ድጓ ማለት

Published by

on

ድጓ ማለት፦

መስተጋብዕ የሚሰበስብ የሚያሰባስብ ማለት ነው፤ በተለያየ ቦታ ያሉ ሊቃውንትን አሰባስቦ በአንድነት ለምስጋና ያቆማልና።

እስትጉቡዕ የተሰበሰበ ማለት ነው፤ ከተለያዩ መጽሕፍት የተውጣጣ ድርሰት ነውና።

ሠርጒ ማለት ነው፤ የቤተ ክርስቲያን ጌጥ ሽልማት ነውና።   

ድግ ማለት ነው፤ ይህም በወገብ የሚታሠር ለሰውነት ብርታት የሚሆንና ድጋፍ የሚሰጥ ነውና። (የሆድ ካሳ የወገብ ምሳ እንዲሉ)

መጽሔት ማለት ነው፤ የራቀውን አቅርቦ የተበተነውን ሰብስቦ የረቀቀውን አጉልቶ የሚያሳይ ማለት ነው፤ ይህም ሰማያዊውን ምሥጢረ ዜማ በሦስት ስልተ ዜማ አቅርቦ አጉልቶ ያሳያልና። 

ፍኖት ማለት ነው፤ ከመላእክት ከተማ ከምስጋና ማማ ያደርሳልና። 

ደብር ማለት ነው፤ ተራራን ሲወጡት ያጽራል ያግራል ከወጡት በኋላ ግን ሁሉን እያዩ ደስ እንዲሰኙ ያደርጋል ይህም ድጓ ሲማሩት ያጽራል ያግራል ከተማሩት በኋላ ግን በመላእክት ቋንቋ ሲያናግር ምሥጢር ሲያስተረጒም ደስ ያሰኛልና።

ደግ ማለት ነው ድርሰቱ ደገኛ ወይም መልካም ድርሰት ነውና በዚህ የሚያገለግሉትን የሚገለገሉትን ለደገኛ ክብር ያበቃልና።

ድግዱገ ጽሕፈት ማለት ነው፤ ጽሕፈቱ ረቂቅና ብዙ ስለሆነ።

ድጓ ብለው የሠየሙት አባ ጊዮርጊስ መሆናቸውን አንዳንድ ጽሑፎች ይጠቁማሉ፤ ይህ ሐሳብ ከዚያ በፊት ምን ተብሎ ይጠራ ነበር የሚል ጥያቄ ሊያስነሣ ይችላል። ማስመስከሪያ ሆኖ የሚያገለግለው ድጓ መጠሪያ ስሙ መጽሔተ ጥበብ ስለሆነ የቀደመ ስሙ ይህ ሊሆን ይችላል። ሌሎች ለማመሳከሪያ የተመረጡ ድጓዎች ያሉ ሲሆን ስማቸውም ዳንኤል፣ ጌታየ እንግዳ እና ብርሃነ ዓለም ተብለው ይታወቃል።

በፊደልና በቁጥር ሲገለጥ ደግሞ የሚከተለውን ይመስላል፤ ደ አራት ቁጥርን ሲወክል ገ ሦስት ቁጥርን ይወክላል፤ ሲደመር ሰባት ይሆናል ይህም ፍጹምነቱን ያሳያል። ዜማው ከሰማይ የተገኘ ፍጹም ሰማያዊ ነውና።

ለየብቻ ሲሆን ድ አራት ክፍል መሆኑን ይሳያል፤ ይህም ወንጌልን ምሳሌ አድርጎ በአራት ክፍል የተከፈለ መሆኑን ለማስረዳት ነው። ጓ የሚለው ፊደል ምዕራፍን ዝማሬን መዋሥዕትን ያሳያል። አጠቃላይ የቅዱስ ያሬድ ድርሰቶች አምስት ተብለው የሚታወቁ ቢሆንም አሁን በተሰጠው ገለጻ መሠረት ሰባት ይሆናሉ ማለት ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ ከሦስቱ ባሕርያተ ነፍስ የተፈጠረ ሰው እግዚአብሔርን በዜማ አመስግኖ የመንግሥቱ ወራሽ እንዲሆን እግዚአብሔር ባወቀ በሊቁ በቅዱስ ያሬድ በኩል የሰጠን መንፈሳዊ ሀብት ማለት ነው።  

Leave a Reply

Discover more from በመካነ ራማ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ኤላም የትምህርት ማዕከል

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading