፱ መዝሙር ኪነ ጥበቡ
ከጥቅምት ፫ – ፱
፱.፩ (በ፫/የ) ኪነ ጥበቡ መንክር ወዕፁብ ኪነ ጥበቡ መንክር ወዕፁብ ለዘሀሎ መልዕልተ አርያም አርአየ ምሕረቶ በላዕሌነ ዘከለሎ ለሰማይ በከዋክብት ብሩህ (አ) ወለምድርኒ አሠርገዋ በጽጌያት ንጹሕ (አ) ወሠርዐ ሰንበተ ለነባሪ ያዕርፉ ባቲ (አ) መዓዛሆሙ ለቅዱሳን ከመ ጽጌ ደንጐላት ዘውስተ ቈላት ጸገዩ ቀንሞስ ምስለ ናርዶስ።
ትርጕም፦
በአርያም ከፍታ የሚኖር እግዚአብሔር የጥበቡ ብልሃት ዕፁብ ድንቅ ነው ምሕረቱን በእኛ ላይ አሳየ ሰማይን በብሩሃን ከዋክብት የጋረደ እሱ ምሕረቱን በእኛ ላይ አሳየ አገልጋዮች ያርፉባት ዘንድ ሰንበትን ሠራ የቅዱሳን መዓዛ በምድረ በዳ እንዳለ የሱፍ አበባ ነው ቀንሞስ ከናርዶስ ጋር አበቡ።
፱.፪ የዕለቱ ምንባባት፦
ኤፌ ፮፥፩ – ፲፤
ራእይ ፲፪፥፩ – ፲፫፤
ግብ ፯፥፳፫ – ፴፤
ወንጌል፦ ሉቃ ፲፪፥፲፮ – ፴፪
ቅዳሴ፦ ዘእግዝእትነ ማርያም
፱.፫ የዕለቱ ምስባክ፦
ተዘከር እግዚኦ ከመ መሬት ንሕነ፤
ወሰብእሰ ከመ ሣዕር መዋዕሊሁ፤
ወከመ ጽጌ ገዳም ከማሁ ይፈሪ። መዝ ፻፪፥፲፬
ትርጕም፦
አቤቱ እኛ አፈር እንደሆንን አስብ፤
ሰውስ ዘመኑ እንደ ሣር ነው፤
እንደ ዱር አበባ እንዲሁ ያፈራል።
ምሥጢር፦
አቤቱ እኛ ፈራሽ በስባሽ አቅም የለሽ እንደሆንን አስብ አስበህ ዝም አትበለን የተጫነንን የኃጢአት የባርነት ቀንበር በራሳችን መስበርና ማስወገድ አይቻለንምና አቤቱ ከወደቅንበት አንሣን፤
የሰው ዘመኑ እንደ ሣር ነው ማለት ያ ፈጥኖ ደርቆ እንደሚጠፋ ፈጥኖ ያልፋል ይጠፋል ሲል ነው፤
እንደ ዱር አበባ ያፈራል “ይትነገፍ – ይረግፋል” ሲል ነው መልክ ጠፊ አበባ ረጋፊ ነውና።
አንድም እንደ ዕፀ ከንቱ ይሆናል ሲል ነው። ዕፀ ከንቱ፦ በነግህ ትበቅላለች በሠለስት ታብባለች በቀትር ታፈራለች በተስዓት ትደርቃለች በሠርክ ኳ ኰርኳ ብላ (ተነቃቅላ) ትወድቃለች ከዚህ ደረሰች አትባልም።
በነግህ መብቀሏ ሰው የመወለዱ ምሳሌ ነው። በሠለስት ማበቧ የማደጉ፤ በቀትር ማፍራቷ ቤት ንብረት አበጅቶ የመኖሩ፤ በተስዓት መድረቋ የማርጀቱ፤ በሠርክ ተነቃቅላ መውደቋና ከዚህ ደረሰች አለመባሏ ሰው ሞቶ ወደመቃብር ወርዶ አፈር ትቢያ የመሆኑ ምሳሌ ነው።
፲ መዝሙር ወመኑ መሐሪ
ከጥቅምት ፲ – ጥቅምት ፲፮
፲.፩ (በ፫/ሙ) ወመኑ መሐሪ ዘከማከ ወመኑ መሐሪ ዘከማከ ምስለ ኖኅ ኪዳነ ዘአቀምከ (ወ) ምስለ ኖኅ ኪዳነ ዘአቀምከ ለደቂቀ እስራኤል መና ዘአውረድከ (ወ) ለደቂቀ እስራኤል መና ዘአውረድከ ወበጽጌያት ምድረ አሠርጎከ (ወ) ወበጽጌያት ምድረ አሠርጎከ ወሥነ ገዳምኒ ምስለ ቅዱሳኒከ (ወ) ወከመ ወሬዛ ኀየል መላትሒሁ ጉርዔሁ መዓርዒር አምሳሉ ዘወይጠል (ወ) ሰማየ ወምድረ ዘአንተ ፈጠርከ ፀሐየ ወወርኀ ዘአስተዋደድከ (ወ) በከዋክብት ሰማየ ዘከለልከ ወበጽጌያት ምድረ አሠርጎከ (ወ) ቀደሳ ወአክበራ አዕበያ ለሰንበት ወአልዓላ እምኵሉ ዕለት ወመኑ መሐሪ ዘከማከ ወኵሉ ይሴፎ ኪያከ።
ትርጕም፦
እንደ አንተ ያለ ይቅር ባይ ማነው? ከኖኅ ጋር ቃል ኪዳንን ያቆምህ/ያጸናህ፤ ለእስራኤል ልጆች መናን ያወረድህ፤ ምድርን በአበቦች ያስጌጥህ እንደ አንተ ያለ ይቅር ባይ ማነው? የምድረ በዳ ውበት ከቅዱሳንህ ጋር ነው ጉንጮቹ እንደብርቱ ዋሊያ ናቸው ጉረሮው ጣፋጭ ነው ፌቆ ምሳሌው ነው ሰማይና ምድርን የፈጠርህ ፀሐይና ጨረቃን ያስማማህ አንተ ነህ በከዋክብት ሰማይን የጋረድህ በአበቦችም ምድርን ያስጌጥህ አንተ ነህ ሰንበትን ቀደሳት አከበራት ከዕለታት ሁሉ ከፍ ከፍ አደረጋት እንዳንተ ያለ ይቅር ባይ ማነው ሁሉ አንተን ተስፋ ያደርጋል።
፲.፪ የዕለቱ ምንባባት፦
፩ቆሮ ፲፥፩ – ፲፬፤
ራእይ ፲፬፥፩ – ፮፤
ግብ ፬፥፲፱ – ፴፩፤
ወንጌል፦ ማቴ ፲፪፥፩ – ፳፪፤
ቅዳሴ፦ ዘእግዝእትነ ማርያም
፲.፫ የዕለቱ ምስባክ፦
ጻድቅሰ ከመ በቀልት ይፈሪ
ወይበዝኅ ከመ ዘግባ ዘሊባኖስ
ትኩላን እሙንቱ ውስተ ቤተ እግዚአብሔር መዝ ፺፩፥፲፪
ትርጕም፦
ጻድቅ እንደ ዘንባባ ያፈራል።
እንደ ሊባኖስ ዝግባም ይበዛል።
በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ የተተከሉ ናቸው።
ምሥጢር፦
ጻድቅ ሕዝቅያስ እንደ ዘንባባ ያፈራል ማለት ትሞታለህ ከተባለ በኋላ ዕድሜ ተጨምሮለታልና። አንድም ኢዮብን ይመለከታል ከተፈተነ በኋላ ቀድሞ የነበረው ሁሉ በዕጥፍ ተመልሶለታልና። አንድም ሁሉንም ጻድቃን ይመለከታል ፍሬ በረከታቸው ብዙ ነውና ከነሱ አልፎ ለእኛ የሚጠቅም ሆኗልና። ለአብነት ሐዋርያና ወንጌላዊ የሆነ ቅዱስ ማቴዎስን ብናነሣ የጻፈልን ባለ ፳፰ ምዕራፍ ወንጌል ምን ያህል እንደጠቀመን ነፍሳችን ምን ያህል በቃሉ እየረካችና ከቁስለ ኃጢአት በየቀኑ እንዴት እንደምትፈወስ ስንመለከት እንደዘንባባ የበዛ የአገልግሎቱ ፍሬ ግልጥ ብሎ ይታየናል። እንደ ሊባኖስ ዝግባ ይበዛል ሲል ደግሞ ቅዱሳኑ የተሰጣቸውን ክብርና በእነሱ ተልእኮና ምልጃ ተጠቃሚው ምን ያህል ብዙ እንደሆነ ያሳያል።
በእግዚአብሔር ቤት የተተከሉ ናቸው ሲልም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለውን የቅዱሳን ድርሻ ያሳያል ማለት የማይጠፋ ስምና የዘለዓለም መታሰቢያ ያላቸው መሆኑን ያሳያል። ኢሳ ፶፮፥፭
ጥቅምት ፲፪ በዓለ ቅዱስ ሚካኤል ወማቴዎስ ወንጌላዊ
ዘነግህ ምስባክ፦
ወአልዐልኩ ኅሩይየ እምሕዝብየ፤
ወረከብክዎ ለዳዊት ገብርየ፤
ወቀባዕክዎ ቅብዐ ቅዱሰ። መዝ ፹፰፥፲፱፤
ትርጒም፦
ከሕዝቤ የመረጥሁትን ከፍ ከፍ አደረግሁ፤
ባሪያዬን ዳዊትን አገኘሁ፤
የተቀደሰ ዘይትንም ቀባሁት።
ምሥጢር፦
አልዐልኩ እምሕዝብየ ኅሩይየ እምሕዝብየ ብለህ ግጠም፤ ከወገኖቼ መርጬ ወዳጄ ዳዊትን ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ፤ ቦ ለመንግሥት የመረጥሁት ዳዊትን በመንግሥት ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ፤
ወዳጄ ዳዊትን ለልቡናየ የታመነ ሆኖ አገኘሁት፤ ብእሴ ምእመነ ዘከመ ልብየ – እንደ ልቤ የታመነ ሰው እንዲል፤ ቦ ለመንግሥት የበቃ ሆኖ አገኘሁት፤
ልዩ ቅብዐ መንግሥት ቀባሁት፤ ቦ ልዩ ቅብዐ መንግሥት ቀብቼ አነገሥሁት፤ ክብሩን ሲያይ ነው እንጂ ቅብዑስ አንድ ነው።
ወንጌል፦ ማቴ ፲፱፥፩ – ፲፮፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
፩ጢሞ ፭፥፲፱ – ፍጻሜ፤
ይሁዳ ፩፥፱ – ፲፬፤
ግብ ፲፫፥፳፪ – ፳፱፤
ወንጌል፦ ማቴ ፱፥፱ – ፴፪፤
ቅዳሴ፦ ዘጎርጎርዮስ ዘኑሲስ
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
እስመ መምህረ ሕግ ይሁብ በረከተ፤
ወየሐውር እምኃይል ውስተ ኃይል፤
ወያስተርኢ አምላከ አማልክት በጽዮን።
ጥቅምት ፲፬ በዓለ ቅዱስ አቡነ አረጋዊ ወገብረ ክርስቶስ ሰማዕት
ዘነግህ ምስባክ፦
ይባርኩከ ጻድቃኒከ፤
ስብሐት ይብሉ ለመንግሥትከ፤
ወይነግሩ ኃይለከ። መዝ ፻፵፬፥፲፤
ትርጒም፦
ጻድቃንህ ያመሰግኑሃል፤
ለመንግሥትህ ክብር ይገባል ይላሉ፤
ኃይልህን ይነግራሉ።
ምሥጢር፦
ወዳጆችህ ጻድቃን ያመሰግኑሃል፤
ለጌትነትህ ክብር ምስጋና ይገባል ይላሉ፤ ቦ ለጌትነትህ የክብር ምስጋና ይገባል እያሉ ምስጋና ያቀርባሉ፤
ከሃሊነትህን ይናገራሉ ያስተምራሉ።
ወንጌል፦ ዮሐ ፲፬፥፰ – ፲፭፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
፩ቆሮ ፯፥፴፮ – ፍጻሜ
፩ጴጥ ፪፥፲፰ –፳፩፤
ግብ ፰፥፳፮ – ፍጻሜ፤
ወንጌል፦ ማቴ ፲፱፥፳፮ ߺ ፍጻሜ፤
ቅዳሴ፦ ዘሠለስቱ ምዕት (ግሩም) አው ዘሐዋርያት
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
አልቦ ነገር ወአልቦ ነቢብ ዘኢተሰምዐ ቃሎሙ፤
ውስተ ኵሉ ምድር ወጽአ ነገሮሙ፤
ወእስከ አጽናፈ ዓለም በጽሐ ነቢቦሙ። መዝ ፲፰፥፫፤
፲፩ መዝሙር ጳጳሳት
ጥቅምት ፲፯ በዓለ ቅዱስ እስጢፋኖስ
፲፩.፩ (በ፭/ው) ጳጳሳት ቀሳውስት ወዲያቆናት ሊቃነ ካህናት ሥዩማነ ቤተ ክርስቲያን እለ ሎሙ ሕግ ወሎሙ ሥርዓት ብፁዕ እስጢፋኖስ ምስለ ኵሎሙ ቅዱሳን ለከ የዐርጉ ስብሐተ እግዚኣ ለሰንበት አሠርጐካ ለምድር በስነ ጽጌያት ወሠራዕከ ሰንበተ ለሰብእ ዕረፍተ ወብውሕ ለከ ትኅድግ ኃጢአተ ረቢ ንብለከ ረቢ ሊቅ ነአምን ብከ።
ትርጕም፦
ጳጳሳት ቀሳውት ዲያቆናት የካህናት አለቆች ሕግና ሥርዓት ያላቸው የቤተ ክርስቲያን ኃላፊዎች ናቸው እስጢፋኖስ ከቅዱሳን ጋር ብፁዕ ነህ የሰንበት ጌታ ለአንተ ምስጋናን ያቀርባሉ ምድርን በአበባ አስጌጥሃት ለሰው ዕረፍት ይሆን ዘንድ ሰንበትን ሠራህ ኃጢአትን ይቅር ትል ዘንድ ሥልጣን አለህ መምህር እንልሃለን መምህር ሊቅ ሆይ እናምንብሃለን።
፲፩.፪ የዕለቱ ምንባባት፦
፪ጢሞ ፩፥፫ – ፲፭፤
፩ጴጥ ፭፥፪ – ፭፤
ግብ ፯፥፶፬ – ፍጻሜ፤
ወንጌል፦ ሉቃ ፳፩፥፩ ߺ ፯፤
ቅዳሴ፦ ዘእግዝእትነ ማርያም
ምስባክ፦ አንተ ፈጠርከ ፀሐየ ወወርኃ በል ከመዝሙር በጊዜሁ፤
፲፪ መዝሙር ሠርዐ ሰንበተ
ለእመ ኮነ በዓለ ገብርኤል በሰንበት አመ ፲ወ፱ ለጥቅምት
፲፪.፩ (በ፬/ዑ) ሠርዐ ሰንበተ ለዕረፍት ሠርዐ ሰንበተ ለዕረፍት ኵሉ ነባሪ ወቀናዪ ያዕርፉ ባቲ ግብረ እደዊከ አዳም ለሐኰ ለሰብእ በአርአያከ ወበአምሳሊከ (ግ) ፈጠርካሆሙ ለመላእክት ከመ ይትለአኩከ (ግ) አሠርጎኮ ለሰማይ በከዋክብት ወለምድርኒ በሥነ ጽጌያት ግብረ እደዊከ አዳም እግዚኦ ፈድፋደ ቃልከ ጥዑም።
ትርጕም፦
ለዕረፍት ሰንበትን ሠራ አሠሪና ሠራተኛ ያርፉባት ዘንድ፤ የእጅህ ሥራ ያማረ ነው ሰውን በአርአያህና በአምሳልህ ሠራኸው ያገለግሉህ ዘንድ መላእክትን ፈጠርሃቸው ሰማይን በከዋክብት አስጌጥኸው ምድርን በአበቦች ውበት አስጌጥሃት የእጅህ ሥራ ያማረ ነው አቤቱ ቃልህ ፈጽሞ የሚጥም ነው።
፲፪.፪ የዕለቱ ምንባባት፦
ቲቶ ፫፥፰ – ፲፪፤
፩ዮሐ ፪፥፳፪ -ፍ፤
ግብ ፳፥፳፰ – ፴፩፤
ወንጌል፦ ማቴ ፮፥፳፭ – ፍጻሜ፤
ቅዳሴ፦ ዘእግዝእትነ ማርያም
፲፪.፫ የዕለቱ ምስባክ፦
ወሶበሂ ይትዋቀሥ ይጻእ ተመዊዖ፤
ወጸሎቱሂ ትኩኖ ጌጋየ፤
ወይኩና መዋዕሊሁ ኅዳጠ። መዝ ፻፰፥፯፤
ትርጕም፦
በሚከራከር ጊዜ ተረትቶ ይውጣ፤
ጸሎቱም በደል ትሁንበት፤
ዘመኖቹም ጥቂት ይሁኑ።
ምሥጢር፦
ተከራክሮ በጉባኤ በቆመ ጊዜ ድል ተነሥቶ አፍሮ ይመለስ፤
ትረባኛለች ትጠቅመኛች ብሎ የለመናት ልመናው እዳ በደል ትሁንበት፤
ዘመኖቹ ይነሱ፤ ኃጥእ ዘመኑን ሳይፈጽም ይቀሠፋልና።
፲፫ በጊዜሁ ኀለፈ ክረምት
ከጥቅምት ፲፯ – ፳፫
፲፫.፩ (በ፮/ሥ) በጊዜሁ ኀለፈ ክረምት ቆመ በረከት ናሁ ጸገዩ ጽጌያት ናርዶስ ፈረየ በውስተ ገነት ቀንሞስ ቀናንሞስ ከርካዕ ምስለ እንጎታት ክርስቶስ ሠርዐ ሰንበተ ነአኵቶ ለዘጸገወነ ሠናይቶ።
ትርጕም፦
ክረምት በጊዜው/በሰዓቱ አለፈ በረከት ቆመ (በጋ ተተካ) እነሆ አበቦች አበቡ ናርዶስ አፈራ ቀንሞስ ቀናንሞስ (ቀረፋ) ሎሚ ከሽቱ ጋር አፈራ ክርስቶስ ሰንበትን ሠራ መልካሙን የሰጠንን እናመሰግነዋለን።
፲፫.፪ የዕለቱ ምንባባት፦
ሮሜ ፯፥፩ – ፲፬፤
ራእይ ፳፩፥፳፩ – ፍ፤
ግብ ፳፪፥፩ – ፮፤
ወንጌል፦ ማቴ ፮፥፳፭ – ፍ፤
ቅዳሴ፦ ዘእግዝእትነ ማርያም
፲፫.፫ የዕለቱ ምስባክ፦
አንተ ፈጠርከ ፀሐየ ወወርኀ፤
ወአንተ ገበርከ አድባረ ምድር ኵሎ፤ (አድባረ ወምድረ ኵሎ)
ክረምተ ወሐጋየ ዘአንተ ፈጠርከ። መዝ ፸፫፥፲፮
ትርጉም፦
አንተ ፀሐይና ጨረቃን ፈጠርህ።
አንተ የምድር ዳርቻዎችን ሁሉ ሠራህ።
በጋንና ክረምትን አንተ አደረግህ።
ምሥጢር፦
ፀሐይ ጨረቃን የፈጠርህ አንተ ነህ።
(አድባረ) ተራራውን ኮረብታውን
(ወምድረ) ደልዳላውን መሬት የፈጠርህ አንተ ነህ።
ዘጠኝ ወር በጋን ሦስት ወር ክረምትን የፈጠርህ (የሠራህ) አንተ ነህ።
አንድም አንተ ፈጠርከ ፀሐየ ወወርኃ – ለኢያሱ ፀሐይ ጨረቃን ያቆምህለት አንተ ነህ።
አድባረ ወምድረ – ሙሴ አሮንን ሰባ ሊቃናትን ያስነሣህ አንተ ነህ።
ክረምተ ወሐጋየ – ዘመነ ኤልያስን ያመጣህ አንተ ነህ። ሦስት ዓመት ከመንፈቅ ድርቅ ሆኗልና።
አንድም ፀሐይ ሊቀ ካህናቱን ወርኅ ንጉሡን ያስነሣህ አንተ ነህ።
አድባረ ወምድረ – ልዑላኑን ትሑታኑን የፈጠርህ አንተ ነህ።
ክረምተ ወሐጋየ፦ ተማርከው ሲሄዱ የሚጠጡት አጥተው ማድጋቸውን እያንኳኩ ወርደዋል በሚጠት ጊዜ ዝናም እየዘነመላቸው በየወንዙ ውኃ ሞልቶላቸው እየጠጡ ወጥተዋልና።
አንድም አንተ ፈጠርከ ፀሐየ ወወርኃ – ፀሐይ ጨለማ ጨረቃ ደም እንዲሆን ያደረግህ አንተ ነህ።
አድባረ ወምድረ – ሐዋርያትን ሰባ አርድእትን ያስነሣህ አንተ ነህ።
ክረምተ ወሐጋየ – ኦሪትን ወንጌልን የሠራህ። በክረምት ቅጠል እንጂ ፍሬ እንዳይገኝ በኦሪትም ተስፋ እንጂ ሀብት ሥርየት አልተሰጠምና። በበጋ ፍሬ እንዲገኝ በወንጌል ሀብት ሥርየት ተገኝቷልና።
አማራጭ የወንጌለ ማቴዎስ ንባብ፦ ማቴ ፲፮፥፩፤
ወመጽኡ ኀቤሁ ፈሪሳውያን ወሰዱቃውያን እንዘ ያሜክርዎ ወይሴአልዎ ትእምርተ እምሰማይ ያርእዮሙ – ሰዱቃውያንና ፈሪሳውያን ሲፈትኑት ከሰማይ ምልክት አሳየን ሊሉት መጡ።
ወአውሥአ ወይቤሎሙ እምከመ መስየ ወኮነ ሕዋየ ትብሉ ጽሕወ የመሸ ድንግዝግዝታ የሆነ እንደሆነ ብራ ያድራል ትላላችሁ። እስከ ያቅየሐይሕ ሰማይ – ሰማይ አልፎ አልፎ በቀይ ሰብኳልና።
ወእምከመ ጽሕወ ትብሉ ዮምሰኬ ይዘንም – የነጋ እንደሆነ ግን ዛሬ ይዘንማል ትላላችሁ። እስመ ያቅየሐይሕ ሰማይ ድሙነ – ደመና ዳር እስከ ዳር ገጥሞ ይፈልቃልና። ኦ መደልዋልን ገጸ ሰማይኑ ተአምሩ ፈክሮ – እናንት ግብዞች የሰማዩን ፊት ማለት የሰማይን ግብር እናውቃለን ትላላችሁ። ወተአምረ መዋዕልሰ እፎ ኢተአምሩ – በዘመናችሁ የተደረገውን ተአምር አለማወቃችሁ ስለምነው?
አንድም እምከመ መስየ – ሥጋ የለበሰ ተስፋ የደረሰ እንደሆነ ተስፋ አልደረሰም ሥጋ አለበሰም ትላላችሁ። እስመ ያቅየሐይሕ ሰማይ – የተነገረው ትንቢት የተቆጠረው ሱባኤ ገና ነው ትላላችሁና። እምከመ ጽሕወ – ሐሳዊ መሢሕ ሲወለድ ግን ገና ዛሬ ሥጋ ለበሰ ተስፋ ደረሰ ትላላችሁ። በሐሰት ተሸፍኖ አምላክ ነኝ ብሏልና።
ገጸ ሰማይኑ ተአምሩ ፈክሮ – ሰማያዊ ልደቴን እናውቃለን ትላላችሁ። ወተአምረ መዋዕልሰ – በዘመናችሁ የተደረገውን ምድራዊ ልደቴን አለማወቃችሁ ስለምንነው?
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ብለው በአንደበታቸው የሚናገሩ ሰዎች ሁሉ አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ በምንም በምን እንደማያንስ በልባቸው አስረግጠው ማመንና መመስከር ይጠበቅባቸዋል። ያለበለዚያ ገጸ ሰማይኑ ተአምሩ ፈክሮ ወተአምረ መዋዕልሰ እፎ ኢተአምሩ ተብለው እንደተገሠጹ አይሁድ መሆን ነውና።
ቅዱሳት መጻሕፍት በተለየ አካሉ ሰው ሆኖ የሠራውን የአድኅኖት ሥራ አጉልተው ቢናገሩም ድኅነታችን የተፈጸመው ግን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ አንዲት ፈቃድ መሆኑን ለቅጽበት መዘንጋት የለብንም። ቀዳማዊ (ሰማያዊ) ልደቱ ከአባቱ እንዲያንስ እንዳላደረገው ሁሉ ደኃራዊ (ምድራዊ) ልደቱም ከአባቱ እንዲያንስ አላደረገውምና።
ጥቅምት ፳፩ በዓለ እግዝእትነ ማርያም
ዘነግህ ምስባክ፦
ወትቀውም ንግሥት በየማንከ፤
በአልባሰ ወርቅ ዑፅፍት ወኁብርት፤
ስምዒ ወለትየ ወርእዪ ወአጽምዒ ዕዝነኪ።
ወንጌል፦ ሉቃ ፩፥፴፱ – ፶፯፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
ሮሜ ፲፥፱ – ፲፮፤
፪ዮሐ ፩፥፭ – ፰፤
ግብ ፪፥፲፬ – ፳፪፤
ወንጌል፦ ዮሐ ፲፩፥፴፰ – ፵፮፤
ቅዳሴ፦ ዘወልደ ነጐድጓድ
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
ወገሠጸ ነገሥተ በእንቲአሆሙ፤
ኢትግሥሡ መሲሐንየ፤
ወኢታሕስሙ ዲበ ነቢያትየ። መዝ ፻፬፥፲፬፤
ትርጒም፦
ስለእነርሱ ነገሥታቱን ገሠጸ፤
የቀባኋቸውን አትዳሱ፤
በነቢያቴም ላይ ክፉ አታድርጉ።
ምሥጢር፦
ነገሥታቱን እነፈርዖንን እነአቤሜሌክን ስለእነሱ ተቆጣ፤
እንዘ ይብል ያለበት ነው፤ ቅቡዓንየ ሲል ነው የከበሩ አብርሃም ይስሐቅ ያዕቆብን በዕደ መዓት አትዳሱ ብሎ፤ መቼ ተቀባና እንዲህ አለ ቢሉ ቅቡዓኑን ወልዷልና፤ ቦ ቅብር ኀበ ዘፈቀድከ እስመ ከመ ንጉሥ አንተ እምታሕተ እግዚአብሔር – ከእግዚአብሔር በታች አንተ እንደ ንጉሥ ነህና ከወደድህበት ቅበር” ብለዉታልና። ዘፍ ፳፫፥፮፤
በወዳጆቼ በአብርሃም በይስሐቅ በያዕቆብ ክፉ ሥራ አትሥሩ ብሎ፤
ነቢያት አላቸው ወላድያነ ነቢያት ናቸውና፤ ቦ ኃላፍያትን መጻእያትን ያውቃሉና፤ ቦ ደጋግ ሲል ነው፤ “ይጸሊ ለከ አብርሃም እስመ ከመ ነቢይ ውእቱ – እሱ እንደ ነቢይ ደግ ነውና ይጸልይልህ” እንዲል ዘፍ ፳፥፯፤
፲፬ ጸገየ ወይን
ከጥቅምት ፳፫- ፳፱
፲፬.፩ (በ፭/ሴ) ጸገየ ወይን ወፈርየ ሮማን ወፈርዩ ኵሉ ዕፀወ ገዳም ቀንሞስ ዕቊረ ማየ ልብን ሠርዐ ለነ ሰንበተ ለዕረፍተ ዚአነ ጸገዩ ጽጌያት ጸገዩ ደንጐላት (ሠ) ኀለፈ ክረምት ቆመ በረከት ተሠርገወት ምድር በሥነ ጽጌያት (ሠ) እግዚኣ ለሰንበት ወአቡሃ ለምሕረት ሠርዐ ለነ ሰንበተ ለዕረፍተ ዚአነ ሠርዐ ለነ ሰንበተ ለዕረፍት ወለመድኃኒት።
ትርጕም፦
ወይን አበበ ሮማን አፈራ ማየ ልብን የተባለ ሽቱ የተከማቸበት ቀንሞስ ያለበት የምድረ በዳ ዛፎች ሁሉ አፈሩ’ ለእኛ ዕረፍት ሊሆን ሰንበትን ሠራ አበቦች አበቡ ሱፎች አበቡ ክረምት አለፈ በረከት ቆመ (ተተካ) ምድር በአበቦች ውበት አጌጠች የሰንበት ጌታ የምሕረት አባት ለእኛ ዕረፍት ይሆን ዘንድ ሰንበትን ሠራ፤ ለዕረፍትና ለመድኃኒት።
፲፬.፪ የዕለቱ ምንባባት፦
ሮሜ ፲፩፥፲፫ – ፳፭፤
ራእይ ፲፪፥፲፫ – ፍ፤
ግብ ፲፩፥፩ – ፲፪፤
ወንጌል፦ ማቴ ፳፩፥፴፫ – ፍጻሜ፤
ቅዳሴ ፦ ዘእግዝእትነ ማርያም
፲፬.፫ የዕለቱ ምስባክ፦
ዓፀደ ወይን አፍለስከ እምግብጽ፤
ሰደድከ አሕዛበ ወተከልከ ኪያሃ፤
ወፄሕከ ፍኖተ ቅድሜሃ። መዝ ፸፱፥፰፤
ትርጉም፦
ከግብጽ የወይንን ግንድ አፈለስህ/አመጣህ፤
አሕዛብን አባረርህ እርሷንም ተከልህ፤
በፊቷ መንገድን ጠረግህ።
ምሥጢር፦
ዓፀደ ወይን ጒንደ ወይን ይላል የወይኒቱን ሐረግ ከግብጽ አፈለስህ አለ እስራኤልን ከግብጽ አወጣህ “በለስ ዘይቤ እስራኤል እሙንቱ – በለስ የተባሉት ቤተ እስራኤል ናቸው” እንዲል ኢሳ ፭፥፯
አሕዛብን ከሀገራቸው አስወጥተህ አባቶቻችንን በደረሰ መከራቸው በታነፀ ግንባቸው አኖርሃቸው።
በፊታቸው መንገድን ጠረግህላቸው አለ የተነሡባቸውን ጠላቶቻቸውን እየወጉ ድል እያደረጉ ወጥተዋልና። አንድም ሚጠተ ሥጋውን ሚጠተ ነፍሱን አደርግህላቸው።
ጥቅምት ሃያ ሰባት
ጥቅምት ፳፱ ተዝካረ ልደቱ ለእግዚእነ
ዘነግህ ምስባክ
ምስሌከ ቀዳማዊ በዕለተ ኃይል፤
በብርሃኖሙ ለቅዱሳን፤
ወለድኩከ እምከርሥ እምቅድመ ኮከበ ጽባሕ። ትርጒምና ምሥጢር መዝሙር ወእንዘ ሀለዉ ላይ ተመለከት።
ወንጌል፦ ሉቃ ፪፥፩ – ፰፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
፪ቆሮ ፮፥፩ – ፲፪፤
፩ዮሐ ፫፥፯ – ፲፪፤
ግብ ፱፥፳ – ፳፫፤
ወንጌል፦ ማር ፰፥፴፬ – ፍጻሜ
ቅዳሴ፦ ዘእግዝእትነ ማርያም
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
ወታቀንተኒ ኃይለ በጸብዕ፤
ወአዕቀጽኮሙ ለኵሎሙ እለ ቆሙ ላዕሌየ በመትሕቴየ፤
ወመጠውከኒ ዘባኖሙ ለፀርየ። መዝ ፲፯፥፴፱፤
ትርጒም፦
በሰልፍ ጊዜ ኃይልን ታስታጥቀኛለህ፤
በበላዬ የቆሙትን ሁሉ በበታቼ ትጥላቸዋለህ፤
የጠላቶቼን ጀርባ ሰጠኸኝ።
ምሥጢር፦
በሰልፍ ጊዜ ኃይልን እንደ ዝናር ታስታጥቀኛለህ፤
በጠላትነት የተነሡብኝን በመከራ አሰነካከልሃቸው፤ ቦ ከበላዬ የነበሩትን በጠላትነት የተነሡብኝን ከእኔ በታች አደረግሃቸው፤
ይሁዳ እዴከ ዲበ ዘባኖሙ ለፀርከ ባልኸው ጠላቶቼን አንገታቸውን ቀለስ ወገባቸውን ጎንበስ አድርገህ አስገዛኸኝ፤ ቦ ጀርባቸውን መልሰህ አንገታቸውን ቀልሰህ ለውግ አስመችተህ ሰጠኸኝ።
፲፭ ትወጽእ በትር
ለእመ ኮነ በዓለ እግዚአብሔር በሰንበት አመ ፳ወ፱ ለጥቅምት መዝሙር ትወጽእ በትር
፲፭.፩ (በ፩/ዝ) ትወጽእ በትር እምሥርወ ዕሤይ ወየዐርግ ጽጌ ይእቲ በትር አምሳለ ማርያም ቅድስት ይእቲ ወጽጌ ዘወጽአ እምኔሃ አምሳሉ ለወልድ ኀደረ ላዕሌሃ ቃል ሥጋ ኮነ ወተወልደ እምኔሃ።
ትርጕም፦
ከዕሤይ ሥር በትር ትወጣለች ከበትሩ አበባ ይወጣል ይህች በትር የማርያም ምሳሌ ናት ከእሷ የወጣው አበባ የወልድ አምሳል ነው በእሷ አደረ ቃል ሥጋ ሆነ ከሷ ተወለደ።
ምንባብና ምስባክ የክርስቶስ ሠርዐን በል።
፲፮ ክርስቶስ ሠርዐ ሰንበተ
ከጥቅምት ፴ – ኅዳር ፭
(በ፮/ፋኝ) ክርስቶስ ሠርዐ ሰንበተ ክርስቶስ ሠርዐ ሰንበተ ወጸገወነ ዕረፍተ ከመ ንትፈሣሕ ኅቡረ አዕፃዳተ ወይን ጸገዩ ቀንሞስ ፈረየ ሰሎሞን ጥቀ ኢለብሰ ከመ አሐዱ እምእሉ።
ትርጕም፦
ክርስቶስ ሰንበትን ሠራ በአንድነት እንደሰት ዘንድ ዕረፍትን ሰጠን የወይን ስፍራዎች አበቡ ቀንሞስ አፈራ ሰሎሞን ስንኳ ከነዚያ እንደ አንዱ አልበሰም።
የዕለቱ ምንባባት፦
ቈላ ፩፥፩ – ፲፪፤
ያዕ ፩፥፩ – ፲፫፤
ግብ ፲፫፥፮ – ፲፮፤
ወንጌል፦ ማቴ ፮፥፳፭ – ፍጻሜ፤
ቅዳሴ፦ ዘእግዝእትነ ማርያም
የዕለቱ ምስባክ፦
ወይከውን ከመ ዕፅ እንተ ትክልት ኀበ ሙሐዘ ማይ፤
እንተ ትሁብ ፍሬሃ በበጊዜሃ፤
ወቈጽላኒ ኢይትነገፍ። መዝ ፩፥፫፤
ትርጕም፦
በውኃ ፈሳሶች ዳር እንደ ተተከለች፤
ፍሬዋን በየጊዜው እንደምትሰጥ፤
ቅጠሏም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል።
ምሥጢር፦
ዕፅ – ሰውነቱ፤ ሙሐዘ ማይ – ረድኤተ እግዚአብሔር፤ ፍሬ – ልጁ፤ ቆጽል – የልጅ ልጁ ሁሉ ተጠብቆለት ይኖራል።
ከወገኑ ሰው የማይሞትበት አለና እንዲህ አለ? ቢሉ በረድኤተ እግዚአብሔር ተጠብቆ ከኖረ ልጁ ወገኑ ያለጊዜው አይሞትምና ሀብቱ ንብረቱ በከንቱ አይጠፋምና።
አንድም ፍሬ ፡- ደጋጉ ገንዘብ፦ ወርቁ እንቊው ፈረስ በቅሎው ላሙ በሬው ነው።
ቅጠል፡- ጥቃቅኑ ገንዘብ የልብስ ወገን ብስጡ ብሳጡ ብሳስያጡ ምንጣፉ ነው።
አንድም ፍሬ፦ አሥራቱ በኲራቱ ነው።
ቅጠል፦ አስተናጺሐከ ግበር – አጥርተህ አድርግ እንዲል አጥርቶ የሚሰጥ ሰው ነው አንድም ከአሥር አንድ የግድ ነው ብሎ ከዘጠኝ አንድ የሚሰጥ ሰው ነው።
አንድም ፍሬ፦ ምግባሩ የቀናለት፤
ቅጠል፦ ሃይማኖቱ የጸናለት ሰው ነው።
ከቅጠል ፍሬ እንዲበልጥ ከሃይማኖት ምግባር ይበልጣል ማለት አይደለም በቅጠል መሠረትነት ፍሬ እንዲገኝ በሃይማኖት መሠረትነት ምግባር ይሠራልና ሃይማኖትን በቅጠል ምግባርን በፍሬ መስሎ ተናገረ።

