ለመብዝኅቶሙ ይሰዐኖሙ አልዕሎ ሕሊናት ኀበ እግዚአብሔር ወይትከሀሎሙ አልዕሎ አእዳው ወአዕይንት ኀበ ሰማይ

Published by

on

“ለመብዝኅቶሙ ይሰዐኖሙ አልዕሎ ሕሊናት ኀበ እግዚአብሔር ወይትከሀሎሙ አልዕሎ አእዳው ወአዕይንት ኀበ ሰማይ – ለብዙዎች (ለወጣንያን) ሕሊናቸውን ወደ እግዚአብሔር ከፍ ማድረግ ይሳናቸዋል እጃቸውን ወደሰማይ መዘርጋትና ዐይናቸውን ማቅናት ግን ይቻላቸዋል” ፊልክስዩስ ተስእሎ ፳፪

ክርስትና ዕለቱን ተዘርተው ዕለቱን የሚበቅሉበትና የሚያድጉበት ሳይሆን ቀስ በቀስ እያደጉ ከፍጹምነት የሚደርሱበት ሕይወት ነው። አበው እንኳን በሱባኤ በዘወትርም ከዘረጉ ሳያጥፉ ከቆሙ ሳያርፉ በተዘክሮተ እግዚአብሔር ይኖራሉ።
በእኛ ደረጃ ለእኛ ከማይቻሉን ነገሮች አንዱ ሰቂለ ሕሊና ወይም አልዕሎ ሕሊና ነው። ሊቁም “ለመብዝኅቶሙ ይሰዐኖሙ – ለብዙዎቹ ይሳናቸዋል አይቻላቸውም” ብሎ እንደነገረን ይህ ጸጋ በቀላሉና በቶሎ የሚገኝ አይደለም። ከዚህ ያልተናነሰው ወይም ወደዚህ ወደሰቂለ ሕሊና ለመድረስ መሰላል የሚሆነውን ለይቶ ሲናገር ሁለት መሠረታዊ ነጥቦችን አንሥቷል። አንዱ እጅን ከፍ አድርጎ መዘርጋት ሲሆን ሁለተኛው ወደሰማይ አቅንቶ መመልከት ነው።
ሁለቱም ተግባራት ከባድ የሚሆኑብን እንኖር ይሆናል። እጃችንን ከፍ አድርጎ መዘርጋት የሚያቅተን ብንኖር እጃችን ደምን ተመልቶ ሊሆን ይችላል። ነቢዩ ኢሳይያስ እንደገሠጸን። “እጃችሁን ወደእኔ ብትዘረጉ ዐይኔን ከእናንተ እሰውራለሁ ልመናንም ብታበዙ አልሰማችሁም እጆቻችሁ ደምን ተመልተዋልና” ብሎ፤ ኢሳ ፩፥፲፭፤
ዐይናችንንም ቀና ማድረግ የተሳነን ብንኖር የኃጢአታችን ብዛት አንገታችንን አስደፍቶን ይሆናል። ንጉሡ ሕዝቅያስ እንደተናገረው። “ደክማ አዕይንትየ ወስዕንኩ ነጽሮ ኀበ እግዚአብሔር ሰማየ – ዐይኖቼ ደከሙ ወደ ሰማይ ወደ እግዚአብሔር ቀና ብሎ ማየት ተሳነኝ” እንዳለ ኢሳ ፴፰፥፲፬
እጅን መዘርጋትም ሆነ ዐይንን ወደሰማይ ማቅናት ብርቱ መሳሪያዎች ናቸው። ግን ሲደረጉ ከልብ መሆን አለባቸው፤ ትርፉ ድካም ብቻ እንዳይሆን።
የሊቀ ነቢያት ሙሴ እጆች ሲዘረጉ ኢሎፍላውያን ድል ይሆኑ ነበር በተቃራኒው የሙሴ እጆች ሲታጠፉ እስራኤል ድል ይሆን ነበር ሙትና ቁስለኛውም ይጨምር ነበር።
ሃይማኖት አለን የምንል እኛ በተለያየ ነገር በመድከማችን እየሆነ ያለው ሁሉ ለመስማት የሚዘገንን ሆነ።
አባታችን አብርሃም ሥላሴን በቤቱ ለማስተናገድ የበቃውና ሎጥም ከሰዶም ጥፋት ለመዳን የቻለው ዐይናቸውን አቅንተው በማየትና ያዩትን ወደ ተግባር ለመለወጥ ባሳዩት ቁርጠኝነትና ፍጥነት ነው።
ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊትም ሕዝቡንና ሀገሩን ከጥፋት መታደግ የቻለው ዐይኑን አቅንቶ በማየቱ ነው። እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ።
“ዳዊትም ዐይኖቹን አነሣ የእግዚአብሔር መልአክ በምድርና በሰማይ መካከል ቆሞ የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም ተዘርግቶ አየ ዳዊትም ሽማግሌዎችም ማቅ ለብሰው በግምባራቸው ተደፉ” ተብሎ ፪ዜና ፳፩፥፲፮፤
ይሁንና የማይቻለውን ስላልተቻለን ባናደርገውም የሚቻለንን አለማድረጋችን ምን ሊባል ይችላል! እጅን መዘርጋት፣ ዐይንን ወደ ሰማይ ማቅናት።
ይህንን የሚያነቡ እርስዎና እኔ መሠረታዊው ችግራችን ይህ ነው። ይገርማል! ከዚህ የቀለለ የትና መቼ እናገኝ ይሆን?
ሀገሬ ያጣችው ቤተ ክርስቲያኔ ያጣችው ይህንን ነው እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች ተብሎ በተነገረላት መሬት ላይ በቅሎ የዚህ ጸጋ ተጠቃሚ የሆነ ትውልድ።

የምንችለውን ከልብ በማድረግ ሱባኤውን ብንጀምረው እግዚአብሔር የሰማይ መስኮትን ከፍቶ የምንፈልገውን ሁሉ በመስጠት ይቅርታውን ባበዛልን ነበር።
“ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ” እንደተባለው እጆቻችንን ዘርግተን ዐይናችንን ወደሰማይ አቅንተን ለራሳችንና ለሀገራችን እናልቅስ በንስሐ ሕይወትም እንመላለስ።

ከብርሃን የተገኘህ ለዓለሙ ሁሉ የምታበራ ብርሃን ረቂቁን ምሥጢር ትገልጥና እኛን ታድን ዘንድ የተገለጽህ አቤቱ ገጸ ልቡናችንን የሸፈነውን ድንቁርና አርቅልን። አሜን!

Leave a Reply

Discover more from በመካነ ራማ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ኤላም የትምህርት ማዕከል

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading