ኵሉ ዘይደዊ እምነ አባግዕ የዐሥርዎ ወየዐፅዉ ላዕሌሁ ውስተ ጽልመት ወይሁብዎ ካልአ ሲሳየ ወኢየኀድግዎ ያጼኑ ነፋሰ ጥዑመ ወኢያቀርብዎ ኀበ ምርዓይ ወኢያሰትይዎ እምነቅዕ ዘሀሎ በአፍኣ ወናሁኬ በዝየ ይከውን ካህን ህየንተ ማዕሠር – ከበጎች ወገን የታመመውን በግ ለይተው ከጨለማ አግብተው ያስሩታል ደጅ ይዘጉበታል ደረቅ ሣር ይሰጡታል ነፋስ ካለበት አያሰማሩትም የጠራ ውኃ የለመለመ ሣር አይሰጡትም እንደዚሁ ሁሉ የካህኑ ቃል እንደ ማሠሪያ ነው። ተግሣጽ ዘዮሐንስ አፈወርቅ ፲፯
በግ የታመመ እንደሆነ ለይተው በጨለማ ቦታ ያስሩታል ደረቅ ሣር ይሰጡታል የጠራ ውኃ የለመለመ ሣር አይሰጡትም ነፋስ ካለበት አያስሩትም ከዳነ በኋላ ግን ይህን ሁሉ ያደርጉለታል።
በበግ የተመሰሉ ምእመናን ናቸው። “ወይጼውዖን ለአባግዒሁ በበአስማቲሆን ወያወጽኦን ወያፍሮንን – በጎቹን በየስማቸው ይጠራቸዋል ያወጣቸዋል ያሰማራቸዋል እንዲል ዮሐ ፲፥፫፤
እንደ ደዌ፦ የኃጢአት ደዌ ነው፤ “ዘይሠሪ ለከ ኵሎ ኃጢአተከ ዘይፌውሰከ እምኵሉ ደዌከ – ኃጢአትህን ሁሉ ይቅር የሚልህ ደዌህንም ሁሉ የሚፈውስህ እርሱ ነው” እንዲል መዝ ፻፪፥፫፤
ልዑለ ቃል ኢሳይያስም “ነሥአ ደዌነ ወፆረ ሕማመነ – ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸከመ” ብሏል ኢሳ ፶፫፥፬፤ ማቴ ፰፥፲፯፤
እንደ መለየት፦ ከሰው መለየት ነው፤
እንደ ማሰሪያ፦ ቃለ ካህን ነው፤
እንደ ጨለማ፦ ጽኑዕ ቀኖና ነው፤
እንደ ደረቅ ሣር፦ ጥሬ መብላት ውኃ መጠጣት ነው፤
እንደ ነፋስ፦ ልጅነት ነው፤
እንደ ለምለም ሣር እንደ ጥሩ ውኃ፦ ሥጋ ወደሙ ነው።
ንስሐ ገብተው ወደ አምላካቸው ለተመለሱ ምእመናን ይህ ሁሉ ይደረግላቸዋልና እንዲህ አለ።
አንድ መምህረ ንስሐ በበግ ለተመሰሉ ምእመናን ይህንን ሁሉ አድርጎ ለመንግሥተ እግዚአብሔር የማብቃት መንፈሳዊ ግዴታ አለበት፤ ይሁን እንጂ የበጎቹ ፈቃድና ትብብር ከሌለ ብቻውን ይህን ያደርግ ዘንድ ይከብደዋል።
እንዲህ አድርጎ ከደዌ ኃጢአት እንዲፈወሱ የሚረዳውን መምህረ ንስሐ ምክሩን አለመስማት፣ ትእዛዙን አለመቀበል፣ እንደ ወግ አጥባቂ ወይም ሸክም እንደሚያበዛ አድርጎ ማየት ራስን ይጎዳል።
የሕክምና ባለሙያዎች ሆድን ያህል ውስብስብ አካል አፍርሰው የሚሠሩት ሰውየውን ለመጉዳት አይደለም፤ በሽታውን አስወግደው ጤናውን ለመመለስ ነው። መንፈሳዊው ሐኪምም እንዲሁ ነው።
የታመመ ሰው ሕክምና አልወስድም እንደማይል በኃጢአታዊ ሕመም የሚሰቃይ ሰውም የሚሰጠውን መንፈሳዊ ሕክምና አልወስድም አይልም።
ካህኑ እንደማሠሪያ ነው።


Leave a Reply