ጥር ፫ በዓለ ቅዱስ አቡነ ሊባኖስ
ዘነግህ ምስባክ፦
በርህ ሠረቀ ለጻድቃን፤
ወለርቱዐነ ልብ ትፍሥሕት፤
ይትፌሥሑ ጻድቃን በእግዚአብሔር። መዝ ፺፮፥፲፩፤
ትርጒም፦
ብርሃን ለጻድቃን ወጣ፤
ለልበ ቅኖችም ደስታ፤
ጻድቃን በእግዚአብሔር ደስ ይላቸዋል።
ምሥጢር፦
ለትሩፋን ሚጠት ተደረገላቸው፤ ቦ ለምእመናን ክርስቶስ ተወለደላቸው፤
ቅን ልቡና ትሑት ሰብእና ላላቸው ለትሩፋን ተድላ ደስታ ተደረገላቸው፤ ቦ ለምእመናን ልጅነት ተሰጣቸው፤
ትሩፋን ቦ በቁሙ ጻድቃን በእግዚአብሔር አምነው ደስ ይላቸዋል።
ወንጌል፦ ማቴ ፭፥፩ – ፲፯፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
ሮሜ ፲፩፥፳፭ – ፍጻሜ፤
፩ጴጥ ፪፥፩ – ፲፩፤
ግብ ፳፰፥፲፯ – ፍጻሜ፤
ወንጌል፦ ፪፥፲፫ – ፍጻሜ፤
ቅዳሴ፦ ዘእግዝእትነ ማርያም
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
እስመ በእንቲአሁ ይቀትሉነ ኵሎ አሚረ፤
ወኮነ ከመ አባግዕ ዘይጠብሑ፤
ንቃሕ እግዚኦ ለምንት ትነውም። ትርጒምና ምሥጢሩን ነሐሴ ፳፬ ላይ ተመልከት።
ጥር ፬ በዓለ ቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ
ዘነግህ ምስባክ፦
አልቦ ነገር ወአልቦ ነቢብ ዘኢተሰምዐ ቃሎሙ፤
ውስተ ኵሉ ወጽአ ነገሮሙ፤
ወእስከ አጽናፈ ዓለም በጽሐ ነቢቦሙ።
ወንጌል፦ ማቴ ፬፥፲፯ – ፍጻሜ፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
፩ጢሞ ፮፥፩ – ፲፩፤
፩ዮሐ ፩፥፩ – ፍጻሜ፤
ግብ ፬፥፰ ፳፬፤
ወንጌል፦ ፳፩፥፳ – ፍጻሜ፤
ቅዳሴ፦ ዘወልደ ነጐድጓድ
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
ወበኀቤየሰ ፈድፋደ ክቡራን አዕርክቲከ እግዚኦ፤
ወፈድፋደ ጸንዑ እምቀደምቶሙ፤
እኌልቆሙ እምኆፃ ይበዝኁ። መዝ ፻፴፰፥፲፯፤
ትርጒም፦
አቤቱ ወዳጆችህ በእኔ ዘንድ እጅግ የከበሩ ናቸው፤
ከቀደምቶቻቸውም እጅግ ጸኑ፤
እቈጥራቸዋለሁ ከአሸዋም ይልቅ ይበዛሉ።
ምሥጢር፦
በጠላቶቼ ዘንድ ነው እንጂ በእኔ ዘንድስ ወዳጆችህ ክቡራን ናቸው፤ ቦ ትሩፍ ይህ ሁሉ መከራ የመጣብህ ነቢያት ካህናትን እንጂ ባታከብር ነው ትለኝ እንደሆነ የሌላውን አላውቅም እንጂ በእኔ ዘንድስ ባለሟሎችህ ፈጽሞ ንዑዳን ክቡራን ናቸው፤
ከቀደሙት ከአኃው እንደ ዳንኤል አንበሳ ያሰገደ፣ እንደ ሠለስቱ ደቂቅ እሳት ያበረደ የለምና፤ ከቀደሙት የኋለኞቹ ጸኑ፤
እቈጥራቸዋለሁ ከአሸዋ ይበዛሉ ማለት ዐበይት ነቢያት ደቂቀ ነቢያት ሐዋርያት አርድእት ሊቃውንት መምህራን እስከ ዕለተ ምጽአት የሚነሡ ምእመናን እያለ ይሄዳልና።
፳፰ ንጉሥኪ ጽዮን
መዝሙር ንጉሥኪ ጽዮን ከጥር ፮ – ፲
፳፰.፩ (በ፪/ሩ) ንጉሥኪ ጽዮን ለትውልደ ትውልድ መጽአ ኀቤነ ዘኪያሁ ይሴፈዉ ሰማያት ወምድር ዕበይ ለነገሥት ብርሃኖሙ ለእለ ይጸመድዎ አክሊለ ሰማዕት ሠያሜ ካህናት ዓምዳ ወድዳ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን በቤተ ልሔም ተወልደ ወበናዝሬት ተሐፅነ ኢተዘኪሮ አበሳነ ኢኀደገነ ፍሥሐ ኮነ ዘውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ።
ምልጣን፦ ኢተዘኪሮ አበሳነ ኢኀደገነ ዘውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ።
ትርጉም፦
ጽዮን (ምእመን) ሆይ ሰማያትና ምድር (ሰዎችና መላእክት) ተስፋ የሚያደርጉት ንጉሥሽ ወደእኛ መጣ ለነገሥታት ክብራቸው ለሚያገለግሉት ብርሃናቸው ካህናትን የሚሾም እርሱ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን መሠረቷና ምሰሶዋ/ጉልላቷ ነው በቤተ ልሔም ተወለደ በናዝሬት አደገ በደላችንን ሳያስብ ሳይተወንም ደስታ ሆነ ይኸውም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
፳፰.፪ የዕለቱ ምንባባት፦
ሮሜ ፲፭፥፩ – ፲፬፤
፩ዮሐ ፬፥፲፬ – ፍ፤
ግብ ፲፫፥፴፪ – ፵፬፤
የዕለቱ ወንጌል፦ ማቴ ፪፥፲፱ – ፍ፤
ቅዳሴ፦ ዘዲዮስቆሮስ
፳፰.፫ የዕለቱ ምስባክ፦
ናሁ ሰማዕናሁ በኤፍራታ፤
ወረከብናሁ ውስተ ዖመ ገዳም፤
ንበውዕ እንከሰ ውስተ አብያቲሁ ለእግዚአብሔር። መዝ ፻፴፩፥፮
ትርጕም፦
እነሆ በኤፍራታ ሰማነው፤
ዛፍ በበዛበት ቦታ አገኘነው፤
እንግዲህስ ወደ እግዚአብሔር ማደሪያዎች እንገባለን።
ምሥጢር፦
ዳዊት በኤፍራታ ግብር/ሱባኤ ገባ ሲሉ ሰማን።
ዋዕየ ፀሐይ እንደዝናም በሚፈላበት/በሚወርድበት በረሃ ግብር/ሱባኤ ገብቶ አገኘው።
እንኪያስ ዳዊት ለእኛ ብሎ ግብር/ሱባኤ ከገባ እኛም ከፋርስ ከባቢሎን ወጥተን ወደኢየሩሳሌም እንመለሳለን።
አንድም ጌታችን በኤፍራታ ቤተ መቅደስ ትሠራለች ሲል ሰማነው (የቤተ መቅደስ ነገር የተገለጠው ለነቢዩ ናታን ቢሆንም ሱባኤ የገቡት አንድ ላይ ነውና ሰማዕናሁ አለ)
ሰባ ዘመን ምድረ በዳ ሆና በኖረች በኢየሩሳሌም ተሠርቶ አገኘነው።
እንኪያስ ከሰባ ዘመን በኋላ የእግዚአብሔር ማደሪያ ወደምትሆን ቤተ መቅደስ እንገባለን፤ ከሰባ ዘመን በኋላ የባቢሎንን ንጉሥ እበቀለዋለሁ ያለው አይቀርምና፤
አንድም በነቢያት አድሮ ከሰማያት እወርዳለሁ ከድንግል ማርያም እወለዳለሁ ሲል ሰማነው።
የሕዝቡን የአሕዛቡን ሥጋ ተዋሕዶ አገኘነው።
አንድም በኤፍራታ ተወልዶ በግዕዘ ሕፃናት ሲያለቅስ ሰማነው።
በጨርቅ ተጠቅልሎ በበረት ተጥሎ አገኘነው።
ከአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን በኋላ ወደመንግሥተ ሰማያት እንገባለን፤ በሐሙስ ዕለት እትወለድ እምወለትከ ያለው አይቀርምና፤
አንድም ምሳሌ ዘርዕን ሲያስተምር ሰማነው።
በገዳም ኅብስት አበርክቶ ሲመግብ አገኘነው።
አንድም ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን ወልደ እጓለ እመሕያው ክርስቶስን ይይዙታል ይሰቅሉታል በሦስተኛው ቀን ይነሣል ሲል ሰማነው።
በቀራንዮ በተተከለ መስቀል ተሰቅሎ አየነው።
ወደ ቤተ መቅደስ እንገባለን፤ ንግሥት ዕሌኒ መስቀሉን ካገኘች በኋላ ጌታችን ተአምራት ባደረገባቸው መካናት ሁሉ ቤተ መቅደስ አሠርታለችና።
ጥር ፮ በዓለ ግዝረቱ ለእግዚእነ
ዘነግህ ምስባክ፦
ወይከውን ቡሩከ ስሙ ለዓለም፤
እምቅድመ ፀሐይ ሀሎ ስሙ፤
ወይትባረኩ ቦቱ ኵሎሙ አሕዛበ ምድር። መዝ ፸፩፥፲፯፤
ትርጒም፦
ስሙ ለዘለዓለም ቡሩክ ነው፤
ከፀሐይ አስቀድሞ ስሙ ነበረ፤
የምድር አሕዛብ ሁሉ በእሱ ይባረካሉ።
ምሥጢር፦
የሰሎሞን ስሙ ይከብራል፤ ቦ የጌታ ስሙ ክቡር ምስጉን ነው፤
የሰሎሞን ስሙ ተወልዶ ፀሐይ ከማየቱ አስቀድሞ ነበረ፤ ተፀንሶ ሳለ ነቢዩ ስሙን ሰሎሞን በዪው ብሏታልና፤ ቦ የጌታ ስሙ ከፀሐይ አስቀድሞ ነበረ፤ “እምቅድመ ይትወለድ አብርሃም ሀሎኩ አነ” እንዳለው ያለ ነው፤
በዚህ ዓለም ያሉ አሕዛብ በሰሎሞን ይመራረቁበታል፤ ሰሎሞንን ያነገሠ ያንግሥህ ያከበረ ያክብርህ እየተባባሉ፤ ቦ ምእመናን በጌታችን ክብረ ሥጋ ክብረ ነፍስ ያገኛሉ።
ወንጌል፦ ሉቃ ፪፥፰ ߺ ፳፪፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
ሮሜ ፲፭፥፰ ߺ ፲፬፤
፪ጴጥ ፪፥፩ ߺ ፱፤
ግብ ፯፥፪ ߺ ፱፤
ወንጌል፦ ሉቃ ፬፥፳፬ ߺ ፴፫፤
ቅዳሴ፦ ዘዲዮስቆሮስ
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
ወገሠጸ ነገሥተ በእንቲአሆሙ፤
ኢትግሥሡ መሲሐንየ፤
ወኢታሕስሙ ዲበ ነቢያትየ።
ጥር ፯ በዓለ ቅድስት ሥላሴ
ዘነግህ ምስባክ፦
ሣህሉ ለእግዚአብሔር መልዐ ምድረ፤
ወበቃለ እግዚአብሔር ጸንዐ ሰማያት፤
ወእምእስትንፋሰ አፉሁ ኵሉ ኃይሎሙ። መዝ ፴፪፥፭፤
ትርጒም፦
የእግዚአብሔር ይቅርታው ምድርን መላ፤
በእግዚአብሔር ቃል ሰማዮች ጸኑ፤
ሠራዊታቸውም ሁሉ በአፉ እስትንፋስ።
ምሥጢር፦
የእግዚአብሔር ይቅርታው ዓለምን መላ ማለት ምድርንና በምድር ያለውን ፈጠረ፤ ቦ ደቂቀ አዳምን ፈጠረ፤
ሰባቱ ሰማያት ለይኵን ባለው ቃሉ ተፈጥረው ጸኑ፤ ቦ መላእክትን ፈጠረ፤
ከረቂቅ ሥልጣኑ የተነሣ ሰማይ ከነግሱ ምድር ከነልብሱ በእሱ ሥልጣን ተፈጥረው ጸኑ፤ ሦስት ጊዜ መላልሶ ተናገረ ለአጽንኦተ ነገር፤ ቦ ለአጠይቆ አካላት፤ ሣህሉ ለእግዚአብሔር ያለው እግዚአብሔር አብን፣ ወበቃለ እግዚአብሔር ያለው እግዚአብሔር ወልድን፣ ወእምእስትንፋሰ አፉሁ ያለው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን ነው።
ቦ ለእኔ ያደረገውን ይቅርታውን ለሌላውም አደረገው፤ ሁሉ ሰማው ሁሉ አወቀው ሲል እንዲህ አለ።
ወንጌል፦ ማቴ ፳፰፥፲፮ ߺ ፍጻሜ፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
ቈላ ፪፥፲ ߺ ፲፮፤
፩ዮሐ ፪፥፳፭ ߺ ፍጻሜ፤
ግብ ፳፪፥፯ ߺ ፳፪፤
ወንጌል፦ ማቴ ፪፥፳፩ ߺ ፍጻሜ፤
ቅዳሴ፦ ዘእግዚእነ አው ዘዲዮስቆሮስ
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
የሐዩ ወይሁብዎ እምወርቀ ዓረብ፤
ወዘልፈ ይጼልዩ በእንቲአሁ፤
ወኵሎ አሚረ ይድኅርዎ።
ጥር ፲፩ በዓለ ጥምቀት
ዘነግህ ምስባክ፦
ባሕርኒ ርእየት ወጐየት፤
ወዮርዳኖስኒ ገብአ ድኅሬሁ፤
አድባር አንፈርዐፁ ከመ ሐራጊት። መዝ ፻፲፫፥፫፤
ትርጒም፦
ባሕር አየች ሸሸችም፤
ዮርዳኖስም ወደኋላው ተመለሰ፤
ተራሮች እንደ ኮርማዎች ዘለሉ።
ምሥጢር፦
ባሕረ ኤርትራ እስራኤልን አይታ ሸሸች፤
ዮርዳኖስም ወደኋላው ተመለሰ፤ በኢያሱ ጊዜ ከላይ እስከ ቀልያተያርም ከታች እስከ ባሕረ ፄው ተከፍሎላቸው ተሻግረዋልና፤
ሙሴ አሮን እንደ ጊደር ዘለሉ፤ ተድላ ደስታውን መናገር ነው።
ቦ ባሕር ትሩፋንን አይታ ሸሸች፤ ትሩፋን ከባቢሎን በወጡ ጊዜ ሰባት ወንዝ ከፍሎ አሻግሯቸዋልና፤ “ወእሰጥቅ ሎሙ ሰብዓተ አፍላጋተ ከመ ይሑርዎን በአሣዕን ከመ አመ ወጽኡ እምግብፅ – ከግብጽ እንደወጡበት ጊዜ በጫማ ይሄዱባቸው ዘንድ ሰባት ወንዞችን እከፍልላቸዋለሁ” እንዲል፤
ዮርዳኖስም ወደኋላው ተመለሰ፤ ሐተታ ከቀደመው ይገባል
ቦ ባሕር ጌታችንን አይታ ሸሸች፤
ዮርዳኖስም ወደኋላው ተመለሰ፤ ጌታችን በተጠመቀ ጊዜ ዮርዳኖስ ወደኋላው ተመልሷልና፤ “ነድ ለማየ ባሕር ከበቦ ማይ ኀበ የሐውር ጸበቦ – እሳት የባሕሩን ውኃ ከበበው ውኃው የሚሄድበት ጠበበው” እንዲል፤
ወንጌል፦ ማቴ ፫፥፲፫ – ፍጻሜ፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
ቲቶ ፫፥፬ – ፰፤
፩ዮሐ ፭፥፭ – ፲፫፤
ግብ ፲፥፴፬ – ፴፱፤
ወንጌል፦ ሉቃ ፫፥፳፩ – ፍጻሜ፤
ቅዳሴ፦ ዘዲዮስቆሮስ
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
ርእዩከ ማያት እግዚኦ፤
ርእዩከ ማያት ወፈርሁ፤
ደንገጹ ቀላያተ ማያት ወደምፀ ማያቲሆሙ። መዝ ፸፮፥፲፮፤
ትርጉም፦
አቤቱ ውኆች አዩህ፤
ውኆች አይተው ፈሩ፤
የውኆች ጥልቆች ተነዋወጡ፤ ውኆቻቸውም ጮሁ።
ምሥጢር፦
ማያተ ኤርትራ ማያተ ዮርዳኖስ አዩህ፤
አይተውህ ፈሩ፤
ውኃነታቸውም ደፈረሰ፤ ይህም የተደረገውን ተአምር ለማስረዳት ነው።
የጥምቀት ሥርዐት አፈጻጸም፦
በፍትሕ መንፈሳዊ “ወበእንተ ዕለተ ልደትሰ ወጥምቀት በውእቱ ዘመን ዘተጋብኡ ጉባኤ በኒቅያ አዘዙ ከመ ይኩን ቊርባን ቦሙ በሌሊት – ስለ ልደትና ጥምቀት ግን በዚያ ዘመን በኒቅያ የተሰበሰቡ ሊቃውንት ቅዳሴው በሌሊት ይሆን ዘንድ አዘዙ” በተባለው መሠረት የልደት፣ የጥምቀትና የትንሣኤ ቅዳሴ መንፈቀ ሌሊት ነው፤ ፍ.ነ አንቀጽ ፲፥፭፻፺፭፤
የጥምቀቱ ከሁለቱ የሚለይበት መንገድ ከቅዳሴ በኋላ እንደገና ተመልሰን መጥተን አገልግሎቱ የሚቀጥል መሆኑ ነው፤ ከሌሊቱ አገልግሎት በኋላ የጥምቀትን ምሥጢርና ክብር የሚገልጡ ንባባት ይነበባሉ፤ ውዳሴ ማርያም፣ አንቀጸ ብርሃን፣ መልክአ ማርያም፣ መልክአ ኢየሱስ ይደገማል፤ ሥርዐተ ቅዳሴ ይደርሳል፤ የቅዱስ ጳውሎስ መልእክትና ግብረ ሐዋርያት ይነበባሉ።
ባሕርኒ የሚለው ምስባክ ተሰብኮ አራቱ ወንጌላት ይነበባሉ፤ ከዚያ የዘጠኙ ሊጦን ጸሎት ይቀጥላል፤ መስተብቊዕ በእንተ ሰላም ተብሎ በሰላም ይዘጋል። ከዚያ እግዚኦታ ደርሶ ዲያቆኑ ስግዱ ይላል ይ.ካ ፍትሐት ዘወልድ ይደግማል፤ አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ በአማን አብ ቅዱስ በአማን ወልድ ቅዱስ በአማን ውእቱ መንፈስ ቅዱስ የሚለው እስከ ፍጻሜው በዜማ ይባላል። ቀጥሎ የቅዱስ ያሬድ ድርሰት የሆኑት አርያምና አቡን ይከተላሉ። አሐዱ ከተባለ በኋላ ጸበል ወደ መርጨት ስለሚኬድና ግርግር ስለሚኖር ወንጌላቱ እንደተነበቡ ወደ አርያምና አቡን ይኬዳል።
ከጥምቀተ ባሕር ወደ ድንኳን በመመለስ ዮም ፍሥሐ ኮነ የሚለው ሰላም ተዘሞ እየተሸበሸበ ጉዞ ይጀመራል። በሰባት ምዕራፍ የተከፈለ ጉዞ ይደረጋል፤ ሰባተኛው ከቅጽረ ቤተ ክርስቲያን የሚደረገው ነው፤ ታቦታቱ ሲነሡ የተመራውና የተዘመመው ሰላም ስላልተጸፋ ዓራራይና ቅንዋት ተጸፍቶ በሰላም ይደመደማል። ቃለ ምዕዳን ተሰጥቶ የበዓሉ ፍጻሜ ይሆናል።
ጥር ፲፪ ቃና ዘገሊላ
ዘነግህ ምስባክ፦
እስመ መምህረ ሕግ ይሁብ በረከተ፤
ወየሐውር እምኃይል ውስተ ኃይል፤
ወያስተርኢ አምላከ አማልክት በጽዮን።
ወንጌል፦ ማቴ ፩፥፩ – ፲፪፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
ሮሜ ፱፥፩ – ፲፯፤
ይሁዳ ፩፥፱ – ፲፬፤
ግብ ፲፥፴፬ – ፴፱፤
ወንጌል፦ ዮሐ ፪፥፩ – ፲፩፤ አው ዮሐ ፩፥፵፬ – ፍጻሜ፤
ቅዳሴ፦ ዘኤጲፋንዮስ
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
ወምስካይነ አምላኩ ለያዕቆብ፤
ንዑ ትርአዩ ግብሮ ለእግዚአብሔር፤
ዘገብረ መንክረ በዲበ ምድር። መዝ ፵፭፥፯፤
ትርጒም፦
የያዕቆብ አምላክ መጠጊያችን ነው፤
የእግዚአብሔርን ሥራ ታዩ ዘንድ ኑ፤
በምድር ላይ ያደረገውን ድንቅ።
ምሥጢር፦
የያዕቆብ ፈጣሪ አንባ መጠጊያችን ነው፤ ቦ የያዕቆብ ፈጣሪ ከሥጋችን ሥጋ ከነፍሳችን ነፍስ ነሥቶ ሰው ሆነ፤
የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ ታዩ ዘንድ ኑ፤
በዚህ ዓለም የሠራውን ድንቅ ሥራ ቦ ምሥጢረ ሥጋዌውን ታዩ ዘንድ ኑ።
፳፱ ሖረ ኢየሱስ
መዝሙር ሖረ ኢየሱስ ከጥር ፲፪ – ፲፰
፳፱.፩ (በ፫/ሙ) ሖረ ኢየሱስ በትፍሥሕት ውስተ ከብካብ እንዘ ይገብር ተአምረ ወመንክረ በውስተ አሕዛብ (ሖ) አርአዮሙ ስብሐቲሁ አምኑ ቦቱ አርዳኢሁ (ሖ) ወይቤሎሙ ቅድሑ ማየ ወምልዕዎን ለመሳብክት እስከ አፉሆን (ሖ) ጥዒሞ አንከረ ሊቀ ምርፋቅ በረከተ ዘአምላክ ገብረ (ሖ) ቤዛነ ተስፋነ ወልደ አምላክ ወለማይኒ ረሰዮ ወይነ።
ትርጕም፦
ኢየሱስ በአሕዛብ ውስጥ ድንቅ የሆነ ተአምር እያደረገ በደስታ ወደሠርግ ሄደ ጌትነቱን ገለጠላቸው ደቀመዛሙርቱም አመኑበት ውኃ ቀድታችሁ ጋኖቹን እስከአፋቸው ምሏቸው አላቸው አሳዳሪው አምላክ ያደረገውን በረከት ቀምሶ አደነቀ ወልደ አምላክ ቤዛችን ተስፋችን ነው ውኃውን ወይን አደረገው።
፳፱.፪ የዕለቱ ምንባባት፦
ዕብ ፪፥፩ – ፲፪፤
፩ዮሐ ፭፥፩ – ፲፫፤
ግብ ፲፥፴፬ – ፴፱፤
ወንጌል፦ ዮሐ ፪፥፩ – ፲፬
ቅዳሴ፦ ዘዲዮስቆሮስ
፳፱.፫ የዕለቱ ምስባክ፦
እስመ መምህረ ሕግ ይሁብ በረከተ፤
ወየሐውር እምኃይል ውስተ ኃይል፤
ወያስተርኢ አምላከ አማልክት በጽዮን። መዝ ፹፫፥፮
ትርጕም፦
የሕግ መምህር በረከትን ይሰጣልና፤
ከኃይል ወደኃይል ይሄዳል፤
የአማልክት አምላክ በጽዮን ይታያል።
ምሥጢር፦
ዘሩባቤል መምህረ ሕግ ነውና በረከትን ይሰጣል። አንድም መምህረ ሕግ ዘሩባቤል በረከትን ይሰጣል፤ ይሰጣልና ከኃይል ወደኃይል ይሄዳል፤ ይሄዳልና የካህናት ፈጣሪ በሰባ ዘመን ሚጠተ ሥጋውን በማድረግ ይገለጣል።
አንድም ሊቀ ጳጳሳት መምህረ ሕግ ነውና በረከትን ይሰጣል፤ አንድም መምህረ ሕግ ሊቀ ጳጳሳት በረከትን ይሰጣል፤ ይሰጣልና ከእውቀት ወደእውቀት ይሄዳል፤ ይሄዳልና የካህናት ፈጣሪ በአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን በማኅፀነ ማርያም በልብሰተ ሥጋ ይገለጣል።
ጥር ዐሥራ ሦስት በዓለ እግዚአብሔር
ዘነግህ ምስባክ፦
መኑ አምላክ ዐቢይ ከመ አምላክነ፤
አንተ እግዚአብሔር ባሕቲትከ ዘትገብር መንክረ፤
አርአይኮሙ ለሕዝብከ ኃይለከ። መዝ ፸፮፥፲፫፤
ትርጒም፦
እንደ አምላካችን ያለ ታላቅ አምላክ ማነው?
ድንቅ ተአምራትን የምታደርግ አምላክ አንተ ብቻ ነህ፤
ለሕዝብህ ኃይልህን አሳየሃቸው።
ምሥጢር፦
እንደ ፈጣሪያችን ያለ ገናና ፈጣሪ ማነው ማን አለ? ማዳን መታደግ የሚቻለው?
ድንቅ ሥራ የምትሠራ አንተ ብቻ ነህ፤
ለወገኖችህ ለትሩፋን ኃይልህን ከሃሊነትህን ገለጥህላቸው አለ ኃይል አደርግህላቸው።
ወንጌል፦ ዮሐ ፬፥፵፫ – ፵፯፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
፩ቆሮ ፲፥፩ – ፲፬፤
፩ጴጥ ፩፥፲ – ፳፪፤
ግብ ፪፥፳፪ – ፴፫፤
ቅዳሴ ዘኤጲፋንዮስ
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
ነጽረኒ ወስምዐኒ እግዚኦ አምላኪየ፤
አብርሆን ለአዕይንትየ ከመ ኢይኑማ ለመዊት፤
ወከመ ኢይበሉኒ ጸላእትየ ሞዕናሁ። መዝ ፲፪፥፫፤
ትርጒም፦
አቤቱ አምላኬ ተመልከተኝ ስማኝም፤
ለሞት እንዳያንቀላፉ ዐይኖቼን አብራቸው፤
ጠላቶቼ አሸነፍነው እንዳይሉ።
ምሥጢር፦
አቤቱ በዐይነ ምሕረት ተመልክተህ ልመናዬን ስማኝ፤ ልመናዬን ሰምተህ በዐይነ ምሕረት ተመልከተኝ፤
የሞት እንቅልፍ እንዳያንቀላፉ ዐይኖቼን አብራቸው፤ አሁን ለዘለዓለም አኑረኝ ማለት አይደለም ዕድሜ ሰጥተህ ለንስሐ ሞት አብቃኝ ማለት ነው እንጂ፤
ጠላቶቼ ድል ነሣነው እንዳይሉ፤ ቦ ተኝቶ አግኝተነው ድል ነሣነው እንዳይሉ።
ጥር ፲፭ በዓለ ቅዱስ ቂርቆስ ወቅድስት ኢየሉጣ
ዘነግህ ምስባክ፦
ወሥጋሆሙኒ ለጻድቃኒከ ለአራዊተ ገዳም፤
ወከዐዉ ደሞሙ ከመ ማይ ዐውዳ ለኢየሩሳሌም፤
ወኃጥኡ ዘይቀብሮሙ። መዝ ፸፰፥፪፤
ትርጒም፦
የጻድቃንህ ሥጋ ለምድር አራዊት ምግብ ሆነ፤
ደማቸውንም በኢየሩሳሌም ዙሪያ እንደ ውኃ አፈሰሱ፤
የሚቀብራቸውም አጡ።
ምሥጢር፦
የወዳጆችህን ሬሳ ቀን ለአዕዋፍ ሌሊት ለአራዊት ምግብ አደረጉ፤
ደማቸውንም በኢየሩሳሌም እንደ ውኃ አፈሰሱ፤
አጥቦ ገንዞ አጥፎ አጎናጥፎ የሚቀብራቸው አጡ፤ ርስቱ የመቃብያን ነው ያሉ እንደሆነ ዐሥራ አራት ዕልፍ ሰው ተቀብሮ አያልቅምና፤ ርስቱ የመቃቢስ ዘሞዓብ ልጆች ነው ያሉ እንደሆነ የሚቀብራቸው አጥተው ዐሥራ አራት ቀን በአደባባይ ሰንብተዋልና፤ ርስቱ የመቃቢስ ዘብንያም ልጆች ናቸው ያሉ እንደሆነ ጌታ በኅሱር እጅ አይቀበሩ ሲል ሠውሯቸዋልና።
ወንጌል፦ ዮሐ ፲፮፥፩ – ፭፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
ዕብ ፲፪፥፩ – ፲፩፤
፩ጴጥ ፬፥፲፩ – ፲፭፤
ግብ ፲፮፥፲፬ – ፲፱፤
ወንጌል፦ ማቴ ፲፰፥፩ – ፲፪፤
ቅዳሴ፦ ዘዲዮስቆሮስ
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
አኅለፍከነ ማዕከለ እሳት ወማይ፤
ወአውጻእከነ ውስተ ዕረፍት፤
እበውእ ቤተ ምስለ መባዕየ። መዝ ፷፭፥፲፪፤
ትርጒም፦
በእሳትና በውኃ መካከል አሳለፍኸን፤
ወደ ዕረፍትም አወጣኸን፤
መባዬን ይዜ ወደቤትህ እገባለሁ።
ምሥጢር፦
በእሳትና በውኃ መካከል አሳለፍኸን፤ በግብፅ ዝናም አይዘንምም ለሐድሶተ ንስር ያህል በአምስት በአምስት መቶ ዘመን ያካፋል እንጂ፤ ያን ጊዜ ቀን ገጥሞት እሳትና በረድ እንደሰምና ፈትል ተጣምቶ ወርዷል፤ “የእንጦጦ መምር አይናገር፣ ቢናገር በዓመት ያውም ሬት” እንዲሉ፤
ከኤርትራ ወደምድረ በዳ አወጣኸን።
ቦ በእሳትና በውኃ መካከል አሳለፍኸን ይላሉ ሠለስቱ ደቂቅ፤ እሳት አለው በቀደመ ግብሩ፤ ውኃ አለው በኋላ ግብሩ፤ ቦ በእሳትና በውኃ መካከል አሳለፍኸን፤ እሳት ያለው የባቢሎንን ጦር ነው፤ ውኃ ማለቱ ከባቢሎን ሲወጡ ሰባት ወንዝ ተከፍሎላቸዋልና፤
ከፋርስ ከባቢሎን ዕረፍት ወደአለባት ወደ ኢየሩሳሌም አወጣኸን።
ቦ በሲኦልና በገሃነም መካከል አሳልፍኸን፤ ቦ ጥምቀትን ልጅነትን ሰጠኸን፤
ዕረፍተ ነፍስ ወዳለባት ወደ መንግሥተ ሰማያት አገባኸን፤
ከሁለት መቶ ዐሥራ አምስት ዓመት በኋላ ቦ ከሰባ ዘመነ በኋላ ቦ ከአምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመት በኋላ መባዬን ይዤ ማደሪያህ ወደምትሆን ወደቤተ መቅደስህ እገባለሁ።
ጥር ፲፰ ዝርወተ ዐፅሙ ለቅዱስ ጊዮርጊስ
ዘነግህ ምስባክ፦
እስመ ኀልቀ ከመ ጢስ መዋዕልየ፤
ወነቅፃ ከመ ሣዕር አዕፅምትየ፤
ተቀሠፍኩ ወይብሰ ከመ ሣዕር ልብየ። መዝ ፻፩፥፫፤
ትርጒም፦
ዘመኔ እንደ ጢስ አልቋልና፤
አጥንቶቼም እንደ ሣር ደርቀዋልና፤
ተቀሠፍሁ ልቤ እንደ ሣር ደረቀ።
ምሥጢር፦
ጢስ በኖ እንዲጠፋ ዘመኔ በመከራ ጠፋ ማለት በመከራ ተፈጸመ፤
ሰውነቴ እንደ ሣር ደረቀ፤
ሰባ ዘመን በሠውጠ መከራ ተገረፍሁ ልቡናዬም እንደ ሣር ደረቀ ማለት አእምሮ ተለየኝ፤
ወንጌል፦ ዮሐ ፲፩፥፲፱ – ፴፫፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
ሮሜ ፰፥፴፭ – ፍጻሜ፤
፩ጴጥ ፫፥፩ – ፯፤
ግብ ፲፯፥፴ – ፍጻሜ፤
ወንጌል፦ ማቴ ፭፥፵፪ – ፍጻሜ፤
ቅዳሴ፦ ዘወልደ ነጐድጓድ
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
ወእምኵሉ ያድኅኖሙ እግዚአብሔር፤
እግዚአብሔር የዐቅብ ኵሎ አዕፅምቲሆሙ፤
ወኢይትቀጠቀጥ አሐዱ እምውስቴቶሙ። መዝ ፴፫፥፲፱፤
ትርጒም፦
እግዚአብሔር ከሁሉ ያድናቸዋል፤
እግዚአብሔር አጥንቶቻቸውን ሁሉ ይጠብቃል፤
ከእነርሱ አንዱም አይሰበርም።
ምሥጢር፦
እግዚአብሔር ከመከራው ሁሉ ያድናቸዋል፤
ሰውነታቸውን ቦ ወገናቸውን ከመከራ ይጠብቀዋል፤
ከእነሱ አንዱ ስንኳ አይጠፋም፤ ቦ ከዐፅማቸው አንድ ስንኳ አይጠፋም፤ ዐፅመ ኤልሳዕን እንደ ጠበቀ ይጠብቃቸዋልና፤ የሰማርያ ሰዎች ሲዋጉ ከእስራኤል አንዱ ተወግቶ ከኤልሳዕ መቃብር ወደቀ ዐፅሙ ቢነካው ተነሣ፤ ቦ የሶርያ ሰዎች በጠላትነት ተነሡባቸው እስራኤል ለመዋጋት ሲሄዱ አንድ ሰው ሞተባቸው ለመቅበር የማያደርሷቸው ቢሆን እንዲገራቸው ከኤልሳዕ መቃብር ጭረው ቀበሩት አፈፍ ብሎ ተነሥቶ መግነዙን አጠርቅሞ/አገልድሞ በሰይፍ ሲገርፍ ውሏል፤ ቅዱስ ጊዮርጊስንም ሦስት ጊዜ ሞቶ ተነሣ ይለዋልና።
፴ እሙነ ኮነ ልደቱ
መዝሙር እሙነ ኮነ ልደቱ ከጥር ፲፱ – ፳፭
፴.፩ (በ፮/ፋኝ) እሙነ ኮነ ልደቱ እሙነ ኮነ ልደቱ ለመድኃኒነ ክርስቶስ (እ) እምሰማያት ወረደ ወእመላእክት ተአኵተ ወእማርያም ተወልደ (እ) በቤተ ልሔም ተወልደ ወበናዝሬት ተሐፅነ ወአስተርአየ ገሃደ (እ) ውእቱ አክሊለ ሰማዕት ውእቱ መድኃኔ ነገሥት ኖላዊሆሙ ለአሕዛብ እሙነ ኮነ ልደቱ ብርሃነ ኮነ ምጽአቱ ለመድኃኒነ ክርስቶስ።
ትርጉም፦
የመድኃኒታችን ክርስቶስ ልደቱ የታመነ ሆነ ከሰማያት ወረደ ከድንግል ተወለደ በመላእክት ዘንድ ተመሰገነ በቤተ ልሔም ተወለደ በናዝሬት አደገ በግልጽ ታየ እርሱ የሰማዕታት አክሊል የነገሥታት መድኃኒት/ኃይል የአሕዛብ ጠባቂ ነው የመድኃኒታችን ልደቱ እሙን አመጣጡም ብርሃን ነው።
፴.፪ የዕለቱ ምንባባት፦
፪ቆሮ ፩፥፲፫ – ፍጻሜ፤
፩ዮሐ ፪፥፳፪ – ፍጻሜ፤
ግብ ፲፫፥፳ – ፳፰፤
ወንጌል፦ ሉቃ ፪፥፵፪ – ፍጻሜ፤
ቅዳሴ፦ ዘዲዮስቆሮስ
፴.፫ የዕለቱ ምስባክ፦
እግዚአብሔር እግዚእ አስተርአየ ለነ፤
ግበሩ በዓለ በትፍሥሕት በኀበ እለ ያስተሐምምዎ፤
እስከ አቅርንቲሁ ለምሥዋዕ። መዝ ፳፲፯፥፳፯
ትርጕም፦
ጌታ እግዚአብሔር ተገለጠልን፤
በሚያስተነትኑበት በደስታ በዓልን አድርጉ፤
እስከመሠዊያው ቀንድ ድረስ።
ምሥጢር፦
በምልዓት ያለ እግዚአብሔር በረድኤት ተገለጠ አንድም በሥጋ ማርያም ተገለጠ፤
ለእሱ ከሚያስተነትኑ በሱ ስም ከሚያስተምሩ ከነቢያት ከካህናት አብነት ነሥታችሁ የብሉዩን በዓል አክብሩ፤
አንድም ከሐዋርያት አብነት ነሥታችሁ የሐዲሱን በዓል አክብሩ።
አንድም ከሰማዕታት አብነት ነሥታችሁ መከራ ተቀበሉ። አንድም ምግባር ሠርታችሁ ዕረፍተ ነፍስ አግኙ።
አቅርንተ ምሥዋዑን ስብ እስከመምላት ደርሳችሁ። አንድም አቅርንተ ምሥዋዑን እስከመያዝ ደርሳችሁ። አዶንያስ የመሠዊያውን ቀንድ ይዞ እንደተማፀነ ፩ነገ፩፥፶፤
አንድም ቤተ ክርስቲያንን እስከመሙላት ደርሳችሁ። አንድም መስቀል ቀኖት እስከመቀበል ደርሳችሁ በዓልን አድርጉ።
ጥር ፳፩ በዓለ ዕረፍታ ለእግዝእትነ ማርያም
ዘነግህ ምስባክ፦
ትሴብሖ ኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር፤
ወሰብሒዮ ለአምላክኪ ጽዮን፤
እስመ አጽንዐ መናሥግተ ኆኃትኪ።
ወንጌል፦ ዮሐ ፪፥፳፩ – ፍጻሜ፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
ገላ ፬፥፩ – ፲፪፤
፪ዮሐ ፩፥፩ – ፯፤
ግብ ፯፥፴ – ፴፭፤
ወንጌል፦ ሉቃ ፩፥፵፮ – ፶፮፤
ቅዳሴ፦ ዘእግዝእትነ ማርያም
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
በከመ ሰማዕነ ከማሁ ርኢነ፤
በሀገረ እግዚአ ኃያላን በሀገረ አምላክነ፤
እግዚአብሔር ሣረራ ለዓለም።
፴፩ በጽሐ ዕለተ ወሊዶታ
ለእመ ኮነ በዓለ ማርያም በዕለተ እሑድ አመ ፳ወ፩ ለጥር
፴፩.፩ (በ፱/ሮ) በጽሐ ዕለተ ወሊዶታ ወወለደት ወልደ ዘበኵራ አስከበቶ እሙ ውስተ ጎለ ዕብን ለሕፃን እስመ አልቦሙ መካን ውስተ ማኅደሮሙ (በ) ወሀለዉ ኖሎት ውስተ ውእቱ መካን ይተግሁ ወይሄልዉ ወየዓቅቡ መራዕይሆሙ ወስብሐተ እግዚአብሔር ሠረቀ ላዕሌሆሙ ወይቤሎሙ መልአክ ኢትፍርሁ እዜንወክሙ ዐቢየ ፍሥሐ ዘይከውን ለክሙ (በ) እስመ ተወልደ ለክሙ ዮም መድኅን ዘውእቱ እግዚእ በሀገረ ዳዊት (በ) ወይቤሉ እሙንቱ ሰብእ ኖሎት ናንሶሱ ወንብጻሕ እስከ ቤተ ልሔም በጽሐ ዕለተ ወሊዶታ ወወለደት ወልደ ዘበኵራ መንጦላዕተ ደመና ሠወራ።
ምልጣን፦ ወበጽሐ ዕለተ ወሊዶታ ወወለደት ወልደ ዘበኵራ መንጦላዕተ ደመና ሠወራ።
ትርጕም፦
የምትወልድበት ቀን ደረሰ የበኵር ልጇን ወለደች እናቱ ሕፃኑን በበረት ውስጥ አስተኛችው ለማደሪያ ስፍራ አልነበራቸውምና በዚያ ስፍራ እረኞች ተግተው መንጋቸውን ይጠብቁ ነበር የእግዚአብሔር ክብር በነሱ ላይ ተገለጠ መልአኩም አትፍሩ አላቸው የሚሆንላችሁን ደገኛ ደስታ እነግራችኋለሁ ዛሬ መድኅን እርሱም ጌታ በዳዊት ሀገር ተወልዶላችኋልና እነዚያ እረኞች እንመላለስ እስከ ቤተ ልሔም ድረስ እንሂድ አሉ የምትወልደበት ቀን ደረሰ የበኵር ልጇን ወለደች የደመና መጋረጃ ሠወራት።
፴፩.፪ የዕለቱ ምንባባት፦
ገላ ፬፥፩ – ፲፪፤
፪ዮሐ ፩፥፩ – ፯፤
ግብ ፯፥፴ – ፴፭፤
ወንጌል፦ ሉቃ ፪፥፮ – ፳፤
ቅዳሴ፦ ዘእግዝእትነ ማርያም
ምስባክ፦ በከመ ሰማዕነ ከማሁ ርኢነ፤
በሀገረ እግዚአ ኃያላን በሀገረ አምላክነ፤
እግዚአብሔር ሣረራ ለዓለም።
፴፪ ተወልደ ኢየሱስ
መዝሙር ተወልደ ኢየሱስ ከጥር ፳፮ – የካቲት ፪
፴፪.፩ (በ፪/ል) ተወልደ ኢየሱስ በቤተ ልሔም ዘይሁዳ ተወልደ ኢየሱስ በተድላ መለኮት ተወልደ ተወልደ ተወልደ ተጠምቀ ወሠርዐ ሰንበተ ለዕረፍት ከመ ንትፈሣሕ በልደቱ ወንትሐሠይ በአስተርእዮቱ ዘከመዝኬ ልደቱ ለክርስቶስ እምድንግል።
ትርጕም፦
ኢየሱስ በቤተ ልሔም ዘይሁዳ ተወለደ በአምላክነቱ ሥልጣን ተወለደ ተወለደ ተጠመቀ ለዕረፍት ሰንበትን ሠራ በልደቱ ደስ እንሰኝ ዘንድ በመገለጡ እንከብር ዘንድ። የክርስቶስ ከድንግል መወለዱ እንደዚህ ነው።
፴፪.፪ የዕለቱ ምንባባት፦
ሮሜ ፩፥፩ – ፲፪፤
፩ጴጥ ፩፥፲፫ – ፳፪፤
ግብ ፲፱፥፩ – ፲፩፤
ወንጌል፦ ሉቃ ፪፥፴፮ – ፍ፤
ቅዳሴ፦ ዘዲዮስቆሮስ
፴፪.፫ የዕለቱ ምስባክ፦
በከመ ሰማዕነ ከማሁ ርኢነ፤
በሀገረ እግዚአ ኃያላን በሀገረ አምላክነ፤
እግዚአብሔር ሣረራ ለዓለም። መዝ ፵፯፥፰
ትርጕም፦
እንደሰማን እንዲሁ አየን፤
በሠራዊት ጌታ ከተማ በአምላካችን ሀገር፤
እግዚአብሔር ለዓለም አጸናት።
ምሥጢር፦
እነሰናክሬም መጡ ሲባል እንደሰማን መጥተው በለኪሶን ሰፍረው አየን፤
አንድም መሞታቸውን ከነቢያት ቃል እንደሰማን ሞተው አየን፤
አንድም በከመ ርኢነ ሰማዕነ ይላል የሠራዊቱን ሞት እንዳየን የንጉሡን ሞት ሰማን፤ ሰናክሬም የሞተው ወደሀገሩ ተመልሶ በራሱ ልጆች በዘነዘና ተወግሮ ነውና፤
አንድም ነቢያት ክርስቶስ ይወርዳል ይወለዳል ሲሉ እንደሰማን ከእመቤታችን ተወልዶ አየነው፤
አንድም እነሆ ወደኢየሩሳሌም እንወጣለን የሰውን ልጅ ይይዙታል ይሰቅሉታል በሦስተኛው ቀን ይነሣል ሲል እንደሰማነው በመስቀል ተሰቅሎ ሞቶ ተነሥቶ አየነው።
እግዚአብሔር ቤተ እስራኤልን በረድኤት አጸናት። አንድም እመቤታችን እንድትችለው አደረጋት/አጸናት።
ሰማይና ምድር የማይወስኑትን እሷ ወስናዋለችና። መተርጒማን ለመወሰንማ ሰማይና ምድርስ ወስነውት የለምን ብለው ጠይቀው “ሰማይና ምድር ቢወስኑት እመቤታችንን ምክንያት አድርገው ነው እሷ ግን የወሰነችው በባሕርይዋ ነው” በማለት ልዩነቱን አስረድተዋል።
፴፫ ኢየሩሳሌም ትቤ
መዝሙር ኢየሩሳሌም ትቤ ከጥር ፳፱ – የካቲት ፭
፴፫.፩ (በ፫/ደ) ሃሌ ሉያ ሃሌ ሃሌ ሉያ ኢየሩሳሌም ትቤ ተወልደ ንጉሥየ ወአምላኪየ (ኢ) በቤተ ልሔም ተወልደ በተድላ መለኮት (ኢ) አክሊለ ሰማዕት ሠያሜ ካህናት (ኢ) ዘይሴብሕዎ ሐራ ሰማይ በማኅበረ ቅዱሳን (ኢ) አጥመቆ ዮሐንስ ለኢየሱስ በፈለገ ዮርዳኖስ ኢየሩሳሌም ትቤ ኢየሩሳሌም አእኰተቶ።
ትርጕም፦
ኢየሩሳሌም ንጉሤ አምላኬ ተወለደ አለች በአምላክነቱ ሥልጣን በቤተ ልሔም ተወለደ የሰማዕታት አክሊል ካህናትን የሚሾም እርሱ ነው የሰማይ ሠራዊት በቅዱሳን ኅብረት የሚያመሰግኑት እርሱ ነው ዮሐንስ ኢየሱስን በዮርዳኖስ ወንዝ አጠመቀው ኢየሩሳሌም አለች ኢየሩሳሌም አመሰገነችው።
፴፫.፪ የዕለቱ ምንባባት፦
ገላ ፬፥፳፩ – ፍ፤
፩ጴጥ ፪፥፩ – ፱፤
ግብ ፭፥፲፯ – ፳፱፤
ወንጌል፦ ሉቃ ፪፥፵፪ – ፍ፤
ቅዳሴ፦ ዘዲዮስቆሮስ
፴፫.፫ የዕለቱ ምስባክ፦
ትሴብሖ ኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር፤
ወሰብሒዮ ለአምላክኪ ጽዮን፤
እስመ አጽንዐ መናሥግተ ኆኃትኪ። መዝ ፻፵፯፥፩
ትርጕም፦
ኢየሩሳሌም እግዚአብሔርን ታመስግናለች፤
ጽዮን ሆይ አምላክሽን አመስግኚ፤
የደጆችሽን መወርወሪያ አጽንቷልና።
ምሥጢር፦
በኢየሩሳሌም ገጠር ያሉ ሰዎች እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤
በከተማ ያሉ ሰዎች ፈጣሪያችን እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤
ኃያላንኪ ሲል ነው የኃያላንሽን/የአርበኞችሽን ሥልጣን በረድኤት አጽንቷልና፤ ውስጠ ምሥጢሩ በሲኦል በሥቃይ የነበሩትና በሲኦል ውስጥ ሆነው ነገር ግን እደ እግዚአብሔር እንደ ድንኳን ሆናላቸው ከሥቃይ ተጠብቀው ይኖሩ የነበሩ ደጋግ አበው በአንድነት በተስፋ የጌታችንን ከእመቤታችን መወለድ ሲጠባበቁ መኖራቸውን ያስረዳል። ዛሬም ባለው የየዕለት እንቅስቃሴያችን ተነሳሒ ኃጥእና ሥርየት ያገኘ ተነሳሒ በንስሐ ሕይወት ውስጥ እየተመላለሱ እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑ መሆናቸውን ያስረዳል።
ጥር ፳፱ ተዝካረ ልደቱ ለእግዚእነ
ዘነግህ ምስባክ፦
ምስሌከ ቀዳማዊ በዕለተ ኃይል፤
በብርሃኖሙ ለቅዱሳን፤
ወለድኩከ እምከርሥ እምቅድመ ኮከበ ጽባሕ።
ወንጌል፦ ሉቃ ፲፪፥፲፮ ߺ ፵፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
፩ጢሞ ፫፥፲፬ ߺ ፍጻሜ፤
፩ዮሐ ፩፥፱ ߺ ፍጻሜ፤
ግብ ፫፥፲፪ ߺ ፲፯፤
ወንጌል፦ ዮሐ ፩፥፯ ߺ ፲፭፤
ቅዳሴ፦ ዘእግዝእትነ ማርያም
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
እስመ ፈላሲ አነ ውስተ ምድር፤
ወነግድ ከመ ኵሉ አበውየ፤
ስሕተኒ ከመ አዕርፍ። መዝ ፴፰፥፲፪፤
ትርጒም፦
እኔ በምድር ላይ መጻተኛ ነኝና፤
እንደ አባቶቼም ሁሉ እንግዳ ነኝና፤
አርፍ ዘንድ ተወኝ።
ምሥጢር፦
በዚህ ዓለም መጻተኛ ነኝና፤
እንደ አባቶቼ እንደ አብርሃም ይስሐቅ ያዕቆብ አድሮ ሂያጅ ነኝና፤ ከጌራራ ወደፍልስጥኤም ከፍልስጥኤም ወደጌራራ ሲመላለሱ እንደነበር፤
አርፍ ዘንድ መንግሥተ ሰማያትን ሰጥተህ አሳርፈኝ፤ ቦ በሞት ከመከራው አሳርፈኝ፤ ጸጋ ክብር ሀብት ሥርየት ሰጥተህ ከፍዳ አሳርፈኝ።

