ወርኃ ነሐሴ

፷፬ ዮም ንወድሳ

መዝሙር ዮም ንወድሳ ከነሐሴ ፩ነሐሴ ፯

፷፬.፩ (በ፩/ኒ) ዮም ንወድሳ ለማርያም በእንተ ዘተወልደ እምኔሃ መንክር ግርማ ኃይለ ልዑል ጸለላ ፆረቶ በከርሣ ውእቱኒ ቀደሳ (መ) እግዚኣ ለሰንበት ወአቡሃ ለምሕረት መንክር ግርማ ኃይለ ልዑል ጸለላ አማን መላእክት ይኬልልዋ። 

ትርጕም፦

ዛሬ (ኑ) ማርያምን እናመስግናት (ጌታችን) ከሷ ስለተወለደ በሚያስደንቅ ግርማ የልዑል ኃይል ጋረዳት በማኅፀኗ ወሰነችው እሱም አከበራት የሰንበት ጌታ የይቅርታ አባት በሚያስደንቅ ግርማ የልዑል ኃይል ጋረዳት በእውነት መላእክት ያመስግኗታል።

፷፬.፪ የዕለቱ ምንባባት፦

፩ቆሮ ፰፥፩ – ፍ፤

፩ጴጥ ፬፥፩ – ፮፤

ግብ ፳፮፥፩ – ፳፬፤

ወንጌል፦ ማቴ ፲፪፥፴፰ – ፍጻሜ፤ 

ቅዳሴ – ዘእግዝእትነ ማርያም

፷፬.፫ የዕለቱ ምስባክ፦

እምነ ጽዮን ይብል ሰብእ፤

ወብእሲ ተወልደ በውስቴታ፤

ወውእቱ ልዑል ሣረራ። መዝ ፹፮፥፭

ትርጕም፦

ሰው እናታችን ጽዮን ይላል፤

በውስጧ ሰው ተወለደ፤

እርሱ ራሱ ልዑል መሠረታት።

ምሥጢር፦

ሰው ሁሉ ቤተ መቅደስ እናታችን እግዚአብሔር አባታችን ይላል፤

ተወልደ በውስቴታ ይነግሥ በውስቴታ ሲል ነው። ሕዝቅያስ በኢየሩሳሌም ተወልዶ በኢየሩሳሌም ይነግሣል አንድም ዘሩባቤል በባቢሎን ተወልዶ በኢየሩሳሌም ይነግሣል፤

ልዑል እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን በረድኤት አጸናት፤

አንድም በጸጋ ከሥላሴ የተወለደ ሰው ሁሉ እመቤታችን፤ ቤተክርስቲያን እናታችን እግዚአብሔር ወልድ አባታችን ይላል፤

ጌታ ከእመቤታችን ተፀነሰ ፅንሱን ልደት ልደቱን ፅንስ ይለዋልና አንድም በሥጋ ተወለደ አንድም ምእመናን ከቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ልደትን ተወለዱ፤

እግዚአብሔር እመቤታችንን በንጽሕና በቅድስና አጸናት ማለት እንድትችለው አደረጋት አንድም ቤተ ክርስቲያንን በደሙ አከበራት።

፷፭ ወይብሉ ኵሎሙ

ለእመ ኮነ በዓለ ሐዋርያት አመ ፭ ለነሐሴ መዝሙር ወይብሉ ኵሎሙ

፷፭.፩ (በ፭/ን) ወይብሉ ኵሎሙ ሐዋርያቲሁ ለእግዚእነ ሰአሊ ለነ ማርያም እምነ አግዓዚት ሰአሊ ለነ ማርያም እምነ ዘኮንኪ ማኅደረ መለኮት ሰአሊ ለነ ማርያም እምነ ማርያም ቅድስት እንተ አልባቲ ነውር ጽርሕ ንጽሕት አንቀጸ አድኅኖ ሰሎሞን ይቤላ ርግብየ ሠናይት አንቀጸ አድኅኖ ጳውሎስኒ ይቤላ ደብተራ ፍጽምት አንቀጸ አድኅኖ ኢሳይያስኒ ይቤላ ሐዳስዩ ጣዕዋ አንቀጸ አድኅኖ ሐዳስዩ ጣዕዋ ፀምር ፀዓዳ አንቀጸ አድኅኖ አንቀጸ አድኅኖ እንተ ኮነት ምክሐ ለኵሎን አንስት አንቀጸ አድኅኖ አንቀጸ አድኅኖ ዘጽድቅ ረሰያ አንቀጸ አንቀጸ አንቀጸ አድኅኖ አግዓዚት።

ትርጕም፦

የጌታችን ሐዋርያት ሁሉም አሉ ነፃ የምታወጪ ማኅደረ መለኮት የሆንሽ እናታችን ማርያም ለምኝልን አሉ እናታችን ማርያም ነውር የሌለባት ቅድስት ንጽሕት አዳራሽ የጽድቅ በር ናት። ሰሎሞን መልካሟ ርግቤ ይላታል ጳውሎስ ደብተራ ፍጽምት ይላታል ኢሳይያስ ንጽሕት እምቦሳ ፀዓዳ ግምጃ ይላታል ለሴቶች ሁሉ መመኪያ የሆነች የጽድቅ በር ናት ነፃ የምታወጣ የጽድቅ በር አደረጋት። 

፷፭.፪ የዕለቱ ምንባባት፦

ርሜ ፮፥፲፪ – ፍጻሜ፤

ያዕ ፬፥፩ – ፍጻሜ፤

ግብ ፯፥፵፬ – ፶፩፤

ወንጌል፦ ዮሐ ፯፥፴፪ – ፍጻሜ፤

ቅዳሴ፦ ዘእግዝእትነ ማርያም

፷፭.፫ የዕለቱ ምስባክ፦

ዘይሁብ ሲሳየ ለኵሉ ዘሥጋ፤

እስመ ለዓለም ምሕረቱ፤

ግነዩ ለአምላከ ሰማይ። መዝ ፻፴፭፥፳፮፤

ትርጕም፦

ለሥጋ ሁሉ ምግብን የሚሰጥ፤

ምሕረቱ ለዘለዓለም ነውና፤ 

የሰማይን አምላክ አመስግኑ።

ምሥጢር፦

ለሥጋዊ ለደማዊ ፍጥረት ሁሉ ምግብን የሚሰጥ እሱ ነው፤

ቸርነቱ ለዘለዓለም ነውና አንድም ቸርነቱ ለሰው ነውና፤

ሰማይን ለፈጠረ አምላክ ተገዙ።

አንድም በዝናም አብቅሎ በፀሐይ አብስሎ በነፋስ ለይቶ ፍጥረቱን የሚመግብ እሱ ነው አንድም ሥጋውን ቆርሶ ደሙን አፍስሶ ምእመናን የሚመግብ እሱ ነው። 

ነሐሴ በዓለ ፅንሰታ ለማርያም 

ዘነግህ ምስባክ፦

መሠረታቲሃ ውስተ አድባር ቅዱሳን፤ 

ያበድሮን እግዚአብሔር ለአናቅጸ ጽዮን፤ 

እምኵሉ ተዐይኒሁ ለያዕቆብ። ትርጒሙንና ምሥጢሩን ኅዳር  ፲፩ ላይ ተመልከት። 

ወንጌል፦ ማቴ ፩፥፩ – ፲፯፤ 

ዘቅዳሴ ምንባብ፦ 

ዕብ ፱፥፩ – ፲፩፤

፩ጴጥ ፪፥፮ – ፲፰፤

ግብ ፲፥፩ – ፴፤

ወንጌል፦ ማቴ ፲፮፥፲፫ – ፳፬፤

ቅዳሴ፦ ዘእግዝእትነ ማርያም 

ዘቅዳሴ ምስባክ፦ 

ብፁዕ ብእሲ ዘአንተ ገሠጽኮ እግዚኦ፤ 

ወዘመሀርኮ ሕገከ፤ 

ከመ ይትገኀሥ እመዋዕለ እኩያት። መዝ ፺፫፥፲፪፤

ትርጒም፦ 

አቤቱ አንተ የገሠጽኸው ብፁዕ ነው፤ 

ሕግህንም ያስተማርኸው፤ 

ከክፎዎች ዘመናት ይወገድ ዘንድ። 

ምሥጢር፦ 

አንተ የመከርኸው አንተ ያስተማርኸው ንዑድ ክቡር ነው፤ ቦ በመከራ የሠራኸው የቀጣኸው ትሩፍ ቦ ማናቸውም ሰው ንዑድ ክቡር ነው፤ 

ሕግህንም ያስተማርኸው ንዑድ ክቡር ነው፤ 

ከክፉ ወራት ይርቅ ዘንድ፤ ቦ እመዋዕለ እኩያን – እኩያን ነገሥታት ከነገሡባቸው ዘመናት ይርቅ ዘንድ። 

ነሐሴ ፲፪ በዓለ ቅዱስ ሚካኤል 

ዘነግህ ምስባክ፦ 

በቅድመ መላእክቲከ እዜምር ለከ፤ 

ወእሰግድ ውስተ ጽርሐ መቅደስከ፤ 

ወእገኒ ለስምከ።

ወንጌል፦ ማቴ ፳፭፥፴፩ – ፍጻሜ፤ 

ዘቅዳሴ ምንባብ፦ 

፩ቆሮ ፱፥፲፯ – ፍጻሜ፤

ይሁዳ ፩፥፰ – ፲፬፤

ግብ ፳፬፥፩ – ፳፪፤

ወንጌል፦ ማቴ ፳፪፥፩ – ፲፭፤

ቅዳሴ፦ ዘእግዝእትነ ማርያም 

ዘቅዳሴ ምስባክ፦ 

እግዚኦ ኵነኔከ ሀቦ ለንጉሥ፤ 

ጽድቀከኒ ለወልደ ንጉሥ፤ 

ከመ ይኰንኖሙ ለሕዝብከ በጽድቅ። መዝ ፸፩፥፩፤ 

ትርጒም፦ 

አቤቱ ፍርድህን ለንጉሥ ስጠው፤ 

ጽድቅህንም ለንጉሥ ልጅ፤ 

ሕዝብህን በጽድቅ ይዳኝ ዘንድ። 

ምሥጢር፦ 

ስለልጁ ስለ ሰሎሞን ተናግሮታል ከዐሥሩ አርእስት አንዱ ይህ ነው፤ የወልደ እግዚአብሔርም ነገር አለበት፤ ዳዊት ልሕቀ ወኀለፈ መዋዕሊሁ ይላል በተወለደ በሰማንያ በነገሠ በአርባ ዓመቱ አረጀ፤ ስለምን ፈጥኖ አረጀ ቢሉ ከኖኅ ወዲህ ዘመን እየተከፈለ መጥቷልና፤ ወይኩን መዋዕሊሁ ለሰብእ ምዕት ወዕሥራ ወገብኡ ኀበ ምዕት ወዕሥራ የሰው ዘመኑ መቶ ሃያ ይሁን ወደመቶ ሃያ ተመለሱ እንዲል፤ ቦ የቀን ዘለሳ የማታ ግስገሳ ያማታው ነበርና፤ ቦ እሱ ራሱ በተናገረው ወመዋዕለ ዓመቲነ ሰባ ክራማት ብሎ፤ ቦ መልአከ መደምስስ በዐውደ ዖርና ሲቀሥፍ አይቶ ደንግጦ ኃይል ተከፍሎበት ነበርና፤ 

ከአጊት የተወለደ አዶንያስ የዳዊትን ማርጀት የሰሎሞንን ሕፃንነት አይቶ የአባቴን መንግሥት ቋሚ ለጓሚ ሲይዘው አያለሁኝን ወንድሜ አቤሴሎም መንግሥቱ ያልጸናለት ከቤተ ክህነት ከቤተ መንግሥት ሰው ባይዝ ነው ብሎ ከቤተ ክህነት አብያታርን ከቤተ መንግሥት ኢዮአብን ይዞ በዘፌልቲ በዘኬልቲ አርዶ ጠጅቶ ነገሥሁ አለ። ነቢዩ ናታን ሰማዕኪኑ ቤርሳቤህ ከመ ነግሠ አዶንያስ ወልደ አጊት የአጊት ልጅ አዶንያስ እንደነገሠ ሰማሽ አላት፤ ምነው ነቢየ እግዚአብሔር ነገር ሠራበት? ቢሉ ሁሉን ሲጠራ እሱን አልጠራውም ነበርና፤ ነቢየ እግዚአብሔርስ በዚህ ነገር አይሠራም ብሎ የሰሎሞን መንግሥት የእግዚአብሔር ፈቃድ እንደሆነ የአዶንያስ ፈቃደ እግዚአብሔር እንዳልሆነ አውቆ ነው፤ ቦ የአጊት ልጅ አዶንያስ እንደነገሠ አልሰማሽምን አላት ብሰማስ ምን አደርጋለሁ አለችው ሂጂና ተሐሰወኑ ቃልከ ብለሽ ንገሪው እኔ በኋላ መጥቼ ነገርሽን አቀናልሻለሁ አላት። 

ሄዳ ተሐሰወኑ ቃልከ ከመ ሰሎሞን ወልድየ ይነግሥ ህየንቴየ ወይነብር ዲበ መንበርየ ልጄ ሰሎሞን ስለእኔ ይነግሣል በዙፋኔ ላይ ይቀመጣል ብለህ ነግረኸኝ አልነበረምን ምነው ቃልህ አበለብኝሳ እንከሰ አነ ወወልድየ ሰሎሞን ንከውን ኃጥአነ ነዳያነ ሲል ነው ከእንግዲህ ወዲህ እኔና ልጄ ሰሎሞን ስንኳን መንግሥት የዕለት ራት የጣት ቀለበት የሚሰጠን አናገኝም አለችው። ሳይመልስላት ነቢዩ ናታን ከደጅ ቁሟል አሉት ግባ በሉት አለ ገባ፤ ምነው አዶንያስን ስታነግሥ ሳትጠራኝ እስከዛሬ ስንኳን የመንግሥት ነገር ማናቸውንም ነገር ቢሆን እኔን ሳትይዝ የምትሠራው አልነበረም አለው፤ ነገራቸው አንድ እንደሆነ አውቆ ጸውዕዋ ለቤርሳቤህ ቤርሳቤህን ጥሯት አለ ምነው አሁን ገባች አላልንምን ቢሉ የእስራኤል ነገሥታት ሚስቶች ነቢያት ካህናት ሲመጡ አብረው አይቀመጡም ነበርና ወደእልፍኝ ገብታ ነበርና መጣች ሕያው እግዚአብሔር ዘቤዘዋ ለነፍስየ እምኵሉ ምንዳቤየ ከመ ሰሎሞን ወልድየ ይነግሥ ህየንቴየ ወይነብር ዲበ መንበርየ ልጄ ሰሎሞን ስለእኔ ይነግሣል ከዙፋኔ ይቀመጣል ስንኳን ከዚህ ቀደም ልሰጠበት ከእንግዲህም ወዲህ እንዳልሰጥበት ሕያው እግዚአብሔርን አለው፤ 

ይህስ ከሆነ ሺህ ዓመት ንገሥ ብለው ወጥተው ሄደዋል እሱም የዋለ ያደረ እንደሆነ ጠላት ይነሣበታል ነገር ይበዛበታል ብሎ ጸውዑ ሊተ ናታንሃ ነቢየ ወሳዶቅሃ ካህነ ወብንያስሃ ወዘፌልቲ ወዘኬልቲ ቀኛዝማቹን ግራዝማቹን ጥሩልኝ ብሎ አስጠርቶ ልጄ ሰሎሞንን በእኔ በቅሎ አስቀምጣችሁ የእኔን ዘውድ ደፍታችሁ በግዮን አንግሡት በዐሥራ ሁለቱ ነገድ ሊነግሥ እሻለሁ አላቸው እንዳዘዛቸው አደረጉ። ወእምድኅረ አኅለቁ መሲሐ ይላል ቀቢዐ ሲል ነው እነሰሎሞንን ያያል፤ ወእምድኅረ አኅለቁ ምሳሐ ይላል በሊዐ ሲል ነው እነአዶንያስን ያያል፤ የአብያታር ልጅ ዮናታን ይባላል አባቴን ቢምረው ከአቅርንተ ምሥዋዑ ገብተህ ተማጸን ልበለው ብሎ ሄደ፤ አዶንያስ አሻግሮ አይቶ ባእ አንተ እስመ ብእሲ ኃያል ወሠናየ ዜና ትዜኑ አንተ ባለ አእምሮ ሰው ግባ በጎ ወሬ ታወራለህና አለው፤ አባቱ ዳዊትን ኢትቢት በአራቦት አላ አፍጥን አዲወ ዮርዳኖስ ሲለው ሰምቶ ነበርና፤ ነጋሪቱን ጥሩንባውን ቀንደ መለከቱን እየሰማ ሲያወጣ ሲያወርድ ነበርና ይህ የምሰማው ነጋሪት ጥሩንባ ቀንደ መለከት ምንድን ነው አለው። 

ዳዊት ነቢዩ ናታንን ካህኑ ሳዶቅን ብንያስን ኬልቲን ፌልቲን አስጠርቶ ልጄ ሰሎሞንን በእኔ በቅሎ አስቀምጣችሁ የእኔን ልብስ አልብሳችሁ የእኔን ዘውድ ደፍታችሁ በግዮን አንግሡት በዐሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል ሊነግሥ አዝዣለሁና ብሏቸው አንግሠው ሲመለሱ ነው አለው፤ ወአኀዙ ይሰረቁ ይላል ካስማውን እየነቀሉ ከአቅርንተ ምሥዋዑ ገብተው ተማፀኑ የቀሩትን በምክንያት እያወጣ ተበቅሏቸዋል አብያታርን ግን አንተ የአባቴ የአደራ ልጅ ነህ ብሎ ከከተማ አትውጣ ብሎ ከሹመቱ ሽሮ ትቶታል። ከዚህ በኋላ ሰሎሞንን ከታላቅ ዙፋን ዳዊትን ከታሽ ዙፋን አስቀምጠዋቸዋል ስለምን ቢሉ ከእንግዲህ ወዲህ አንተ ንጉሠ ነገሥት ነህ ሲሉ፤ ቦ ዳዊትን በታላቅ ሰሎሞንን በታናሽ ዙፋን አስቀምጠዋቸዋል ስለምን ቢሉ ለቡራኬ እንዲመች፤ 

ከዚህ በኋላ ስለአራት ነገር ይጸልያል እግዚኦ ኵነኔከ ብሎ ፈጣሪውን ይለምናል፤ ኰንን በጽድቅ ብሎ ልጁን ይመክራል፤ ወይወርድ ከመ ጠል ውስተ ፀምር ነገር ያላወቀ ፍርድ ያልጠነቀቀ የዐሥራ ሁለት ዓመት ብላቴና አነገሠብን አትበሉ ጠል ከመስክ የተስማማ እንደሆነ የልጄ የሰሎሞን ነገርም ከሰው ልቡና የተስማማ ነው ብሎ ሕዝቡን ይመክራል፤ ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ እስራኤል ብሎ ፈጣሪውን ያመሰግናል፤ የእስራኤል ፈጣሪ ሳልሞት በሕይወት ልጄን በዙፋኔ ላይ አስቀምጦ ዐይኔን በዐይኔ ያሳየኝ ይክበር ይመስገን ብሎ፤ 

አቤቱ የባሕርይ አገዛዝህን ለሰሎሞን የጸጋ አድርገህ ስጠው፤ ቦ ለንጉሥ ክርስቶስ የባሕርይ አገዛዝን ስጠው፤ ቦ የባሕርይ አገዛዝህን በሥጋ ስጠው፤ አሁን ዳዊት ለጌታ የሚጸልይለት ጌታ በዳዊት ልመና የሚያገኝ ሆኖ አይደለም ጌታ ከእርሱ እንዲወለድ መናገር ነው፤

እውነተኛ ፍርድህን ለእኔ ለንጉሥ ልጅ ለሰሎሞን ግለጥለት፤ ቦ የባሕርይ ፍርድን ይፈርድ ዘንድ ለአንተ ለንጉሡ ልጅ ለክርስቶስ ስጠው፤ ስለሥጋ እንግድነት፤ ቦ ለእኔ ለዳዊት ልጅ ለክርስቶስ ገንዘብ አድርግለት፤ ወልደ ዳዊት ይለዋልና፤ ዕውራን በሆሣዕና ወልደ ዳዊት እንዳሉ፤ ወገኖቹን እውነት ፈርዶ ይገዛቸው ዘንድ፤ 

፷፮ መንክረ ከሠተ

ለእመ ኮነ ደብረ ታቦር በሰንበት መዝሙር መንክረ ከሠተ

፷፮.፩ ምስባክ ዘነግህ

ደብር ርጉዕ ወደብር ጥሉል፤ 

ለምንት ይትነሥኡ አድባር ርጉዓን፤ 

ደብር ዘሠምሮ እግዚአብሔር የኀድር ውስቴቱ። መዝ ፷፯፥፲፭፤ 

ትርጒም፦ 

የጸና ተራራና የለመለመ ተራራ ነው። 

የጸኑ ተራራዎች ለምን ይነሣሉ? 

እግዚአብሔር ያድርበት ዘንድ የወደደው ተራራ ይህ ነው። 

ምሥጢር፦ 

ርጉዕ ትሩፍ በሃይማኖት የጸና ጥሉል በረድኤት የለመለመ ነው፤ ቦ ርጉዕ ምእመን በሃይማኖት የጸና ጥሉል በልጅነት የለመለመ ነው። 

በኢየሩሳሌም ጸንተው ይኖሩ የነበረ ሰብአ ከነዓን ከሀገራቸው ወጥተው ለምን ይሄዳሉ? ለምን ይሄዳሉ ብትል እግዚአብሔር የወደደው ትሩፍ ወርሷት ይኖር ዘንድ ነው ብዬ እመልስልሃለሁ። ቦ በኢየሩሳሌም ጸንተው የሚኖሩ እስራኤል ወጥተው ለምን ይሄዳሉ ቢሉ ቢበድሉ አይደለምን? ቢመለሱ ወርሰዋት ይኖሩ ዘንድ ነው። ቦ በይሁዳ በሰማርያ ይኖሩ የነበሩ እነአጀም ኮንታ ከይሁዳ ከሰማርያ ለምን ወጥተው ይሄዳሉ ቢሉ እግዚአብሔር የወደደው ትሩፍ ወርሷት ይኖር ዘንድ ነው። 

በሰው ልቡና ጸንተው ይኖሩ የነበሩ አጋንንት ከሰው ልቡና ወጥተው ለምን ይሄዳሉ ቢሉ ማደሪያው በሚሆን በምእመን እግዚአብሔር ያድርበት ዘንድ ነው። ሰውነቱን እንደ ድንኳን ልቡናውን እንደ ዙፋን ፍትወታት እኩያትን ኃጣውእ ርኵሳትን እንደ አጥር አድርገው ይኖሩበታልና፤ እግዚአብሔር ባደረበት ሰይጣን፣ ሰይጣን ባደረበት እግዚአብሔር አያድርምና፤ እስመ የኀድር ቦን ይላል እግዚአብሔር ለዘለዓለሙ አድሮባቸው ይኖራልና።  

ወንጌል፦ ማቴ ፲፯፥፩ – ፲፬፤ 

፷፮.፪ የዕለቱ ምንባባት፦

ዕብ ፲፩፥፳፫ – ፴፤

፪ጴጥ ፩፥፲፭ – ፍ፤

ግብ ፯፥፵፬ – ፶፩፤

ወንጌል፦ ማቴ ፲፯፥፩ – ፲፬፤ ሉቃ ፱፥፳፰ – ፴፰፤

ቅዳሴ – ዘእግዝእትነ ማርያም

፷፮.፫ ዘቅዳሴ ምስባክ፦

ታቦር ወአርሞንኤም በስመ ዚአከ ይትፌሥሑ፤

ወይሴብሑ ለስምከ፤

መዝራዕትከ ምስለ ኃይል። መዝ ፹፰፥፲፪፤ 

ትርጕም፦

ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል፤

ስምህንም ያመሰግናሉ፤

ክንድህ ከኃይልህ ጋር ነው።

ምሥጢር፦

ታቦርና አርሞንኤም በስምህ አምነው በተደረገላቸው ነገር ደስ ይላቸዋል። በሀገሪቱ ሰዎቹን መናገር ነው። ባርቅ ዲቦራ ሲሣራን ድል ነሥተውላቸው እስራኤል ደስ ብሏቸዋልና። 

ምነው ይህማ የተደረገው በደብረ ታቦር አይደለምን ስለምን አርሞንኤምን አነሣ ቢሉ መጽሐፍ አንዱን ከአንዱ አስጠግቶ መናገር ልማዱ ነውና። አንድም አባራሪ ፈረሰኛ ተባራሪ እግረኛ ከደረሰ ብሎ ነው።

ስምህን ያመሰግናሉ ለስምህ ምስጋና ያቀርባሉ።

ሥልጣንህ ኃይል ከማድረግ ጋር ተገለጸላቸው።

አንድም ሐዋርያት በደብረ ታቦር በአርሞንኤም ብርሃነ መለኮትህን አይተው ደስ ይላቸዋል። ስለምን አርሞንኤምን አነሣ ብርሃነ መለኮቱ የተገለጠው በደብረ ታቦር አይደለምን ቢሉ ብርሃኑ እስከ አርሞንኤም ደርሷልና።

ስምህን ያመሰግናሉ ለስምህ ምስጋና ያቀርባሉ።

መንፈስ ቅዱስ ከወልድ ጋር ተገለጸላቸው።

፷፯ ዛቲ ይእቲ ማርያም 

መዝሙር ዛቲ ይእቲ ማርያም ከነሐሴ ፰ – ፲፬

፷፯.፩ (በ፪/ብ) ዛቲ ይእቲ ማርያም ማኅደረ መለኮት እንተ ተሰምየት ሰንበተ ክርስቲያን በከመ ይቤ ዳዊት በመዝሙር አንሣእኩ አዕይንትየ መንገለ አድባር አድባረ ድኁኃን ተሰምየት ዛቲ ይእቲ ቅድስት ድንግል ተዓቢ እምኵሉ ፍጥረት ኢያውዓያ እሳተ መለኮት።

ትርጕም፦

የክርስቲያን ሰንበት/ዕረፍት የተባለች የመለኮት ማደሪያ ይህች ማርያም ናት ዳዊትበመዝሙር ዐይኖቼን ወደ ተራራዎች አነሣሁ እንዳለ፤ ለድኅነት የተመረጡ የሚጥጉባት ተራራ የተባለች ይህች ቅድስት ድንግል ማርያም ናት ከፍጥረት ሁሉ ትበልጣለች ባሕርየ መለኮቱ አላቃጠላትምና።

፷፯.፪ የዕለቱ ምንባባት፦

ዕብ ፲፩፥፰ – ፲፱፤

፪ዮሐ ፩፥፩ – ፰፤

ግብ ፳፯፥፴፩ – ፴፰፤ 

ወንጌል፦ ሉቃ ፩፥፴፱ – ፵፮፤

ቅዳሴ፦ ዘእግዝእትነ ማርያም

፷፯.፫ የዕለቱ ምስባክ፦

አንሣእኩ አዕይንትየ መንገለ አድባር፤

እምአይቴ ይምጻእ ረድኤትየ፤

ረድኤትየሰ እምኀበ እግዚአብሔር። መዝ ፻፳፥፩፤

ትርጕም፦

ዐይኖቼን እደ ተራራ አነሣሁ፤

ረድኤቴ ከወዴት ይምጣ?

ረድኤቴ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።

ምሥጢር፦ 

ዐይኖቼን በተስፋ ወደ ኢየሩሳሌም አቀናሁ፤ አንድም ምነው? ጊዜው ደርሷል አታወጡኝምን እያልሁ ወደ ነቢያት ወደ ካህናት ዐይኖቼን አቀናሁ፤ አንድም ዐይኖቼን ወደ ተራራው አቀናሁ፤ እንወጣለን እያሉ በየተራራው ይቅበዘበዙ ነበርና፤

ረዳቴ ከየትም ከየት ይደረግልኝ ይታዘዝልኝ እንደሆነ ብዬ፤

እንዲህስ እንዳልል የእኔ ረድኤት ከእግዚአብሔር ዘንድ ይደረግልኛል ይታዘዝልኛል።

፷፰ ተጋቢኦሙ

ለእመ ኮነ በዓለ ሐዋርያት አመ ፲ወ፭ ለነሐሴ መዝሙር ተጋቢኦሙ

፷፱.፩ (በ፩/ቆ) ተጋቢኦሙ በደመና ሰማይ ኵሎሙ ሐዋርያቲሁ ተበሀሉ በበይናቲሆሙ ምንተኑመ አስተጋብአነ ውስተ ዛቲ አንቀጽ ለለአሐዱ ይቤሎ ጴጥሮስ ለጳውሎስ ጸሊኬ እኁየ ጳውሎስ ወኢትናፍቅ ቅድመ እግዚአብሔር ይቤሎ ጳውሎስ ለጴጥሮስ እፎ አነ እጼሊ ዘእምቅድሜክሙ እስመ ሐዲስ ተክል አነ ወተፈሥሑ ኵሎሙ ሐዋርያት በእንተ ዘይቤሎሙ ጳውሊ አብዕዋ ቤታ ለማርያም ኦ ትቤ ማርያም ንሥእዎ ወአንብብዎ ለዝንቱ መጽሐፍ ኦ ትቤ ማርያም እወጽእ እምዝንቱ ሥጋየ ወአሐውር ውስተ ሕይወት ዘለዓለም ኦ ትቤ ማርያም ተዘከርኬ ዮሐንስ ዘይቤለከ ሊቅ አመ ትረፍቅ ዲበ እንግድዓሁ።

ትርጕም፦

ሁሉም ሐዋርያት ተሰብስበው እርስ በእርሳቸው እንዲህ ተባባሉ እያንዳንዳችንን ከዚች በር ላይ ምን ሰበሰበን? ጴጥሮስ ጳውሎስን ወንድሜ ጳውሎስ በእግዚአብሔር ፊት ጸልይ አትጠራጠር አለው ጳውሎስ ጴጥሮስን ከእናንተ ፊት እንዴት እጸልያለሁ እኔ አዲስ ተክል ነኝና አለው ጳውሎስ ስላላቸው ነገር ሐዋርያት ሁሉ ደስ አላቸው እመቤታችንን ወደ ቤቷ አስገቧት ኦ! ማርያም እንዲህ አለች ይህንን መጽሐፍ ወስዳችሁ አንብቡት ከዚህ ሥጋዬ እወጣለሁ ወደ ዘለዓለም ሕይወት እሄዳለሁ ኦ! ማርያም እንዲህ አለች ዮሐንስ! አጠገቡ በተቀመጥህ ጊዜ መምህር የነገረኸን አስብ አለችው።  

፷፰.፪ የዕለቱ ምንባባት፦

ሮሜ ፲፭፥፳፰ – ፍ፤

ይሁዳ ፩፥፳ – ፍ፤

ግብ ፬፥፲፮ – ፳፫፤ 

ወንጌል፦ ሉቃ ፲፩፥፳፯ – ፳፱፤

ቅዳሴ፦ ዘአበዊነ ሐዋርያት

፷፰.፫ የዕለቱ ምስባክ፦

ህየንተ አበውኪ ተወልዱ ለኪ ደቂቅ፤

ወትሠዪሚዮሙ መላእክተ ለኵሉ ምድር፤

ወይዘክሩ ስመኪ በኵሉ ትውልደ ትውልድ። መዝ ፵፬፥፲፮፤

ትርጕም፦

በአባቶችሽ ፈንታ ልጆች ተወለዱልሽ፤

በምድርም ሁሉ ላይ ገዥዎች አድርገሽ ትሾሚያቸዋለሽ፤

ለልጅ ልጅ ሁሉ ስምሽን ያሳስባሉ።

ምሥጢር፦

ርስዒ ሕዝበኪ ወቤተ አቡኪ ብሎ ነበርና ስለ አባቶችሽ ፈንታ ልጆች ተተኩልሽ፤

በአራቱ ማዕዘን አለቆች አድርገሽ ትሾሚያቸዋለሽ፤ ምነው የሚሾምማ ንጉሡ አይደለምን ቢሉ እገሌ ይሾም እያለች እያማለደች የምታሾም ስልሆነ፤ አንድም እሷም በበኩሏ ቀኛዝማች ግራዝማች ደጃዝማች እያለች ትሾማለችና።

የሰብለ ወንጌል የሮማነ ወርቅ ልጆች ነን እያሉ ስምሽን ለልጅ ልጅ ይጠራሉ።

አንድም ስለ ዐበይት ነቢያት ፈንታ ሐዋርያት ስለ ደቂቅ ነቢያት ፈንታ ሰባ አርድእት አንድም ስለ ዓበይት ነቢያት ፈንታ ደቂቅ ነቢያት ስለ ደቂቅ ነቢያት ፈንታ ሐዋርያት ስለ ሐዋርያት ፈንታ ሰባ አርድእት ስለ ሰባ አርድእት ፈንታ ሊቃውንት መምህራን ተተኩልሽ።

በአራቱ ማዕዘን አለቆች አድርገሽ ትሾሚያቸዋለሽ፤ ማኅበሩ አንድ ሁነው የሚሾሙ ስለሆነ። አንድም ትሰምዪዮሙ ይላል ስምዖን የተባለውን ጴጥሮስ ሳውል የተባለውን ጳውሎስ ልብድዮስ የተባለውን ታዴዎስ ዲዲሞስ የተባለውን ቶማስ እያልሽ አንድም ሐዋርያት ሰባ አርድእት ሊቃውንት እያልሽ ስም ታወጪላቸዋለሽ። አንድም እመቤታችን ለደቅስዮስ መንበር ለኒቆላዎስ ዐፅፍ ሰጥታቸዋለችና። አንድም ትሰምዪዮሙ አፈ ወርቅ ልሳነ ወርቅ እያልሽ ስም ታወጪላቸዋለሽ።

ተዘከራ ለአሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንተ ሀለወት እምጽንፍ እስከ አጽናፈ ዓለም – ከጽንፍ እስከ ጽንፍ ያለች አንዲቱን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስብ እያሉ ስምሽን ለልጅ ልጅ ይጠራሉ። አንድም ስምሽን በአራቱ ማዕዘን ይጠራሉ ሰአሊ ለነ ቅድስት ሳይላት የሚውል የለምና። 

ነሐሴ ፲፮ በዓለ ፍልሰታ ለማርያም 

ዘነግህ ምስባክ፦ 

ወትቀውም ንግሥት በየማንከ፤ 

በአልባሰ ወርቅ ዑፅፍት ወኊብርት፤ 

ስምዒ ወለትየ ወርእዪ ወአጽምዒ ዕዝነኪ።   

ወንጌል፦ ሉቃ ፩፥፴፱ – ፶፯፤ 

ዘቅዳሴ ምስባክ፦ 

ሮሜ ፰፥፴፩ – ፍጻሜ፤

፪ዮሐ ፩፥፩ – ፯፤

ግብ ፩፥፲፪ – ፲፭፤

ወንጌል፦ ፳፮፥፳፮ – ፴፩፤ 

ቅዳሴ፦ ዘእግዚእነ 

ዘቅዳሴ ምስባክ፦ 

ቀደሰ ማኅደሮ ልዑል፤ 

እግዚአብሔር ውስተ ማዕከላ ኢትትሀወክ፤ 

ወይረድኣ እግዚአብሔር ፍጽመ። 

፷፱ ንዒ ርግብየ

መዝሙር ንዒ ርግብየ ከነሐሴ ፲፯ነሐሴ ፳

፷፱.፩ (በ፫/ፈ) ንዒ ርግብየ ሠናይት ርግብየ ይቤላ በእንተ የውሃታ ወሠናይት በእንተ አርምሞታ (ን) ዕፀ ጳጦስ ይእቲ እንተ በአማን ይብልዋ ቅድስተ ቅዱሳን (ን) ወይቤላ መልአክ ተፈሥሒ ፍሥሕት ቡርክት አንቲ እምአንስት (ን) መንፈስ ቅዱስ ይመጽእ ላዕሌኪ ወኃይለ ልዑል ይጼልለኪ (ን) ጽርሕ ንጽሕት አግዓዚት ሰመያ ማኅደረ መለኮት (ን) ከመ ፍሕሦ ቀይሕ ከናፍርኪ ከመ ዘውገ ማዕነቅ ኅንብርትኪ (ን) መላሕትኪ ከመ ወይን ወጼና አንፍኪ እምኵሉ አፈው (ን) ወትወጽእ እምግበበ አናብስት እምታዕካ ዘነገሥት እምቅድመ ሃይማኖት (ን) ኵለንታኪ ሠናይት አልብኪ ነውር ወኢምንትኒ ላዕሌኪ ንዒ ርግብየ ሠናይት ንዒ ርግብየ ሠናይት።

ትርጕም፦

መልካሚቱ ርግቤ ነዪ ስለ የዋህነቷ ርግቤ ይላታል በዝምታዋ ያማረች ናት በእውነት ዕፀ ጳጦስ ናት ቅድስተ ቅዱሳን ይሏታል መልአኩ ደስ የተሰኘሽ ደስ ይበልሽ አንቺ ከሴቶች ተለይተሽ ቡርክት ነሽ አላት መንፈስ ቅዱስ ወዳንቺ ይመጣል የልዑል ኃይል ይጋርድሻል ነጻ የምታወጣ ንጽሕት አዳራሽ ናት ማኅደረ መለኮት ብሎ ጠራት ከናፍሮችሽ እንደ ቀይ አበባ ናቸው ጎንሽ እንደ ዋኖስ ነው ጉንጮችሽ እንደ ወይን ናቸው የአፍንጫሽ ሽታ ከሽታ ሁሉ በላይ ነው ከአናብስት ጉድጓድ ትወጣለች ከነገሥታት አዳራሽ ከሃይማኖት በፊት። ሁለንተናሽ ውብ ነው በላይሽ ላይ ምንም ነውር የለብሽም መልካሚቱ ርግቤ ነዪ።

፷፱.፪ የዕለቱ ምንባባት፦

፩ቆሮ ፯፥፲፫ – ፲፰፤

ያዕ ፬፥፲፩ – ፍ፤

ግብ ፲፰፥፱ – ፲፰፤

ወንጌል፦ ማቴ ፳፭፥፩ -፲፫

ቅዳሴ ፡- ዘእግዝእትነ ማርያም 

፷፱.፫ የዕለቱ ምስባክ፦

ክነፈ ርግብ በብሩር ዘግቡር፤

ወገበዋቲሃኒ በሐመልማለ ወርቅ፤

አመ አዘዘ ሰማያዊ ንጉሥ ላዕሌሃ። መዝ ፷፯፥፲፫፤

ትርጕም፦

ከብር እንደ ተሠሩ እንደ ርግብ ክንፎች፤

በቅጠልያ ወርቅ እንደ ተለበጡ ላባዎች ትሆናላችሁ፤

ሰማያዊ ንጉሥ በላይዋ ባዘዘ ጊዜ።

ምሥጢር፦

ጽሪት ሕግ ታገኛላችሁ፤

ሕጎቿ በኢታምልክ የጸኑ፤

ኪያሃ ሲል ነው እሷን ጠብቁ ብሎ ባዘዘ ጊዜ።

አንድም ንጽሐ ሥጋን ንጽሐ ነፍስን ንጽሐ ልቡናን የያዘች ድንግል እመቤታችንን ታገኛላችሁ፤

ልቡናዋ ይኩነኒ በማለት የጸና፤

ከእሷ ተወልጄ አድናችኋለሁ ብሎ ባዘዘ ጊዜ። 

ዓዲ ምስባክ፦

አዋልደ ንግሥት ለክብርከ፤

ወትቀውም ንግሥት በየማንከ፤

በአልባሰ ወርቅ ዑፅፍት ወኁብርት። መዝ ፵፬፥፱

ትርጕም፦

የንግሥት ሴቶች ልጆች ለክብርህ ናቸው፤

ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች፤

በወርቅ ልብስ ተጎናጽፋና ተሸፋፍና።

ምሥጢር፦

የዕቴጌ ልጆች ለክብርህ ናቸው፤

ዕቴጌ በቀኝህ ትቀመጣለች፤

ወርቀ ዘቦ ግምጃ ደርባ ደራርባ ለብሳ ተጐናጽፋ።

አንድም ይትቀነያ ያለበት ነው የንጉሥ ልጅ ንጉሥ እንዲሉ፤ የንጉሥ የምእመን ልጆች ለጌትነትህ ይገዛሉ፤

ምእመን በሰጠሃት ክብር ጸንታ ትኖራለች፤

ምግባር ሃይማኖትን ይዛ።

አንድም በእመቤታችን ያመኑ የእመቤታችን ልጆች ለጌትነትህ ይገዛሉ፤

እመቤታችን በድንጋሌ ሥጋ በድንጋሌ ሕሊና ጸንታ ትኖራለች አንድም ትነብር ሲል ነው በቀኝህ ትቀመጣለች ወነበረት ድንግል በየማነ ወልዳ ወአምላካ – ድንግል በልጇና በአምላኳ ቀኝ ተቀመጠች እንዲል፤

ንጽሐ ሥጋን ንጽሐ ነፍስን ንጽሐ ልቡናን አንድ አድርጋ ይዛ።

ነሐሴ ፳፩ በዓለ እግዝእትነ ማርያም 

ዘነግህ ምስባክ፦ 

ወትቀውም ንግሥት፤ 

ዘቅዳሴ ምንባብ፦ 

፩ቆሮ ፯፥፳፭ – ፍጻሚ፤

፪ዮሐ ፩፥፩ – ፯፤

ግብ ፲፮፥፲፫ – ፲፰፤

ወንጌል፦ ማቴ ፳፭፥፩ – ፲፬፤

ቅዳሴ፦ ዘእግዝእትነ ማርያም 

ዘቅዳሴ ምስባክ፦ 

አዋልደ ንግሥት በል 

ይሁበነ ዝናመ

መዝሙር ይሁበነ ዝናመ ከነሐሴ ፳፪ነሐሴ ፳፮

፸.፩ (በ፫) ይሁበነ ዝናመ በጊዜሁ ይሁበነ ዝናመ በጊዜሁ ወይሁበነ እክለ በረከት (ይ) ያርኁ ክረምተ ይገብር ምሕረተ ወይሁበነ ዝናመ በረከት (ይ) ከሢቶ ዐይኖ ሰፊሖ የማኖ ይፌኑ ሣህሎ ወበዘአእመረ ይሴባሕ (ይ) ወሠርዐ ሰንበተ ለሰብእ ዕረፍተ ወብውህ ሎቱ ይኅድግ ኃጢአተ (ይ) ዐይነ ኵሉ ነፍስ ይሴፎ ኪያሁ ይሁቦሙ ሲሳዮሙ በጊዜሁ።

ትርጕም፦

ዝናምን በጊዜው ይሰጠናል የበረከት እህልን ይሰጠናል ክረምትን ይከፍታል ምሕረትን ያደርጋል የበረከት ዝናምን ይሰጠናል ዐይኑን ገልጦ ቀኙን ዘርግቶ ይቅርታውን ይልካል ባወቀ መንገድ ይመሰገናል ለሰው ዕረፍት ይሆን ዘንድ ሰንበትን ሠራ ኃጢአትን ይቅር ይል ዘንድ ሥልጣን አለው የሰው ሁሉ ዐይን እሱን ተስፋ ያደርጋል በጊዜው ምግባቸውን ይሰጣቸዋል።

፸.፪ የዕለቱ ምንባባት፦

ዕብ ፫፥፩ – ፍ፤

ያዕ ፭፥፩ – ፲፪፤

ግብ ፳፪፥፩ – ፳፪፤

ወንጌል፦ ዮሐ፮፥፵፩ – ፍጻሜ፤

ቅዳሴ፦ ዘኤጲፋንዮስ

፸.፫ የዕለቱ ምስባክ፦

ዐይነ ኵሉ ነፍስ ይሴፎ ኪያከ፤

አንተ ትሁቦሙ ሲሳዮሙ በጊዜሁ፤

ትሰፍሕ የማነከ ወታጸግብ ለኵሉ እንስሳ ዘበሥርዓትከ። መዝ ፻፵፬፥፲፮

ትርጕም፦

የሰው ሁሉ ዐይን አንተን ተስፋ ያደርጋል፤

አንተ ምግባቸውን በየጊዜው ትሰጣቸዋለህ፤

ቀኝህን ትዘረጋለህ በሥርዓትህ ለሚኖሩ እንስሳ ሁሉ ታጠግባለህ።

ምሥጢር፦

የሰው ሁሉ ሰውነት አንተን ተስፋ አለኝታ ያደርጋል።

በየጊዜው ምግባቸውን ትሰጣቸዋለህና በዘር ጊዜ ዘሩን በመከር ጊዜ መከሩን። አንድም የበልጉን በበልግ የመከሩን በመከር ትሰጣቸዋለህና።

እጀ ሰፊ ነህና እጅህን ዘርግተህ በሥርዓትህ ጸንተው ለሚኖሩ ለእንስሳት ምግባቸውን ሰጥተህ ደስ ታሰኛቸዋለህ። ከሰው በቀር ከሥርዓቱ የወጣ የለምና።

፸.፬ መልእክት፦

በሥጋዊውም ሆነ በመንፈሳዊው ሕይወታችን እግዚአብሔርን ተስፋ ማድረግ ጠቃሚ ነው። “ከአርያም ኃይልን እስክትለብሱ በኢየሩሳሌም ቆዩ” “አስቀድማችሁ መንግሥቱንና ጽድቁን ሹ” የሚሉት ቃላተ ወንጌል በተስፋ መኖርን የሚገልጡ ናቸው። በዘወትር ጸሎታችንም “ትምጻእ መንግሥትከ – መንግሥትህ ትምጣልን” እያልን እንድንጸልይ አምላካችን ያዘዘን ተስፋ ያላዩትን እንዳዩ ያልያዙትን እንደያዙ አድርጎ የሚሳይ መነጽር ስለሆነ ነው።

በተስፋ የሚኖር ሰው ቢወድቅ ለመነሣት፣ ቢሰበር ለመጠገን፣ ቢወጣ ተመልሶ ለመግባት፣ ቢጠራጠር መምህራንን ጠይቆ ለመረዳት፣ ቢረክስ ለመቀደስ፣ ቢጠፋ ለመመለስ እድል ያለው ነው። ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ብሎ እንዳስተማረን። “እንግዲህ ወዳጆች ሆይ የዚህ ተስፋ ቃል ካለን በእግዚአብሔር ፍርሃት ቅድስናን ፍጹም እያደረግን ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን እናንጻ”  ፪ቆሮ፯፥፩

ዘበሥርዐትከ የሚለውን ቃል መተርጉማን ሲያብራሩ ከሰው በቀር ከሥርዓቱ የወጣ የለም ብለዋል። ይህንን ማብራሪያ ከልባችን በማስተዋል ያለሥርዓት መሄድ ያስከፈለውንና የሚያስከፍለውን ዋጋ በመገንዘብ ያለሥርዓት እንድንሄድ የሚገፋፋንን የራሳችንን ፍላጎትና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን እንድንዳፈርና በዚያ መንገድ እንድንሄድ አላስፈላጊ ልምምድ ከሚያለማምዱን ወይም በተጽእኖ ከሚገፋፉን አካላት በመራቅና መንፈሳዊ በረከትና ጸጋ የምናገኝበት ላይ እንድናተኩር፣ 

በሥርዓት መሄድ ያለውን ጥቅም ቀምሰን ሌሎችም እንዲቀምሱት በማድረግ ሥርዓት የለሾችን እየመከርንና ወደመዳን ሊያመጣ በሚችል ወቀሳ እየወቀስንና ሥርዓተ አልበኝነትን አርቀን በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እየተመራን መንፈሳዊ አገልግሎታችንን ልናከናውን ያስፈልጋል።

መንግሥተ ሰማያትን ተስፋ የሚያደርግ ማንነት ካለን በዚህ ዓለም የሚታየው ነገር ሁሉ የሚያጓጓንና ወዳልተፈለገ አቅጣጫ የሚወስደን አንሆንም ከዕለት ወደዕለት ኃይላችንን እያደስን በትዕግሥት መንግሥተ እግዚአብሔርን እንጠባበቃለን እንጂ። ብፁዕ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ እንደነገረን።

“በተስፋ ድነናልና፤ ነገር ግን ተስፋ የሚደረግበቱ ነገር ቢታይ ተስፋ አይደለም የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል? የማናየውን ግን ተስፋ ብናደርገው በትዕግሥት እንጠባበቃለን” ሮሜ፰፥፳፬

ነሐሴ ፳፬ በዓለ ዕረፍቱ ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት ወቶማስ 

ዘነግህ ምስባክ፦  

እስመ መምህረ ሕግ ይሁብ በረከተ፤ 

ወየሐውር እምኃይል ውስተ ኃይል፤ 

ወያስተርኢ አምላከ አማልክት በጽዮን። 

ወንጌል፦ ዮሐ ፲፥፩ – ፳፪፤

ዘቅዳሴ ምንባብ፦ 

ሮሜ ፰፥፴፭ – ፍጻሜ፤

፩ጴጥ ፭፥፩ – ፮፤

ግብ ፳፥፳፰ – ፴፩፤

ወንጌል፦ ማቴ ፲፥፲፮ – ፍጻሜ፤

ቅዳሴ፦ ዘሠለስቱ ምዕት 

ዘቅዳሴ ምስባክ፦ 

እስመ በእንቲአሁ ይቀትሉነ ኵሎ አሚረ፤ 

ወኮነ ከመ አባግዕ ዘይጠብሑ፤ 

ንቃሕ እግዚኦ ለምንት ትነውም። መዝ ፵፫፥፳፪፤

ትርጒም፦ 

ስለእርሱ ሁልጊዜ ይገድሉናልና፤ 

እንደሚታረዱ በጎች ሆነናል፤ 

አቤቱ ንቃ ለምን ትተኛለህ? 

ምሥጢር፦ 

በእሱ ስም ስላመንን በእሱ ስም ስላስተማርን በእሱ ስም ስለተጠራን ዘወትር መከራ ያመጡብናልና፤ ወሞተ ዳንኤል ብዙኀ ጊዜያተ በእንተ አምላኩ – ዳንኤል ስለ አምላኩ ብዙ ጊዜ ሞተ እንዲል፤ 

ለሞት የሚያበቃ መከራ ስላመጡብን ለልደት ለጥምቀት ለፋሲካ እንደሚታረዱ በጎች ሆንን፤ ቦ ዘይጠብሕዎሙ ይላል ለልደት ለጥምቀት ለፋሲካ እንደሚያርዷቸው በጎች ሆንን፤ የዓመት በዓልን በግ ከስቷልና ይወፍር አንሷልና ይደግ የሚለው የለም ሁሉ ደሙ ይፍሰስ ይለዋል እነሱንም ያገኘ ሁሉ መከራ ያጸናባቸዋልና፤ 

አቤቱ በሥራ በመፍረድ ተነሥ እንጂ ለምን ዝም ትላለህ አሁን በጌታ መተኛት መነሣት ኑሮበት አይደለም አለመራዳቱን በመተኛት መራዳቱን በመነሣት መስሎ ተናገረ እንጂ። 

ነሐሴ ፳፱ ተዝካረ ልደቱ ለእግዚእነ 

ዘነግህ ምስባክ፦ 

ምስሌከ ቀዳማዊ በዕለተ ኃይል፤ 

በብርሃኖሙ ለቅዱሳን፤ 

ወለድኩከ እምከርሥ እምቅድመ ኮከበ ጽባሕ። 

ወንጌል፦ ሉቃ ፪፥፩ – ፰፤ 

ዘቅዳሴ ምንባብ፦ 

ገላ ፫፥፲፭ – ፳፩፤

፩ዮሐ ፬፥፱ – ፲፰፤

ግብ ፳፥፳፰ – ፴፩’፤

ወንጌል፦ ማቴ ፭፥፩ – ፲፯፤

ቅዳሴ፦ ዘእግዚእነ 

ዘቅዳሴ ምስባክ፦ 

እዜምር ወዕሌቡ ፍኖተ ንጹሐ፤ 

ማዕዜ ትመጽእ ኀቤየ፤ 

ወአሐውር በየውሃተ ልብየ ማዕከለ ቤትየ። መዝ ፻፥፩፤ 

ትርጒም፦ 

እዘምራለሁ ንጹሕ መንገድንም አስተውላለሁ፤ 

ወደእኔ መቼ ትመጣለህ? 

በቤቴ መካከል በልቤ ቅንነት እሄዳለሁ። 

ምሥጢር፦ 

እንኪያስ እኔም አመሰግንሃለሁ ንጹሕ ሕግህንም ልብ አደርጋለሁ ይለዋል ትሩፍ ጌታን፤ ቦ ይቅር ትለኛለህ ትፈርድልኛለህ ብዬ በውስጥ በአፍአ በነፍስ በሥጋ አመሰግንሃለሁ ንጹሕ ሕግህንም እመለከታለሁ ልብ አደርገዋለሁ፤ 

ምሕረተ ወፍትሐ አኀሊ ለከ ይቅር እልሃለሁ እፈርድልሃለሁ ትላለህ እንጂ በረድኤት ወደእኔ መቼ ትመጣለህ ይለዋል ትሩፍ ጌታን፤ ቦ እዜምር እሌቡ ትላለህ እንጂ በጸሎት በአምልኮት ወደእኔ መቼ ትመጣለህ ይለዋል ጌታ ትሩፍን፤ 

እኔስ በወገኖቼ መካከል በቅን ልቡና በዐሥሩ ቃላት ጸንቼ መቼ እኖራለሁ፤ ቦ በወገኖቼ መካከል በኀዲገ በቀል ጸንቼ እኖራለሁ።  

፸፩ ሰንበት ተዐቢ

መዝሙር ሰንበት ተዐቢ ነሐሴ ፳፯ እና ፳፰

፸፩.፩ (በ፭) ሰንበት ተዐቢ እምኵሉ ዕለት ሰንበት ተዓቢ እምኵሉ ዕለት ወሰብእ ይከብር እምኵሉ ፍጥረት (ሰ) አዕበያ ኖኅ በውስተ ታቦት አብርሃም አክበራ በውስተ ምሥዋዕ (ሰ) አዘዞሙ ሙሴ ለሕዝብ ያክብሩ ሰንበተ በጽድቅ (ሰ) አዝዞሙ እግዚኦ ለደመናት ያውርዱ ዝናመ ዲበ ምድር ሰንበት ተዐቢ እምኵሉ ዕለት ወሰብእ ይከብር እምኵሉ ፍጥረት። 

ትጕም፦

ከዕለት ሁሉ ሰንበት ትከብራለች ከፍጥረት ሁሉ ሰው ይከብራል ኖኅ በመርከብ ውስጥ አገነናት አብርሃም በመሥዋዕት አከበራት ሙሴ ሰንበት ያከብሩ ዘንድ ጉባኤውን አዘዛቸው አቤቱ በምድር ላይ ዝናምን ያዘሙ ዘንድ ደመናትን እዘዛቸው ከዕለት ሁሉ ሰንበት ትከብራለች ከፍጥረት ሁሉ ሰው ይከብራል።

፸፩.፪ የዕለቱ ምንባባት፦

ዕብ ፯፥፭ – ፍ፤

ያዕ ፪፥፲፬ – ፍ፤

ግብ ፯፥፩ – ፱፤

ወንጌል፦ ሉቃ ፲፪፥፲፮ – ፳፯፤

ቅዳሴ፦ ዘአትናቴዎስ

፸፩.፫ የዕለቱ ምስባክ፦

ወሐመልማለ ለቅኔ እጓለ እመሕያው፤

ዘይሁቦሙ ሲሳዮሙ ለእንስሳ፤

ወለእጕለ ቋዓት እለ ይጼውዕዎ። መዝ ፻፵፮፥፱፤

ትርጕም፦

ልምላሜውን ለሰው ልጆች አገልግሎት የሚያበቅል፤

ለእንስሳትና ለሚጠሩት ቍራዎች ምግባቸውን የሚሰጣቸው እሱ ነው።

ምሥጢር፦ 

እህሉን ተክሉን የሚያበቅል እሱ ነው ያንን እየተመገበ በሥጋ በነፍስ ለእግዚአብሔር እንዲገዛ፤ አንድም ለሰው ለሚገዛ ለእንስሳ ልምላሜውን የሚያበቅል እሱ ነው፤

ለእንስሳት ምግባቸውን የሚሰጣቸው እሱ ነው በእንስሳ ሁሉን መናገር ነው፤

ለሚለምኑት ለዕጕለ ቋዓት – ለቍራዎች ልጆች ምግባቸውን የሚሰጣቸው እሱ ነው፤ እሱ ባወቀ ይለምኑታልና እንዲህ አለ፤ አንድም ለእለ ኢይጼውዕዎ ይላል ለማይለምኑት ለዕጕለ ቋዓት ምግባቸውን የሚሰጣቸው እሱ ነው። ቋዕ/አሞራ ሲወልድ ፍህም መስሎ ይወለዳል እናት አባቱ ምን ጉድ ተወለደብን ብለው ጥለዉት ይሄዳሉ ሲርበው ጧ ጧ እያደረገ አፉን ይከፍተዋል ተሐዋስያን ርጥበት ሲሹ ይገባሉ ግጥም አድርጎ ይዞ ይመገባቸዋል። አንድም ተሐዋስያን ሲያልፉ በእስትንፋሱ እየሳበ እስከ አርባ ቀን ድረስ ይመገባቸዋል ከአርባ ቀን በኋላ ጸጕር ያበቅላል በመልክ ይመስላቸዋል ተመልሰው መጥተው ያሳድጉታልና እንዲህ አለ።

፸፪ አምላኪየ ኄር

መዝሙር አምላኪየ ኄር ነሐሴ ፳፱ እና ፴

፸፪.፩ (በ፭/ሴ) አምላኪየ ኄር አንሥአኒ በትንሣኤከ ጎሐ ጽባሕ ዘአንተ ሠራዕከ (አ) ከመ ኢይርሳዕ ሰብሖ ስምከ (አ) ከመ ትጽገብ ምድር እምፍሬ ተግባርከ (አ) ዐይነ ኵሉ ነፍስ ይሴፎ ኪያከ (አ) እስመ በእንተ ሰብእ ሰንበተ ሠራዕከ አምላኪየ ኄር አንሥአኒ በትንሣኤከ መሐሪ ወትረ ስቡሕ ስምከ።

ትርጕም፦

የማለዳውን ብርሃን የሠራህ/ብርሃንን በነግህ የፈጠርህ ቸር አምላኬ ሆይ በትንሣኤህ አንሣኝ። ስምህን ማመስገንን እንዳልረሳ፤ ምድር/የሰው ልጅ ከሥራህ ፍሬ ትጠግብ ዘንድ፤ የሰው ሁሉ ዐይን አንተን ተስፋ ያደርጋል፤ ለሰው ዕረፍት ይሆን ዘንድ ሰንበትን ሠርተሃልና ቸሩ አምላኬ ሆይ በትንሣኤህ አንሣኝ ይቅር ባይ አቤቱ ስምህ ዘወትር ምስጉን ነው።

፸፪.፪ የዕለቱ ምንባባት፦

ሮሜ ፲፫፥፩ – ፍጻሜ፤

፩ጴጥ ፪፥፪ – ፲፩፤

ግብ ፳፯፥፴፫ – ፍጻሜ፤ 

ወንጌል፦ ማቴ ፬፥፲፪ – ፲፯፤

ቅዳሴ፦ ዘእግዚእነ

፸፪.፫ የዕለቱ ምስባክ፦

እስመ ኀቤከ እጼሊ እግዚኦ፤

በጽባሕ ስምዐኒ ቃልየ፤

በጽባሕ እቀውም ቅድሜከ ወአስተርኢ ለከ። መዝ ፭፥፪፤

ትርጕም፦

አቤቱ ወደ አንተ እጸልያለሁና፤

በማለዳ ቃሌን ስማኝ፤

በማለዳ በፊትህ እቆማለሁ እገለጥማለሁ።

ምሥጢር፦

አምኜ ወደ አንተ መላልሼ እጸልያለሁ እለምናለሁና፤

ዕለት ዕለት ልመናዬን ስማኝ አንድም ፈጥነህ ስማኝ፤

ዕለት ዕለት አንድም ማልጄ በመሥዋዕት በጸሎት ከቤተ መቅደስ ገብቼ እገለጣለሁና።