ብእሲ ሶበ ርእየ ፍቁሮ ትትመየጥ ነፍሱ ወትትፌሣሕ ልቡ ወትትሐሠይ ሕሊናሁ ኅድግሰ በርእየተ ገጹ በዘክሮተ ስሙኒ ይትፌሣሕ ወይትሐሠይ ፈድፋደ
– ሰው ወዳጁን ባየ ጊዜ ነፍሱ ትመለሳለች ልቡናው ደስ ትሰኛለች ሕሊናው ሐሴት ታደርጋለች ፊቱን ማየቱን ተወውና ስሙን በመጥራቱ እንኳ ፈጽሞ ደስ ይለዋል
ተግሣጽ ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ፳፮
ያለንበት ወቅት ተዘክሮተ እግዚአብሔርን ገንዘብ ለማድረግና መንፈሳዊ ልምምዳችንን ለማሳደግ መንፈሳዊ ጥረት የምናደርግበት ጊዜ ነው ምክንያቱም ዓለማችን እንደ ኔትወርክ በአንድ አይነት አሳሳቢና ከጠቢባኑ ሁሉ በላይ በሆነ ችግር ውስጥ ወድቃ እኛም ነገ ደግሞ ምን ያሰሙን ይሆን በሚል ስጋት ወጥተን እስክንገባ ድረስ የጤናችንና የነጻነት እንቅስቃሴያችን በጥያቄ ምልክት እየተመራ ያለ በመሆኑ ነው።
በጨነቀንና በቸገረን ሰዓት የምንወደውን ሰው መልክ ማየትና ድምጹን መስማት ምን ያህል የሚያስደተን እንደሆነ ሊቁ ነግሮናል። ለዚህ ነው የእግዚአብሔርን ድምጽ ለመስማት ጊዜው የበለጠ ምቹ የሚሆነው። ከእግዚአብሔር በላይ የማይከዳና የማይለወጥ ታማኝ ወዳጅ የለምና።
እንርሳ ብንል እንኳ መርሳት የማንችልባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ናቸው። በየሄድንበት ስፍራ ስለወቅታዊው ወረርሽኝ በሰፊው እንሰማለን። የሚስል ወይም የሚያስነጥስ ሰው ባየን ቁጥር የእኛም ስጋት ይጨምራል።
በዚሁ ልክ ስለዘለዓለማዊው ሕይወታችንና ስለመንፈሳዊው ጤንነታችን በየደረስንበት ልንሰማና ልናይ ያስፈልጋል። ብቻችንን የምንሻገረው ምንም አይነት ወንዝ የለም። ብቻችንን የምናቋርጠው ምንም አይነት በረሃ የለም። ብቻችንን ድል የምናደርገው ምንም አይነት ኃይል የለም። ብቻችንን የምናስወግደው ምንም አይነት ወረርሽኝ የለም።
እግዚአብሔር የሌለበትና የማይከብርበት ሕይወት አልጫ ነው። የአልጫ መጨረሻው ደግሞ በእግር መረገጥ ነው።
መጨረሻችን በእግረ አጋንንት መረገጥ እንዳይሆን በፍጹም ፍቅሩ ወዶን እስከ ሞት የደረሰልልንን ድምጹን ለመስማት እንጓጓ።



Leave a Reply