በእንተ ምንትኑ ኢረከበ ኤሳው ሥርየተ – ኤሳው ሥርየት ያላገኘው ስለምንድን ነው?
ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ስለኤሳው ሲናገር ይህንን ጥያቄ ይጠይቅና ምላሹን ሲያስቀምጥ እንዲህ ይላል።
እስመ ውእቱ ኢነስሐ በከመ ይደሉ – እንደሚገባ ሆኖ ንስሐ አልገባምና ሥርየት አላገኘም። ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረን ወደቀደመ ክብሩና በረከቱ ለመመለስ ፈልጎ ንስሐ የሚገባበት መንገዱ እስኪጠፋው ድረስ ግራ ተጋብቷል።
“ወኃጥአ ፍኖተ በዘይኔስሕ – ንስሐ የሚገባበትን መንገድ አጣ” እንዲል ዕብ ፲፪፥፲፯፤
እያለቀሰ ፈልጎታል ግን አልተሳካለትም። የዚህንም ምክንያት ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሲያብራራ “ወኤሳውሰ ነስሐ በአንብዕ ዘተሣልቆ ወመዓት – ኤሳው ግን የቁጣ የብስጭት የዘበት ንስሐ ገባ” ብሏል። በቁጣ በብስጭት በዘበት የሚደረግ ንስሐ የትም እንደማያደርስና ለሥርየተ ኃጢአት እንደማያበቃ ከዚህ መረዳት እንችላለን።
ንስሐ የሚገባ ሰው ሊያደርጋቸው ከሚገቡት መንፈሳዊ ተግባራት አንዱ የሠራውን ኃጢአት አለመርሳትና ዘወትር ማሰብ ነው። ምክንያቱም እኛ በደላችንን ስናስብ እግዚአብሔር ይረሳልናልና። ሊቁ እንደነገረን። “ወእመሰ አዘከርናሃ ንሕነ ይረሥዓ ለነ ፈጣሪ ሎቱ ስብሐት – እኛ ኃጢአታችንን ብናስባት ክብር ምስጋና ይግባውና ፈጣሪ ይረሳልናል”
ጥፋታቸውን እያሰቡ በወላጆቻቸው ፊት አንገታቸውን የሚደፉ ልጆች ከወላጆቻቸው የሚያገኙትን የማጽናኛ ቃል ወላጆችና ልጆች በትክክል ያውቃታል። ወላጆች የሚፈልጉት ማጥፋታቸውን አውቀው ከዳግም ጥፋት እንዲቆጠቡ እንጂ ባለፈው ጥፋታቸው እየተሳቀቁ እንዲኖሩ ስላልሆነ የትናትናውን ይረሱላቸዋል። ወደአጠገባቸው አቅርበውም በሚያጽናና ቃል ያባብሏቸዋል። ለወደፊቱ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ በምሳሌ ይመክሯቸዋል። እግዚአብሔርም በደላቸውን እያሰቡ ከፊቱ ለሚቆሙ ልጆቹ እንዲሁ ነው።
አሁንም ሊቁ እንደሚያስተምረን “እስመ ኃጢአትሰ ሶበ ይትአመኑ ባቲ ተኀፅፅ ወትደክም – ኃጢአት በደል መሆኗን አምነው በተቀበሏት ጊዜ ትጎድላለች ትደክማለች”
ጥፋቴን አምኛለሁ አጥፍቻለሁ ይቅርታ አድርግልኝ እያለው ልጁን የሚቀጣ አባት ካለ ወይም ልጇን የምትቀጣ እናት ካለች የአባትነትንና የእናትነትን ምሥጢርና ክብር ያልተረዱ ናቸው።
ለጸሎት እግዚአብሔር ፊት ስንቆምና በደል ጥፋታችን ሲታወሰን በዚህም ምክንያት እግዚአብሔርን መበደላችን ግልጽ ብሎ ሲታየን ተከማችቶ የነበረው የኃጢአት ክምር እየጎደለ፤ በርትቶ የነበረው የኃጢአት አቅምና ኃይል እየደከመ ይሄዳል።
ይህ ደግሞ የሚሆነው የሠሩትን ኃጢአት በጉያ ደብቆ እንደ ቃኤል እኔ ምን አውቃለሁ በሚል መንፈስ አይደለም። ብዙዎቻችን የቃኤል አይነት ድካም ይታይብናል።
ወንድሙን ገድሎ ወንድምህሳ ሲባል እኔ የት እንዳለ አላውቅም እኔ የአቤል ጠባቂ ነኝ በማለት ድርብ ኃጢአት ሠራ።
ሊቁ በአንጻር ሲናገር “ርኢከኑ ኦ እኁየ ዘከመ እፎ ወሰከ ግብረ ኃጢአት ወእከይ አቡሁሰ ኢገብረ ከመዝ – ወንድሜ ሆይ እንዴት አድርጎ ክፋትና ኃጢአት እንደጨመረ አየህ? አባቱ ግን እንደ እርሱ አላደረገም” በማለት የአባቱን ፈለግ መከተል ሲገባው በራሱ መንገድ መሄዱን በአንጻር ያስረዳል። አባቱ አዳም እርቃኑን መሆኑን ባየ ጊዜ ወደጫካ ገብቷል የት ነህ ሲለውም እራቁቴን ስለሆንሁ ፈራሁ ብሏል።
እንደ አባታችን አዳም ማጥፋታችንን አውቀንና አምነን እራቁታችንን እንድንቆም ያደረገንን ለእግዚአብሔር ስንነግር ራቁታችንን ለመሸፈን እግዚአብሔር ልብስ ያዘጋጃል።
ድካማችን ሁሉ ያለፍሬ እንዳይቀር እንደኤሳው በቁጣ በብስጭት በዘበት ሳይሆን በፍጹም ትሕትና ከአምላካችን ፊት እንቁም።



Leave a Reply