፴፯ ተቀነዩ ለእግዚአብሔር
መዝሙር ዘዘወረደ
፴፯.፩ (በ፩/ዩ) ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሃት ወተሐሠዩ ሎቱ በረዓድ እስመ ለዓለም ምሕረቱ ለትውልደ ትውልድ ጽድቁ ንሕነሰ ሕዝቡ ባዑ ቅድሜሁ በተጋንዮ ወውስተ አዕፃዲሁ በስብሐት እመንዎ (እ) ንጹም ጾመ ወናፍቅር ቢጸነ ወንትፋቀር በበይናቲነ (እ) አክብሩ ሰንበተ ተገበሩ ጽድቀ እስመ ሰንበትሰ በእንተ ሰብእ ተፈጥረት (እ) ምሕረተ ወፍትሐ አሐሊ ለከ እዜምር ወዕሌቡ ፍኖተ ንጹሐ እስመ ለዓለም ምሕረቱ ለትውልደ ትውልድ ጽድቁ ንሕነሰ ሕዝቡ አባግዓ መርዔቱ።
ትርጉም፦
ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ በረዓድ ደስ ይበላችሁ ምሕረቱ ለዘለዓለም ነውና ጽድቁም ለልጅ ነውና እኛ ወገኖቹ ነን። በምስጋና ወደፊቱ ቅረቡ በቤተ መቅደሱ በምስጋና እመኑት። ጾምን እንጹም ባልንጀራችንን እንውደድ እርስ በእርሳችን እንፋቀር። ሰንበትን አክብሩ ጽድቅን ሥሩ ሰንበት ስለሰው ተፈጥራለችና። ምሕረትን ፍርድን እቀኛለሁ እዘምራለሁ ንጹሕ መንገድን አስተውላለሁ። ምሕረቱ ለዘለዓለም ነውና ጽድቁም ለልጅ ልጅ ነውና እኛ ወገኖቹ ነን ያውም የመንጋው በጎች የነአብርሃም ወገኖች ነን።
፴፯.፪ የዕለቱ ምንባባት፦
ዕብ ፲፫፥፯ – ፲፮፤
ያዕ ፬፥፮ – ፍ፤
ግብ ፳፭፥፲፫ – ፍ፤
ወንጌል፦ ዮሐ ፫፥፲ – ፳፭
ቅዳሴ፦ ዘእግዚእነ
፴፯.፫ የዕለቱ ምስባክ፦
ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሃት፤
ወተሐሠዩ ሎቱ በረዓድ፤
አጽንዕዋ ለጥበብ ከመ ኢይትመዓዕ እግዚአብሔር። መዝ ፪፥፲፩
ትርጉም፦
ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ፤
በረዓድም ደስ ይበላችሁ፤
እግዚአብሔር እንዳይቆጣ ጥበብን አጽኗት።
ምሥጢር፦
ከላይ ወሕዝብኒ ነበቡ ከንቶ – ሕዝቡም ከንቱ ነገርን ተናገሩ ማለትም ስቅሎ ስቅሎ ብለው ተናገሩ ብሎ ነበርና እናንተ ግን በፍርሃት በረዓድ በመንቀጥቀጥ ለእግዚአብሔር ተገዙ አለ።
በመገዛታችሁም ደስ ይበላችሁ፤ ዋጋ ያለበት ነውና፤ ደስ ሳይሰኙ መገዛት ዋጋ አያሰጥምና።
አንድም (ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሃት ወበረዓድ እንዘ ትትሐሠዩ) ይላል ደስ እያላችሁ በፍርሃት በረዓድ ተገዙ።
ጽሕፈት ድጉሰትን እርሻ ቁፋሮን አጽንታሁ ያዙ። ጽፋችሁ ደጉሳችሁ አርሳችሁ ቆፍራችሁ ብሉ ብላቸው አይሆንም አሉ ብሎ እግዚአብሔር በረኃብ እንዳይቀጣችሁ።
አንድም ኢታምልክን ጠብቁ አሥሩ ቃላትን ብሠራላቸው አንጠብቅም አሉ ብሎ እግዚአብሔር እንዳይፈርድባችሁ።
አንድም ኦሪትን ወንጌልን ጠብቁ ኦሪትን ወንጌልን ብሠራላቸው አንጠብቅም አሉ ብሎ እግዚአብሔር እንዳይፈርድባችሁ።
አንድም ጥበብ ወልድን እመኑባት “ጥበብ ሐነፀት ላቲ ቤተ ወአቀመት ሰባተ አዕማደ – ጥበብ ቤትን ሠራች ሰባት ምሰሶዋንም አቆመች” እንዲል ምሳ ፱፥፩፤ ባታመሰግኑ እናንተ ይቀርባችኋል እንጂ ምስጋናው አይጐድልበትም ሲል ነው “ጥበብ ትዌድስ ርእሳ – ጥበብ ራሷን ታመሰግናለች” እንዲል ሲራ ፳፬፥፩፤
ልጄን በሥጋ ብሰድላቸው አላመኑበትም ብሎ እንዳይፈርድባችሁ።
መጋቢት ፭ በዓለ ዕረፍቱ ለአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ
ዘነግህ ምስባክ፦
ወትከይድ አንበሳ ወከይሴ፤
እስመ ብየ ተወከለ አድኅኖ፤
ወእከድኖ እስመ አእመረ ስምየ። መዝ ፺፥፲፫፤
ትርጒም፦
አንበሳውንና ዘንዶውን ትረግጣለህ፤
በእኔ ተማምኗልና አድነዋለሁ፤
ስሜንም አውቋልና እጋርደዋለሁ።
ምሥጢር፦
መሮዳህን ሰናክሬምን ትገዛለህ፤
በእኔ አምኗልና አድነዋለሁ፤
ስሜን በአምልኮተ እግዚአብሔር አውቋልና ቦ ወዷልና ከመከራ እሠውረዋለሁ።
ወንጌል፦ ሉቃ ፳፩፥፴፫ – ፴፯፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
ሮሜ ፲፬፥፩ – ፍጻሜ፤
፩ጴጥ ፬፥፩ – ፲፪፤
ግብ ፲፯፥፲፱ – ፍጻሜ፤
ወንጌል፦ ማቴ ፮፥፲፱ – ፍጻሜ፤
ቅዳሴ፦ ዘሠለስቱ ምዕት
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
ክቡር ሞቱ ለጻድቅ በቅድመ እግዚአብሔር፤
እግዚኦ አነ ገብርከ፤
ገብርከ ወልደ አመትከ። መዝ ፻፲፭፥፮፤
ትርጒም፦
የጻድቅ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው፤
አቤቱ እኔ ባርያህ ነኝ፤
ባርያህ የሴት ባርያህም ልጅ ነኝ።
ምሥጢር፦
የጻድቅ ሰው ሞቱ በእግዚአብሔር ዘንድ የከበረ ነው፤ ነፍሱ ከሥጋው ስትለይ በይባቤ መላእክት በቅዳሴ መላእክት በመዝሙረ ዳዊት በመዓዛ ገነት ነውና፤
አቤቱ እኔ ባርያህ ነኝ፤
ከዚያውም ዘንድ የሴት ባርያህ ልጅ የምሆን ባርያህ ነኝ፤ ከወንድ ባርያ ልጅ የሴት ባርያ ልጅ ይታመናልና፤ የወንድ ባርያ ልጅ ይጠረጠራል አሁን ይህ ልጅ የዕገሌ ልጅ ሆኖ ነውን እንዲያው ነው እንጂ ተብሎ፤ ሴት ግን በአደባባይ ትወልደዋለች ታሳድገዋለችና አይጠረጠርም፤ እኔም በአምልኮ ጣዖት የማይጠረጠሩ የጥንት ተገዢዎችህ የአብርሃም የይስሐቅ የያዕቆብ ልጅ ተገዢህ ነኝ።
መጋቢት ፲፪ በዓለ ቅዱስ ሚካኤል ወድሜጥሮስ ሊቀ ጳጳሳት
ዘነግህ ምስባክ፦
አዕይንትየሰ ኀበ መኃይምናነ ምድር፤
ከመ አንብሮሙ ምስሌየ፤
ዘየሐውር በፍኖት ንጹሕ ውእቱ ይትለአከኒ። መዝ ፻፥፮፤
ትርጒም፦
ዐይኖቼ ወደ ምድር ወደ ምእመናን ናቸው፤
ከእኔ ጋር አኖራቸው ዘንድ፤
በንጹሕ መንገድ የሚሄድ እርሱ ያገለግለኛል።
ምሥጢር፦
ዐይነ ልቡናየ ነቢያት ካህናትን ይመለከታል፤
ከእኔ ጋር በመምህርነት አኖራቸው ዘንድ፤
በንጹሕ መምህርነት ጸንቶ የሚኖር ሰው ያገለግለኛል፤ ማገልገል የደቀመዝሙር ብቻ አይደለም መምህርም ያገልግላል ነቅቶ ተግቶ ማስተማርም ማገልገል ነውና።
ወንጌል፦ ማቴ ፭፥፩ ߺ ፲፯፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
፩ቆሮ ፯፥፩ ߺ ፰፤
፪ጴጥ ፪፥፱ ߺ ፍጻሜ፤
ግብ ፳፯፥፩ ߺ ፲፩፤
ወንጌል፦ ፲፰፥፲ ߺ ፳፩፤
ቅዳሴ፦ ዘያዕቆብ ዘሥሩግ
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
ይትዐየን መልአከ እግዚአብሔር ዐውዶሙ፤
ለእለ ይፈርህዎ ወያድኅኖሙ፤
ጠዐሙ ወታእምሩ ከመ ኄር እግዚአብሔር።
፴፰ ግነዩ ለእግዚአብሔር
መዝሙር ዘቅድስት
፴፰.፩ በ (፭/ር) ግነዩ ለእግዚአብሔር ወጸውዑ ስሞ ወንግርዎሙ ለአሕዛብ ምግባሮ ሀቡ ስብሐተ ለስሙ አክብሩ ሰንበተ ተገበሩ ጽድቀ ዝግቡ ለክሙ መዝገበ ዘበሰማያት ኀበ ፃፄ ኢያማስኖ ወኢይረክቦ ሰራቂ ድልዋኒክሙ ንበሩ ዘበላዕሉ ሀልዩ ኀበ ሀሎ ክርስቶስ።
ትርጉም፦
ለእግዚአብሔር ተገዙ ስሙንም ጥሩ ሥራውን ለአሕዛብ ንገሯቸው ለስሙ ምስጋናን ስጡ/አቅርቡ ሰንበትን አክብሩ ጽድቅን ሥሩ ሌባ በማያገኘው ብል በማያጠፋው በሰማያት መዝገብን አከማቹ ክርስቶስ ባለበት ለመሆን በላይ ያለውን እያሰባችሁ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ።
፴፰.፪ የዕለቱ ምንባባት፦
፩ተሰ ፬፥፩ – ፲፫፤
፩ጴጥ ፩፥፲፫ – ፍ፤
ግብ ፲፥፲፯ – ፴፤
ወንጌል፦ ማቴ ፮፥፲፯ – ፳፭
ቅዳሴ፦ ዘኤጲፋንዮስ
፴፰.፫ የዕለቱ ምስባክ፦
እግዚአብሔርሰ ሰማያተ ገብረ፤
አሚን ወሠናይት ቅድሜሁ፤
ቅድሳት ወዕበየ ስብሐት ውስተ መቅደሱ። መዝ ፺፭፥፭
ትርጉም፦
እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ፈጠረ፤
እምነትና በጎነት በፊቱ ናቸው፤
ቅድስና እና የክብር ገናንነት በመቅደሱ ውስጥ ናቸው።
ምሥጢር፦
እግዚአብሔር ሰባቱን ሰማያት ፈጠረ፤
ሃይማኖት ምግባር በፊቱ ነው አለ ምግባር ሃይማኖት የያዘ ሰውን ይወዳል፤
ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ተብሎ መመስገን ዐቢየ ስብሐት መባል ገንዘቡ ነው።
፴፰.፬ መልእክት፦
ሰማይ ማለት ሥዕለ ማይ – የውኃ ንድፍ ማለት ነው አንድም ልዑል ማለት ነው። ቀለሙ/መልኩ ሰማያዊ ነው እጅግ ብሩህ ቢሆን ዐይን ይበዘብዝ ነበርና እጅግም ጨለማ ቢሆን ለዐይን ይከብድ ነበርና። ይህንንም የፈጠረው የዐይን ማረፊያ ይሆን ዘንድ ነው፤ ጠፈር/ሰማይ ባይኖር የሰው የእንስሳ የአራዊት ዐይን ሁሉ ማረፊያ አጥቶ ወልቆ ወልቆ በወደቀ ነበርና።
ይህ ለሥጋዊ እንቅስቃሴአችን ሲሆን ለመንፈሳዊው እንቅስቃሴያችን ደግሞ በተለይ በጊዜ ቅዳሴ የዐይናችን ማረፊያ የሚሆነው ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ነው። አምላክችን ምግባር ከሃይማኖት አንድ አድርጎ የያዘ ሰውን ይወዳል ባልነው መሠረት አስቀድሳለሁ ብሎ ከቤቱ ተዘጋጅቶ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚመጣ ሰው በዕለቱ የታወቀና ድንገተኛ ነገር ካላጋጠመው በስተቀር ሥጋ ወደሙን ይቀበል ዘንድ ወዶና ፈቅዶ የሚኖርበት ክርስቲያናዊው ሕግ ያስገድደዋል ይህን ካላደረገ ዐይኑ ማረፊያ ያጣ ሰው ሆኗል።
“እግዚአብሔርሰ ሰማያተ ገብረ – እግዚአብሔርማ ሰማያትን ፈጠረ” ብሎ ለመዘመር አቅም የሚያንሰው ይሆናል። ዐይናችን ማረፊያ ሲያገኝ ልባችንም በተስፋ የተመላ ይሆናል፤ እንዲህ ከሆነ ዐይን ያላያትን በሰው ልብ ያልታሰበችውን እግዚአብሔር ለወዳጆቹ ያዘጋጃትን ዘለዓለማዊት መንግሥት በተስፋ እየጠበቀ የመኖር ዕድሉ ከቀን ወደቀን ያድጋል “ትምጻእ መንግሥትከ – መንግሥትህ ትምጣልን” እያለ ይጸልያልና።
መጋቢት ፳፩ ተዝካረ በዓላ ለእግዝእትነ
ዘነግህ ምስባክ፦
ሚጥ ገጸከ እምኃጢአትየ፤
ወደምስስ ሊተ ኵሎ አበሳየ፤
ልበ ንጹሐ ፍጥር ሊተ እግዚኦ። መዝ ፶፥፱፤
ትርጒም፦
ከኃጢአቴ ፊትህን መልስ፤
በደሌንም ሁሉ ደምስስልኝ፤
አቤቱ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ።
ምሥጢር፦
ከኃጢአቴ የተነሣ ገጸ መዓትህን ከእኔ መልሰው፤
ኃጢአቴን አስተሥርይልኝ፤
ንጹሕ ልቡናን ፍጠርልኝ፤ አሁን ሌላ ልቡና ፍጠርልኝ ማለት አይደለም ያንኑ ከኃጢአት ንጹሕ አድርግልኝ ሲል ነው።
ወንጌል፦ ዮሐ ፲፪፥፩ ߺ ፲፪፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
ኤፌ ፪፥፲፫ ߺ ፍጻሜ፤
፪ዮሐ ፩፥፩ ߺ ፰፤
ግብ ፯፥፵፬ ߺ ፶፩፤
ወንጌል፦ ሉቃ ፩፥፳፯ ߺ ፴፱፤
ቅዳሴ፦ ዘእግዚእነ
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
ወትቀውም ንግሥት በየማንከ፤
በአልባሰ ወርቅ ዑፅፍት ወኊርብት፤
ስምዒ ወለትየ ወርእዪ ወአጽምዒ ዕዝነኪ።
መጋቢት ፳፯ በዓለ ስቅለቱ ለመድኃኔ ዓለም
ዘነግህ ምስባክ፦
ተንሥኡ ላዕሌየ ሰማዕተ ዐዐመፃ፤
ወዘኢየአምር ነበቡ ላዕሌየ፤
ፈደዩኒ እኪተ ህየንተ ሠናይት። መዝ ፴፬፥፲፩፤ ትርጒሙንና ማብራሪያውን መስከረም ፲፩ ላይ ተመልከት።
ወንጌል፦ ሉቃ ፳፫፥፩ ߺ ፲፯፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
ዕብ ፲፪፥፪ ߺ ፲፰፤
፩ጴጥ ፫፥፲፭ ߺ ፳፤
ግብ ፲፥፴ ߺ ፵፤
ወንጌል፦ ማቴ ፳፯፥፩ ߺ ፶፭፤
ቅዳሴ፦ ዘዮሐንስ አፈወርቅ
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
እግዚብሔርሰ ንጉሥ ውእቱ እምቅድመ ዓለም፤
ወገብረ መድኃኒተ በማዕከለ ምድር፤
አንተ አጽናዕካ ለባሕር በኃይልከ። መዝ ፸፫፥፲፪፤
ትርጒም፦
እግዚአብሔር ግን ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነው፤
በምድርም መካከል መድኃኒትን አደረገ፤
አንተ ባሕርን በኃይልህ አጸናሃት።
ምሥጢር፦
እግዚአብሔር ለዘለዓለሙ ገዥ ነው፤
በማዕከለ ምድር ፍጥረተ ሰብእን አከናወነ፤ ቦ ትሩፋንን ከባቢሎን አውጥቶ ድኅነትን አደረገ፤ ቦ በማኅፀነ ማርያም ድኅነተ ምእመናንን አደረገ፤ ቦ በማዕከለ ምድር በኢየሩሳሌም ድኅነተ ምእመናን የሚሆን ስቅለትን አደረገ፤ አክሊላ ወሕንብርታ ለምድር ይላታልና፤
ውቅያኖስን ያጸናህ አንተ ነህ፤ እስከ ዝየ ብጽሒ ወኢትትድዐደዊ እምወሰንኪ ዳእሙ ይትከወስ ማዕበልኪ በውስቴትኪ ብለህ፤ ቦ ማኅፀነ ማርያም እንዲወሰንህ አደረግህ፤ ቦ ልጅነት በጥምቀት እንዲሰጥ አደረግህ፤ ቦ ዲያብሎስን በገሃነም ወሰንኸው።
መጋቢት ፳፱ በዓለ ፅንሰቱ ለእግዚእነ
ዘነግህ ምስባክ፦
አንሰ ተሠየምኩ ንጉሠ በላዕሌሆሙ፤
በጽዮን በደብረ መቅደሱ፤
ከመ እንግር ትእዛዞ ለእግዚአብሔር። መዝ ፪፥፮፤
ትርጒም፦
እኔ ግን በእነርሱ ላይ ንጉሥ ሆኜ ተሾምሁ፤
በተቀደሰ ተራራው በጽዮን ላይ፤
የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እናገር ዘንድ።
ምሥጢር፦
በጽዮንና በደብረ መቅደሱ አንድ ወገን፤ በሄኖን በቅሩበ ሳሌም እንዳለው ያለ ነው እነሱ ባያውቁ እሩቅ ብእሲ ወልደ ዮሴፍ ይሉኛል እንጂ እኔስ በማኅፀነ ማርያም ነግሻለሁ፤ ጽዮን አላት እመቤታችንን ፀወነ ሥጋ ፀወነ ነፍስ ፀወነ ጻድቃን ወኃጥአን ናትና፤ ደብር አላት ደብረ መቅደሱ ለአብ ደብረ መቅደሱ ለወልድ ደብረ መቅደሱ ለመንፈስ ቅዱስ ይላታልና፤ ደብረ መቅደስ አላት ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ማኅፀኗን ዓለም አድርጎ ተመስግኖባታልና “ድንግል ታደንን ርእሳ መንገለ ከርሣ ወትሰምዕ ድምፀ እመላእክት – ድንግል ራሷን ወደማኅፀኗ ዘንበል ታደርጋለች ከመላእክት ድምፅ ትሰማለች እንዲል።
ቦ እነሱ ባያውቁ አልብነ ንጉሥ ዘእንበለ ቄሣር ይሉኛል እንጂ እኔስ የአብርሃም ዕፃ በምትሆን ደብረ መቅደሱ በተሠራችባት በኢየሩሳሌም ነግሻለሁ፤ ምነው የጌታ መንግሥቱ በኢየሩሳሌም ብቻ ነውና እንዲህ አለ ቢሉ የጌታ መንግሥቱ መታመኑ ትምህርት ታምራት ሠርቶ አስቀድሞ በመቶ ሃያ ቤተሰብ የታመነበት በኢየሩሳሌም ነውና።
ቦ ባያውቁ ሰቅለን ገደልነው ፈርሶ በስብሶ ይቀራል ይሉኛል እንጂ እኔስ በመስቀል ነግሻለሁ፤ መንግሥት አለው መስቀልን የመንግሥት ሥራ ስለሠራበት፤ ደብረ መቅደሱ አለው ከዕለተ ዓርብ አስቀድሞ መላእክት በቀትር እየመጡ ያመሰግኑ ነበር
በዕለተ አርብ በመስቀል ተሰቅሎ አግኝተዉት በመስቀሉ ዙሪያ እንደሻሽ ተነጥፈው እንደ ቅጠል ረግፈው እንደ ግንድ ተረብርበው ለከ ኃይል ለከ ጽንዕ እያሉ አመስግነዉታልና። “ወቀፈፀ እምላዕሌሁ ምክዳነ ወርእየ ኃይላተ ሰማይ ድንጉፃነ በዐውደ መስቀሉ – ከአምላክነቱ ብርሃን ጥቂት ብርሃን ብልጭ አደረገለት መላእክትን በመስቀሉ ዙሪያ እንደሻሽ ተነጥፈው አየ አንድም ድኑናነ ይላል አምላክነ እያሉ ሲሰግዱ አየ” እንዲል፤
የእግዚአብሔር ሕጉ ወንጌልን አስተምር ዘንድ፤ እግዚአብሔር የሦስቱ ስም ነው፤ አንሰ ሶበ እቤ እግዚአብሔር እብል በእንተ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ – እኔ እግዚአብሔር ስል ስለ አብ ስለወልድ ስለ መንፈስ ቅዱስ እላለሁ፤ ከመ በአሐዱ ስም ሥሉሰ ያምልኩ – በአንዱ ስም ሦስቱንም ያመልኩ ዘንድ እንዲል፤
ሕጊቱ የሦስቱም ናት የአብ እንደሆነች ሲያጠይቅ ትምህርትየሰ ኢኮነት እንቲአየ አላ እንቲአሁ ለዘፈነወኒ – ትምህርቴ ከላከኝ ናት እንጂ ከኔ አይደለችም” ይላል ዮሐ ፯፥፲፮
የወልድ እንደሆነች ሲያጠየቅ አንሰ እብለክሙ ይላል ማቴ ፭፥፳፭
የመንፈስ ቅዱስ እንደሆነች ሲያጠይቅ “ወመጺኦ ውእቱ መንፈሰ ጽድቅ ይመርሐክሙ ኀበ ኵሉ ጽድቅ ወዘይመጽእሂ ይነግረክሙ – የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደእውነት ይመራችኋል… የሚመጣውንም ይነግራችኋል” ዮሐ ፲፮፥፲፫
ቦ አነ ወአብ አሐዱ ንሕነ ብየ የአንድነታችንን ምሥጢር አስተምር ዘንድ ዮሐ ፲፥፴
አንድም “ጽንዑ እስመ አነ ሞእክዎ ለዓለም ብየ አስተምር ዘንድ ዮሐ ፲፮፥፴፫
ወንገል፦ ሉቃ ፩፥፳፮ – ፴፱፤
ዘቅዳሴ ምንባብ፦
ዕብ ፩፥፩ – ፍጻሜ፤
፩ጴጥ ፩፥፲፫ – ፳፪፤
ግብ ፲፯፥፲፫ – ፴፤
ወንጌል፦ ፩፥፩ – ፲፭፤
ቅዳሴ፦ ዘእግዝእትነ ማርያም
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
አንተ እግዚኦ አቅደምከ ሣርሮታ ለምድር፤
ወግብረ እደዊከ እማንቱ ሰማያት፤
እማንቱሰ ይትኀጐላ ወአንተሰ ትሄሉ። መዝ ፻፩፥፳፭፤
ትርጒም፦
አቤቱ አንተ አስቀድመህ ምድርን መሠረትህ፤
ሰማያት የእጅህ ሥራ ናቸው፤
እነርሱ ይጠፋሉ አንተ ግን ትኖራለህ።
ምሥጢር፦
አቤቱ ምድርን አስቀድመህ የፈጠርህ አንተ ነህ፤ ሰማይን በኋላ ፈጠረ ማለት አይደለም በዕለተ ፍጥረት ከዚህ እስከ ብሩህ ሰማይ መልቶ ይዞት ነበር ለይኵን ባለ ጊዜ ከሦስት እጅ ተከፍሏል ያን ጊዜ ምድር ታይታለች ሰማይ አልታየምና፤ ቦ ዛሬ ምድር ትታያለች ሰማይ አይታይምና፤
ሰማይ ምድር የሥልጣንህ ፍጥረቶች ናቸው፤
ሰማይ ምድር ያልፋሉ አንተ ግን ለዘለዓለሙ ጸንተህ ትኖራለህ።
ቦ ሥጋን ከነፍስ አስቀድመህ ፈጠርህ፤ ንግበር ሰብአ በአርአያነ ወበአምሳሊነ እንዲል፤ የነፍስና የሥጋ ተፍጥሯቸው አንድ ጊዜ አይደለምን ቢሉ የነፍስ ተፈጥሮ እምኀበ አልቦ ነው ያሉ እንደሆነ የተመቸ፤ ምንም ሥጋ የተፈጠረ በዕለተ ዓርብ ቢሆንም የሥጋ ምክንያት የሚሆኑ አራቱ ባሕርያት የተፈጠሩ እሑድ ነውና፤ ግብር እምግብር ነው ያሉ እንደሆነ ለነገር፤ ከነገር አካል ይቀድማና፤
ነፍሳት የቃልህ ፍጥረት ናቸው፤
ነፍሳት ይጠፋሉ አንተ ግን ለዘለዓለም ጸንተህ ትኖራለህ፤ አባ ለትጹን እንዳሳሿት/እንዳስጠፏት ነፍስ፤ በነፍስስ ጥፋት የለባትም ብሎ ከኃሣርም ከክብርም አልደረሰችም፤ ይህስ መቼ ይሆናል? ከኃሣር ከወጡ መንግሥተ ሰማያት መግባት ነው ከክብርም ከወጡ ገሃነም መውረድ ነው ሦስት ቦታ የለ ኢዘከረ መጽሐፍ አምላካዊ ሠለስተ መካናተ ይላል በኃጢአት መለወጧን ሲያይ፤ ቦ መለያየት የጋራ ከሆነ ብሎ።
፴፱ ቦአ ኢየሱስ
መዝሙር ዘምኵራብ
፴፱.፩ (በ፭/ር) ቦአ ኢየሱስ ምኵራበ አይሁድ ወመሐረ ቃለ ሃይማኖት ወይቤሎሙ ምጽዋተ አበድር እመሥዋዕት አነ ውእቱ እግዚኣ ለሰንበት ወአቡሃ ለምሕረት እግዚኣ ውእቱ ለሰንበት ወልደ እጓለ እመሕያው ኢትግበሩ ቤተ አቡየ ቤተ ምሥያጥ ቤትየሰ ቤተ ጸሎት ይሰመይ ቦአ ምኵራቦሙ ወገሠጾሙ ያርምሙ አንከሩ ምሕሮቶ ሞገሰ ቃሉ ወጣዕመ ነገሩ ወሣዕሣዐ አፉሁ።
ትርጉም፦
ኢየሱስ ወደ አይሁድ ምኵራብ ገባ የሃማኖት ትምህርትን አስተማረ ከመሥዋዕት ይልቅ ምጽዋትን እወዳለሁ አላቸው የሰንበት ጌታ የይቅርታ አባት እኔ ነኝ የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነው የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች ወደምኵራባቸው ገባ ዝም ይሉ ዘንድም ገሠጻቸው ትምህርቱን የቃሉን ሞገስ የነገሩን ጣዕም የአንደበቱን ቅልጥፍና አደነቁ።
፴፱.፪ የዕለቱ ምንባባት፦
ቈላ ፪፥፲፮ – ፍጻሜ፤
ያዕ ፪፥፲፬ – ፍጻሜ፤
ግብ ፲፥፩ – ፱፤
ወንጌል፦ ዮሐ ፪፥፲፪ – ፍ፤
ቅዳሴ፦ ዘእግዚእነ
፴፱.፫ የዕለቱ ምስባክ፦
እስመ ቅንዓተ ቤትከ በልዐኒ፤
ትእይርቶሙ ለእለ ይትዔየሩከ ወድቀ ላዕሌየ፤
ወቀጻዕክዋ በጾም ለነፍስየ። መዝ ፷፰፥፱
ትርጉም፦
የቤትህ ቅናት በልቶኛልና፤
የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቋልና፤
ሰውነቴን በጾም አደከምኋት።
ምሥጢር፦
በቤተ መቅደስህ ሥዕለ ፀሐይ አቁመዉበት መሥዋዕተ እሪያ ሠውተዉበት ዓይቼ የቀናሁት ቅናት እንደእሳት ፈጅቶኛልና አቃጥሎኛልና፤
አንተን የተገዳደሩህ ተግዳሮት በእኔ ደረሰ ማለት ሥዕለ ፀሐይ አቁመው መሥዋዕተ እሪያ ሠውተው እንደተገዳደሩህ እኔንም ለሥዕለ ፀሐይ ስገድ መሥዋዕተ እሪያ ብላ ብለው ተገዳደሩኝ።
አንድም በቤተ መቅደስህ ገበያ አቁመዉበት ዓይቼ የቀናሁት ቅናት እንደ እሳት አቃጥሎኛልና፤
አንተን በቤተ መቅደስህ ገበያ አድርገው እንደተገዳደሩህ እኔም ገበያቸውን ብትፈታባቸው መኑ አብሐከ ትግበር ዘንተ – ይህን ታደርግ ዘንድ ሥልጣን ማን ሰጠህ ብለው ተገዳደሩኝ።
አንድም አንተን በደብረ ኮሬብ በደብተራ ኦሪት ሁለት እጓላተ ላህም አቁመው እንደተገዳደሩህ እኔንም አቡየ ፈነወኒ ወአነ ተፈኖኩ – አባቴ ልኮኝ መጣሁ ብላቸው በእፎ ይብለነ እምሰማይ ወረድኩ እንዘ ለሊነ ነአምር አባሁ ወእሞ – አባቱን እናቱን እያወቅናቸው እንዴት ከሰማይ መጣሁ ይለናል ብለው ተገዳደሩኝ።
አንድም መና ከደመና አውርደህ ብትመግባቸው ምንት ጣዕሙ ለዝ መና – የዚህ መና ጣዕሙ ምንድነው? ይክልኑ እግዚአብሔር ሠሪዐ ማዕድ በገዳም ወይክልኑ ውሂበ ኅብስት ይዝብጥ ኰኵሐ ወያውኅዝ ማየ – እግዚአብሔር ማእድ ሠርቶ ምግብ መስጠት ይችላልን ደንጊያውን መትቶ ውኃ ማፍለቅ ይችላልን ብለው አንተን እንደተገዳደሩህ እኔንም እመ ኢበላዕክሙ ሥጋሁ ለወልደ እጓለ እመሕያው ወኢሰተይክሙ ደሞ አልብክሙ ሕይወት – የወልደ እጓለ እመሕያው ክርስቶስን ሥጋውን ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ ሕይወት የላችሁም ብላቸው በእፎ ይክል የሀበነ ሥጋሁ ከመ ንብላእ – እንበላ ዘንድ ሥጋውን እንዴት ሊሰጠን ይችላል ብለው ተገዳደሩኝ።
አንድም እመሰ ወልደ እግዚአብሔር ለያድኅኖ – የእግዚአብሔር ልጅ ከሆነ እስቲ ያድነው ብለው አንተን እንደተገዳደሩህ እኔንም እመሰ ወልደ እግዚአብሔር አንተ ረድ እስኩ እመስቀልከ ንርአይ ወንእመን ብከ – የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ እስቲ ከመስቀልህ ውረድ አይተን እንመንብህ ብለው ተገዳደሩኝ።
አንድም አንተን ኤልያስ እንዳሉህ እኔንም እሩቅ ብእሲ ወልደ ዮሴፍ አሉኝ።
ሰውነቴን በጾም በቀጠና በስልት አደከምኋት።
፵ አምላኩሰ ለአዳም
መዝሙር ዘመጻጒዕ
፵.፩ (በ፭/ር) አምላኩሰ ለአዳም ለዕረፍት ሰንበተ ሠርዐ ወይቤልዎ አይሁድ በአይ ሥልጣን ትገብር ዘንተ ወይቤሎሙ ኢየሱስ አነኒ እገብር አንትሙኒ እመኑ ለግብርየ ወይቤሎሙ አነ ውእቱ እግዚኣ ለሰንበት እግዚኣ ውእቱ ለሰንበት ወልድ ዋሕድ ወይቤሎሙ ብውሕ ሊተ እኅድግ ኃጢአተ በዲበ ምድር እስብክ ግእዛነ ወእክሥት አዕይንተ ዕውራን አቡየ ፈነወኒ።
ትርጒም፦
የአዳም ፈጣሪ ለዕረፍት ሰንበትን ሠራ አይሁድ ይህንን በማን ሥልጣን ታደርጋለህ ብለው ጠየቁት ኢየሱስም እኔ እሠራለሁ እናንተም ሥራዬን እመኑ የሰንበት ጌታ እኔ ነኝ አላቸው የሰንበት ጌታዋ ወልድ ዋሕድ ነው አላቸው በምድር ላይ ኃጢአትን እተው/ይቅር እል ዘንድ ሥልጣን አለኝ ነጻነትን እሰብክ ዘንድ የዕውራንን ዓይን አበራ ዘንድ አባቴ ላከኝ አላቸው።
፵.፪ የዕለቱ ምንባባት፦
ገላ ፭፥፩ – ፍ፤
ያዕ ፭፥፲፬ – ፍ፤
ግብ ፫፥፩ – ፲፫፤
ወንጌል፦ ዮሐ ፭፥፩ – ፳፭
ቅዳሴ፦ ዘእግዚእነ
፵.፫ የዕለቱ ምስባክ፦
እግዚአብሔር ይረድኦ ውስተ ዐራተ ሕማሙ፤
ወይመይጥ ሎቱ ኵሎ ምስካቤሁ እምደዌሁ፤
አንሰ እቤ እግዚኦ ተሣሃለኒ። መዝ ፵፥፫
ትርጉም፦
እግዚአብሔር በሕማሙ አልጋ ውስጥ ሳለ ይረዳዋል፤
መኝታውንም ከደዌው የተነሣ ይለውጥለታል፤
እኔስ አቤቱ ይቅር በለኝ እላለሁ።
ምሥጢር፦
ታሞ ሳለ በመኝታው ይረዳዋል ማለት ሕመሙን እንዲችለው ያደርጋዋል አንድም አስታማሚ ይሰጠዋል። እሳት በገል ውኃ በቅል ይዞ የሚረዳው ሰው ይሰጠዋል።
ከደዌው አድኖ ጤናውን ይመልስለታል ማለት የሠላሳ ስምንት ዓመቱን ሕመምተኛ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ይለዋል።
እኔ ግን ለይቅርታ ለፈውስ የሚያበቃ ሥራ የለኝምና ይቅር በለኝ እላለሁ።
፵፩ እንዘ ይነብር እግዚእነ
መዝሙር ዘደብረ ዘይት
፵፩.፩ (በ፭/ዩ) እንዘ ይነብር እግዚእነ ውስተ ደብረ ዘይት ወይቤሎሙ ለአርዳኢሁ ዑቁኬ ኢያስሕቱክሙ ወንበሩ ድልዋኒክሙ ብዙኃን ይመጽኡ በስምየ እንዘ ይብሉ አነ ውእቱ ክርስቶስ ወዘአዝለፈ ትዕግሥቶ ውእቱ ይድኅን ወአመ ምጽአቱሰ ለወልደ እጓለ እመሕያው ይትከወስ ኵሉ ኃይለ ሰማያት ወምድር አሜሃ ይበክዩ ኵሎሙ ኃጥአነ ምድር ወይወርድ እግዚእነ እምሰማይ ዲበ ምድር በትእዛዙ ወበቃሉ ወበአዕላፍ መላእክቲሁ በንፍሐተ ቀርን ዘእምኀበ እግዚአብሔር ይምሐረነ አብ በይእቲ ሰዓት እሞተ ኃጢአት እስመ ገባሬ ሕይወት ውእቱ እግዚኣ ለሰንበት።
ትርጒም፦
ጌታችን በደብረ ዘይት ተቀምጦ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው እወቁ እንዳያስቷችሁ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ ብዙዎች በስሜ ይመጣሉ ትዕግሥቱን ያዘወተረ እሱ ይድናል የሰው ልጅ በሚመጣ ጊዜ የሰማያትና የምድር ኃይል ይናወጣል ያን ጊዜ የምድር ኃጥአን ሁሉ ያለቅሳሉ ከእግዚአብሔር ታዞ በሚደረግ የመለከት መነፋት፣ በአዕላፍ መላእክት አጀብ፣ በትእዛዝና በቃል ጌታችን ከሰማይ ወደምድር ይወርዳል በዚያች ሰዓት ከኃጢአት ሞት (በኃጢአት ከሚመጣ ፍርድ) ይማረን የሰንበት ጌታ እሱ ሕይወትን የሚሰጥ ነውና።
፵፩.፪ የዕለቱ ምንባባት፦
፩ተሰ ፬፥፲፫ – ፍ፤
፪ጴጥ ፫፥፯ – ፲፭፤
ግብ ፳፬፥፩ – ፳፪፤
ወንጌል፦ ማቴ ፳፬፥፩ -፴፮
ቅዳሴ፦ ዘአትናቴዎስ
፵፩.፫ የዕለቱ ምስባክ፦
እግዚአብሔርሰ ገሃደ ይመጽእ፤
ወአምላክነሂ ኢያረምም፤
እሳት ይነድድ ቅድሜሁ። መዝ ፵፱፥፫
ትርጒም፦
እግዚአብሔር በግልጥ ይመጣል፤
አምላካችን ዝም አይልም፤
እሳት በፊቱ ይነዳል።
ምሥጢር፦
እግዚአብሔር በሰባ ዘመን በረድኤት ተገልጦ ይመጣል፤
መጥቶም ዝም አይልም በበጎዎቹ አድሮ ይፈርዳል አንድም በበጎዎቹ ካህናት አድሮ ክፉዎችን ካህናት ይዘልፋል።
እሳት በፊቱ ይነዳል ማለት ክፉዎች የሚጠፉበትን መቅሠፍት መናገር ነው።
አንድም እግዚአብሔር አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም በሥጋ ማርያም ይገለጣል።
መጥቶ ዝም አይልም ወንጌልን ያስተምራል አንድም አሌ ለክሙ ጸሐፍት ወፈሪሳውያን – ጻፎችና ፈሪሳውያን ወዮላችሁ እያለ ይዘልፋል
አይሁድ የሚጠፉበት መቅሠፍት በፊቱ ነው።
አንድም በዕለተ ምጽአት የተወጋበትን ኲናት/ጦር የተቸነከረበትን ቀኖት አስይዞ ይመጣል።
ጻድቃንን ንዑ ኀቤየ ብሎ ይጠራል ኃጥአንን ሑሩ እምኔየ ብሎ ያሰናብታል።
ጻድቃን የሚድኑበት ሕይወት ኃጥአን የሚቀጡበት መቅሠፍት በፊቱ አለ።
፵፩.፬ መልእክት ስለ ደብረ ዘይት በመጠኑ፦
አምስተኛው የዓቢይ ጾም ሰንበት ነው።
የዘይት ተራራ (የወይራ ዛፍ ያለበት) ማለት ነው።
ዳዊት መዝሙር ፳፩ን እየጸለየና እያዘነ ያለ ጫማ የወጣበት ተራራ ነው።፪ሳሙ ፲፭፥፴፤
ምሥጢረ ምጽአቱ የተነገረበት ተራራ ነው። ማቴ ፳፬፥፫፤
ቅዱሳን ሐዋርያት ልዩ ምስጋና ያቅረቡበት ተራራ ነው። ሉቃ ፲፱፥፴፯፤
ጌታችን ያድርበት የነበረ ተራራ ነው። ሉቃ ፳፩፥፴፯፤
ምሥጢረ ዕርገቱ የታየበት ተራራ ነው። ግብ ፩፥፲፫፤
፵፪ መኑ ውእቱ
መዝሙር ዘገብር ኄር
፵፪.፩ (በ፭/ር) መኑ ውእቱ ገብር ኄር ወምእመን ዘይረክቦ እግዚኡ በምግባረ ሠናይ ወይሠይሞ ዲበ ኵሉ ንዋዩ ካዕበ ይቤሎ እግዚአብሔር ገብር ኄር ወምእመን ዘበውኁድ ምእመነ ኮንከ ዲበ ብዙኅ እሠይመከ ባዕ ውስተ ፍሥሐሁ ለእግዚእከ።
ትርጉም፦
ጌታው በበጎ ሥራ የሚያገኘውና ባለው ገንዘቡ ሁሉ ላይ የሚሾመው ቸርና ታማኝ አገልጋይ ማነው? ዳግመኛ እግዚአብሔር እንዲህ አለው በጥቂቱ የታመንህ አንተ ቸር አገልጋይ በብዙ እሾምሃለሁ ወደጌታህ ደስታ ግባ።
፵፪.፪ የዕለቱ ምንባባት፦
፪ጢሞ ፪፥፩ ፲፯፤
፩ጴጥ ፭፥፩ – ፲፪፤
ግብ ፩፥፮ – ፱፤
ወንጌል፦ ማቴ ፳፭፥፲፬ – ፴፩
ቅዳሴ፦ ዘባስልዮስ
፵፪.፫ የዕለቱ ምስባክ፦
ከመ እንግር ፈቃደከ መከርኩ አምላኪየ፤
ወሕግከኒ በማዕከለ ከርሥየ፤
ዜኖኩ ጽድቀከ በማኅበር ዓቢይ። መዝ ፴፱፥፰
ትርጉም፦
አምላኬ ሆይ ፈቃድህን ለማድረግ መከርሁ፤
ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው፤
በታላቅ ጉባኤ ጽድቅህን አወራሁ።
ምሥጢር፦
አቤቱ ፈጣሪዬ ወደህ የሠራሃትን ሕግ አስተምር ዘንድ ወደድሁ፤ አንድም መጥዎተ ርእስን (ራስን ለባንጀራ አሳልፎ መስጠትን) አደርግ ዘንድ ወደድሁ፤
ሕግህ በልቡናዬ ተጽፎ ይኖራል አለ ሁል ጊዜ አስበዋለሁ ሲል ነው፤
ቸርነትህን ለብዙ ጉባኤ ነገርሁ።
፵፫ ሖረ ኀቤሁ
መዝሙር ዘኒቆዲሞስ
፵፫.፩ (በ፭/ር) ሖረ ኀቤሁ ዘስሙ ኒቆዲሞስ ወይቤሎ ለኢየሱስ ረቢ ሊቅ ንሕነ ነአምን ብከ ከመ እምኀበ አብ መጻእከ ከመ ትኩን መምህረ እጓለ አንበሳ ሰከብከ ወኖምከ አንሥአኒ በትንሣኤከ።
ትርጉም፦
ስሙ ኒቆዲሞስ የሚባል ሰው ወደኢየሱስ ሄዶ መምህር! ታላቅ መምህር ሆነህ ታስተምረን ዘንድ ከአብ ዘንድ እንደመጣህ እኛ እናምንብሃለን አንተ የአንበሳ ደቦል ክርስቶስ ሸምቀህ ትነሣለህ (ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር አድረህ ትነሣለህ) በትንሣኤህ አንሣኝ።
፵፫.፪ የዕለቱ ምንባባት፦
ሮሜ ፯፥፩ – ፲፪፤
፩ዮሐ ፬፥፲፰ – ፍ፤
ግብ ፭፥፴፬ – ፍ፤
ወንጌል፦ ዮሐ ፫፥፩ – ፲፪
ቅዳሴ፦ ዘእግዝእትነ ማርያም
፵፫.፫ የዕለቱ ምስባክ፦
ሐወፅከኒ ሌሊተ ወፈተንኮ ለልብየ፤
አመከርከኒ ወኢተረክበ ዓመፃ በላዕሌየ፤
ከመ ኢይንብብ አፉየ ግብረ እጓለ እመሕያው። መዝ ፲፮፥፫
ትርጉም፦
በሌሊት ጎበኘኸኝ ልቤንም ፈተንኸው፤
ፈተንኸኝ ዓመፅ አልተገኘብኝም፤
የሰውን ሥራ አፌ እንዳይናገር።
ምሥጢር፦
በሌሊት ጠላቴን ከእጄ ላይ ጠለህ ይገድለው ይሆን አይሆን ብለህ መረመርኸኝ።
ብትመረምረኝ በእጄ መግደል በቃሌ መበደል በልቡናዬ ቂም በቀል አልተገኘብኝም።
ሰው ሰውኛውን ነገር እንዳልናገር። አንድም ግብረ እደ እጓለ እመሕያው ይላል ሰው በቃሉ ፈክሮ ዘምሮ የሚያደርገውን እንዳላደርግ። ጠላትህ ዕገሌን አግኝቸው ነበር አንተ አግኝተኸው ቢሆን ምን ታደርገው ነበር? ይለዋል። የመቼውን! የዘነጋሁትን! አግኝቼውማ ቢሆን አብልቼ አጠጥቼ በሰደድሁት ነበር ይለዋል ቢያገኘው ላይተወው። እሱ ግን ሳኦልን ከአንድ ሁለት ጊዜ አግኝቶ ትቶታልና።
፵፬ ወእንዘ ሰሙን
መዝሙር ዘሆሣዕና
፵፬.፩ (በ፭/ር) ወእንዘ ሰሙን በዓለ ፋሲካ ቀርቡ አርዳኢሁ ለአምላከ ጽድቅ ኀበ ደብረ ዘይት ሙራደ ዐቀብ ሀገረ እግዚአብሔር ወተቀበልዎ ሕዝብ ብዙኃን አዕሩግ ወሕፃናት ነሢኦሙ አዕፁቀ በቀልት እንዘ ይብሉ ሆሣዕና በአርያም ተፅዒኖ ዲበ ዕዋል ቦአ ሀገረ ኢየሩሳሌም በትፍሥሕት ወበሐሤት ይሁቦሙ ኃይለ ወሥልጣነ።
ትርጕም፦
የፋሲካ በዓል ሰሞን ሲሆን ደቀመዛሙርቱ በእግዚአብሔር ሀገር በደብረ ዘይት በዐቀበቱ መውረጃ ወደእውነተኛ አምላክ ቀረቡ ብዙ ወገኖች ሽማግሌዎችና ሕፃናት የዘንባባ ቅጠሎችን ይዘው ሆሣዕና በአርያም እያሉ ተቀበሉት በአህያይቱ ግልገል ላይ ተቀምጦ በደስታና በሐሤት ወደኢየሩሳሌም ገባ ኃይልና ሥልጣንን ይሰጣቸዋል።
፵፬.፪ የዕለቱ ምንባባት፦
ዕብ ፱፥፲፩ – ፍጻሜ፤
፩ጴጥ ፬፥፩ – ፲፪፤
ግብ ፳፰፥፲፩ – ፍጻሜ፤
ወንጌል፦ ዮሐ ፭፥፲፩ – ፴፩፤
ቅዳሴ፦ ዘጎርጎርዮስ
፵፬.፫ የቅዳሴ ምስባክ፦
ቡሩክ ዘይመጽእ በስመ እግዚአብሔር፤
ባረክናክሙ እምቤተ እግዚአብሔር፤
እግዚአብሔር እግዚእ አስተርአየ ለነ። መዝ ፻፲፯፥፳፮፤
ትርጒም፦
በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው፤
ከእግዚአብሔር ቤት መረቅናችሁ፤
ጌታ እግዚአብሔር ተገለጠልን።
ምሥጢር፦
በእግዚአብሔር ስም አምኖ የሚመጣ ዘሩባቤል የከበረ ነው፤ ቦ በእግዚአብሔር አብ ስም የሚመጣ ወልድ ክቡር ምስጉን ነው፤ አቡየ ፈነወኒ ወአነ ተፈኖኩ – አባቴ ላከኝ እኔም መጣሁ ብሎ፤ ቦ አብ መስክሮለት የሚመጣ ወልድ ክቡር ምስጉን ነው፤ ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ብሎ፤ ቦ የእግዚአብሔርነቱን ስም ጠርቶ የሚመጣ ወልድ ክቡር ምስጉን ነው፤
ከቤተ እግዚአብሔር በተገኘው ረድኤት አከበርናችሁ ይላሉ ነቢያት ካህናት፤ ቦ በንፍሐት በተገኘ ሥልጣነ ክህነት አከበርናችሁ ይላሉ ሐዋርያት፤
እግዚአብሔር በሰባ ዘመን ሚጠተ ሥጋውን በማድረግ ተገለጠ፤ ቦ በአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን በልብሰተ ሥጋ ተገለጠ።
ሥርዐተ ዑደት ዘሆሣዕና
መሪ ዕዝል ቦአ ኢየሱስን ይምራ፤ ተመሪ ይመራ፤ ግራና ቀኝ በኅብረት ዝለቅ፤ መሪ ወበልዋ ብሎ ያመልጥን፤ ዕዋሎ ወአድጎ ብለህ ተቀበል፤ አንሺ ያንሣ፤ ሁለተኛ አንሺ ያንሣ፤ ወበልዋ ብለህ በዝማሜ ዘልቀህ ተው፤ አልቦ ከበሮ፤ ይህ ስብሐተ ነግህ ይባላል። ከዚህ በኋላ ኦሪት አንብብ፤ ሠራዒ ካህን መስቀልና ማዕጠንት፣ ንፍቅ ካህን ፀበርት፣ ሠራዒ ዲያቆን መስቀልና ወንጌል፣ ንፍቅ ዲያቆን ጥላ ይዘው በዐቢይ ዜማ እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ እያሉ ዑደት ያደርጋሉ፤ እግዚኦታው ሦስት ጊዜ ነው።
ልኡካን ቅድመ ገጸ መንጦላዕት ዘቤተ መቅደስ (በበሩ መጋረጃና በመንበሩ መካከል የሚሆን መጋረጃ ነው) ቆመው ዲያቆን ዕብ ፱፥፲፩፤ ንፍቅ ዲያቆን ፩ጴጥ ፬፥፩፤ ንፍቅ ካህን ግብ ፳፰፥፲፩፤ ዲያቆን ምስባክ ተፈሣሕኩ ይበል፤ አያይዞ ቁሙ ወአጽምኡ ይበል፤ ይ.ካ ወንጌል ዘማቴዎስ ማቴ ፱፥፱ ያንብብ፤ ይህን እንደ ጨረሱ ከቤተ መቅደስ ወደቅድስት ይውጡ፤ ቅድስት የሚለው የመቅደሱን በር ነው፤ ምስባክ ቡሩክ ዘይመጽእ ይበል ዲያቆን፤ ወንጌል ማቴ ፳፥፳፱ ያንብብ፤ ህየንተ ምዕዋድ መሪ አቡን አርእዩነ ፍኖቶን ይምራ፤ ግራና ቀኝ ንሺ አለው፤ ህየንተ ምዕዋድ ያለው ለምዕዋድ የሚሆን ቦታ ስለሌለ ነው፤ እስመ ዋካ እያሉ ተመልሰው ወደ ቤተ መቅደሱ ይግቡ።
ይ.ካ እንበለ ደዌ ብሎ አቡነ ዘበሰማያት ይስጥ፤ ፀበርቱን ባርኮ ለሁሉም ያድል፤ መስቀል እየተሳለሙ ይቀበሉ፤ ጥንተ መሪ መቶ ዐሥራ ሰባተኛውን መዝሙር ያስተዛዝል፤ ታቦቱን ሦስት ጊዜ ዞረው ወደምዕራብ ይሂዱ፤ ይህም የቅድስቱ ምዕራብ ነው፤ ወይም ድርገት መውረጃው ነው፤ ምስባክ ንፍሑ ቀርነ በል፤ ወንጌል ማቴ ፳፩፥፩ን አንብብ፤ አቡን ሰመያ አብርሃምን በል፤ ሶበ ተዘከርናሃ እያሉ ወደደቡብ ይሂዱ ይህም የቅድስቱ ምቅዋመ አንስት ነው፤ ምስባክ እምአፈ ደቂቅ በል፤ ወንጌል ማር ፲፩፥፩ አንብብ፤ አቡን ወትቤ ጽዮን በል፤ ይብሉ ሆሣዕና እያሉ ወደምሥራቅ ይሂዱ፤ ይህም የቅድስቱ ምሥራቅ ነው፤ ምስባክ እምሥራቀ ፀሐይ በል፤ ወንጌል ሉቃ ፲፱፥፳፰ አንብብ፤ አቡን ባረኮ በል፤ ይብሉ ሆሣዕና እያሉ ወደ ሰሜን ይሂዱ ይህም ምቅዋመ እደው ነው፤ የቅዳሴ መግቢያም ነው፤ ምስባክ ይትፌሥሓ አድባረ ጽዮን በል፤ ወንጌል ዮሐ ፲፪፥፲፪ አንብብ፤ ጥንተ መሪ አቡን ባኡን ይምራ፤ ግራ ቀኝ አንሣ፤ ምልጣኑን ዝመም ጸንጽል ጽፋ፤ ፍትሕዎን እያሸበሸብህ ወደ ቅኔ ማኅሌት ሂድ፤ ይህም ምዕራባዊው ክፍል ነው፤
በዚህ ስፍራ የመዝሙር መሪ ያለተሣሃልከ ሃሌ ሉያ ብሎ አልጺቆ ኢየሱስን ይምራ፤ ግራ ቀኝ በል፤ በሦስተኛው ዝመም፤ አመልጥን፤ ግራ ቀኝ አንሣ፤ ዝመም ጸንጽል ጽፋ፤
ማሳሰቢያ፦ የቤተ መቅደሱ አሠራር ክብ ሆኖ ባለሦስት ክፍል ካልሆነ እዚህ በተገለጠው መንገድ ለማከናወን ይቸግር ይሆናል፤ የምሥራቁን ወደመቅደስ ተመልሰው ገብተው የሚያደርሱ አሉ፤
የዑደቱ ሥርዐት ከተፈጸመ በኋላ ንፍቁ ዲያቆን መሶበ ወርቁን አክብሮ ሠራዒው ዲያቆን ደሙንና ቃለ ዓዋዲውን ይዞ ንፍቅ ካህን መስቀልና ማዕጠንት ይዞ ከቤተ ልሔም መጥተው በምዕራብ በኩል ከቤተ መቅደሱ በር ይቆማሉ፤ ዲያቆን አርኅዉ ይላል፤ ካህኑ ከመቅደስ ፊቱን ወደምዕራብ አድርጎ መኑ ውእቱ ይላል፤ መልሶ ዲያቆኑ አርኅዉ ይላል፤ አሁንም ካህኑ መኑ ውእቱ ይላል፤ በሦስተኛው ዲያቆኑ እግዚአብሔር አምላከ ኃያላን ብሎ አያይዞ አርኅዉ ይላል፤ ካህኑም ይባእ ንጉሠ ስብሐት ይባእ አምላከ ምሕረት ብሎ የመቅደሱን መጋረጃ ይገልጠዋል ይገባሉ፤ ካህናቱም ይባእ ንጉሠ ስብሐት እያሉ ያሸበሽባሉ። ሥርዐተ ቅዳሴው ይቀጥላል።
ድኅረ ቅዳሴ፦ መዝሙረ ዳዊት፣ ውዳሴ ማርያም፣ መልክአ ማርያም፣ መልክአ ኢየሱስ ይደገማል፤ ኑዛዜ ይሰጣል፤ ከልኡካኑ በቀር ሕዝቡ ሁሉ ተቀምጠው ጸሎተ ፍትሐት ይጀመራል፤ ይ.ካ በእንተ እለ ኖሙ ይላል፤ ፍትሐት ዘወልድ ጸሎተ ንስሐ ድግም፤ ከዚያ ሠርሖተ ሕዝብ ይደረጋል።
ዕዝል፦
ቦአ ኢየሱስ ኢየሩሳሌም በስብሐት በዕለተ ሰንበት ወበልዋ ለወለተ ጽዮን ነዋ ንጉሥኪ በጽሐ ዘዕሤቱ ምስሌሁ ወምግባሩ ቅድመ ገጹ ዘየሐጽብ በወይን ልብሶ የዓሥር ዲበ ዘይት ዕዋለ አድጉ።
ትርጒም፦
ኢየሱስ በዕለተ ሰንበት በምስጋና ወደ ኢየሩሳሌም ገባ ለጽዮን ልጅ እነሆ ንጉሥሽ መጣ በሏት ዋጋው ከእሱ ጋር ነው ሥራውም በፊቱ ነው ልብሱን በወይን የሚያጥብ ነው የአህያውን ውርንጫ በዘይት ያሥራል።
ምልጣን፦
ወበልዋ ለወለተ ጽዮን ነዋ ንጉሥኪ በጽሐ ዘዕሤቱ ምስሌሁ ወምግባሩ ቅድመ ገጹ ዘየሐጽብ በወይን አልባሲሁ ወበደመ አስካል ዐፅፎ የዓሥር ዲበ ዘይት ዕዋሎ ወአድጎ።
በምዕዋድ ጊዜ የሚባሉ ምስባኮችና አቡኖች፤
፩ ተፈሣሕኩ እስመ ይቤሉኒ ቤተ እግዚአብሔር ነሐውር፤
ወቆማ እገሪነ ውስተ አዕፃድኪ ኢየሩሳሌም፤
ኢየሩሳሌምሰ ሕንጽት ከመ ሀገር። መዝ ፻፳፩፥፩፤
ትርጒም፦
ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ ስላሉኝ ደስ አለኝ፤
ኢየሩሳሌም ሆይ እግሮቻችን በአደባባዮችሽ ቆሙ፤
ኢየሩሳሌምስ እንደ ከተማ የታነጸች ናት።
ምሥጢር፦
ስለትሩፋን ተናግሮታል፤ በአርእስቱ በእንተ ሐረስተ ምድር የሚል ተጽፎ ይገኛል፤ የእሸቱን ቀዳምያት ይዞ ወደ ቤተ እግዚአብሔር ይሄዳል ይወጣል ከኦሪቱ አቡየ ወጽአ እምካራን የሚል አለ የተማረ እንደሆነ ይህንን አስደግሞ ለሊቀ ካህናቱ ይሰጠዋል ያልተማረ ጨዋ የሆነ እንደሆነ ሊቀ ካህናቱ ተቀብሎ ይህንና ሌሎቹን እንደ አቡነ ዘበሰማያት ደግሞ ይሰደዋል፤ ነቢያት ካህናት የእግዚአብሔር ማደሪያ ወደምትሆን ወደ ኢየሩሳሌም እንሄዳለን ብለዉኛልና ደስ አለኝ፤
ኢየሩሳሌም! እግሮቻችን በአደባባዮችሽ ቆመዋልና ደስ ደስ አለኝ፤ ሳይደረግ እንደተረገ ሆኖ እየታየው እንዲህ አለ፤ ቦ ነሐውር ወይቀውማ እገሪነ ይላል አብነት ካህናት ወደ ኢየሩሳሌም እንሄዳለን እግሮቻችን በኢየሩሳሌም አደባባይ ይቆማሉ ብለዉኛልና ደስ አለኝ፤
ኢየሩሳሌምኒ ይላል ኢየሩሳሌምም ኢየሩሳሌምስ ከመ ሀገርናሃ እንደ ቀደመ ሀገርነቷ በዘር በተክል የታነጸች ናት።
ወንጌል ዮሐ ፱፥፩ – ፵፩፤
አቡን፦(በ፪/ኒ) አርእዩነ ፍኖቶ ወንሑር ቤቶ እስመ እምጽዮን ይወጽእ ሕግ ወቃለ እግዚአብሔር እምኢየሩሳሌም ንሳለማ ለመድኃኒትነ በትፍሥሕት ተቀበልዋ ለታቦት እስመ ዋካ ይእቲ ወብርሃን – ወደቤቱ እንሄድ ዘንድ መንገዱን አሳዩን ከጽዮን ሕግ ይወጣልና የእግዚአብሔርም ቃል ከኢየሩሳሌም፤ መድኃኒታችንን በደስታ እንሳለማት ታቦትን ተቀበሏት ፈጽማ ብርሃን ናትና።
ምልጣን፦ ንሳለማ በል
ምዕዋድ፦ እስመ ዋካ ይእቲ ወብርሃን ዋካ ይእቲ ወብርሃን።
፪ ንፍሑ ቀርነ በዕለተ ሠርቅ፤
በዕምርት ዕለት በዓልነ፤
እስመ ሥርዓቱ ለእስራኤል ውእቱ።
ትርጒም፦
በመባቻ ቀን መለከትን ንፉ፤
በታወቀችው በዓላችን ቀን፤
ለእስራኤል ሥርዓቱ ነውና።
ምሥጢር፦
በሠርቀ ወርኅ ቀን ነጋሪት ምቱ፤ ቦ በዕለተ ሆሣዕና በዕለተ ትንሣኤ ነጋሪት ምቱ፤
በታወቀች በዓላችን በበዓለ ፍሥሕ፣ በበዓለ ሰዊት፣ በበዓለ መጸለት፤ ቦ በታወቀች በዓላችን በሆሣዕና በትንሣኤ፤
በሠርቀ ወርኅ ነጋሪት መምታት ለእስራኤል ሥርዓቱ ነውና፤ ቦ በሆሣዕና በትንሣኤ ነጋሪት መምታት ለእስራኤል ሥርዓቱ ነውና።
ወንጌል ማቴ ፳፩፥፩ – ፲፮፤
አቡን፦ (በ፮/ዩ) ሰመያ አብርሃም ወይቤላ ዛቲ ዕለት በዓለ እግዚአብሔር ንፍሑ ቀርነ በዕለተ ሠርቅ በዕምርት ዕለት በዓልነ ሶበ ተዘከርናሃ ለጽዮን – አብርሃም ሰየማት ይህች በዓል የእግዚአብሔር በዓል ናት አላት በመባቻ ቀን መለከትን ንፉ በታወቀች በዓላችን፤ ጽዮንን ባሰብናት ጊዜ።
ምልጣን፦ ንፍሑ ቀርነ በል
ምዕዋድ፦ ሶበ ተዘከርናሃ ለጽዮን ሶበ ተዘከርናሃ ለጽዮን።
፫ እምአፈ ደቂቅ ወሕፃናት አስተዳሎከ ስብሐተ፤
በእንተ ጸላኢ፤
ከመ ትንሥቶ ለጸላኢ ወለገፋዒ። ትርጒምና ምሥጢሩን ታኅሣሥ ሃያ አራት ላይ ተመልከት።
ወንጌል፦ ማር ፲፩፥፩ – ፲፮፤
አቡን፦ (በ፮/ያ) ወትቤ ጽዮን አርኅዉ ሊተ አናቅጸ ይባኡ ሕዝብ ብዙኃን ወያዕትቱ ዕብነ እምፍኖት ለንጉሥ ለወልደ ዳዊት ንጉሦሙ ለእስራኤል ውእቱ ይብሉ ሆሣዕና በአርያም – ብዙ ወገኖች ይገቡ ዘንድ ጽዮን በሮቹን ክፈቱልኝ ትላለች ለዳዊት ልጅ ለንጉሥ ከመንገድ ድንጋዩን ያስወግዱ የእስራኤል ንጉሣቸው ነው ሆሣዕና በአርያም ይሁን ይበሉ።
ምልጣን፦ ወያዕትቱ በል
ምዕዋድ፦ ይብሉ ሆሣዕና በአርያም ይብሉ ሆሣዕና በአርያም።
፬ እምሥራቀ ፀሐይ እስከነ ዓረብ፤
ወእምጽዮን ሥነ ስብሐቲሁ፤
እግዚአብሔርሰ ገሃደ ይመጽእ። መዝ ፵፱፥፩፤
ትርጒም፦
ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ፤
ከክብሩ ውበት ከጽዮን፤
እግዚአብሔር በግልጥ ይመጣል።
ምሥጢር፦
ከፀሐይ መውጫ እስከ ፀሐይ መግቢያ ድረስ በምልዓት ያለ እግዚአብሔር ካህናትን ጠራ፤
የምስጋናው ጌጥ በምትሆን በኢየሩሳሌም አድሮ የሚኖር እግዚአብሔር ቦ የጌትነቱ ጌጥ በሚሆኑ በጎ ካህናት አድሮ የሚኖር እግዚብሔር ክፉ ካህናትን ለዘለፋ ጠራ “ወነሣእኩ ክልኤተ አብትረ ለአሐቲ ሰመይክዋ ሥነ ወለካልእታ ሐብለ – ሁለት በትሮችን ወሰድሁ አንዲቱን ውበት ሁለተኛይቱን ገመድ ብዬ ጠራኋቸው” እንዲል፤
እግዚአብሔር በሰባ ዘመን በረድኤት ይገለጣል ቦ በሥጋ ማርያም ይገለጣል፤ በዕለተ ምጽአት በክበበ ትስብእት ይገለጣል፤ የተወጋበትን ኲናት የተቸነከረበትን ቀኖት አስይዞ።
ወንጌል፦ ሉቃ ፲፱፥፳፰ – ፵፬፤
አቡን፦ (በ፮/ያ) ባረኮ ያዕቆብ ለይሁዳ ወልዱ ወይቤሎ ሀሎ ንጉሥ ዘይወጽእ እምኔከ ዘየሐፅብ በወይን ልብሶ ወበደመ አስካል ሰንዱኖ ንጉሦሙ ለእስራኤል ውእቱ ይብሉ ሆሣዕና በአርያም – ያዕቆብ ልጁ ይሁዳን ባረከው እንዲህም አለው ከአንተ የሚወጣ ንጉሥ አለ ልብሱን በወይን ቀሚሱንም በዘለላው ደም የሚያጥብ ነው የእስራኤል ንጉሣቸው ነው በአርያም መድኃኒት ይሁን ይላሉ።
ምልጣን፦ ዘየሐፅብ በል
ምዕዋድ፦ ይብሉ ሆሣዕና በአርያም ይብሉ ሆሣዕና በአርያም።
፭ ትሴብሖ ኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር፤
ወሰብሒዮ ለአምላክኪ ጽዮን፤
እስመ አጽንዐ መናሥግተ ኆኃትኪ።
ወንጌል፦ ዮሐ ፲፪፥፲፪ – ፳፮፤
አቡን፦ በ፪/ዩ) ባኡ ውስተ ሀገር ወበዊአክሙ ትረክቡ ዕዋለ አድግ ዕሡረ ፍትሕዎ ወአምጽእዎ ሊተ – ወደሀገር ግቡ ገብታችሁም የታሠረ የአህያ ውርንጫ ታገኛላችሁ ፈትታችሁ አምጡልኝ።
ምልጣን፦ ፍትሕዎ ወአምጽእዎ ሊተ ፍትሕዎ ወአምጽእዎ ሊተ።
ሰላም፦ (በ፩/ዩ) አልጺቆ ኢየሱስ ኢየሩሳሌም ርእያ ለሀገር ወይቤላ ሶበ ተአምሪ ጽዮን ነዋ ንጉሥኪ በጽሐ ብርሃንኪ ዮም ሰላምኪ – ኢየሩሳሌም ደርሶ ሀገሪቱን አያት እንዲህም አላት ጽዮን ብታውቂ እነሆ ንጉሥሽ ብርሃንሽ ደረሰ ሰላምሽ ዛሬ ነው።
ምልጣን፦ ወይቤላ ሶበ ተአምሪ ጽዮን ነዋ ንጉሥኪ በጽሐ ብርሃንኪ፤ተፈሥሒ በሕዝብኪ፤ ይትሐፈሩ ጸላእትኪ፤ ሰላምኪ ሰላምኪ ዮም ሰላምኪ – ጽዮን ብታውቂ እነሆ ንጉሥሽ ብርሃንሽ ደረሰ በወገንሽ ደስ ይበልሽ ጠላቶሽ ያፍሩ ዘንድ፤ ሰላምሽ ዛሬ ነው።
፮ ዘምሩ ለእግዚአብሔር ዘየኀድር ውስተ ጽዮን፤
ወንግርዎሙ ለአሕዛብ ምግባሮ፤
እስመ ተዘከረ ዘይትሐሠሥ ደሞሙ። መዝ ፱፥፲፩፤
ትርጒም፦
በጽዮን ለሚኖር ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤
ሥራውን ለአሕዛብ ንገሩ አስተምሩ፤
ደማቸውን የሚመራመር እርሱ አስቧልና።
ምሥጢር፦
በጽዮን ሰማያዊት በጽዮን ምድራዊት አድሮ ያለ እግዚአብሔርን አመስግኑ አድሮ ለሚኖር ለእግዚአብሔር ምስጋና አቅርቡ፤ ቦ በማኅፀነ ማርያም ያደረ እግዚአብሔርን አመስግኑ ለእሱ ምስጋና አቅርቡ።
ሥራውን ሁሉ ለአሕዛብ ንገሯቸው አስተምሯቸው፤
እንደፈሰሰ ይቅር የማይባል ደማቸውን አስቧልና፤ አስቦ ጠላቶቻቸውን አጥፍቷልና። አንድም ደማቸውን የሚመራመር እግዚአብሔር አስቧልና፤ አስቦ ጠላቶቻቸውን አጥፍቷልና። አንድም ደማቸውን የሚፈላለግ እግዚአብሔር አስቦ ጠላቶቻቸውን አጥፍቷልና። አንድም ጠላቱን በፍዳ የሚመረምር እግዚአብሔር ደማቸውን አስቦ ጠላቶቻቸውን አጥፍቷልና። እንደ ደመ አቤል፤ እንደ ደመ ዘካርያስ።
ሰሙነ ሕማማት
ሥርዐተ ጸሎት ዘሰሙነ ሕማማት
እንደሚታወቀው የሆሣዕና ሥርዐት የሚጀምረው ከሆሣዕና ዋዜማ ነው፤ ይልቁንም ከኒቆዲሞስ ረቡዕ ጀምሮ በዓለ ሆሣዕናው እየተበሠረ ይሰነብታል፤ ቅዳሴውም ከረቡዕ ጀምሮ ቅዳሴ ጎርጎርዮስ ነው፤ በዚህ መልክ የጀመረው የሆሣዕና ሥርዐት ሰኞ ነግህ ላይ ካህናትና ምእመናን በተገኙበት በስግደት ይቀጥላል፤ የሌሊቱ ንባብ ከተፈጸመ በኋላ በዕለተ ሰኑይ በነግህ ዲያቆን ከቅኔ ማኅሌቱ በሴቶች መግቢያ በኩል ወጥቶ ቃለ ዓዋዲ እየመታ ሦስት ጊዜ ይዞራል፤ ሲገባ በወንዶች መግቢያ በር ነው የሚገባው፤ መቶ ሃምሳ መዝሙረ ዳዊት፣ የሰባት ቀን ውዳሴ ማርያም፣ አንቀጸ ብርሃን ይደገማል፤ በሕማማት መልክእ አይደገምም፤ ይ.ካ እንበለ ደዌ ብሎ አቡነ ዘበሰማያት ይሰጣል፤
ወንጌሉን ተከትሎ መሪ አቡን ይመራል፤ ሁለት ጊዜ እየተቀባበሉ ብለው በሦስተኛው አንድ ላይ ይሉታል፤ በመሪ በኩል እየቀደሙ በአንሽ በኩል እየተከተሉ ለከ ኃይል ይላሉ፤ በቀኝ ስድስት ጊዜ በግራ ስድስት ጊዜ በአጠቃላይ ዐሥራ ሁለት ጊዜ ይሆናል፤ አያይዘው ለአምላክ ይደሉ ይላሉ፤
ይህ እንዳለቀ ንባባት ይቀጥላሉ፤ የትርጓሜ መጻሕፍት መምህራን ካሉ ትምህርተ ኅቡዓት፣ ኪዳንና ለሰሙነ ሕማማቱ የሚስማሙ መጻሕፍት እየተመረጡ ይተረጐማሉ። ንባቡ እንዳለቀ ምንተኑ ብሎ ተአምረ ማርያም ተአምረ ኢየሱስ ማንበብ ነው፤ ከዚህ ቀጥሎ ምስባክ ሰብኮ ወንጌል አንብቦ ጽንዐ ዛቲ ማለት ነው፤ ከጽንዐ ዛቲ ቀጥሎ በመሪ በኩል ክርስቶስ አምላክነ፤ በአንሽ በኩል ንሰብሖ ብሎ ኪርያላይሶን ማለት ነው፤ በመጀመሪያ በመሪ በኩል የሚባለውን እየደገሙ ማለት ነው፤ በሁለተኛው እያስተዛዘሉ ማለት ነው፤ አያይዞ አርባ አንድ ኪርያላይሶን አድርሶ የነግሁን ሰላምታ ማድረስ ነው። ይህ እንዳበቃ ካህኑ ጸሎተ ቡራኬ አንብቦ አርባ አንድ ኪርያላይሶን ይሰጣል፤
ሑሩ በሰላም እግዚአብሔር የሃሉ ምስሌክም ንዑ ወተጋብኡ በጊዜ ሠለስቱ ሰዓት ለጸሎት ብሎ ሕዝቡን ያሰናብታል፤ ሥርዐቱን ለመጠበቅ እንጂ የሚሄድ የለም፤ በአንዳንድ ቦታ ከሰኞ እስከ ረቡዕ የተወሰነ ዕረፍት የማድረግ ልምድ አለ፤ ያም ቢሆን ወደቤት ለመሄድና ለመመለስ የሚበቃ ሰዓት አይኖርም፤ እዚያው ሆኖ የግል ጸሎት እያደረሱ ለመቆየት ካልሆነ በቀር።
በሦስት ሰዓት ሃምሳ መዝሙረ ዳዊት ይደገማል፤ ይህም ከመዝሙር አንድ እስከ መዝሙር ሃምሳ ነው፤ ከነቢያት አምስት፤ ከመኃልይ ሁለት ይደገማል፤ ሲደገም እያንዳንዱ መዝሙር ለብቻ እየታደለ ነው፤ የሰው ኃይል ካነሰ ግን መጥኖ ማድረግ ይቻላል፤ የሐሙስና የዓርብ ውዳሴ ማርያም ደግሞ አቡን መምራት ነው። የቀረው ሥርዐት እንደ ነግሁ ይፈጸማል።
በስድስት ሰዓት ሃምሳ መዝሙረ ዳዊት ይደገማል፤ ይህም ከመዝሙር ሃምሳ አንድ እስከ መዝሙር መቶ ድረስ ነው፤ ከነቢያት አምስት ከመኃልይ ሁለት ይደገማል፤ የቀዳሚት፣ የእሑድና የሰኞ ውዳሴ ማርያም ተደግሞ አቡን ይመራል፤ በነግህ እንደተከናወነው አድርጎ መፈጸም ነው።
በዘጠኝ ሰዓት ሃምሳ መዝሙረ ዳዊት ይደገማል፤ ይህም ከመዝሙር መቶ አንድ እስከ ፍጻሜ ድረስ ነው፤ አምስት ነቢያት አንድ መኃልይ ይደገማል፤ የማክሰኞና የረቡዕ ውዳሴ ማርያም ይደገማል፤ ቀጥሎ ያለው ሥርዐት እንደ ነግሁ ሆኖ ይፈጸማል።
በዐሥራ አንድ ሰዓት አቡን፣ ለከ ኃይልና ኪርያላይሶን የለም፤ ንባቡን እስከ መንፈቀ ሌሊት አንብቦ የሰኑይን ሥርዐተ ጸሎት መፈጸም ነው። ግብረ ሕማሙ ለሠርኩ አቡን ያዛል። በቤተ ልሔም ይትበሃል ግን ከላይ ያለው ነው የሚከናወነው።
የማክሰኞና የረቡዕ ሥርዐተ ጸሎት አፈጻጸም እንደ ሰኞ ነው፤ እዚህ ላይ መወሳት ያለበት ነጥብ የዜማው አባባል ሁለት አይነት መልክ ያለው መሆኑ ነው፤ ሰኞና ማክሰኞ በግእዝ ዜማ ይባልና ረቡዕና ሐሙስ ዓራራይ ሆኖ ሰንብቶ ዓርብ ዕዝል ይሆናል፤ ይህ አንደኛው የአባባል ሥርዐት ሲሆን ሁለተኛውና የቤተ ልሔም ሥርዐት መሆኑ የሚታወቀው ሥርዐት ደግሞ ከሰኞ እስከ ሐሙስ ግእዝ ሆኖ ዓርብ ብቻ ነው ዕዝል የሚባለው፤ ጾመ ድጓውም የሚሠራው ግእዙንና ዕዝሉን ብቻ ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሊነሣ የሚችለው የቅዳሴው ዜማ ነው፤ በሰሙነ ሕማማት ያለው የቅዳሴ ዜማ ንባቡም ዜማው ከቅዳሴው የተወሰደ አለመሆኑ ሁሉንም የሚያስማማ ነው፤ በአባባል ግን በችሎታ ላይ የሚወሰን ስለሆነ ጾመ ድጓ ያልተማረ ሰው በቅዳሴው ወዝ ሊያዜም ይችላል፤ ይሁን እንጂ ጊዜ ወስዶ መቀጸል ቢቻል ብዙ ከባድ ስለማይሆን በሰነበተው ቁም ዜማ ፍጻሜው ቢሆን ድንቅ ነው።
በሰሙነ ሕማማት የሚባሉ አቡኖችና ምስጋድ
በማቴዎስ ወንጌል (በ፫/ፈ)
ስምዕዎኬ ለእግዚእነ ኵልክሙ አብያተ ክርስቲያናት ከመ ዘአክበሮሙ ለኦሪት ወለነቢያት በወንጌለ መንግሥት እንዘ ይብል ክርስቶስ ወልደ ዳዊት አሜን አሜን እብለክሙ እስከ አመ የኀልፍ ሰማይ ወምድር የውጣ እንተ አሐቲ ሕርመታ ወአሐቲ ቅርፀታ ኢተኀልፍ እምኦሪት ወእምነቢያት እስከ ሶበ ኵሉ ይትገበር ወይከውን ይቤ እግዚእ ዘበዕብራይስጢ ልሳን በወንጌለ ማቴዎስ ብርሃን ዘእምብርሃን
– አብያተ ክርስቲያናት ሁላችሁ ጌታችን ኦሪትና ነቢያትን እንዳከበራቸው ስሙ፤ በወንጌለ መንግሥት ወልደ ዳዊት ክርስቶስ እውነት እውነት እላችኋለሁ ከኦሪትና ከነቢያት ሁሉ እስኪተገበር እስኪሆን ድረስ ሰማይ ከምድር ጋር እስኪያልፍ ጊዜ አንዲት ቅርፅ አንዲት ነጥብ አንዲት ሠረዝ እንዳማታልፍ እነግራችኋለሁ፤ ከእውነተኛ ብርሃን የተገኘው እውነተኛ ብርሃን ጌታችን በዕብራይስጥ ልሳን በማቴዎስ ወንጌል እንዲህ አለ።
በማርቆስ ወንጌል (በ፫/ፈ)
ስምዕዎኬ ለእግዚእነ ኵልክሙ አብያተ ክርስቲያናት ከመ ዘአክበሮሙ ለኦሪት ወለነቢያት በወንጌለ መንግሥት እንዘ ይብል ክርስቶስ ወልደ ዳዊት ኢይምሰልክሙ ዘመጻእኩ እሥዓሮሙ ለኦሪት ወለነቢያት ወኢ ከመ እንሥቶሙ አላ ዳእሙ ዘእንበለ ከመ እፈጽሞሙ ይቤ እግዚእ በወንጌለ ሰላሙ አማኑኤል ስሙ ማርያም እሙ
– አብያተ ክርስቲያናት ሁላችሁ ጌታችን ኦሪትና ነቢያትን እንዳከበራቸው ስሙ፤ በወንጌለ መንግሥት ወልደ ዳዊት ክርስቶስ ኦሪትና ነቢያትን ልሽራቸው ላፈርሳቸው የመጣሁ አይምሰላችሁ ልፈጽማቸው ነው እንጂ እንዳለ ስሙ፤ ስሙ በአማኑኤል ስሙ በማርያም እሙ በወንጌለ ሰላሙ ጌታችን እንደተናገረ ስሙ።
በሉቃስ ወንጌል (በ፩/ዎ)
ይቤ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዘ ይሜሕረነ በወንጌለ ሉቃስ ወባሕቱ ይቀልል ሰማይ ወምድር ይኅልፍ እምትደቅ አሐቲ ቃል እምኦሪት
– ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሉቃስ ወንጌል ሲያስተምረን እንዲህ አለ፤ ከኦሪት አንዲት ቃል ከምትወድቅ ሰማይ ከምድር ጋር ቢያልፍ ይቀላል።
በዮሐንስ ወንጌል (በ፩/ዎ)
ስብሐት ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ በወንጌል ለዘመሐረነ በኦሪት ወበነቢያት ለዘናዘዘነ በከመ መሐረነ እግዚእነ ስብሐት ለእግዚአብሔር ከመ ናምልኮ ለዘፈጠረነ
– በኦሪት በነቢያት ላጽናናን በወንጌል ላስተማረን ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይገባል፤ ጌታችን እንዳስተማረን እናመልከው ዘንድ ለፈጠረን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይገባል።
ምቅናይ
ለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለም።
አማኑኤል አምላኪየ ለከ ኃይል…
ኦ እግዚእየ ኢየሱስ ክርስቶስ ለከ ኃይል…
ኃይልየ ወጸወንየ ውእቱ እግዚእየ እስመ ኮንከኒ ረዳእየ እብል በአኰቴት አቡነ ዘበሰማያት…
ለአምላክ ይደሉ ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለም
ለሥሉስ ይደሉ…
ለማኅየዊ ይደሉ…
ለዕበዩ ይደሉ…
ለእዘዙ ይደሉ…
ለመንግሥቱ ይደሉ…
ለኢየሱስ ይደሉ…
ለክርስቶስ ይደሉ…
ለሕማሙ ይደሉ…
በስቅለት ለመስቀሉ ይደሉ…
ለከ ይደሉ ኃይል ወለከ ይደሉ ስብሐት ወለከ ይደሉ አኮቴት ኦ እግዚእየ ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለመ ዓለም።
ይህ እንዳለቀ በአንድ በኩል፦ ክርስቶስ አምላክነ ዘመጽአ ወሐመ በእንቲአነ በሕማማቲሁ ቤዘወነ – ወደእኛ የመጣ ክርስቶስ አምላካችን ስለእኛ ታመመ በሕማሙ አዳነን።
በአንድ በኩል፦ ንሰብሖ ወናዕልል ስሞ እስመ ውእቱ ገብረ መድኃኒተ በዕብየ ሣህሉ – እናመስግነው ስሙን ከፍ እናድርግ በይቅርታው ብዛት መድኃኒትን አድርጓልና። ይህ እንዳለቀ ኪርያላይሶን ይቀጥላል፤ አባባሉም መጀመሪያ በማስተዛዘል ነው፤ በሁለተኛው በመቀባበል ነው።
ኪርያላይሶን ኪርያላይሶን ኪርያላይሶን
ኪርያላይሶን ዕብኖዲ ናይን
ታዖስ ናይን
ማስያስ ናይን
ኢየሱስ ናይን
ክርስቶስ ናይን
አማኑኤል ናይን
ትስቡጣ ናይን፤ ይህ እንዳበቃ ሰላምታ ይቀጥላል።
ሥርዐተ ጸሎት ዘዕለተ ሐሙስ
የሌሊቱ ንባብ ከተፈጸመ በኋላ በነግህ ታቦቱ ጥቁር ግምጃ ይለብሳል፤ ቄሱ አሥርቆት አድርጎ ጸሎተ ዕጣን ያደርሳል፤ ዳዊት፣ ነቢያት፣ መኃልየ ሰሎሞን፣ ውዳሴ ማርያም፣ አንቀጸ ብርሃን፣ ሰኞ በነግህ እንደተደረገው ይደረጋል፤ ከተአምር በኋላ ነአኵቶ ተብሎ ሥርዐተ ቅዳሴና ሙሉ ኪዳን ይደርሳል፤ ምስባክ ወጽሕደ ብሎ ወንጌል አንብቦ የቅዳሴውን ጸዋትው መፈጸም ነው፤ ይህ እንዳበቃ ጽንዐ ዛቲ አንብቦ ኪርያላይሶን ይባላል። የሦስት ሰዓትም የስድስት ሰዓትም የዘጠኝ ሰዓትም እንደ ሰኞ ይከናወናል።
ከዚህ በኋላ ሥርዐተ ሕጽበት ይደረጋል፤ ቦታውም በቤተ ክርስቲያኑ ምሥራቃዊ ሥፍራ ነው፤ ይህ የሚሆነው ግን በክብ ወይም ማዕዘናት ባሉት ቤተ ክርስቲያን ነው፤ ሁለት ንብቲራ ማይ መልተው ሥርዐተ ቅዳሴ ያደርሳሉ፤ ዘጠኝ ኪዳን ይደርሳል፤ አሐዱ ተብሎ ማዩ ይባረካል፤ በወይን ጠጅ ሣር፣ በወይን ቅጠል፣ በሎሚ ቅጠል፣ በወይራ ቅጠል፣ ወይም በእራፊ ግምጃ ሥርዐተ ሕጽበት ይከናወናል፤ ሲያጥብም ማዩን በእጁ እየጠለፈ በትእምርተ መስቀል አምሳል እያመሳቀለ እጅና እግራቸውን ነው የሚያጥበው።
ሥርዐተ ሕጽበቱ እየተከናወነ ሐዋርያቲሁ ከበበ የሚለው የቅዱስ ያሬድ ዜማ መቶ ሃምሳኛው መዝሙር እየገባ ይዘመራል። የዐሥራ አንዱ ሰዓት ንባብ ከተፈጸመ በኋላ ጸሎተ ቅዳሴ ይጀምራል።
በጸሎተ ሐሙስ የማይደረጉና የማይባሉ
ምንም እንኳ ጸሎተ ቅዳሴ የሚከናወን ቢሆንም ኑዛዜ የለም፤ የነፍሳተ ሙታን ስም አይጠራም፤ ዲያቆኑ ተንሥኡ ለጸሎት ሲል ስብሐት ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ፤ ካህኑ ሰላም ለኵልክሙ ሲል አቡነ ዘበሰማያት ይባላል እንጂ እግዚኦ ተሣሃለነ፣ ምስለ መንፈስከ አይባልም፤ ወንጌል መሳለም፣ መስቀል ማሳለም የለም፤ ጸሎተ እማኄ አይባልም አይደረግም፤ ጸሎተ ቡራኬ አይደገምም፤ ቃለ ዓዋዲ አይመታም፤ በቃለ ዓዋዲ ወይም በቃጭል ፈንታ ጸናጽል ነው ለአገልግሎት የሚውለው፤ ሐዳፌ ነፍስ አይባልም። በዚህ ቀን የሚለበሰው ልብሰ ተክህኖ ተገልብጦ ነው፤ ይህም የቆየው የብሉይ ኪዳን መሥዋዕት በሐዲሱ ኪዳን ምሥጢረ ቊርባን የተጀመረበት ዕለት ስለሆነ ነው። በቅዳሴ መካከል በዜማ የሚባለው የአቡነ ዘበሰማያት ዜማ በዓራራይ ዜማ አይባልም፤ በግእዝ ዜማ ነው የሚባለው። በመጨረሻም በሠርሖተ ሕዝብ ፈንታ አርባ አንድ ጊዜ ኪርያላይሶን ብሎ ሕዝቡን ማሰናበት ነው።
ምስባክ ዘጸሎተ ሐሙስ ዘሕፅበተ እግር፦
ትነዝሐኒ በአዛብ ወእነጽሕ፤
ተሐፅበኒ እምበረድ ወእፃዓዱ፤
ታሰምአኒ ትፍሥሕተ ወሐሤተ።
ትርጒም፦
በሂሶጵ ትረጨኛለህ እኔም እነጻለሁ፤
ታጥበኛለህ ከበረድ ይልቅ ነጭ እሆናለሁ፤
ደስታና ሐሤትን ታሰማኛለህ።
ምሥጢር፦
ሐመደ ምሥዋዑን፣ ማየ ምንዛኁን፣ ኅራረ ዕጣኑን በአውባን ቅጠል ትረጨኛለህ ከአፍአዊ ኃጢአት ንጹሕ እሆናለሁ፤
ዛቲ ቃል ተሤረየት በደም ህየንተ ቈፅለ ሑስጱ ወተነዝኀት ላዕለ ኵሉ – ይህች ቃል በአሽክት ቅጠል ፈንታ በደም ተነከረች በሁሉ ላይ ተረጨች ማለት ሰውን ሁሉ አከበረች እንዲል፤ ድርሳን ዘዮሐንስ አፈወርቅ ፲፮፥፺፬፤ ነቢያት ካህናት ጊደር አምጥተው አባላ መትተው ደሟን በብርት ተቀብለው ወተት ጨምረው አመድ ነስንሰው አዋሕደው እንዶድ ስሚዛ አሽክት ቅጠል በሐር ጎንጉነው ሕዝቡን ይረጯቸዋል ከአፍአዊ ኃጢአት ከጥቃቅኑ ኃጢአት ይነጹበታልና።
በማየ ንስሐ ታጥበኛለህ እኔም ከበረድ ይልቅ ንጹሕ እሆናለሁ፤
ተዐደዋ ለኃጢአትከ – ኃጢአትህን ይቅር አለህ ብለህ የደስታን ቃል በነቢዩ በናታን አንደበት ታሰማኛለህ፤ ቦ ወኀሊቆ ሰብዓ ዓም እትቤቀሎ ለንጉሠ ባቢሎን ባለው ደስ ታሰኘኛለህ፤
አንድም ደምህን ትረጨኛለህ ከአፍአዊ ከውስጣዊ ኃጢአት ንጹሕ እሆናለሁ፤ ዝንቱ ውእቱ ደምየ ዘይትከዐው ለቤዛ ብዙኀን – ለብዙዎች ቤዛ ሊሆን የሚፈሰው ደሜ ይህ ነው እንዲል ማቴ ፳፮፥፳፰፤
በማየ ገቦ ታጥበኛለህ እኔም ንጹሕ እሆናለሁ፤
በሐሙስ ዕለት ባልኸው ደስ ታሰኘኛለህ።
ክብር ይእቲ፦ ሐዋርያቲሁ ከበበ እግረ አርዳኢሁ ሐፀበ ኮኖሙ አበ ወእመ ወመሐሮሙ ጥበበ ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ ሃሌ ሉያ እንዘ ንብል ኢንትኀጐል – የደቀመዛሙርቱን እግር አጠበ አባትም እናትም ሆናቸው ጥበብን አስተማራቸው አታጥፋን እያልን እናመስግን።
በመጨረሻ፦ እንዘ ንብል ኢንትኀጐል እምከብካበ ወልዳ ለድንግል – ከድንግል ልጅ ሠርግ እንዳንከለከል እንዲህ እያልን እናመስግን።
ዕጣነ ሞገር በ፩ ሐፀበ እግረ አርዳኢሁ ወይቤሎሙ አነኒ ሐፀብኩ እገሪክሙ አንትሙኒ ከመዝ ግበሩ ለቢጽክሙ – የደቀመዛሙርቱን እግር አጠበ እንዲህም አላቸው እኔ እግራችሁን አጠብኋችሁ እናንተም ለወንድሞቻችሁ እንዲህ አድርጉ።
ዘቅዳሴ ምስባክ፦
ወሠራዕከ ማዕደ በቅድሜየ፤
በአንፃሪሆሙ ለእለ ይሣቅዩኒ፤
ወአጽሐድከ በቅብዕ ርእስየ።
ትርጒም፦
በፊቴ ማዕድን አዘጋጀህ፤
በሚያሰቃዩኝ ሰዎች ፊት፤
ራሴን በዘይት ቀባህ።
ምሥጢር፦
ማዕድ ገንዘቤን ለአሕዛብ አሳልፈህ ሰጠህብኝ፤ ቦ ጺዋዌን አመጣህብኝ ተማርኬ ወደአሕዛብ ሀገር እንድሄድ አደረግኸኝ፤ ቦ አሕዛብን ሠርተህ ቀጥተህ ገንዘባቸውን ሰጠኸኝ፤ ቦ ሥጋህን ደምህን ሰጠኸኝ፤ መስቀልን ተሸክመህ ደከምህልኝ።
ይንደደው ይቈጨው ብለህ ሥቃይ በሚያጸኑብኝ በአሕዛብ ፊት፤ ቦ አሕዛብን ይንደዳቸው ይቊጫቸው ብለህ፤ ቦ አጋንንትን ይንደዳቸው ይቊጫቸው ብለህ፤ አይሁድን ይንደዳቸው ይቊጫቸው ብለህ፤
የነጣ ራሴን በቅቤ አለዘብህ፤ ቦ ልቡናየን በሚጠት ደስ አሰኘኸው፤ ተስፋውን ሰምተው ወርደዋልና፤ ወዘይበዝኅ ሕዝበ አውረድከ በትፍሥሕት – ብዙ ሕዝብን በደስታ አወረድህ እንዲል ኢሳ ፱፥፫፤ ቦ ልቡናየን በልጅነት ደስ አሰኘኸው፤ ቦ ልቡናየን ፍቅረ መስቀሉ እንዲያድርበት አደረግኸው መስቀል ኃይላችን ትምክሕታችን ነውና ወአንሰ ሐሰ ሊተ ኢይዜኀር ዘእንበለ በመስቀሉ ለኢየሱስ ክርስቶስ እግዚእነ – ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር በሌላ አልመካም እንዲል ገላ ፮፥፲፬፤
ድኅረ ቅዳሴ ክብር ይእቲ፣ ዝማሬ፣ ዕጣነ ሞገር አለ፤ ይህም በጾመ ድጓው የተካተተ ነው እንጂ እንደሌላው ጊዜ አዲስ የቅኔ ድርሰት አይደለም። ይህን መሰል ቅኔ በጥምቀት ዋዜማ፣ በቀዳም ሥዑር ወይም በዳግም ትንሣኤ ቅዳሜ ይደረጋል፤ የዳግም ትንሣኤው ከቀዳም ሥዑሩ የተዛወረ ነው፤ ቀዳም ሥዑር ቅዳሴ የለምና።
ሥርዐተ ጸሎት ዘዕለተ ዓርብ
የሌሊቱ ንባብ ከተፈጸመ በኋላ በነግህ ሦስት ዲያቆናት ሦስት ቃለ ዓዋዲ ይዘው በሴቶች መግቢያ ወጥተው ሦስት ጊዜ ዞረው በወንዶች መግቢያ ይገባሉ፤ የዳዊት የውዳሴ ማርያም አደጋገም እንደ ሰኞው ነው፤ ዘየዐቢ ካህን እንበለ ደዌ ብሎ አቡነ ዘበሰማያት ከሰጠ በኋላ መሪ አርያም ይመራል፤ አርያሙም መስቀል አብርሃ ነው፤ የሚባለውም ሦስት ጊዜ ነው፤ አያይዞ መሪ በዘጠኝ ሃሌታ አቡን ነአምን ነአምን ይመራል፤ ለከ ኃይል እንደሰኞ ግራና ቀኝ ብሎ ወደንባብ መሄድ ነው፤ ዲያቆን ተንሥኡ ላዕሌየ ሰማዕተ ዐመፃ ብሎ ምስባክ ይሰብካል አያይዞ ወንጌል ይነበባል፤ በዚህ ቀን በአንድ ጊዜ የሚነበቡት ወንጌላት አራት ናቸው፤ በየወንጌሉ ፍጻሜ ወጸቢሖ፣ ጊዜ ሠለስቱ፣ ጊዜ ስድስቱ፣ ጊዜ ተሰዓቱ ይባላሉ፤ ወጸቢሖ እንዳለቀ በኅብረት ቅዱስ እግዚአብሔር እስከተሰቅለ ድረስ ይባላል፤ ዘተንሥአን አይነካም።
በሦስት ሰዓት ሥዕለ ስቅለት ይደረጋል፤ በግራ በቀኝ ሁለት መስቀል ይሆናል፤ የቤተ መቅደሱ መድረክ በልዩ ልዩ ንዋያተ ቅድሳት ያጌጣል፤ ሃምሳ መዝሙረ ዳዊት፣ አምስት ነቢያት፣ ሁለት መኃልይ፣ የሰኞና የማክሰኞ ውዳሴ ማርያም ይደገማል፤ መሪ አርያም ይምጻእ ብርሃንን ይመራል፤ አያይዞ አቡን አርዑተ መስቀሉን ይመራል፤ ንባቡ ከተፈጸመ በኋላ ከምባክ አስቀድሞ ዲያቆን ግፍዖሙን በውርድ ንባብ እያነበበ ካህኑ በቄጤማ ወይም በሰበን ወይም በጧፍ ጽናውን እየወዘወዘ ግፍዖሙን በዜማ ይላል፤ ከዚህ ቀጥሎ ምስባክ ዐገቱኒን ብሎ ወንጌል ማንበብ ነው፤
በስድስት ሰዓት ሃምሳ መዝሙረ ዳዊት፣ አምስት ነቢያት፣ ሁለት መኃልይ፣ የረቡዕ፣ የሐሙስና የዓርብ ውዳሴ ማርያም ይደገማል፤ መሪ አርያም ሐዋዘ ብርሃነን ይመራል፤ አቡን ተሰቅለን ይመራል፤ ለከ ኃይል ብሎ ንባብ ይቀጥላል፤ ካህን ከርቤ ጨምሮ ጽናውን እየወዘወዘ ዲያቆን ንባቡን በውርድ ንባብ እያነበበ ካህኑ ለመስቀልከ ንሰግድ ይላል፤ ቀጥሎ ምስባክ ቀነዉኒ እደውየን ሰብኮ ወንጌል ማንበብ ነው።
በዘጠኝ ሰዓት ሃምሳ መዝሙረ ዳዊት፣ አምስት ነቢያት፣ አንድ መኃልይ፣ የቅዳሜና የእሑድ ውዳሴ ደግሞ መሪ አርያም ብርሃን ትእዛዝከን ይመራል፤ አቡን ሶበ ሰቀልዎን ይመራል፤ ለከ ኃይል ብሎ ንባብ ማንበብ ነው፤ ንባቡ ሲያልቅ ኦ ዘጥዕመን እንደ ግፍዖሙ ካሉ በኋላ ሁለት ካህናት ሦስት ዲያቆናት ግብረ ሕማሙን ይዘው በጥቁር ግምጃ ተሸፍነው አምንስቲቲ ይላሉ፤ ንባቡ እየተነበበ ካህናቱ በዜማ አምንስቲቲ እያሉ ሕዝቡ እየተቀበሉ ሠላሳ ወይም ሠላሳ ስድስት ጊዜ ይባላል፤ በመጨረሻም ተዘከረነ ብሎ አልብሶ ወደምስባክ መሄድ ነው፤ ምስባኩም ወወደዩ ሐሞተ ነው፤ ወንጌል፣ ጽንዐ ዛቲ አንብቦ ኪርያላይሶን ብሎ ሰላምታ አድርሶ የዘጠኝ ሰዓቱን መፈጸም ነው።
በዐሥራ አንድ ሰዓት ሥነ ስቅለቱ ይወርዳል፤ መስቀሉና ንዋያቱ ሁሉ ይነሣሉ፤ መሪ ንዜኑን ይመራል፤ ለከ ኃይል የለም፤ በምሥራቅ መቶ፣ በምዕራብ መቶ፣ በሰሜን መቶ፣ በደቡብ መቶ እግዚኦታ ይደርሳል፤ ሰዓት የሚያንስ ከሆነ የተወሰኑ ካህናት ከመቅደስ ሊያደርሱት ይችላሉ፤ ከእግዚኦታው በኋላ በእንተ እለ ኖሙ ተብሎ ክብር ይእቲ ተስቅለ ክርስቶስ፤ ዝማሬ ኦ ዘክርስቶስ፣ ዕጣነ ሞገር ንዜኑ ይባላል፤
ሊቀ ካህናቱ ንኡስ አነን በንባብ ብቻውን ይላል፤ ጸሎተ ሠለስቱ ደቂቅን፣ ኀበ ባረኩን፣ ግነዩን፣ እግዚኦ ኢትጸመመኒን፣ ብፁዕ ብእሲንና ንሴብሖን አከታትለው ያደርሳሉ። ንሴብሖን መርተው ዘመው ጸንጽለው ዲያቆን ግብረ ሕማሙን አክብሮ ምዕዋድ አድርገው ጸሎት ተደርጎ የዕለቱ መርሐ ግብር ፍጻሜ ይሆናል።
በእንተ ኑዛዜ
ትርጒሙ መጽናናት፣ መረጋጋት፣ ማረጋጋት፣ የልቡና ዕረፍት ማግኘት ማለት ነው። በሌላ በኩል ኃጢአትን ለመምህረ ንስሐ ነግሮ ቀኖና ለመቀበል የሚደረግ ዝግጅት ነው። ከያዝነው ርእስ አንጻር ደግሞ ካህኑ የመጨረሻ ስንብት ለማድረግ ቃለ ሥርየት የሚያደርግበት ሥርዓት ነው። ኑዛዜን በተመለከተ ሁለት አይነት ሐሳብ አለ፤ አንደኛው ሐሳብ ነፍሳት ነጻ ስለወጡ ኑዛዜ መደረግ አለበት የሚል ሲሆን ሁለተኛው ሐሳብ ካሣ ስላልተፈጸመ ኑዛዜ አይኖርም የሚል ነው። ፍትሕ መንፈሳዊም የሚያዘው ሁለተኛውን ነው፤ ቅዳሜ ሰሞኑን እንዳይደረጉ የተከለከሉት ሁሉ እንዲደረጉ ሲፈቅድ መስቀል ማሳለምን ግን “ዘእንበለ ስዒም” ብሎ ለይቶ ያስቀምጠዋል፤ ኑዛዜውን የከለከለው ይህ ነው፤ መስቀል ማሳለም ካለ “እግዚአብሔር ይፍታ” ማለት አለና። ቄጠማ በማደል ጊዜ መስቀል የሚያሳልሙ ካህናት ዐስበ ፃማ ሲያገኙ የማያሳልሙ ካህናት ተግዳሮት ሲገጥማቸው የሚታይበት አጋጣሚ አለ፤ ምንም እንኳ የመስቀሉ ፍቅር በልበ ምእመናን የሚንበለበል መሆኑ ቢታመንም ጉራማይሌ ሥርዐት በማድረግ ልዩነት ከማሳየት የሚመለከተው አካል የሚሻሻለውን አሻሽሎ የሚጸናውን አጽንቶ አንድ አይነት ሥርዐት መከተልና መፈጸም ቢቻል ድንቅ ይሆናል።

