ ቊስቋምን ነው።
ቦ ዖፍኒ፤ ርግብና ዋኖስ ማደሪያ ሲኖራቸው ሥግው ቃል ልጅህ ግን ማደሪያ የለውም፤ “ወልደ ዕጓለ እመሕያውሰ አልቦ ዘያሰምክ ርእሶ – የሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም” እንዲል፤ ማቴ ፰፥፳፤ በዋንዛ በጽድ በዘግባ የተሠራ ቤት የለውም ሲል ነው እንጂ ቀን በምኵራብ ሲያስተምር ውሎ ሌሊት በደብረ ዘይት ተጠግቶ የሚያድርባት የደንጊያ ዋሻ ነበረችው “መዓልተ ይሜሕር በምኵራብ ወሌሊተ ይበይት ውስተ ደብረ ዘይት – ቀን በምኵራብ ሲያስተምር ውሎ ሌሊት በደብረ ዘይት ያድር ነበር” እንዲል ሉቃ ፳፩፥፴፯፤
ወንጌል፦ ሉቃ ፳፪፥፲፬ – ፳፬፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
፪ቆሮ ፰፥፩ – ፲፮፤
፪ዮሐ ፩፥፱ – ፍጻሜ፤
ግብ ፩፥፲፪ – ፲፭፤
ወንጌል፦ ማቴ ፪፥፲፱ – ፍጻሜ፤
ቅዳሴ፦ ዘእግዚእነ
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
ርኢክዎ ለኃጥእ ዐብየ ወተለዐለ ከመ ዐርዘ ሊባኖስ፤
ወሶበ እገብእ ኃጣእክዎ፤
ኀሠሥኩ ወኢረከብኩ መካኖ። መዝ ፴፮፥፴፭፤
ትርጒም፦
ኃጢአተኛን ከፍ ብሎ እንደ ሊባኖስ ዛፍ ረዝሞ አየሁት፤
ብመለስ ግን አጣሁት፤
ፈለግሁት ቦታውን አላገኘሁም።
ምሥጢር፦
ኃጥእ ሰውን እንደ ደጋ ዛፍ ከብሮ ገኖ አየሁት፤ ቦ ሳኦልን እንደ ደጋ ዛፍ ከብሮ ገኖ አየሁት፤
ዘወር ብዬ ባየሁት ጊዜ አጣሁት፤ ቦ ጥቂት ቀን ሲቅላግ ኖሬ ብመጣ አጣሁት፤
ሻሁት እንደ ቀድሞ ከብሮ ገኖ አላገኘሁትም፤ ቦ ስንኳን ሰውነቱን ቦታውን አላገኘሁትም።
ቦ ኃጥእ ሰውን እንደ ደጋ ዛፍ ክብሮ ገኖ አየሁት፤
መለስ ብዬ ባየሁት ጊዜ እንደ ቀድሞ ቤቱ ደምቆ አላገኘሁትም፤
አጥሩ ቅጥሩ ፈርሶ ቦታውንም አላገኘሁትም።
ኅዳር ፯ በዓለ ቅዱስ ጊዮርጊስ
ዘነግህ ምስባክ፦
መንክር እግዚአብሔር በላዕለ ቅዱሳኒሁ፤
አምላከ እስራኤል ውእቱ ይሁብ ኃይለ ወጽንዐ ለሕዝቡ፤
ወይትባረክ እግዚአብሔር። መዝ ፷፯፥፴፭፤
ትርጒም፦
እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ላይ ድንቅ ነው፤
የእስራኤል አምላክ እርሱ ኃይልን ብርታትን ለሕዝቡ ይሰጣል፤
እግዚአብሔር ይመስገን።
ምሥጢር፦
እግዚአብሔር በወዳጆቹ በቅዱሳን አድሮ የሚመሰገነው ምስጋና ቦ የሚሠራው ሥራ ድንቅ ነው፤
የእስራኤል ፈጣሪ ለወገኖቹ ኃይልን ጽንዕን ይሰጣቸዋል፤
ይህን ያደረገ እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን።
ወንጌል፦ ፲፬፥፩ – ፲፭፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
ኤፌ ፭፥፳፫ – ፳፰፤
፩ጴጥ ፬፥፲፪ – ፍጻሜ፤
ግብ ፳፰፥፩ – ፲፩፤
ወንጌል፦ ማቴ ፲፥፲፮ – ፍጻሜ፤
ቅዳሴ፦ ዘባስልዮስ
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
ወይርአዩ አሕዛብ በቅድመ አዕይንቲነ፤
በቀለ ደሞሙ ለአግብርቲከ ዘተክዕወ፤
ይባዕ ቅድሜከ ገዐሮሙ ለሙቁሐን። ትርጉምና ምሥጢሩን መስከረም ፲፩ ላይ ተመልከት።
ኅዳር ፰ በዓለ አርባዕቱ እንስሳ
ዘነግህ ምስባክ፦
እግዚአብሔር ነግሠ ደንገጹ አሕዛብ፤
ዘይነብር ዲበ ኪሩቤል አድለቅለቃ ለምድር፤
እግዚአብሔር ዐቢይ በጽዮን። መዝ ፺፰፥፩፤
ትርጒም፦
እግዚአብሔር ነገሠ አሕዛብ ደነገጡ፤
በኪሩቤል ላይ የተቀመጠ ምድርን አነዋወጣት፤
እግዚአብሔር በጽዮን ታላቅ ነው።
ምሥጢር፦
እግዚአብሔር የመንግሥትን ሥራ ሠራ፤ አሕዛብም ጠፉ፤
በኪሩቤል አድሮ የሚኖር እግዚአብሔር በጼዋዌ ጊዜ ኢየሩሳሌምን በሚጠት ጊዜ ባቢሎንን አጠፋት፤
በጽዮን ሰማያዊት በጽዮን ምድራዊት አድሮ ያለ እግዚአብሔር ገናና ነው።
ወንጌል፦ ማር ፲፮፥፲፬ – ፍጻሜ፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
፩ጢሞ ፭፥፳፩ – ፍጻሜ፤
ራእ ፬፥፮ – ፍጻሜ፤
ግብ ፭፥፳፱ – ፍጻሜ፤
ወንጌል፦ ማቴ ፲፰፥፲ – ፲፭
ቅዳሴ፦ ዘሠለስቱ ምዕት
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
ተፅዕነ ላዕለ ኪሩቤል ወሠረረ፤
ወሠረረ በክነፈ ነፋስ፤
ወረሰየ ጽልመተ ምሥዋሮ። መዝ ፲፯፥፲፤
ትርጒም፦
በኪሩቤል ላይ ተቀምጦ በረረ፤
በነፋስም ክንፍ በረረ፤
መሰ’ወሪያውን ጨለማ አደረገ።
ምሥጢር፦
በይባቤ መላእክት በቅዳሴ መላእክት ሰማየ ሰማያት ዐረገ፤ ቦ ንባብ ሳይሻ ሠረረ ወተፅዕነ ነው በቅዳሴ መላእክት በይባቤ መላእክት ዐረገ በየማነ አብ በዘባነ ኪሩብ ተቀመጠ፤ “ወተለዐለ በሠረገላ መንፈስ ቅዱስ – በመንፈስ ቅዱስ ሠረገላ ከፍ አለ” እንዲል፤
መንፈስ ቅዱስ ባደረባቸው በሐዋርያት ክርስቶስ ተሰበከ፤ “ወርኢኩ ዐቢይ ነፋስ እንዘ ይወጽእ እምባሕር – ታላቅ ነፋስ ከባሕር ሲወጣ አየሁ” እንዲል፤ ቦ ክርስቶስ ባደረባቸው በሐዋርያት ክርስቶስ ተሰበከ፤ ከሆነ በኋላ እንዲህ አለ፤
ሰው ሲሆን ባሕርዩን የማይመረመር አደረገ፤ “እንዘ ሰብእ መኑ ይክል ያእምሮ – ሰው ሲሆን ያውቀው ዘንድ ማን ይችላል” እንዲል፤ ቦ በዕለተ ዓርብ መሰወሪያውን ጨለማ አደረገ፤ ቦ የሠራውን ሥራ የማይመረመር አደረገ።
ኅዳር ፲፩ በዓለ ቅዱስ ኢያቄም ወቅድስት ሐና
ዘነግህ ምስባክ፦
መሠረታቲሃ ውስተ አድባር ቅዱሳን፤
ያበድሮን እግዚአብሔር ለአናቅጸ ጽዮን፤
እምኵሉ ተዐይኒሁ ለያዕቆብ። መዝ ፹፮፥፩፤
ትርጒም፦
መሠረቶቿ በተቀደሱ ተራሮች ናቸው፤
እግዚአብሔር የጽዮንን ደጆች ይወዳቸዋል፤
ከያዕቆብ ድንኳኖች ይልቅ።
ምሥጢር፦
ስለትሩፋን ተናግሮታል፤ የሕዝቅያስ የምእመናንም የእመቤታችንም ነገር አለበት፤ አርእስቱ የትሩፋን ነው ያሉ እንደሆነ የቤተ እስራኤል መሠረቷ በኪዳነ አብርሃም በኪዳነ ይስሐቅ በኪዳነ ያዕቆብ ተጠብቆ ይኖራል፤
አርእስቱ የሕዝቅያስ ነው ያሉ እንደሆነ የቤተ መቅደስ መሠረቷ በአምስቱ በስድስቱ ቆመ ብእሲ ጸንቶ ይኖራል፤
በያዕቆብ ከተማ ካሉ ከሠላሳ ስምንት ሀገረ ምስካይ በሮች ይልቅ እግዚአብሔር የጽዮንን ልጆች ይመርጣቸዋል። ቦ ከከተማው ይልቅ ቤተ መቅደስን ይወዳል፤ ጉባኤ ይነገርበታልና ስሙ ይጠራበታል ይመሰገንበታልና፤
ቦ የእመቤታችን ነገዷ ትውልዷ ከቤተ ክህነትም ከቤተ መንግሥትም ነው፤
እምሕዋሳተ ተዐይኒሁ ለያዕቆብ ሲል ነው፤ በያዕቆብ ከተማ ካሉ ሴቶች ሕዋሳት ይልቅ የእመቤታችንን ሕዋሳት ለተዋሕዶተ ቃለ እግዚአብሔር ይመርጣቸዋል።
ወንጌል፦ ሉቃ ፫፥፳፫ – ፍጻሜ፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
፩ጢሞ ፭፥፭ – ፲፩፤
፩ጴጥ ፫፥፭ – ፯፤
ግብ ፲፮፥፲፬ – ፲፱፤
ወንጌል፦ ሉቃ ፲፰፥፩ – ፱፤
ቅዳሴ፦ ዘእግዝእትነ ማርያም
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
አዋልደ ንግሥት ለክብርከ፤
ወትቀውም ንግሥት በየማንከ፤
በአልባሰ ወርቅ ዑፅፍት ወኊብርት።
ኅዳር ፲፪ በዓለ ቅዱስ ሚካኤል
ዘነግህ ምስባክ፦
እግዚኦ በኃይልከ ይትፌሣሕ ንጉሥ፤
ወብዙኀ ይትሐሠይ በአድኅኖትከ፤
ፍትወተ ነፍሱ ወሀብኮ። መዝ ፳፥፩፤
ትርጒም፦
አቤቱ በኃይልህ ንጉሥ ደስ ይለዋል፤
በማዳንህ እጅግ ሐሤትን ያደርጋል፤
የልቡን ፈቃድ ሰጠኸው።
ምሥጢር፦
አቤቱ ንጉሥ ሕዝቅያስ በአደረግህለት ነገር ያመሰግንሃል፤ ቦ በአደረግህለት ኃይል ደስ ይለዋል፤ ከሰናክሬም እጅ አድነኸዋልና፤ ይትዐሠይ ቢል ዋጋ ያገኛል፤
በትድግናህም እጅግ ደስ ይለዋል፤ ቦ በማዳንህ እጅግ ደስ ይለዋል፤ ከደዌው ፈውሰኸዋልና፤
የለመነውን ልመና ሰጠኸው።
ወንጌል፦ ሉቃ ፲፱፥፲፩ – ፳፰፤
በዓሉ ጸአተ እስራኤል የሚታሰብበት በመሆኑ አዝነመ ሎሙ፤ ወገሠፃ ለባሕረ ኤርትራ፤ ዘነፈቃ ለባሕረ ኤርትራ የመሳሰሉ ምስባኮች ቢባሉ ይገልጡታል።
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
ሮሜ ፱፥፲፯ – ፳፬፤
ይሁዳ ፩፥፱ – ፲፬፤
ግብ ፳፥፳፰ – ፴፩፤
ወንጌል፦ ማቴ ፲፰፥፲፭ – ፳፩፤
ቅዳሴ፦ ዘያዕቆብ ዘሥሩግ ወይም ዘባስልዮስ
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
ይትዐየን መልአከ እግዚአብሔር ዐውዶሙ፤
ለእለ ይፈርህዎ ወያድኅኖሙ፤
ጠዐሙ ወታእምሩ ከመ ኄር እግዚአብሔር።
፲፱ ሎቱ ስብሐት
መዝሙር ሎቱ ስብሐት ከኅዳር ፲፫ – ፲፱
፲፱.፩ (በ፮/ሥ) ሎቱ ስብሐት ወሎቱ አኰቴት ለዘቀደሳ ለሰንበት አልቦ አመ ኢሀሎ ወአልቦ አመ ኢሀሎ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር ዘገብሮ ለሰብእ በአርአያ ዚአሁ ኵሉ ውስተ እዴሁ ውእቱ ይኴንን ሰማያተ ወምድረ ገብረ በከመ ፈቀደ አምላክ ወልደ እግዚአብሔር።
ትርጕም፦
ሰንበትን ላከበራት ለሱ ፍጹም ምስጋና ይገባል ሰውን በራሱ አርአያ የፈጠረ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ያልነበረበት ዘመን የማይኖርበትም ጊዜ አልነበረም አይኖርም ሁሉ በመሐል እጁ የተያዘ ነው የእግዚአብሔር ልጅ አምላክ ሰማያትንና ምድርን እንደወደደ ፈጠረ።
፲፱.፪ የዕለቱ ምንባባት፦
ቈላ ፩፥፲፪ – ፍጻሜ፤
፩ጴጥ ፩፥፲፫ – ፍጻሜ፤
ግብ ፲፱፥፳፩ – ፍጻሜ፤
ወንጌል፦ ዮሐ ፭፥፲፮ – ፳፰
ቅዳሴ፦ ዘአትናቴዎስ
፲፱.፫ የዕለቱ ምስባክ፦
ኵሎ ዘፈቀደ ገብረ እግዚአብሔር፤
በሰማይኒ ወበምድርኒ፤
በባሕርኒ ወበኵሉ ቀላያት። መዝ ፻፴፬፥፮
ትርጕም፦
እግዚአብሔር የወደደውን ሁሉ አደረገ፤
በሰማይም በምድርም፤
በባሕርና በቀላያት ሁሉ።
ምሥጢር፦
ገናና የሆነ እግዚአብሔር የወደደውን ሁሉ እንደፈጠረ አውቃለሁ።
በሰማይም በምድርም በምልዓት ያለ እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ፈጠረ።
በባሕርም በቀላያትም ያለውን ሁሉ ፈጠረ።
ተጨማሪ ማብራሪያ፦
በሰማይኒ ሲል፦
አርባ መዓልት አርባ ሌሊት ዝናም ይዝነም በምድርም ዝናም ይሁን ማለቱን መናገር ነው። ዘፍ ፯፥፲፪
አንድም በገባዖን ፀሐይና ጨረቃ በያሉበት ይቁሙ ብሎ ማዘዙን መናገር ነው። ኢያ ፲፥፲፪
አንድም በዕለተ ዓርብ ፀሐይ ጨለማ ጨረቃ ደም መሆናቸውን ከዋክብት መርገፋቸውን መናገር ነው። ማቴ ፳፯፡፵፭
አንድም ሰማያውያን መላእክት የሚያማልዱበት ሥልጣን የተሰጣቸው መሆኑን መናገር ነው። ዘካ ፩፥፲፪
አንድም ስብሐት ለእግዚአብሔር ብለው ያመስግኑ ሲል ነው።ሉቃ ፪፥፲፫ እና ፲፬
ወበምድርኒ ሲል፦
የቤተ መቅደሱ መጋረጃ ከሁለት መከፈሉን፣ ምድር መናወጧን፣ ዓለቶች መሰነጣጠቃቸውን፣ መቃብራት መከፈታቸውንና ሙታን መነሣታቸውን መናገር ነው። ማቴ ፳፯፥፶፩
አንድም ማኅፀነ ማርያም እንዲወስነው ማድረጉን መናገር ነው።
አንድም ቤተ ክርስቲያንን በቅዱስ ጴጥሮስ ዐለትነት ትመሥረት ማለቱን መናገር ነው።
አንድም ከመሬት የተገኙ ስንዴና ወይን ምግበ ነፍስ እንዲሆኑ ማድረጉን መናገር ነው።
አንድም ተጠምቀ ሰማያዊ በእደ መሬታዊ እያላችሁ ዘምሩ ሲል ነው።
በባሕርኒ ሲል፦
በሙሴ ሕይወት የተፈጸመውን መናገር ነው፤ ከውኃ ዳር ተገኝቶ ለእስራኤል የነጻነት መሪ ሆኗልና። ዘጸ ፪፡፩ – ፲፤
አንድም ባሕረ ኤርትራን ባሕረ ዮርዳኖስን መክፈሉን መናገር ነው። ዘጸ ፲፬፡፳፩፤ “የካህናቱ እግሮች በውኃው ዳር ሲጠልቁ ከላይ የሚወርደው ውኃ ቆመ” እንዲል ኢያ ፫፥፲፭፤
አንድም በነቢዩ ኤልሳዕ የተደረገውን ተአምር መናገር ነው፤ መስጠም የማይችል ቅርፍተ ዕፅ የሚሰጥም ብረትን አውጥቷልና። “ጌታዬ ሆይ ወየው ወየው የተዋስሁት ነበረ ብሎ ጮኸ የእግዚአብሔርም ሰው የወደቀው ወዴት ነው አለ ስፍራውን አሳየው እንጨት ቆርጦ ጣለ ብረቱም ተንሳፈፈ እርሱም ውሰደው አለው እጁን ዘርግቶ ወሰደው” እንዲል ፪ነገ ፮፥፭
አንድም በዮናስ ሕይወት ውስጥ የተደረገውን መናገር ነው፤ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሠ አንበሪ ሰንብቶ ጥፋት ሳያገኘው ወጥቷልና፤ ይህም ለጌታችን ምሳሌ ሆኖ በወንጌል ተሰብኳልና። ማቴ ፲፪፥፵
አንድም ባሕርን ማስገበሩን መናገር ነው፤ እንደ አምላክነቱ ባሕርን አስገብሯልና እንደ ሰውነቱ ገብሯልና። “ወደ ባሕር ሂድና መቃጥን ጣል መጀመሪያ የወጣውን ዓሣ ውሰድና አፉን ስትከፍት እስታቴር ታገኛለህ ያንን ወስደህ ስለእኔና ስለአንተ ስጣቸው አለው” እንዲል ማቴ ፲፯፥፳፯
አንድም በማየ ጥምቀት ልጅነት ይሰጥ ማለቱን መናገር ነው፤ ከውኃና ከመንፈስ ያልተወለደ የእግዚአብሔርን መንግሥት አያያትምና ማለት አይወርሳትምና። ዮሐ ፫፡፭፤
፳ አምላክ ፍጹም
መዝሙር አምላክ ፍጹም ከኅዳር ፳ – ፳፮
፳.፩ (በ፭/ን) አምላክ ፍጹም በህላዌሁ ዘሀሎ እምቅድመ ይትፈጠር ዓለም ዘበመንግሥቱ ይኴንን ዓለመ ሰማየ ገብረ ለስብሐቲሁ ዓለመ ፈጠረ ወምድረ ሣረረ ወገሠጸ ባሕረ ወገሠጾሙ ለኵሉ ፍጥረት እለ ውስተ ደይን ያዕርፉ ባቲ አብ ቀደሳ ለሰንበት ቅረቡ ኀቤሁ ለአምላከ ጽድቅ ማኅደር ለንጹሐን ከመ ትንሥኡ አክሊለ ስብሐት ዘአስተዳለወ ለእለ ያፈቅርዎ ጸንዑ በጸጋ በሥን ወበሃይማኖት ወረሱ አክሊለ ስምዕ በእምነቶሙ እለ እምዓለም አሥመርዎ ለእግዚኦሙ መምህረ ቅዱሳን አክሊለ ሰማዕት ሠያሜ ካህናት።
ትርጕም፦
ዓለም ሳይፈጠር የነበረ እግዚአብሔር በአኗኗሩ(በባሕርዩ) ፍጹም ነው በጌትነቱ ዓለምን ይገዛል ጌትነቱን ለመግለጥ ሰማይን ሠራ ዓለምን ፈጠረ ምድርን መሠረተ ባሕርን ገሠጸ ፍጥረታትን ሁሉ ገሠጸ በሥቃይ ያሉ ያርፉ ዘንድ ሰንበትን ቀደሳት የንጹሐን ማረፊያ በምትሆን በመንግሥተ ሰማያት ለሚወዳቸው ያዘጋጀውን የምስጋና አክሊል ትቀበሉ ዘንድ ወደጽድቅ አምላክ ቅረቡ በገድል በምግባርና በሃይማኖት ጸንተው ከጥንት ጀምሮ ያገለገሉት በእምነታቸው የምስክርነት አክሊልን ወረሱ የቅዱሳን መምህር የሰማዕታት አክሊል ካህናትን የሚሾም እርሱ ነው።
፳.፪ የዕለቱ ምንባባት፦
ዕብ ፲፪፥፳፭ – ፍጻሜ፤
ያዕ ፫፥፬ – ፲፫፤
ግብ ፳፩፥፳፯ – ፍጻሜ፤
ወንጌል፦ ማቴ ፰፥፳፫ – ፍጻሜ፤
ቅዳሴ፦ ዘእግዚእነ
፳.፫ የዕለቱ ምስባክ፦
ቅረቡ ኀቤሁ ወያበርህ ለክሙ፤
ወኢይትሐፈር ገጽክሙ፤
ዝንቱ ነዳይ ጸርሐ ወእግዚአብሔር ሰምዖ። መዝ ፴፪፥፭
ትርጕም፦
ወደእርሱ ቅረቡ ያበራላችሁማል፤
ፊታችሁም አያፍርም፤
ይህ ችግረኛ ጮኸ እግዚአብሔርም ሰማው።
ምሥጢር፦
በሕግ በአምልኮ ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ብርሃነ ረድኤቱን ያበራላችኋል አንድም ከመከራ አድኖ ደስ ያሰኛችኋል።
ፊታችሁ አያፍርም፤ የሰው ኀፍረቱ የሚታወቀው በፊቱ ነውና። አንድም መሪያችሁ ፊታውራሪያችሁ ድል አይነሣም ማለት ድል አድርጎ ይመለሳል።
ኅዳር ፳፩ ተዝካረ በዓላ ለእግዝእትነ ማርያም
ዘነግህ ምስባክ፦
ዕግትዋ ለጽዮን ወሕቀፍዋ፤
ወተናገሩ በውስተ ማኅፈዲሃ፤
ደዩ ልበክሙ ውስተ ኃይላ። መዝ ፵፯፥፲፪፤
ትርጒም፦
ጽዮንን ክበቧት እቀፏትም፤
በቅጥሮቿም ተናገሩ፤
በብርታቷ ልባችሁን አኑሩ።
ምሥጢር፦
ጽዮንን ክበቧት አስጨንቋት ይላል ሰናክሬም፤
በየበሩ ቆማችሁ አውኩ ደንፉ አግሩ ይላል ሰናክሬም፤
በልቡናችሁ ብዙ ገንዘቧን እናጣዋለን አትበሉ ይላል ሰናክሬም።
ቦ ሰናክሬም ጽዮንን ክበቧት ብሎ ነበረ ይላል ሕዝቅያስ፤
በየበሩ ቆማችሁ አውኩ ደንፉ አግሩ ብሎ ነበረ ይላል ሕዝቅያስ፤
በልቡናችሁ ገንዘቧን እናጣዋለን አትበሉ ብሎ ነበረ ይላል ሕዝቅያስ።
ቦ ጽዮንን ክበቧት አይዞሽ አይዞሽ በሏት ይላል ሕዝቅያስ፤
በአምስቱ በስድስቱ ቆመ ብእሲ ቆማችሁ አመስግኑ ይላል ሕዝቅያስ፤
በኃይሏ በበረከቷ እንከብራለን ብላችሁ አስቡ።
ወንጌል፦ ማቴ ፳፫፥፩ – ፍጻሜ፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
፪ቆሮ ፮፥፲፪ – ፍጻሜ፤
፩ጴጥ ፪፥፭ – ፲፩፤
ግብ ፯፥፵፬ – ፶፱፤
ወንጌል፦ ማቴ ፳፩፥፵፪ – ፍጻሜ፤
ቅዳሴ፦ ዘእግዝእትነ ማርያም
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
እስመ ኀረያ እግዚአብሔር ለጽዮን፤
ወአብደራ ከመ ትኩኖ ማኅደሮ፤
ዛቲ ይእቲ ምዕራፍየ ለዓለም። መዝ ፻፴፩፥፲፫፤
ትርጒም፦
እግዚአብሔር ጽዮንን መርጧታልና፤
ማደሪያው ትሆን ዘንድ ወዷታልና፤
ይህች ለዘለዓለም ማረፊያዬ ናት።
ምሥጢር፦
እግዚአብሔር እመቤታችንን መርጧታልና፤ “ይትባረክ እግዚአብሔር ዘወደየ ዘንተ ስብሐተ ውስተ አፉየ እስመ ሎቱ ጥበብ ወሙዓት – ይህን ምስጋና በአፌ ያኖረ እግዚአብሔር ይመስገን ጥበብ ማሸነፍ ለእሱ ነውና” እንዲል፤
እናቱ ትሆን ዘንድ መርጧታልና፤
የዘለዓለም ማደሪያ ትሆነው ዘንድ የዘለዓለም ማረፊያዬ እሷ ናት አለ፤ ምነው ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን አይደለም ቢሉ የዘለዓለም ዋጋ የሚያሰጥ ስለሆነ እንዲህ አለ፤ ለዘለዓለም ወላዲተ አምላክ የምትባል ስለሆነ፤
፳፩ ይቤሉ እስራኤል
መዝሙር ይቤሉ እስራኤል ከኅዳር ፳፯ – ታኅሣሥ ፫
፳፩.፩ (በ፪/ብ) ይቤሉ እስራኤል ኢርኢነ ወኢሰማዕነ ዘዕውሩ ተወልደ ወተከሥተ አዕይንቲሁ በሰንበት ለእመ እምኀበ እግዚአብሔር ኢኮነ እመ ኢገብረ ዘንተ ወይቤልዎ ምንተ ትብል በእንተ ዘአሕየወከ ዘአሕየወኒ ይቤለኒ ኢትንግር ወእምዝ ዘየአኪ ኢይርከብከ።
ትርጕም፦
እስራኤል ዕውር ሆኖ ተወልዶ ዐይኖቹ በሰንበት የተፈወሱለት ሰው አላየንም አልሰማንም አሉ ከእግዚአብሔር ዘንድ ባይሆን ይህንን ባላደረገ ነበር ስለአዳነህ ምን ትላለህ አሉት ያዳነኝ ከዚህ የባሰ እንዳያገኝህ ለማንም አትናገር አለኝ።
፳፩.፪ የዕለቱ ምንባባት፦
፩ቆሮ ፪፥፩ – ፍጻሜ፤
፩ዮሐ ፭፥፩ – ፮፤
ግብ ፭፥፴፩ – ፍጻሜ፤
ወንጌል፦ ዮሐ ፱፥፩ – ፍጻሜ፤
ቅዳሴ፦ ዘእግዚእነ
፳፩.፫ የዕለቱ ምስባክ፦
ደቂቀ እጓለ እመሕያው እስከ ማዕዜኑ ታከብዱ ልበክሙ፤
ለምንት ታፈቅሩ ከንቶ ወተኀሡ ሐሰተ፤
አእምሩ ከመ ተሰብሐ እግዚአብሔር በጻድቁ። መዝ፬፥፪
ትርጕም፦
እናንተ የሰው ልጆች እስከመቼ ድረስ ልባችሁን ታከብዳላችሁ?
ከንቱ ነገርን ለምን ትወዳላችሁ? ሐሰትንስ ለምን ትሻላችሁ?
እግዚአብሔር በጻድቁ እንደተመሰገነ እወቁ።
ምሥጢር፦
እናንተ የመነናውያን ልጆች እስከመቼ ድረስ ልቡናችሁን ታጸናላችሁ? ሠራዒ መጋቢ የለም በማለት ልቡናችሁን ለምን ታጸናላችሁ?
ከንቱ ነገርን ማለትም ሠራዒ መጋቢ የለም ማለትን ለምን ትወዳላችሁ?
ሐሰትን ለምን ትናገራላችሁ? እግዚአብሔር የለም ማለትን።
እግዚአብሔርማ ኖሮ በጻድቁ በኖኅ በጻድቁ በሎጥ በጻድቁ በሕዝቅያስ እንደተመሰገነ እወቁ።
ኅዳር ፳፬ በዓለ ፳ወ፬ ካህናተ ሰማይ
ዘነግህ ምስባክ
ወአስተዮሙ ከመ ዘእምቀላይ ብዙኅ፤
ወአውኀዘ ማየ ከመ ዘእምአፍላግ፤
ወአውጽአ ማየ እምዕብን። መዝ ፸፯፥፲፭፤
ትርጒም፦
ከብዙ ጥልቅ እንደሚገኝ ያህል አጠጣቸው፤
ውኃንም እንደ ወንዞች አፈሰሰ፤
ውኃን ከዓለት አፈለቀ።
ምሥጢር፦
ከጥልቁ ባሕር አጠጣቸው፤ ቦ ከጥልቁ ባሕር አብዝተው እንዲጠጡ አብዝቶ ሰጣቸው፤ ቦ ስፉሕ ሲል ነው እንደ ጣና እንደ ምጥዋ አብዝቶ አጠጣቸው፤
ከፈሳሽ ውኃ አፈሰሰላቸው፤ ቦ እንደ ዐባይ እንደ በሽሎ አድርጎ አፈሰሰላቸው፤
ውኃን ከጭንጫ አፈለቀላቸው።
ወንጌል፦ ዮሐ ፬፥፲ ፳፯፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
፩ጢሞ ፭፥፲፯ – ፍጻሜ፤
ያዕ ፭፥፲፪ – ፍጻሜ፤
ግብ ፳፪፥፲፰ – ፳፪፤
ወንጌል፦ ማቴ ፲፫፥፴፮ – ፵፫፤
ቅዳሴ፦ ዘሠለስቱ ምዕት
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
ባርክዎ ለእግዚአብሔር ኵልክሙ መላእክቲሁ፤
ጽኑዓን ወኃያላን እለ ትገብሩ ቃሎ፤
ወእለ ትሰምዑ ቃለ ነገሩ። መዝ ፻፪፥፳፤
ትርጒም፦
ሁላችሁ መላእክት እግዚአብሔርን አመስግኑ፤
ጽኑዓን ኃያላን የምትሆኑ ቃሉን የምታደርጉ፤
የነገሩን ቃል የምትሰሙ።
ምሥጢር፦
መላችሁ የእስራኤል አለቆች እግዚአብሔርን አመስግኑ፤
ተናግሮ የሠራውን ሕጉን የምትሰሙ የምታደርጉ የእስራኤል አለቆች እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ቦ ጽኑዓን ኃያላን የምትሆኑ ነቢያት ካህናት እግዚብሔርን አመስግኑ፤
ከምስዓል ከአዕናቊ የነገሩን ምሥጢር የምታውቁ ካህናት እግዚአብሔርን አመስግኑ።
ኅዳር ፳፭ በዓለ ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕት
ዘነግህ ምስባክ፦
ፍትሕ ወርትዕ ተድላ መንበርከ፤
ሣህል ወጽድቅ የሐውር ቅድመ ገጽከ፤
ብፁዕ ሕዝብ ዘየአምር የብቦ። መዝ ፹፰፥፲፬፤
ትርጒም፦
የዙፋንህ መሠረት ፍትሕና ርትዕ ነው፤
ይቅርታና እውነት በፊትህ ይሄዳል፤
እልልታን የሚያውቅ ሕዝብ ብፁዕ ነው።
ምሥጢር፦
ፍትሕና ርትዕ ምቹ ዙፋንህ ናቸው፤ ቦ አናቦ፤ ፍትሕ ርትዕ የጌትነትህ ጌጥ ናቸው፤ የነገሥታት የዙፋናቸው ጌጥ የወርቅ የዕንቊ ፈርጥ እንደሆነ፤
ይቅርታ ቸርነትህ በፊት ጸንቶ ይኖራል፤
ያፈቅር ሲል ነው ምስጋናን የሚወድ ሰው ንዑድ ክቡር ነው፤ ቦ ምሥጢሩን አውቆ የሚጸልይ ሰው ንዑድ ክቡር ነው፤ ምሥጢሩን ሳያውቅ የሚጸልይ የሚያመሰግን ዐይን በሌለው፣ ምሥጢሩን አውቆ የሚጸልይ የሚያመሰግን ዐይን ባለው ሰው ይመሰላሉ፤ ዐይነ ሥውር በትሩን ኳ ኳ እያደረገ ሲሄድ አራዊት ዐይን መኖር አለመኖሩን አያውቁምና ይሸሻሉ፤ ኋላ ግን ዐይን እንደሌለው ሲያውቁ ተመልሰው መጥተው ይተናኮሉታል፤ ዐይን ያለው ተከትሎ ሄዶ ራስ ራሳቸውን ቀጥቅጦ ይገድላቸዋል፤ እንደዚሁም ሁሉ ምሥጢሩን የማያውቅ ሰው ሲጸልይ አጋንንት ምሥጢር ማወቅ አለማወቁን አያውቁምና ይሸሻሉ፤ ኋላ ግን ተመልሰው መጥተው አጽንተው ይዋጉታል፤ ምሥጢሩን አውቆ የሚደግም ሰው ግን ከኃይለ ቃሉ ሲደርስ መላልሶ ይጸልይባቸዋል እንደ ጢስ ተነው እንደ ጉም በነው ይጠፋሉ።
ወንጌል፦ ማቴ ፳፥፳ – ፳፬፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
፪ቆሮ ፯፥፬ – ፲፪፤
፩ጴጥ ፬፥፲፪ – ፍጻሜ፤
ግብ ፭፥፲፩ – ፲፯፤
ወንጌል፦ ማቴ ፲፥፲፮ – ፴፪፤
ቅዳሴ፦ ዘወልደ ነጐድጓድ
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
ልሳነ ከለባቲከ ላዕለ ጸላእቱ፤
አስተርአየ ፍናዊከ እግዚኦ፤
ፍናዊሁ ለአምላክነ ለንጉሥ ዘውስተ መቅደስ። መዝ ፷፯፥፳፫፤
ትርጒም፦
የውሾችህ ምላስ በጠላቶቹ ላይ ነው፤
አቤቱ መንገድህ ተገለጠ፤
የአምላካችን የንጉሡ መንገድ በመቅደሱ ውስጥ ነው።
ምሥጢር፦
ላዕለ ጸላእትከ ሲል ነው የወዳጆችህ የእስራኤል አንደበት በጠላቶችህ በግብፃውያን ላይ ነው፤ ግብፃውያን በሰጠሙ ጊዜ እስራኤል ንሴብሖ ለእግዚአብሔር ብለው አመስግነዋልና፤
ከዚህ እስራኤልን ከለባት አላቸው ከዚያ እነአቤሴሎምን ከለባት አላቸው አይጣላምን ቢሉ አይጣላም፤ ከዚህ እስራኤልን ከለባት አላቸው ውሻ ጌታውን ያውቃል የጌታውን ቤት ይጠብቃል
“ከልብሰ የአምር እግዚኡ ወየዐቅብ ቤተ እግዚኡ – ውሻ የጌታውን ቤት ያውቃል የጌታውን ቤት ይጠብቃል” እንዲል፤ እስራኤም ጌታቸውን ያውቃሉ የጌታቸውን ሕግ ይጠብቃሉና።
ከዚያ እነአቤሴሎምን ከለባት አላቸው? ውሻ ምን ቢጠግብ መልከፍከፉን አይተውም፤ አቤሴሎምም ከአባቱ ዕቁባት ደርሷልና።
ቦ የሙሴ የአሮን አንደበት በረድ ይዝነም እሳት ይወረድ በማለት በግብፃውያን ላይ ነው፤
አቤቱ ጎዳናህ በኤርትራ ተገለጠ፤ ቦ ሕግህ በዚህ ዓለም ተገለጠ፤
ለአምላክነ እና ለንጉሥ አንድ ወገን ነው፤ የፈጣሪያችን ጎዳናው ወደምድረ በዳ የሚያደርስ ነው፤ ቦ የፈጣሪያችን ሕጉ ወደ ገነት ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚያደርስ ነው።
ኅዳር ፳፱ ተዝካረ ልደቱ ለእግዚእነ
ዘነግህ ምስባክ፦
ምስሌከ ቀዳማዊ በዕለተ ኃይል፤
በብርሃኖሙ ለቅዱሳን፤
ወለድኩከ እምከርሥ እምቅድመ ኮከበ ጽባሕ።
ወንጌል፦ ሉቃ ፪፥፩ – ፰፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
ፊልጵ ፫፥፩ – ፲፭፤
፩ጴጥ ፭፥፩ – ፲፫፤
ግብ ፳፯፥፴፱ – ፍጻሜ፤
ወንጌል፦ ዮሐ ፲፥፩ – ፳፪፤
ቅዳሴ፦ ዘባስልዮስ
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
ኪያየ ይጸንሑ ኃጥአን ይቅትሉኒ፤
እስመ ስምዐከ ለበውኩ፤
ለኵሉ ግብር ርኢኩ ማኅለቅቶ። መዝ ፻፲፰፥፺፭፤
ትርጒም፦
ኃጥአን ያጠፉኝ ዘንድ ጠበቁኝ፤
ምስክርህን አስተውያለሁና፤
የሥራውን ሁሉ ፍጻሜ አየሁ።
ምሥጢር፦
ኃጥአን የባቢሎን ሰዎች እኔን ለመግደል ይሸምቃሉ፤
አምልኮትህን ልብ አድርጌአለሁና፤
የሠራኸውን ሁሉ ፍጻሜውን አየሁት አለ ኅልፈተ ዓለምን ነው፤ ቦ ቢገዙ ቢነዱ ሁሉ ያልፋል ሲል ነው።

