ሃይማኖትሰ ሃይማኖተ ጽድቅ በእንተ እግዚአብሔር

Published by

on

ፊልክስዩስ ተስእሎ ፻፺፮

ሊቁ ይህን ኃይለ ቃል መነሻ አድርጎ እንደሚከተለው አባታዊ ምክሩንና መልእክቱን ያስተላልፍልናል።

፩. ሃይማኖትሰ ሃይማኖተ ጽድቅ በእንተ እግዚአብሔር – ሃይማኖት ማለት በአካል ሦስት በባሕርይ አንድ ብሎ ማመን ነው። ይህም ምሥጢረ ሥላሴ ብለን የምናውቀውና የምናምነው ነው። የማይከፈል አንድነት የማይጠቀለል ሦስትነት የሚነገርበት፣ አንድነት በሦስትነት ሦስትነት በአንድነት የሚነገርበት፣ ልጅነት ያልተከተለው አባትነት፣ አባትነት ያልቀደመው ልጅነት፣ እርጅና የሌለበት ሥርፀት የሚነገርበት ምሥጢር ምሥጢረ ሥላሴ ይባላልና።

፪. ወአሚን ቃላቲሁ – በአካላዊ ቃልነቱ አንድም ለይኵን ባለው ቃሉ ማመን ነው። አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ የየራሳቸው ፍጹም አካል፣ ፍጹም መልክ፣ ፍጹም ገጽ አላቸው። ሰው ሆኖ ያዳነን ከሦስቱ አካላት አንድ አካል አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በጥንተ ተፈጥሮ በአንድነቱ በሦስትነቱ የፈጠረን እርሱ በእርሱ ፈቃድ በአባቱ ፈቃድ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ በሐዲስ ተፈጥሮ ሊፈጠረን ወደእኛ መጣ ከኃጢአት በቀር እኛን ሆነ ወደቀደመ ክብራችንና ርስታችን መለሰን። እስከዛሬ ዓለምን የሚመራውና የሚመግበው አንድ ጊዜ ይሁን ብሎ የተናገረው ቃሉ ነው። “እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስ ነው ሕይወትም ነው” እንዲል ዮሐ ፮፥፷፫፤

፫. ወተስፋሂ ርእዮተ ልብ ለዓለም ኀበ እግዚእ – ተስፋ የተባለውም በጌታችን ሆኖ መንግሥተ ሰማያትን ማየት ነው። ዳግመኛ እመጣለሁ እኔ ወዳለሁበት እወስዳችኋለሁ ተስፋ ሰጥቶናል። ከዚህ በመነሳት ሁልጊዜ “መንግሥትህ ትምጣልን” እያልን እንጸልያለን።

፬. ወፍቅርሂ ከዊነ አሐዱ ልብ – ፍቅርም በልብ አንድ መሆን ነው። በልብ የሌለ አንድነት ከአፍአ አይመጣም። መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ የወረደውና ያደረው በአንድ ልብ ሆነው ተሰብስበው ሳሉ ነበር። ወደ ቤተ እግዚአብሔር የሚደረግ ጉዞ ሁሉ መሠረቱ የልብ አንድነት ነው። ለውጥ የሚመጣው፣ ችግር የሚወገደው፣ ከታሰበው የሚደረሰው፣ የልብ አንድነት ሲኖር ብቻ ነው። እኛም በምንጠቀምበት እግዚአብሔርም በሚከብርበት መንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ መመላለስ ያልተቻለን ነፍስና ሥጋችን የሚፈልጉት ለየቅል ሆኖብን ነው። “እኛ የሥጋን ሥራ እንሠራለን በሥጋ መንገድም እንሄዳለን አንተ ግን የመንፈስን ሕግ አስረዳን የመንፈስን መንገድ ምራን” እንዳለ ሊቁ በቅዳሴው መንገዳችን ሁሉ የሥጋና የሥጋ ሆኖብን በፍቅር አንድ መሆን ቸግሮናል። አንድ ቤተ ሰብእ እንኳ አንድ መሆን ተስኖት አንዱ መኝታ ቤት አንዱ ሳሎን አንዱ ጎረቤት አንዱ መሸታ ቤት ምርጫው እየሆነ ዓለምን ግራ መጋባት ከቦ ያስጨንቃታል።
ፍቅር ይሏል ከልብ አንድ መሆን ነው። “ፍጹም ፍቅር ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላል” እንዳለ ሐዋርያው የሀገራችን መታመስና መታወክ ምንጩ ፍርሃትን አውጥቶ የሚጥለው ፍቅር በየልቡናችን አለመኖሩ ነው።

ራሄል አልቅሳ ዕንባዋን ወደሰማይ እስክትረጨው ድረስ የእስራኤል ሞትና መከራ እንደቀጠለ ነበር። ራሄል ልጆቿ ልጆች አልሆኗትምና መጽናናት አልተቻላትም። መሪር ዕንባን አነባች ልዑል እምልዑላን የሆነው መንበሩን በሰማይ ዘርግቶ ምድርን የእግሩ መረገጫ ያደረገው በዓለሙ ሁሉ ምሉዕ የሆነው አምላከ አማልክት እግዚአብሔር የራሄልን ዕንባ ተመለከተ ጩኸቷን ሰማ። በአንጻረ ራሄል “የሕዝቤን ጩኸት ሰማሁ” አለ እግዚአብሔር ።

የራሄል መሪር ዕንባ መገለጫ የልጆቿ ሞት ቢሆንም እያሉ በቁም የሞቱ የወገኖቿ መከራ ከልጆቿ ሞት ጋር ሲደመር ከዓውሎ ነፋስ የሚፈጥን በሚመስል መልኩ ዕንባዋ የጸባዖትን ደጅ አንኳኵቶ አስከፈተ።

ባለፉት ጊዜያት ስንት አይነት ሞትና አሟሟት ታየ ከልብ በፍቅር አንድ የሆነ ሕዝብ የሌለን መሆኑን የደረሰብን ግፍና መከራ በአደባባይ መሰከረ። በሩቅ ያሉ የመከራውን አይነት እየዘረዘሩ ሲጽፉና ሲናገሩ የጉዳዩ ባለቤቶች ግን በተለያየ ምክንያት ዝምታን መርጠዋል።

Leave a Reply

Discover more from በመካነ ራማ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ኤላም የትምህርት ማዕከል

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading