ትእምርተ መዊዕ – የማሸነፍ ምልክት

Published by

on

ትእምርት ማለት ምልክት፣ አምሳል፣ አብነት፣ ዐላማ ማለት ነው፤ ተአምር የሚለውም የዚሁ አምሳያ ነው፤ ትእምርት የሚለው ከሚታይ ምልክት ጋር የተያያዘ ሲሆን ተአምር የሚለው አስደናቂ ከሆነ ድርጊት ጋር የተያያዘ ነው።

“ወይከውነክሙ ሕዝቅኤል ትእምርተ ከመ ኵሉ ዘገብረ ትገብሩ – እንዳደረገው ታደርጉ ዘንድ ሕዝቅኤል ምልክት ይሆናችኋል” የሚለው ትንቢታዊ ቃል “ትእምርት” የሚለውን ምልክት ወይም አብነት የሚል ትርጉም ሰጥቶት እናነባለን ሕዝ ፳፬፥፳፬፤

ኢትቅርቡ ኀበ ኵሉ ብእሲ ዘቦቱ ትእምርት – ምልክት ወዳለው ሰው ሁሉ አትቅረቡ የሚለው ደግሞ ምልክት ከመቅሠፍት እንደሚያድን የሚያስረዳ ቃል ነው ሕዝ ፱፥፮፤

ሁለቱን ነጥቦች ያነሣነው በምክንያት ነው፤ አብነት የሚሆን ሰውና ምልክት የሚሆን ዐላማ ያስፈልገናልና። ቅዱስ ኤፍሬም ስለ እመቤታችን ሲናገር “ትእምርተ ዋሕዱ ረሰየኪ አብ – አብ የልጁ ምልክት አደረገሽ” ብሏል። ስትወልደው እናትነቷ ድንግልናዋን እንዳልለወጠው ሁሉ ሰው ሲሆን አምላክነቱ አልተለወጠምና፤ ድንግል ወእም ስትባል እንድትኖር አምላክ ወሰብእ ሲባል ይኖራልና። ይህንንም ነቢዩ ኢሳይያስ አስቀድሞ “ወናሁ እግዚአብሔር እግዚእ ይሁበክሙ ትእምርተ ናሁ ድንግል ትፀንስ ወትወልድ ወልደ ወትሰምዮ ስሞ አማኑኤል – እነሆ ጌታ እግዚአብሔር ምልክት ይሰጣችኋል ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች” ብሎ ገልጦታል ኢሳ ፯፥፲፬፤

አብነት ከሚሆኑን መምህራንን ካህናትን፤ ምልክት ከሚሆኑን አጽዋማትን በዚህ መልእክታችን ውስጥ አብነትና ምልክት አድርገን እንይዛቸዋለን።

ዐቢይ ጾምን ስንጾም አርእስተ ኃጣውእ የሚባሉት ድል መነሣታቸውን በመገንዘብ ነው፤ እነዚህም፦ ስስት፣ ትዕቢትና ፍቅረ ንዋይ ናቸው። የእነዚህ ድል መንሻ ማሣሪያዎችም ትዕግሥት፣ ትሕትናና ጸሊዐ ንዋይ ናቸው።

ሊቀ ነቢያት ሙሴ ወደ ደብረ ሲና እንዲወጣ በታዘዘ ጊዜ ሕዝቡን ሰብስቦ “ወደእናንተ እስክንመለስ ድረስ በዚህ ቆዩን አሮንና ሖር ከእናንተ ጋር ናቸው ነገር ያለበት ቢኖር ወደእነርሱ ይምጣ” ብሏቸው ነበር። ዘጽ ፳፬፥፲፫፤

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ቅድመ ዕርገቱ “በጎቼን አሰማራ ጠቦቶቼን ግልገሎቼን ጠብቅ” ብሎ ለቅዱስ ጴጥሮስ መንፈሳዊ ኃላፊነት ሰጥቶታል ዮሐ ፳፩፥፲፭፤

ከላይ ባነበብናቸው ጥቅሶች መነሻነት መምህራንን ካህናትን አብነት አድርገን መንፈሳዊ ሕይወታችንን በአግባቡ መምራት ይጠበቅብናል። ይህን ስናደርግ የማሸነፍ ምልክት በእጃችን እንዳለን አንዱ ማረጋገጫ መሆኑን እንገነዘባለን። ባለንበት ዘመን አንዱ ፈተናችን መንፈሳዊ አባት የለንም ብሎ የመደምደም ክፉ አመለካከት ነው። የለንም ብለን ከደመደምን ቢኖርም ልንጠቀምበት አንችልም። መንፈሳዊ ሕይወትን ያለ አብነት ለመምራት በእኛ ደረጃ እንቸገራለን። ቅዱስ ያሬድ “ኢኃደጋ ለምድር እምቅድመ ዓለም ወእስከ ለዓለም እንበለ ካህናት ወዲያቆናት – ከጥንት እስከ ዛሬ ምድርን ያለካህናትና ያለዲያቆናት አልተዋትም” ብሎ የዘመረው በየዘመኑ ሰው ስለማይጠፋ ነው።

ሁለተኛው ነጥብ ምልክት የሚለው ነው

ለእመ ፈቀድከ ይፍርሁ ሰይጣናት እምኔከ መንንኬ ፍተወታተ ወይእቲ ፍትወት ወአፍቅሮ ንዋይ ወስብሐት ብጡል – ሰይጣናት ከአንተ የተነሣ ይፈሩ ዘንድ ከወደድህ ሥጋዊ ፈቃድን ናቅ ይህችውም ስስት ናት ተከታዩዋ ደግሞ ፍቅረ ንዋይ ናት እነዚህን የሚያጅባቸው ደግሞ ትዕቢት ነው ተብሎ የተመዘገበው የማሸነፍን ምልክት ይዘን በድል አድራጊነት እንድንመላለስ ነው።

ፈቃደ ሥጋ የሚሠለጥንባቸውን እነዚህን ድል ለማድረግ የምንጠቀምባቸውን መሣሪያዎች ሊቁ ሲያስረዳን “በኅድዓት ወበጾም ወበጸሎት ሞዖ ለሰይጣን – በኅድዓት፣ በጾምና በጸሎት ሰይጣንን ድል አደረገው” በማለት ይዘረዝራል።

ኅድዓት ያለው መረጋጋትን ወይም ትዕግሥትን ነው፤ ጾም ያለው ጸሊዐ ንዋይን ነው፤ ጸሎት ያለው ትሕትናን ስግደትን ነው፤ እነዚህን ገንዘብ አድርጎ የሚጋደል ክርስቲያን እሱ ብቻውን ሳይሆን በእነዚህ መሣሪያዎች እየታገዘ ወደ ድል አደባባይ የሚገሠግሥ ብርቱ አርበኛ ነው።

ወመኑ ውእቱ ዘይመውዖ ለዓለም ዘእንበለ ዘየአምን ከመ ኢየሱስ ውእቱ ወልደ እግዚአብሔር – ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ከሚያምን በቀር ዓለምን የሚያሸንፈው ማነው? ፩ዮሐ ፭፥፭፤

ትእምርተ መዊዕ – የማሸነፍ ምልክት!   በምንም በምን ለሽንፈት የማያጋልጥ የጸና የማሸነፊያ ምልክትና መሣሪያ ይህ ነው። በዚህ ለመኖር አምላከ ቅዱሳን እግዚአብሔር ይርዳን።

ይቆየን!

Leave a Reply

Discover more from በመካነ ራማ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ኤላም የትምህርት ማዕከል

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading