ኢየአክለከሁ ርእየ እሳት – እሳት ማየት አይበቃህምን? ፊልክስዩስ ተስእሎ ፷፬
መነኮሳት አበው ምግባቸውን በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ያዘጋጃሉ፤ እንግዳ ሲመጣ ለእንግዳ ሽሮ ይሠራሉ፤ በዚህ ጊዜ ደቀመዝሙሩ ለመጣው እንግዳ ሽሮ እየሠራ ሳለ የእሳቱ ሁኔታ ገርሞት ትኩር ብሎ ይመለከት ጀመር፤ የሚያየው በዓመት አንድ ጊዜ ነውና፤ እሱም እድል ከገጠመው ነው፤ መምህሩም አንተ ልጅ! እሳት ማየቱ አይበቃህምን አለው።
የተሸነፍንበት ይማርከናልና አይበቃህምን አለው፤ “ሰው ለተሸነፈበት ለእርሱ ተገዝቶ ባሪያ ነው” እንዲል ፪ጴጥ ፪፥፲፱፤
የተፈቀደልን ቢሆን እንኳ እንዲሠለጥንብን ሳይሆን እንድንሠለጥንበት ነው መጻሕፍት የሚነግሩን።
“ሁሉ ተፈቅዶልኛል ሁሉ ግን አይጠቅምም ሁሉ ተፈቅዶልኛል በእኔ ላይ ግን አንድ ነገር እንኳ አይሠለጥንብኝም” እንዲል ፩ቆሮ ፮፥፲፪፤
በዚህ መነሻነት (እሳት ማየት አይበቃህምን በሚለው መነሻነት) የሚከተሉትን ነጥቦች እናነሳለን
፩. የማይገባ ግንብ ለመገንባት የምንጠቀመውን እሳት ማየት አይበቃንምን?
“ከምሥራቅም ተነሥተው በሄዱ ጊዜ በሰናዖር ምድር አንድ ሜዳ አገኙ በዚያም ተቀመጡ እርስ በርሳቸውም ኑ ጡብ እንሥራ በእሳትም እንተኵሰው ተባባሉ ጡቡም እንደ ድንጋይ ሆነላቸው የምድርም ዝፍት እንደ ጭቃ ሆነችላቸው እንዲህም ኑ ለእኛ ከተማና ራሱ ወደ ሰማይ የሚደርስ ግንብ እንሥራ በምድር ላይ ሳንበተንም ስማችንን እናስጠራው አሉ” ዘፍ ፲፩፥፪፤
እነዚህ ሰዎች በድርጊታቸው፦
- አንድ የነበረውን የምድር ቋንቋ ለዋውጠዋል።
- ባገኙት አጋጣሚና ስፍራ ሁሉ የሚሠሩትን ለይተው አላወቁም።
- በትርጓሜያችን እንደተገለጠው በንስሐ ሕይወት ለመኖር ከመወሰን ይልቅ በግንባቸው የሚመጣባቸውን አደጋ መከላከል እንደሚችሉ ገምተዋል። ኖኅ መርከብ ሠርቶ መዳኑን ያውቃሉና።
፪. አብረን በሠራነው በደል በሌሎች የምንፈርደውን የፍርድ እሳት ማየት አይበቃንምን?
“ከሦስት ወር በኋላ ለይሁዳ ምራትህ ትዕማር ሴሰነች ደግሞም በዝሙት እነሆ ፀነሰች ብለው ነገሩት ይሁዳም አውጡአትና በእሳት ትቃጠል አለ እርስዋም ባወጡአት ጊዜ ወደ አማትዋ እንዲህ ብላ ላከች ለዚህ ለባለ ገንዘብ ነው የፀነስሁት ተመልከት ይህ ቀለበት ይህ አምባር ይህ በትር የማን ነው?” ዘፍ ፴፰፥፳፬፤
ይሁዳ እንዴት፣ ለምን፣ መቼ፣ የት የሚለውን ሳያጣራ በሰማው ብቻ ወስኖ “በእሳት ትቃጠል” የሚል ፍርድ ፈረደ፤ በዚህ መንገድ የፍትሕ ሚዛን የሚያጋድልባቸው ብዙዎች ናቸው።
በቅዱስ ወንጌልም፦ “መላልሰው በጠየቁት ጊዜ ቀና ብሎ ከእናንተ ኃጢአት የሌለባት በድንጋይ ይውገራት አላቸው” የሚል ቃል ተመዝግቧል ዮሐ ፰፥፥፯፤
ከጠጉራችን ቁጥር በላይ በሆነ ኃጢአት ውስጥ ሆነን ሌላውን ኃጢአተኛ ብለን እንፈርድበታለን። ፈራጁ ዝም ያለን ከጽድቃችን የተነሣ ሳይሆን ለኃጥኡም ለጻድቁም ፍጹም ፍቅር ያለው ስለሆነ ብቻ ነው።
፫. የታዘዝነውን ትተን ያልታዘዝነውን ለማድረግ የሚገፋንን እሳት ማየት አይበቃንምን?
“የአሮንም ልጆች ናዳብና አብዩድ በየራሳቸው ጥናውን ወስደው እሳት አደረጉበት በላዩም ዕጣን አኖሩበት በእግዚአብሔርም ፊት እርሱ ያላዘዛቸውን ሌላ እሳት አቀረቡ እሳትም ከእግዚአብሔር ፊት ወጥቶ በላቸው በእግዚአብሔርም ፊት ሞቱ” ዘሌ ፲፥፩፤
በሳኦልም ሕይወት ተመሳሳይ ነገር ተከሥቷል።
“ሳኦልና ሕዝቡ ለአጋግ ለተመረጡትም በጎችና በሬዎች ለሰቡትም ጥጆችና ጠቦቶች፥ ለመልካሞቹም ሁሉ ራሩላቸው ፈጽሞ ሊያጠፉአቸውም አልወደዱም ነገር ግን ምናምንቴንና የተናቀውን ሁሉ ፈጽመው አጠፉት የእግዚአብሔርም ቃል ሳኦል እኔ ከመከተል ተመልሶአልና ትእዛዜንም አልፈጸመምና ስላነገሥሁት ተጸጸትሁ ብሎ ወደ ሳሙኤል መጣ” ፩ሳሙ ፲፭፥፱፤
በአጠቃላዩ ሲታይም ሰውን በመፍጠሩ እንደተጸጸተና በመቶዎች ይቆጠር በነበረው የሰው ልጅ እድሜ ላይ ገደብ የጣለበትም ሁናቴ በመጽሐፍ ተመዝግቧል፤ ዘፍ ፮፥፫፤
የዚህም ፍጻሜው “እግዚአብሔር የእስራኤልን መንግሥት ዛሬ ከአንተ ቀደዳት፥ ከአንተም ለሚሻል ለጎረቤትህ አሳልፎ ሰጣት የእስራኤል ኃይል እንደ ሰው የሚጸጸት አይደለምና አይዋሽም አይጸጸትምም አለው” የሚለውን አስደንጋጭ ቃል መስማት ሆኗል።
፬. የሚገሥጸንን መልእክት ለማቃጠል የምናዘጋጀውን እሳት ማየት አይበቃንምን?
“ንጉሡም በዘጠነኛው ወር በክረምት ቤት ተቀምጦ ነበር፥ በፊቱም በምድጃ ውስጥ እሳት ይነድድ ነበር ይሁዲም ሦስት ወይም አራት ዓምድ ያህል ባነበበ ቍጥር ንጉሡ በካራ ቀደደው ክርታሱም በምድጃ ውስጥ ባለው እሳት ፈጽሞ እስኪቃጠል ድረስ በምድጃ ውስጥ ወዳለው እሳት ጣለው ንጉሡም ይህንም ቃል ሁሉ የሰሙ ባሪያዎቹ ሁሉ አልፈሩም ልብሳቸውንም አልቀደዱም ነገር ግን ኤልናታንና ድላያ ገማርያም ክርታሱን እንዳያቃጥል ንጉሡን ለመኑት፥ እርሱ ግን አልሰማቸውም” ኤር ፴፮፥፳፪፤
ካህናቶቿን፣ ምእመናኖቿን፣ መጻሕፍቶቿን፣ የሚታይና የማይታይ ማንነቷን የሚገልጡትን ሁሉ እየፈለጉ የማውደሙ ሂደት ከነኢዮአቄም የተወረሰ ይመስላል። ቀድሞ የተዘጋጀውን በእሳት ቢያወድሙትም እርሱ እግዚአብሔር ነውና እንደገና በአዲስ እንዲዘጋጅ ያደርገዋል። ሁሉ ይቻለዋልና።
፭. የሚሻለንን ባለመምረጥ የሚጠብቀንን እሳት በቸልተኝነት ማየት አይበቃንምን?
“እጅህ ወይም እግርህ ብታሰናክልህ ቈርጠህ ከአንተ ጣላት፤ ሁለት እጅ ወይም ሁለት እግር ኖሮህ ወደ ዘላለም እሳት ከምትጣል ይልቅ አንካሳ ወይም ጉንድሽ ሆነህ ወደ ህይወት መግባት ይሻልሀል ዓይንህ ብታሰናክልህ አውጥተህ ከአንተ ጣላት፤ ሁለት ዓይን ኖሮህ ወደ ገሃነመ እሳት ከምትጣል ይልቅ አንዲት ዓይን ኖራህ ወደ ሕይወት መግባት ይሻልሃል” ማቴ ፲፰፥፰፤
እንደ ስምዖን ሰፋዬ አሣዕን ያሉ አበው ዐይናቸውን፣ እንደ አትናቴዎስ ዘአንጾኪያ ያሉ አበው እጃቸውን፣እንደ መርትያኖስ ያሉ አበው እግራቸውን እያወጡ እየቆረጡ ጥለዋል፤ ለእሳትም አሳልፈው ሰጥተዋል።
በሌላ መንገድ ደግሞ ቤተሰባዊ ተጽእኖ እሳት ሆኖ እንዳያቃጥለን ማለትም ከሃይማኖት እንዳያወጣን መንፈሳዊ ጥንቃቄ የምናደርግበት ምሥጢር ይነገርበታል። ይህም በዐይን የተመሰለችው ሚስት ናት፤ በእጅ የተመሰሉት ልጆች ሲሆኑ በእግር የተመሰሉት ቤተ ሰቦች ናቸው።
በሦስተኛ ደረጃ እኛ ራሳችን ለአካላችን እሳት እንድንሆንበት የሚያስረዳ ምሥጢርም ይነገርበታል። ይህም ዐይንህን በአንቃዕድዎ፣ እጅህን በሰፊህ፣ እግርህን በቀዊም ሥራው ቅጣው ተብሎ ተመሥጥሮበታል። ይህን ስናደርግ ክፉው መንፈስና አሠራሩ በእኛ ውስጥ ስፍራ ስለማይኖረው የገባው ፈጥኖ ወጥቶ ይሄዳል፤ የወጣውም ተመልሶ ቢመጣ ማረፊያ ቦታ አያገኝም፤ እሳቱን ለብሰን እሳት እንሆንበታለንና።
በመልካም አኗኗር ባለመኖር ፍጻሜያችን የሚደመደም ከሆነ በመጨረሻው የፍርድ ቀን የምንሰማው ቃልም “እናንተ ርጉማን፥ ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ” የሚለውን ነው ማቴ ፳፭፥፵፩፤
፮. የምናውቀውን እውነት እንደማናውቅ የምንሆንበትን እሳት ማየት አይበቃንምን?
“ስምዖን ጴጥሮስም ቆሞ እሳት ይሞቅ ነበር እንግዲህ አንተ ደግሞ ከደቀ መዛሙርቱ አይደለህምን? አሉት እርሱም አይደለሁም ብሎ ካደ ጴጥሮስ ጆሮውን የቈረጠው ዘመድ የሆነ ከሊቀ ካህናቱ ባሮች አንዱ በአትክልቱ ከእርሱ ጋር እኔ አይቼህ አልነበረምን? አለው ጴጥሮስም እንደ ገና ካደ፥ ወዲያውም ዶሮ ጮኸ” ዮሐ ፲፰፥፳፭፤
፯. ከእኛ ጋር አልተባበሩም ያልናቸውን ለማጥፋት የምንመኘውን እሳት ማየት አይበቃንምን?
“በፊቱም መልክተኞችን ሰደደ ሄደውም ሊያሰናዱለት ወደ አንድ ወደ ሳምራውያን መንደር ገቡ ፊቱም ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚሄድ ስለ ነበረ አልተቀበሉትም ደቀ መዛሙርቱም ያዕቆብና ዮሐንስ አይተው ጌታ ሆይ ኤልያስ ደግሞ እንዳደረገ እሳት ከሰማይ ወርዶ ያጥፋቸው እንል ዘንድ ትወዳለህን? አሉት እርሱ ግን ዘወር ብሎ ገሠጻቸውና ምን ዓይነት መንፈስ እንደ ሆነላችሁ አታውቁም የሰው ልጅ የሰውን ነፍስ ሊያድን እንጂ ሊያጠፋ አልመጣም አለ። ወደ ሌላ መንደርም ሄዱ” ሉቃ ፱፥፶፪፤
የግእዙ ንባብ “ኢያእመርክሙኑ መጠና ለነፍስክሙ – የሰውነታችሁን መጠን አላወቃችሁምን?” የሚል ኃይለ ቃል አለው። ይህም ሁለት ምሥጢርን ያስተረጉማል።
የመጀመሪያው ብታገሣችሁ ነው እንጂ ውስጣችሁ ቢመረመር እሳት ከሰማይ ወርዶ እንዲበላቸው ከምታስቧቸው ሰዎች የተለያችሁ ናችሁን የሚል ነው። የትዕግሥት አባት ኢዮብ “ሰማይኒ ኢኮነ ንጹሐ በቅድሜሁ – ሰማይ እንኳ በፊቱ ንጹሕ አይደለም” እንዳለ በፊቱ ማንም ንጹሕ ሊሆን አይችልምና ነው። ኢዮ ፲፭፥፲፬፤
ሁለተኛው ነጥብ የተሰጣቸውን የሐዋርያነት ጸጋ የሚያስረዳ ነው “ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም ባሪያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና ወዳጆች ብያችኋለሁ ከአባቴ የሰማሁትን ሁሉ ለእናንተ አስታውቄአችኋለሁና” እንዲል ዮሐ ፲፭፥፲፭፤
በመጨረሻም “እንዲህ ሊሆን አይገባም” የሚል ተግሣጻዊ መልእክቱን በሚያጐላው ሐዋርያዊ ቃል መልእክታችንን ወደፍጻሜ እናቅርበው።
“መርከቦች ደግሞ ይህን ያህል ታላቅ ቢሆኑ በዐውሎ ነፋስም ቢነዱ የመሪ ፈቃድ ወደሚወደው ስፍራ እጅግ ታናሽ በሆነ መቅዘፊያ ይመራሉ እንዲሁም አንደበት ደግሞ ትንሽ ብልት ሆኖ በታላላቅ ነገር ይመካል እነሆ ትንሽ እሳት እንዴት ያለ ትልቅ ጫካ ያቃጥላል አንደበትም እሳት ነው አንደበት በብልቶቻችን መካከል ዓመፀኛ ዓለም ሆኖአል ሥጋን ሁሉ ያሳድፋልና የፍጥረትንም ሩጫ ያቃጥላል በገሃነምም ይቃጠላል የአራዊትና የወፎች የተንቀሳቃሾችና በባሕር ያለ የፍጥረት ወገን ሁሉ በሰው ይገራል ደግሞ ተገርቶአል ነገር ግን አንደበትን ሊገራ ማንም ሰው አይችልም የሚገድል መርዝ የሞላበት ወላዋይ ክፋት ነው በእርሱ ጌታንና አብን እንባርካለን በእርሱም እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን ከአንድ አፍ በረከትና መርገም ይወጣሉ ወንድሞቼ ሆይ ይህ እንዲህ ሊሆን አይገባም” ያዕ ፫፥፬፤
ይቆየን



Leave a Reply