አእምር ከመ ማዕከለ መሥገርት ተኀልፍ

Published by

on

አእምር ከመ ማዕከለ መሥገርት ተኀልፍ ወከመ ቀልቀል ታንሶሱ – በወጥመድና በወጥመድ መካከል እንደምታልፍ በገደልና በገደል መካከል እንደምትመላለስ እወቅ ሲራክ ፱፥፲፫

የጥቅሱ ዐቢይ መልእክት ወጥመዱ ይይዘኛል በገደሉም እወድቃለሁ ብለህ እንደምትጠነቀቅ በመንፈሳዊ ሕይወትህም ተጠንቀቀህ ኑር የሚል ነው።

ልዑለ ቃል በመባል የሚታወቀው ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ ይህንን የሚያጠናክር ቃል ሲናገር እንዲህ አለ

“ፍርሃት ወፀድፍ ወመሥገርት ላዕሌሆሙ ለእለ ይነብሩ ውስተ ምድር – በምድር ላይ በሚኖሩ ሰዎች ፍርሃት፣ ገደልና ወጥመድ አለባቸው” ኢሳ ፳፬፥፲፯፤

ትርጓሜያችንም ፎሀ፣ ቴልጌል፣ ስልምናሶርና ናቡከደነጾር የፍርሃት፣ የገደልና የወጥመድ ምሳሌ መሆናቸውን ያመሠጥራል።

ይህንን ንባበ ትንቢት ወደገዳመ ቆርንቶስ ይዘነው ስንሄድ ስስትን ትዕቢትንና ፍቅረ ንዋይን እናይበታለን፤ እነዚህ የፍርሃት፣ የገደልና የወጥመድ ምንጭ ናቸውና።

ለጥንቃቄ ደግሞ የችግሩን አይነትና የሚያመጣውን ጉዳት ለይቶ ማወቅ አስፈላጊ ነው።

ቅዱስ ጳውሎስ “ለቡ ዘእቤለከ የሀብከ እግዚአብሔር ጥበበ በኵሉ – የምነግርህን አስተውል እግዚአብሔር ጥበብን/ማስተዋልን ይስጥህ” ብሎታል ጢሞቴዎስን፤ ፪ጢሞ ፪፥፯

ማስተዋላችን ወይም በጥበብ መኖራችን ከሚገለጥባቸው መንገዶች አንዱ የንስሐ መንገድ ነው።  

“ተዘከር በበይነ ምንት ወደቀ ነስሕ እንከ ወእመ አኮሰ እመጽእ ወአድለቀልቃ ለማኅቶትከ እምነ መካና – በምን ምክንያት እንደወደቅህ አስብ ንስሐ ግባ ካልሆነ ግን እመጣለሁ መብራትህን ከሥሯ እነቅላታለሁ” ተብሏልና ራእ ፪፥፭

ስለንስሐ ስንነጋገር የሚከተሉትን ለዛሬ እናንሣ።

፩ ንስሐ እሳት ነው።

እሳት ላይ ያረፈ ዕጣን ወይም እሳት ያረፈበት ዕጣን መዓዛ አለው፤ ከሩቅ የሚሸትና ደስ የሚል መዓዛ።

ብፁዕ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ “አስተበቊዐክሙ አኀዊነ በሣህሉ ለእግዚአብሔር ረስዩ ነፍስተክሙ መሥዋዕተ ቅዱሰ ለእግዚአብሔር – ወንድሞቻችን ሰውነታችሁን ለእግዚአብሔር የተቀደሰ መሥዋዕት ታደርጉ ዘንድ በእግዚአብሔር ይቅርታ እማልዳችኋለሁ” ይላል ሮሜ ፲፪፥፩

አያይዞ የተቀደሰ የሚለውን ሲገለጽ “ሕያወ ወሥሙረ ወኅሩየ ይኩን ቊርባንክሙ ወቅኔክሙ ነባቢ – ሕያው፣ የተወደደና የተመረጠ ይሁን መገዛታችሁም ተናጋሪ ይሁን” ብሏል።

ይህም እግዚአብሔር አባታችን፣ ቤተ ክርስቲያን እናታችን፣ መንግሥተ ሰማያት ርስታችን እያልን እየመሰከርን እንገዛለንና ነባቢ አለ።

በሌላ ጥቅስም እንዲህ ብሏል “ወተአውቀ በላዕሌነ መዓዛ አእምሮቱ በኵሉ በሐውርት እስመ መዓዛሁ ለክርስቶስ ንሕነ በኀበ እግዚአብሔር በእንተ እለ ይድኅኑ ወእለሂ ይትኀጐሉ – የእውቀቱ መዓዛ በአራቱ ማዕዘን በእኛ ላይ ታወቀ አምነው ለሚጠቀሙ ክደው ለሚጐዱ በእግዚአብሔር ዘንድ የክርስቶስ መዓዛ እኛ ነንና” ፪ቆሮ ፪፥፲፬፤

፪ የተበታተነ ኃይልን አሰባስቦ ለድል መዘጋጀት ነው።

“ወሶበ ሰምዐ አብርሃም ከመ ተፄወወ ሎጥ ኆለቆሙ ለእሊአሁ ወለኵሎሙ ሰብአ ቤቱ ወኮኑ ሠለስቱ ምዕት ዐሠርቱ ወሰመንቱ ወዴገኖሙ ወተለዎሙ እስከ ዳን ወበጽሖሙ ሌሊተ ምስለ ደቂቁ ወቀተሎሙ – አብርሃም ሎጥ እንደተማረከ በሰማ ጊዜ ወገኖቹንና ቤተሰቡን ቈጠራቸው ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት ሆኑ እስከ ዳን ተከተላቸው ከልጆቹ ጋር በሌሊት ደረሰባቸው ወጋቸውም”  ተብሎ እንደተጻፈ ዘፍ ፲፬፥፲፬፤

ሳኦል በአመለካከት ተለያይቶ የነበረውን ሕዝብ በጥበብ አንድ አድርጎ መርቶ ለድል በመብቃቱ “ንዑ ነሐድስ መንግሥቶ ለሳኦል – ኑ የሳኦልን መንግሥት እናድስ ማለት እናጽና” ተብሎለታል ፩ሳሙ ፲፩፥፲፬፤

አንድነት የሌለው ሕዝብና ባለቤት የሌለው ንዋይ/ንብረት ያገኘ ሁሉ እንደፈለገ የሚገለልበትና ተገቢ ክብር የሌለውና ጥንቃቄ የማይደረግለት ነውና። የተገዛና የተውሶ እቃ በእኩል ጥንቃቄና እንክብካቤ እንደማይያዝ ማለት ነው።

፫ በጠላት እጅ ላለመውደቅና መዘበቻ ላለመሆን ብርቱ ትግል/ሰልፍ ነው።

“ሰልፍም በሳኦል ላይ ጠነከረ ቀስተኞችም አገኙት እርሱም ከቀስተኞቹ የተነሣ እጅግ ተጨነቀ ሳኦልም ጋሻ ጃግሬውን እነዚህ ቈላፋን መጥተው እንዳይወጉኝና እንዳይሳለቁብኝ ሰይፍህን መዘህ ውጋኝ አለው ጋሻ ጃግሬው ግን እጅግ ፈርቶ ነበርና እንቢ አለ ሳኦልም ሰይፉን ወስዶ በላዩ ወደቀ” እንዲል ፩ሳሙ ፴፩፥፫፤

ይህ የሳኦል ኅልፈተ ሕይወት በራስ ጨክኖ የመወሰንና ሞትን ሕይወት አድርጎ አርቆ የማየት ጥበብን ያሳያል። የምንጓዝበት የንስሐ መንገድ የሞት ያህል እንኳ የሚያስፈራና የሚመር ቢመስል በጠላታችን  በዲያብሎስ እጅ ወድቀን መሳለቂያ ከምንሆን በሰይፈ ንስሐ ላይ ራሳችንን ጥለን ለሕይወት ብንዘጋጅ ጠላቻን ዲያብሎስን እናሳፍረዋለን። በንስሐ ውስጥ ሆነን የምንሞተው ሞት የሕይወታችንን በር ለማንኳኳትና ለማስከፈት አቅም አለውና።   

 ስለዚህ ይህን ኃይለ ቃል እያስታወስን እራሳችንን ለንስሐ እናዘጋጅ። “አእምር ከመ ማዕከለ መሥገርት ተኀልፍ ወከመ ቀልቀል ታንሶሱ – በወጥመድና በወጥመድ መካከል እንደምታልፍ በገደልና በገደል መካከል እንደምትመላለስ እወቅ” ሲራክ ፱፥፲፫

Leave a Reply

Discover more from በመካነ ራማ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ኤላም የትምህርት ማዕከል

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading