ወርኃ የካቲት

፴፬ መሐሩነ እለ ቀደሙነ 

መዝሙር መሐሩነ ከየካቲት ፮፲፪

፴፬.፩ (በ፪/ኒ) መሐሩነ እለ ቀደሙነ ምጽአቶ ለክርስቶስ ልደቶ ጥምቀቶ አስተርእዮቶ ዜነዋ መልአክ ለማርያም ወይቤላ ትወልዲ ወልደ ወበጽሐ ዕለተ ወሊዶታ ዘዮሐንስ አጥመቆ ወስዕነ ጠይቆቶ መለኮተ ዚአሁ ወስምዖን ተወከፎ ውስተ ሕፅኑ ወአስተርአየ ሕሊናሁ ውእቱ የማኑ ወምክሩ ለአብ ያድኅነነ መጽአ።

ትርጕም፦

የቀደሙ አባቶቻችን የክርስቶስን መምጣት መወለድ መጠመቅ መገለጥ አስተማሩን መልአኩ ለማርያም አበሠራት ወንድ ልጅ ትወልጃለሽ አላት የመውለጃዋ ቀን ደረሰ ዮሐንስ ያጠመቀው ቢሆንም መለኮታዊ ባሕርዩን መርምሮ ማወቅ አልተቻለውም ስምዖን በእቅፉ ተቀበለው የአብ ሕሊናው ተገለጠ የአብ ምክሩ ቀኙ ያድነን ዘንድ መጣ።

፴፬.፪ የዕለቱ ምንባባት፦

፩ጢሞ ፭፥፭ – ፲፩፤

ያዕ ፭፥፲፫ – ፍጻሜ፤

ግብ ፫፥፲፯ – ፍጻሜ፤

ወንጌል፦ ሉቃ ፪፥፳፪ – ፴፭

ቅዳሴ፦ ዘዲዮስቆሮስ

፴፬.፫ የዕለቱ ምስባክ፦

ዘያጸግባ እምበረከቱ ለፍትወትከ፤

ዘይሔድሳ ከመ ንስር ለውርዙትከ፤

ገባሬ ሣህል እግዚአብሔር። መዝ ፻፪፥፭

ትርጕም፦

ምኞትህን ከበረከቱ የሚያጠግባት፤

ጎልማሳነትህን እንደንስር የሚያድሳት፤

እግዚአብሔር ይቅርታ አድራጊ ነው።

ምሥጢር፦

ሰውነትህን ከበረከቱ ሰጥቶ ደስ የሚያሰኛት ጌትነቱ ነው፤

ሰውነትህን እንደ ዖፈ ፊንክስ የሚያድሳት ጌትነቱ ነው።

ዖፈ ፊንክስ ብልየት ያገኘው እንደሆነ ከቆላ ወርዶ ከሁለት ከሦስት ላይ እንጨት ይሰበስባል አንድም ባለወጎች ይሰበስቡለታል ተራራ ተራራ ያህል ሲሆን ከውቅያኖስ አብዶ የሚባል ድኝነት ያለው ጭቃ አለ ከዚያ ሄዶ ተቀብቶ ከተቆለለው እንጨት ላይ ሆኖ ሁለት ክንፉን ያማታዋል ወይወጽእ እሳት እማዕከለ ክነፊሁ ይላል እሳት ከክንፉ ወጥቶ ያቃጥለዋል በዚያ ሀገር ዝናም አይዘንምም በአምስት በአምስት መቶ ዘመን ለሐድሶተ ንስር ያህል ካፊያ ያካፋል እንጂ፤ ነጋውን (በበነጋው) ትል ያህል ሆኖ ያድራል በሁለተኛው ቀን ዖፈ ድንቢጥ ያህላል በሦስተኛው ቡላል (ርግብ) ያህላል በአራተኛው ቀን አካለ መጠን አድርሶ ይሄዳል።

አንድም ሰውነትህን እንደ እርኩም የሚያድሳት ጌትነቱ ነው። እርኩም አርባ ቀን ከመብል ተከልክሎ አፉን ከደንጊያ ላይ ያጠራጠሰው (የመታው) እንደሆነ እንደዋንጫ ውልቅ ብሎ ይወድቅለታል ይታደሳል።

አንድም ሰውነትህን የሚያድሳት ጌትነቱ ነው። እባብ ብልየት ያገኘው እንደሆነ አርባ ቀን ከምግብ ተከልክሎ በስቁረተ ዕፅ በስቁረተ ዕብንም ቢሉ አልፎ ሲሄድ ተገፎ ይወድቅለታል ይታደሳል። አንድም ሰውነትህን በትንሣኤ ዘጉባኤ የሚያድሳት ጌትነቱ ነው፤ ነውና ጌትነቱን አትርሳ።

አንድም ዐቢይ ንስር ሲያረጅ ከባሕር ወርዶ ፫ መዓልት ፫ ሌሊት አድሮ ብልየቱን ገፎ ታድሶ ይወጣል፤ ምሳሌ ነው፤ ንስር የእስራኤል። በእስራኤል የቆጠሩ እንደሆነ በኢኮንያን ተማርከው በሰላትያል ተስፋውን አግኝተው በዘሩባቤል ወጥተዋል። በአሕዛብ የቆጠሩ እንደሆነ በናቡከደነፆር ተማርከው በዮርማሮዴቅ ተስፋውን ሰምተው በብልጣሶር ወጥተዋል። አንድም ንስር የምእመናን፤ ባሕር የጥምቀት፤ ብልየት የፍዳ፤ ሕዳሴ የልጅነት ምሳሌ፤ ፫ መዓልት ፫ ሌሊት መሆኑ ጥምቀት በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም የሚፈጸም የመሆኑ ምሳሌ ነው።

የካቲት በዓለ ስምዖን 

ዘነግህ ምስባክ፦  ዘያጸግባ በል። 

ወንጌል፦ ሉቃ ፪፥፴፮ ߺ ፵፤ 

ዘቅዳሴ ምንባብ፦  ከመዝሙሩ ላይ የተጻፈውን በል። 

ዘቅዳሴ ምስባክ፦ 

ጐሥዐ ልብየ ቃለ ሠናየ፤ 

ወአነ አየድዕ ግብርየ ለንጉሥ፤ 

ከመ ቀለመ ጸሐፊ ዘጠበጠበ ይጽሕፍ ልሳንየ። መዝ ፵፬፥፩፤

ትርጒም፦ 

ልቤ መልካም ነገርን ተናገረ፤ 

እኔም ሥራዬን ለንጉሥ እናገራለሁ፤ 

አንደበቴ እንደ ፈጣን ጸሐፊ ብርዕ ነው። 

ምሥጢር፦ 

ልቡናየ በጎ በጎውን አውጥቶ አውርዶ ተናገረ፤ ቦ ልቡናየ አብ አካላዊ ቃል እኔን አስገኘ ይላል ወልድ፤ ልብነቴ አካላዊ ቃልን አስገኘ ይላል አብ፤ 

ለንጉሥ ለክርስቶስ ትንቢት ግብሬን አቀርባለሁ፤ የነቢይ ግብሩ ትንቢት፣ የካህን ግብሩ መሥዋዕት እንዲሉ፤ 

ከመ ብርዐ ጸሐፊ ሲል ነው፤ ጽሑፍ ኃጢአታ ለይሁዳ በቀለመ ሐፂን ውስተ ሰሌዳ ኰኵሕ – የይሁዳ ኃጢአቷ በድንጋይ ሰሌዳ በብረት ቀለም የተጻፈ ነው እንዲል፤ ዘጠበጠበን ዘይሤኒ ሲል ነው፤ ጦቢት ጦብያ ማለት ያማረ ማለት እንደሆነ፤ አንደበቴ እንዳማረ እንደተወደደ ብርዐ ጸሐፊ ትንቢትን ይናገራል፤ ቦ ጸሐፊ ቀለምን ጠብ ጠብ አድርጎ እንዲጽፍ አንደበቴ ትንቢትን ይናገራል፤ ልቡናውን ከብራና፣ ትንቢቱን ከቀለም፣ አንደበቱን ከብርዐ ጸሐፊ አግብቶ ይናገራል።  

የካቲት ፲፪ በዓለ ቅዱስ ሚካኤል 

ዘነግህ ምስባክ፦ 

ይትዐየን መልአከ እግዚአብሔር ዐውዶሙ፤ 

ለእለ ይፈርህዎ ወያድኅኖሙ፤

ጠዐሙ ወታእምሩ ከመ ኄር እግዚአብሔር። 

ወንጌል፦ ማቴ ፳፭፥፴፩ ߺ ፍጻሜ፤ 

ዘቅዳሴ ምንባብ፦ 

፩ቆሮ ፭፥፮ ߺ ፍጻሜ፤

ይሁዳ ፩፥፱ ߺ ፲፱፤

ግብ ፳፰፥፴ ߺ ፍጻሜ፤ 

ወንጌል፦ ማቴ ፳፥፳፬ ߺ፳፱፤ 

ቅዳሴ፦ ዘዲዮስቆሮስ 

ዘቅዳሴ ምስባክ፦ 

ወበኀቤየሰ ፈድፋደ ክቡራን አዕርክቲከ እግዚኦ፤ 

ወፈድፋደ ጸንዑ እምቀደምቶሙ፤ 

እኌልቆሙ እምኆፃ ይበዝኁ። 

የካቲት ፲፮ ኪዳነ ምሕረት 

ዘነግህ ምስባክ፦  

ዘያነብራ ለመካን ውስተ ቤቱ፤ 

ወያስተፌሥሓ ለእመ ውሉድ፤ 

ዘያነብራ ለመካን ውስተ ቤቱ። መዝ ፻፲፪፥፱፤ 

ትርጒም፦ 

መካኒቱን በቤቱ የሚያኖራት እርሱ ነው፤ 

ደስ የተሰኘችንም የልጆች እናት የሚያደርጋት እርሱ ነው፣ 

ምሥጢር፦ 

ልጅ የሌላት መካኒቱን ከፋርስ ከባቢሎን አውጥቶ በማደሪያው በኢየሩሳሌም የሚያኖራት እርሱ ነው፤ ሚጠት ደረሰ ቢሏት እኔ ልጅ የለኝ ማን ያወጣኛል ብላለችና፤

የልጆች እናት የነበረችውን ደስ የሚያሰኛት እሱ ነው፤ ሚጠት ደረሰ ቢሏት ልጆቼ ሁሉ በፋርስ በባቢሎን ሞተው አልቀው ማን ያወጣኛል ብላለችና።  

ቦ መካን ካህናትን በማደሪያው በኢየሩሳሌም የሚያኖራቸው እርሱ ነው፤ መካን አላቸው ሰባ ዘመን ከትምህርት ተከልክለዋልና፤ 

ነቢያትን ደስ የሚያሰኛቸው እርሱ ነው፤ እመ ውሉድ አላቸው ልጅ ከአብራክ እንዲገኝ ትንቢትም የሚገኝ ከልቡና ነውና። 

ቦ ወንጌልን እንድትነገር የሚያደርጋት እርሱ ነው፤ መካን አላት በመልከ ጼዴቅ ጊዜ ታይታ ጠፍታለችና፤ ቦ ምእመናንን በገነት በመንግሥተ ሰማያት የሚያኖራቸው እርሱ ነው፤ መካን አላቸው አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ልጅነት አጥተዋልና፤ 

ኦሪትን እንድትነገር አድርጎ ሕዝቡን ደስ የሚያሰኛቸው እርሱ ነው፤ እመ ውሉድ አላት ከሙሴ ከአሮን ጀምሮ እስከ ሐና እስከ ቀያፋ ድረስ ሥርዓቷን የሚያስተምሩ ሊቃነ ካህናት አልጠፋባትምና።

ወንጌል፦ ሉቃ ፩፥፭ ߺ ፲፰፤ 

ዘቅዳሴ ምንባብ፦  

ገላ ፬፥፩ ߺ ፲፪፤

፪ዮሐ ፩፥፬ ߺ ፰፤

ግብ ፩፥፲፫ ߺ ፲፭፤ 

ወንጌል፦ ሉቃ ፩፥፴፱ ߺ ፶፯፤

ቅዳሴ፦ ዘእግዝእትነ ማርያም 

ዘቅዳሴ ምስባክ፦ 

እስመ ትቤ ለዓለም አሐንጽ ምሕረተ፤ 

በሰማይ ጸንዐ ጽድቅከ፤ 

ኪዳነ ተካየድኩ ምስለ ኅሩያንየ። ትርጒምና ምሥጢሩን መዝሙር በቀዳሚ ገብረ ላይ ተመልከት። 

፴፭ ተበሀሉ ጻድቃን 

መዝሙር ተበሀሉ ከየካቲት ፲፫ – ፳

፴፭.፩ (በ፮/ሥ) ተበሀሉ ጻድቃን በበይናቲሆሙ እንዘ ይብሉ ቦኑ ዘርኢክምዎ ለልዑል ኢሳይያስኒ ይቤ ርኢክዎ ለልዑል ርኢክዎ ለልዑል ርእየ ወስዕነ ጠይቆቶ ሙሴኒ ይቤ ዘርእዮ በዓምደ ደመና ርኢክዎ ለልዑል ርእየ ወስዕነ ጠይቆቶ ማርያምኒ ትቤ እንተ ፆረቶ በከርሣ ርኢክዎ ለልዑል ርእየት ወክህለት ጠይቆቶ ዮሐንስኒ ይቤ ዘአጥመቆ በዮርዳኖስ ርኢክዎ ለልዑል ርእየ ወስዕነ ጠይቆቶ አኀውየ በትፍሥሕት ንግበር በዓለነ እስመ አስተርአየ ዘኢያስተርኢ ክርስቶስ ወልደ እግዚአብሔር።

ትርጕም፦

ጻድቃን እርስ በርእሳቸው ልዑልን ያያችሁት አላችሁን ተባባሉ ኢሳይያስ ልዑልን አየሁት አለ አየው እንጂ መረዳት አልቻለም በዓምደ ደመና ያየው ሙሴ ልዑልን አየሁት አለ አየው መረዳት ግን አልቻለም በማኅፀኗ የወሰነችው ማርያም ልዑልን አየሁት አለች አይታ ቻለችው ተረዳችው በዮርዳኖስ ያጠመቀው ዮሐንስ ልዑልን አየሁት አለ አየው እንጂ አልተረዳውም ወንድሞቼ ሆይ በዓላችንን በደስታ እናድርግ የማይታይ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ታይቷልና።

፴፭.፪ የዕለቱ ምንባባት፦

ዕብ ፲፪፥፲፪ – ፳፪፤

፪ጴጥ ፩፥፲፱ – ፍ፤

ግብ ፯፥፳፱ – ፴፭፤ 

ወንጌል፦ ዮሐ ፲፥፴፬ – ፍ፤

ቅዳሴ፦ ዘዲዮስቆሮስ

፴፭.፫ የዕለቱ ምስባክ፦

እግዚአብሔር ስቡሕ በምክረ ቅዱሳን፤

ዐቢይ ወግሩም ዲበ ኵሎሙ እለ ዐውዱ፤

እግዚኦ አምላከ ኃይላን መኑ ከማከ። መዝ ፹፭፥፯፤

ትርጕም፦

እግዚአብሔር በቅዱሳን ምክር ምስጉን ነው፤

በዙሪያው ባሉት ሁሉ ላይ ታላቅና ግሩም ነው፤ 

አቤቱ የኃያላን አምላክ እንደ አንተ ያለ ማነው?

ምሥጢር፦

እግዚአብሔር በመላእክት ቃል አንድም በነቢያት በካህናት ቃል የተመሰገነ ነው፤

በመንበረ መንግሥቱ ዙሪያ ባሉ በሱራፌል በኪሩቤል ላይ አንድም በዓለም ዙሪያ ባሉ በአሕዛብ ሁሉ ዘንድ ግሩም ነው ገናና አምላክ ነው፤

አቤቱ የኃያላኑ ባለቤት (የመላእክት የነአብርሃም የጌዴዎን የነዮፍታሔ የነሶምሶን ፈጣሪ) ማዳን መታደግ የሚቻለው እንዳንተ ያለ ማነው?  

፴፮ ወብዙኃን 

መዝሙር ዘቅበላ (ወብዙኃን)

፴፮.፩ (በ፭/ዩ) ወብዙኃን ኖሎት መጽኡ ወስዕኑ ከሢቶታ ለዕብን እምአፈ አዘቅት እስከ ይመጽእ ያዕቆብ ዘክቡት ውስተ ሐቌሁ ዘሀሎ ይሠጎ እምሰብእ ከሠተ ወአስተየ መርዔቶ ወከማሁመ መጽኡ ብዙኃን ነቢያት ወስዕኑ ከሢቶታ ለጥምቀት እስከ ይመጽእ ዐቢይ ኖላዊ እምሰማይ ከሠተ ወአጥመቀ ብዙኃነ አሕዛበ በውስቴታ መንክር ተአምሪሁ ለመድኃኒነ በከመ ወጽአት በትር እምሥርወ ዕሤይ በአምሳለ በትረ ያዕቆብ በዘይርዒ አባግዒሁ ይእቲኬ ማርያም ይእቲ ወበእንተ ዘይቤ ትወጽእ በትር ወየዓርግ ጽጌ ውእቱኬ ዋሕድ ውእቱ ውእቱኬ ወልደ አምላክ ውእቱ።

ምልጣን:-  ውእቱኬ ዋሕድ ውእቱ ውእቱኬ ወልደ አምላክ ውእቱ።

ትርጉም፦

ብዙ እረኞች መጡ ከጉድጓዱ አፍ ላይ የተገጠመችዋን ድንጋይ ለማንሳት አልቻሉም ሰው ይሆን ዘንድ ያለው በወገቡ ያለ ያዕቆብ እስኪመጣ ድረስ። እሱ ከፍቶ በጎቹን አጠጣ እንደዚሁ ብዙ ነቢያት መጡ ጥምቀትን መግለጥ አልቻሉም ዐቢይ ኖላዊ ከሰማይ እስኪመጣ ድረስ። እሱ ጥምቀትን ገለጠ በውስጧ ብዙ አሕዛብን አጠመቀ። የመድኃኒታችን ምልክቱ የሚያስደንቅ ነው ከዕሤይ ሥር በትር እንደወጣች፤ በጎቹን በሚጠብቅባት በያዕቆብ በትር አምሳል፤ ይህችውም ማርያም ናት በትር ትወጣለች አበባውም ከፍ ከፍ ይላል ማለቱ ወልድ ዋሕድ ነው። እርሱ የአምላክ ልጅ ነው።

፴፮.፪ የዕለቱ ምንባባት፦ 

ሮሜ ፱፥፩ – ፲፯፤

፩ጴጥ ፪፥፳ – ፍ፤

ግብ ፲፩፥፩ – ፲፬፤

ወንጌል፦ ዮሐ ፬፥፩ – ፳፯፤

ቅዳሴ፦ ዘእግዚእነ 

፴፮.፫ የዕለቱ ምስባክ፦

አግረረ ለነ አሕዛበ ወሕዝበ ታሕተ እገሪነ፤

ወኀረየነ ሎቱ ለርስቱ፤

ሥኖ ለያዕቆብ ዘአፍቀረ። መዝ፵፮፥፫

ትርጕም፦

አሕዛብን ከእኛ በታች ወገኖችንም ከእግራችን በታች አስገዛልን፤

ለርስቱ መረጠን፤

የያዕቆብን ውበት የወደደ እርሱ ነው።

ምሥጢር፦

አሥሩን ነገድ ሁለቱን ነገድ በእጃችን ጭብጥ በእግራችን እርግጥ አድርጎ አስገዛልን ይላሉ ነቢያት ካህናት።

አንድም ምእመናነ እስራኤልን ምእመናነ አሕዛብን በእጃችን ጭብጥ በእግራችን እርግጥ አድርጎ አስገዛልን ይላሉ ሐዋርያት።

ርስት ሊሆነን ርስቱ ኢየሩሴሌምን አንድም መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ መረጠን።

የያዕቆብን ምግባር ሃይማኖት የወደደ እሱ ነው። አንድም የወደደ እሱ ኀረየነ – መረጠን። አንድም የያዕቆብን ሥጋ ለመዋሐድ የወደደ እሱ ነው። የወደደ እሱ መረጠን። “ወሥኑሰ ለያዕቆብ ዘይቤ ይእቲ ሥጋ እንተ ነሥኣ መድኅን እማርያም – የያዕቆብ ውበት ያላት መድኅን ከእመቤታችን የነሣት ሥጋ ናት” እንዲል

የካቲት ፳፩ ተዝካረ በዓላ ለእግዝእትነ 

ዘነግህ ምስባክ፦ 

ወትቀውም ንግሥት በየማንከ፤ 

በአልባሰ ወርቅ ዑፅፍት ወኊብርት፤ 

ስምዒ ወለትየ ወርእዪ ወአጽምዒ ዕዝነኪ። 

ወንጌል፦ ሉቃ ፩፥፵፮ ߺ ፶፯፤

ዘቅዳሴ ምንባብ፦ 

ፊል ፩፥፲ ߺ ፍጻሜ፤

፩ጴጥ ፭፥፭ ߺ ፍጻሜ፤

ግብ ፲፫፥፩ ߺ ፯፤ 

ወንጌል፦ ሉቃ ፳፪፥፳፬ ߺ ፴፩፤

ቅዳሴ፦ ዘእግዝእትነ ማርያም 

ዘቅዳሴ ምስባክ፦ 

ኪያከ ተወከሉ ወኢተኀፍሩ፤ 

አንሰ ዕፄ ወአኮ ሰብእ፤ 

ምኑን በኀበ ሰብእ ወትሑት በውስተ ሕዝብ። መዝ ፳፩፥፭፤

ትርጒም፦ 

አንተን አመኑ አላፈሩም፤ 

እኔ ግን ትል ነኝ ሰው አይደለሁም፤ 

በሰው ዘንድ የተናቅሁ በሕዝብም ዘንድ የተዋረድሁ ነኝ። 

ምሥጢር፦ 

በአንተ አመኑ መከራ መጥቶባቸው አላፈሩም፤ 

እኔ ትል ነኝ ሰው አይደለሁም፤ ብዝኀ ትሕትና እንዲህ ያናግረዋል፤ ቦ አንተስ ብታምንብኝ እንደእነዚያ አድንህ አልነበረምን ትለኝ እንደሆነ እኔስ እንስሳ ነኝ ባለአእምሮ ሰው አይደለሁም፤ አእምሮ ቢኖረኝማ የጎልማሳ ሚስት በነሣሁ ጎልማሳ ባስገድልሁ ነበርን? ቦ እኔ በቃለ ገብርኤል የተወለድሁ ነኝ በልማደ ብእሲ ወብእሲት የተወለድሁ አይደለሁም፤ ቦ እኔ ወላፍ ትል ነኝ እሩቅ ብእሲ አይደለሁም፤ ወላፍ የሚባል ነጭ ትል አለ ዓሣ ይወደዋል መሠግራነ ዓሣ በመቃጥን አድርገው ከባሕር ይጥሉታል ዓሣው እሱን እይዛለሁ ሲል ራሱ ይያዛል፤ ጌታም በመልዕልተ መስቀል ኤሎሄ ኤሎሄ ሲል ሰምቶት እንደ እሩቅ ብእሲ ሊቆራኘው ቀረበ በእሳት ጃንጅር አስሮ በነፋስ አውታር ወጥሮ አስለፍልፎታል ረቂቅ ወዝ ወዝቷል ወልህበ ልህበተ ወተዐፅበ ዕፅበተ – መላብን ላበ መጨነቅን ተጨነቀ እንዲል፤ ቦ ንህብ ነኝ በዘርዐ ብእሲ የተፀነስሁ አይደለሁም፤ ንህብ የሚወለድ የንብ አውራ ሲጮህ በድምፅ ነው፤ ወተአነዝር እግዝእቶን ለአንህብት እንዲል፤ የጌታም ፅንስ በድምፀ ገብርኤል ነውና፤ ከመ ንህብ ዘእምቃል ንባብ – ከቃል ንግግር የተነሣ እንደንብ እንዲል፤ 

በነአቤሴሎም ዘንድ የተናቅሁ ነኝ በሠራዊቱም ዘንድ የተዋረድሁ ነኝ፤ ቦ በሐና በቀያፋ የተናቅሁ ነኝ በአይሁድም ዘንድ የተዋረድሁ ነኝ። 

የካቲት ፳፱ ተዝካረ ልደቱ ለእግዚእነ 

ዘነግህ ምስባክ፦

ወኢሰምዑኒ ሕዝብየ ቃልየ፤ 

ወእስራኤልኒ ኢያጽምዑኒ፤ 

ወፈነውኩ ሎሙ በከመ ምግባሮሙ። መዝ ፹፥፲፩፤

ትርጒም፦ 

ሕዝቤ ቃሌን አልሰሙኝም፤ 

እስራኤልም አላደመጡኝም፤ 

እንደ ሥራቸው ላክሁባቸው። 

ምሥጢር፦ 

ወገኖቼ ሁለቱ ነገድ ቃሌን አልሰሙም፤ 

ዐሥሩም ነገድ አላደመጡኝም፤ ቦ ሕዝብየ እስራኤል ኢሰምዑኒ ወኢያጽምዑኒ ቃልየ ብለህ አቅና፤ ወገኖቼ እስራኤል ምክሬን ትምህርቴን ፈጽመው አልተቀበሉኝም። 

እንደተናገሩ ይመልሱ እንደተለሙ ያርሱ እንዲሉ እንደ ሥራቸው መጠን ፍዳውን አመጣሁባቸው።

ወንጌል፦ ማቴ ፳፪፥፩ ߺ ፭፤

ዘቅዳሴ ምንባብ፦    

ሮሜ ፰፥፫ ߺ ፲፪፤

፩ዮሐ ፬፥፯ ߺ ፲፰፤

ግብ ፱፥፳ ߺ ፴፪፤

ወንጌል፦ ሉቃ ፪፥፩ ߺ ፳፩፤ 

ቅዳሴ፦ ዘእግዚእነ 

ዘቅዳሴ ምስባክ፦ 

እግዚአብሔር ይቤለኒ ወልድየ አንተ፤ 

ወአነ ዮም ወለድኩከ፤ 

ሰአል እምኔየ እሁበከ አሕዛበ ለርስትከ። ትርጒምና ምሥጢሩን መስከረም ፳፱ ላይ ተመልከት።