በእንተ ጥምቀት
ወበውእቱ መዋዕል በጽሐ ዮሐንስ መጥምቅ እንዘ ይስብክ በገዳመ ይሁዳ ዘዮርዳኖስ
- ከመ ናዝራዊ ይሰመይ ወልድየ ብሎ ነበርና ናዝሬት በገባበት ወራት፤ ሃያ አምስቱን ዘመን አንድ ወገን አድርጎ ወበውእቱ መዋዕል አለ።
- በዮሐንስ አርባውን ቀን እንደ አንድ ቀን አድርጎ ወአመ ሳኒታ እንዳለ።
- ቦ ወተወሊዶ ብሎ ነበርና ሰው በሆነበት ወራት፤
- ቦ ለዮሐንስ ሠላሳ ሲመላው ለጌታ መንፈቅ ሲቀረው በዚያ ወራት የዮርዳኖስ አውራጃ በምትሆን በይሁዳ ምድረ በዳ ዮሐንስ መጥምቅ እያስተማረ ደረሰ።
በገዳም አለ?
- ቦታው ነውና፤
- ቦ በገዳም እንጨት ሰባሪ ወኃ ቀጂ አይታጣምና፤
- ቦ በገዳም ፆር ይቀላል፤ ለወጣንያን አብነት ለመሆን፤ በገዳም ፆር ይጸናል፤ ለፍጹማን አብነት ለመሆን፤
- ቦ ገዳም የአይሁድ ልቡና ነው፤ በገዳም እህል ተክል እንዳይገኝ በአይሁድ ልቡና ምግባር ሃይማኖት አይገኝምና።
- ቦ ኢሳይያስ ቃለ ዓዋዲ ዘይሰብክ በገዳም ብሎ የተናገረልኝ እኔ ነኝ ሲል።
እንዘ ይብል ነስሑ እስመ ቀርበት መንግሥተ ሰማያት – መንግሥተ ሰማያት በልጅነት፣ ልጅነት በሃይማኖት፣ ሃይማኖት በጥምቀት ልትሰጥ ቀርባለችና ንስሐ ግቡ እመኑ እያለ እያስተማረ ደረሰ።
እስመ ዝንቱ ውእቱ ዘተብህለ በኢሳይያስ ነቢይ እንዘ ይብል ቃለ ዓዋዲ ዘይሰብክ በገዳም – በገዳም የሚያስተምር አዋጅ ነጋሪ ተብሎ በኢሳይያስ ቃል የተነገረለት ይህ ዮሐንስ ነውና።
ቃለ ዓዋዲ፣ አዕዋዴ ቃል ይላል፤ ትምህርቱን ከዚያም ከዚያም የሚያደርስ ማለት ነው፤
የእግዚአብሔርን መንገድ ጥረጉ፤
ጥርጊያውን የቀና አድርጉ፤
ንጉሥ በመጣ ጊዜ ተራራው ኮረብታው ተንዶ ጐድጓዳው ተመልቶ ሥሩ ተነቅሎ ደንጊያው ተለቅሞ ለፈረስ ለሠረገላ እንዲመች ተደልድሎ ይቆያል በዚያ ግስ ተናገረው፤ የእግዚአብሔር ማደሪያ ሰውነታችሁን ከኃጢአት ከጣዖት ንጹሕ አድርጉ።
የዮሐንስ ልብሱ የግመል ጠጉር ነበር፤ ማስተማሩ ነገሥታት ካባ ላንቃ ያልብሱኝ ብሎ ነው የሚል እንዳይኖር፤ መንፈሳዊ እንጂ ሥጋዊ አለመሆኑን ለማስረዳት ነው።
ግመል ምን ጠጉር አላት ቢሉ ከጋማዋ ከጅራቷ ቢፈልጉ ጥቂት አይታጣምና።
ልብሱን ሲል ወንበዴ እንዳይጣላው ብላ እናቱ ያንን ሠርታ አልብሳው ነበርና።
ቦ ግመል በቀለኛ ናት አጥብቆ የመታትን እስከ ስድስት ሰባት ዓመት አትዘነጋም ባጥ ብላ ትረግጠዋለች፤ ስፍራ ሲመቻት ገፍታ ገደል ትጥለዋለች፤ እሱም ወይወድይዎሙ ውስተ እቶነ እሳት ወደ እሳት ይጥሏቸዋል የምትል ሕገ በቀል ወንጌልን አስተምራለሁ ሲል።
ቦ ግመል ሁለት ግብር አላት፤ እንደ ላም እንደ በሬ ምንዛኅ ታወጣለች፤ እንደ ፈረስ እንደ በቅሎ ሰኰናዋ ጽፉቅ ነው፤ እሱም ሕገ አሕዛብ ወሕዝብ ወንጌልን አስተምራለሁ ሲል።
ቦ ገመሎ የሚባል ዕፅ አለ ቆርጠው አድርቀው ከባሕር የጣሉት እንደሆነ ጭረት ይወጣዋል ያንን ታታ አልብሳዋለች፤ ለጊዜው ኑሮው በገዳም ነውና ልብሱን ሲል ወንበዴ እንዳይጣላው ነው፤ ፍጻሜው ግን ለምእመናን አብነት ለመሆን ተርታ ልብስ ለብሳችሁ አልባሌ መስላችሁ ኑሩ ለማለት ነው።
በወገቡ ጠፍር ይታጠቅ ነበር፤ እንዲህ ማድረጉ ነገሥታት የወርቅ ዝናር ያስታጥቁኝ ብሎ ነው የሚል እንዳይኖር ነው፤ መንፈሳዊ ነውና።
የሚታጠቅበት መታጠቂያ ደመ ነፍስ የተለየው እንደሆነ እሱም ከሥጋዊ ግብር ልዩ ነኝ ሲል ነው፤
አስቀድመው ከደመ ነፍስ ይለዩታል፤ ከውኃ ይነክሩታል፤ ጠጉሩን ይመልጡታል ያለፉታል፤ ቀለም ያገቡታል።
ከደመ ነፍስ እንደመለየት መክሮ አስተምሮ ከሥጋዊ ግብር ይለያል፤
ከውኃ እንደመንከር ያጠምቃቸዋል ያስተምራቸዋል፤
እንደ ማልፋት ምግባር ሃይማኖት ያስይዛቸዋል ያሠራቸዋል፤
ቀለም እንደማግባት ጸጋ ክብር ያሰጣቸዋል።
ምሥጢሩ እንስሳዊት ፍትወት በባሕርዩ እያለች በገቢር እንዳላወቃት ያጠይቃል።
ምግቡ አንበጣና የበረሃ ማር ነበር
ቦ አንቦጣ የሚባል ቅጠል ደቁሶ ጨው ነስንሶ ይመገብ ነበር።
ቦ አንበጣን በልሳነ አቴና ቀምሲስ ይለዋል በእኛ ሰበቦት የጋጃ ማር ማለት ነው። መዓረ ገዳም ሲል የማጓ ማር ሲል ነው።
ሁሉም እየሄዱ ኃጢአታቸውን እየተናዘዙ ይጠመቁ ነበር፤
ጥምቀት ከሦስት ወገን ነው፤ መዝገበ ውሉድ ፍቁራን የምትባል የጌታ ጥምቀት፤ ጥምቀተ ዮሐንስ፤ ጥምቀተ አይሁድ፤
ቦ ስምንት ወገን ነው፤ አራቱ ምሳሌ አራቱ አማናዊ፤ አጥመቃ ለምድር በማየ አይኅ፤ ወለኵሎሙ አበዊነ አጥመቆሙ ሙሴ በደመና ወበባሕር፤ ወተጠምቃ እገሪሆሙ ለካህናት፤ ጥምቀተ ዮሐንስ ምሳሌ ነው።
መዝገበ ውሉድ ፍቁራን የምትባል የጌታ ጥምቀት፤ አንብዐ ንስሐ፤ ደመ ሰማዕታት፤ ባሕረ እሳት ናቸው።
ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ብዙዎቹ ወደጥምቀቱ ሲመጡ ባየ ጊዜ እናንተ የእፉኝት ልጆች ከሚመጣው መቅሠፍት ታመልጡ ዘንድ ማን ነገራችሁ ለንስሐ የሚያበቃችሁን መልካም ሥራ ሥሩ አብርሃም አባት አለን በማለት የምታመልጡ አይምሰላችሁ ለአብርሃም ከእነዚህ ድንጋዮች ልጆችን ሊያስነሣለት ይችላል ከዛፉ ሥር ምሳር ተዘጋጅቷልና ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል ወደእሳትም ይጣላል አላቸው።
እነዚህ አካላት ጻድቃን መስለው ኃጢአታቸውን ሰውረው ተርታ ልብስ ለብሰው የኦሪትን ፍርሰት የወንጌልን ሕንጸት እናያለን ብለው የመጡ ናቸው።
አባቶቻቸው ወደው ባወጡት ስም ትውልደ አራዊተ ምድር ብሏቸዋል፤ ወንድማቸው ዮሴፍን ሸጠው ክፉ አውሬ በላው ብለዋልና፤
አራዊተ ምድር ያለው አርዌ ገሞራዊትን ነው፤ አፈ ማኅፀንዋ ጠባብ ነው ዘሩን በአፏ ተቀብላ አባለ ዘሩን ቆርጣ ታስቀረዋለች በፅንስ ጊዜ አባት ይሞታል፤ በሚወለዱበት ጊዜ ልጆቹ የእናታቸውን ሥጋ በልተው ሆዷን ቀደው ይወጣሉ በዚህ ጊዜ እናት ትሞታለች።
እሊህም እንደ አባት የሆኗቸው ነቢያትን እንደ እናት የሆኗቸው ሐዋርያትን ገድለዋልና እንዲህ አለ።
የአብርሃምን ሥራ ሳይሠሩ አብርሃም አባታችን ይሉ ነበርና በልባችሁ አብርሃም አባት አለን በማለታችሁ ከሚመጣው መቅሠፍት የምታመልጡ አይምሰላችሁ ብሏቸዋል።
ሦስት ዋና የመቅሠፍት ጊዜያት አሉ፤ በጥጦስ፣ በሐሳዊ መሲሕና በምጽአት፤ ከነዚህ መቅሠፍታት ማምለጥ የተቻለውና የሚቻለው ንስሐ በመግባትና ወደ እግዚአብሔር በመመለስ ነው።
ከእነዚህ ድንጋዮች ሲል ድንጋይ ያላቸው አሕዛብን ነው፤
- ደንጊያ ያመልካሉና፤
- ድንጊያ ይቡስ ነው ይቡሳነ አእምሮ ናቸውና፤
- ደንጊያ ቈሪር ነው ቈሪራነ አእምሮ ናቸውና፤
- ደንጊያ ክቡድ ነው ክቡዳነ አእምሮ ናቸውና፤
ምሳር የተባለው ንስሐ፣ ትምህርተ ወንጌል፣ ሥልጣነ ክህነት ነው።
እኔ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ ጫማውን እሸከም ዘንድ የማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ከእኔ ይልቅ ይበረታል እርሱ በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም ያጠብቃችኋል መንሹ በእጁ ነው አውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል ስንዴውን በጎተራ ይከታል ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል።
ለጠጅ ብርሌን ለልብስ ገላን አጥበው እንዲያዘጋጁ ለእሱ ጥምቀት በሚያበቃ ጥምቀት አጠምቃችኋለሁ፤
- ለእሱ ተአምኖ ኃጣውእ በሚያበቃ ተአምኖ ኃጣውእ አስተምራችኋለሁ፤
- እርሱ የባሕርይ አምላክ ነው፤
- ባሕርዩን ልመረምር አይቻለኝም፤
- እርሱ ከሚያደርጋቸው መለኮታዊ ተአምራት አንዱን ስንኳ ማድረግ አይቻለኝም፤
- አሣዕነ መርገምን ከምእመናን ለአንዱ አርቅለት ዘንድ አይቻለኝም፤
እሺ ብትሉ በመንፈስ ቅዱስ እሺ ባትሉ ግን በገሃነመ እሳት ያጠምቃችኋል ቦ በመንፈስ ቅዱስ እሳትነት ያጠምቃችኋል።
መንፈስ ቅዱስ በእሳት ለምን ተመሰለ?
- እሳት ምሉዕ ነው፤ መንፈስ ቅዱስም ምሉዕ ነውና።
- እሳት በምልዐት ሳለ ቡላድ ካልመቱ አይገለጽም፤ መንፈስ ቅዱስም ቋንቋ ሲያናግር ምሥጢር ሲያስተረጉም እንጂ አድሮ ሳለ አይታወቅምና።
- እሳት ከቡላዱ ሲወጣ በመጠን ነው፤ ኋላ በእንጨት እያቀጣጠሉ ያሰፉታል፤ መንፈስ ቅዱስም በጥምቀት ሲሰጥ በመጠን ነው ኋላ በሥራ ያሳፉታልና።
- እሳት ጣዕም መዓዛ ያመጣል፤ መንፈስ ቅዱስም ጣዕመ ጸጋን መዓዛ ጸጋን ያመጣልና።
- እሳት በመጠን ቢሞቁት ሕይወት ይሆናል፤ ከመጠኑ አልፎ የሞቁት እንደሆነ ግን ያቃጥላል፤ መንፈስ ቅዱስም በሚገባ በተጻፈው የመረመሩት እንደሆነ ሕይወት ይሆናል፤ በማይገባ ከተጻፈው ወጥቶ የመረመሩት እንደሆነ ግን ይቀሠፋልና።
- እሳት ያቀረቡለትን ሁሉ ያቃጥላል፤ መንፈስ ቅዱስም ሕዝብ አሕዛብ የጸለዩትን ጸሎት ያቀረቡትን መሥዋዕት ይቀበላልና።
- እሳት ውኃ ገደል ካልከለከው ሁሉን ላጥፋ ቢል ይቻለዋል፤ መንፈስ ቅዱስም ቸርነቱ ካልከለከው ሁሉን ላጥፋ ቢል ይቻለዋልና።
- እሳት ዱር ይገልጣል፤ መንፈስ ቅዱስም ምሥጢርን ይገልጣልና።
- እሳት የበላው መሬት ለእህል ለተክል ይመቻል፤ መንፈስ ቅዱስም ያደረበት ሰውነት ለገድል ለትሩፋት ይመቻልና።
- እሳት ከዛኅላቸው ሳይሳተፍ ሰባቱን መዓድናት ያጠራቸዋል፤ መንፈስ ቅዱስም ከግብራቸው ሳይሳተፍ ሁሉን ያነጻልና።
- እሳት ከአንዱ ፋና ሃምሳ ስሳ ፋና ቢያበሩለት ተከፍሎ የለበትም፤ መንፈስ ቅዱስም ተከፍሎ ሳይኖርበት እስከ ምጽአት ሲሰጥ ይኖራልና።
- በእሳት ቀድሞ ሰብአ ሰዶምን ሰብአ ገሞራን ከእስራኤል አንዱን ኅብር አጥፍቶበታል ለመዓት እንጂ ለምሕረት አልተፈጠረም እንዳይሉ ለምሕረትም እንደተፈጠረ ለማጠየቅ።
- ሸክላ ሠሪ ሠርታ ስትጨርስ ነቅ ያገኝበት እንደሆነ እንደገና መልሳ ከስክሳ በውኃ ለውሳ በእሳት ታድሰዋለች፤ ከብልየት መታደስ በመንፈስ ቅዱስ ነውና።
መንሽ ሦስት ጣት አለው፤ የሦስትነት ምሳሌ፤ መያዣው የአንድነት ምሳሌ፤
- ጻድቃንን ከኃጥአን የሚለይበት ሥልጣን ገንዘቡ ነው፤
- በጎ ሕሊናን ከክፉ ሕሊና የሚለይበት ሥልጣን ገንዘቡ ነው፤
“ያን ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ ሊጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ ዮሐንስ ግን እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል አንተ ወደእኔ ትመጣለህን ብሎ አይሆንም አለው፤ ጌታችን ኢየሱስም መልሶ አንድ ጊዜ ተው ይህ ለእኛ ደስታችን ነውና ጽድቅን ልንፈጽም ይገባናል አለው”
ለጌታ ሠላሳ ሲመላው ለዮሐንስ መንፈቅ ሲያልፈው ያን ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ ይጠመቅ ዘንድ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ።
ባሪያ ወደ ጌታው ይሄዳል እንጂ ጌታ ወደ ባሪያው ይሄዳልን? ባሪያ በጌታው እጅ ይጠመቃል እንጂ ጌታ በባሪያው እጅ ይጠመቃልን ቢሉ ጌታ የመጣው ለትሕትና ነውና፤ ቦ ለአብነት ነው።
ጌታችን ዮሐንስን መጥተህ አጥምቀኝ ብሎት ቢሆን ኖሮ ዛሬም ነገሥታት መኳንንት መጥታችሁ አጥምቁን ባሉ ነበርና ሂዳችሁ ተጠመቁ ለማለት አብነት ለመሆን ነው።
“ይህ ደስታችን” ሲል
- ራሱን ከምእመናን አግብቶ ነው፤ እናንተም ስትጠመቁ መንፈስ ቅዱስ ይወርድላችኋል ለማለት፤
- ራሱን ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አንድ አድርጎ ተናግሮታል፤ አብ ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ብሎ ሲመሰክር መንፈስ ቅዱስ በአምሳለ ርግብ ወርዶ ከራሱ ላይ ሲቀመጥ አንድነት ሦስትነት ይገለጣልና።
- ጽድቅን ልንፈጽም ይገባናል ሲልም፦ በማኅፀን የተጀመረው ቸርነት ሊፈጸም ይገባል ሲል ነው።
ጥምቀቱን በዮርዳኖስ ያደረገው ስለምን ነው ቢሉ? ትንቢቱ ምሳሌው ይፈጸም ዘንድ ነው።
ትንቢት፦
ባሕርኒ ርእየት ወጐየት ወዮርዳኖስኒ ገብአ ድኅሬሁ ርእዩከ ማያት ወፈርሁ ተብሎ ተነግሯል።
ምሳሌ፦
ዮርዳኖስ ከላይ ነቁ አንድ ነው ዝቅ ብሎ በደሴት ይከፈላል ከታች ወርዶ ይገናኛል።
ከላይ ነቁ አንድ እንደሆነ ሁሉ የሰው ሁሉ ነቁ አንድ አዳም ነው።
ዝቅ ብሎ በደሴት እንዲከፈል እስራኤል በግዝረት አሕዛብ በቊልፈት ተለያይተዋል።
ከታች ወርዶ በወደብ እንዲገናኝ ሕዝብና አሕዛብ በክርስቶስ በጥምቀት አንድ ሆነዋልና።
ቦ አብርሃም ለአምስቱ ነገሥተ ሰዶም ረድቶ አራቱን ነገሥተ ኮሎዶጎሞር ድል ነሥቶ ሲመለስ ደስ ቢለው በመዋዕልየኑ ትፌኑ ቃለከ ወሚመ ታርእየኒሁ ኪያሃ ዕለተ አው አልቦ አለ፤ እሱን አታየውም ምሳሌውን ታያለህ ዮርዳኖስን ተሻግረህ ሂድ አለው ዮርዳኖስን ተሻግሮ መልከ ጼዴቅን አግኝቶ ኅብስተ በረከት ጽዋዐ አኰቴት ይዞ ተቀብሎታል፤ ዮርዳኖስ የጥምቀት፣ አብርሃም የምእመናን፣ መልከ ጼዴቅ የቀሳውስት፣ ኅብስተ በረከት ጽዋዐ አኰቴት የሥጋ ወደሙ።
ቦ ኢዮብ በዮርዳኖስ ተጠምቆ ከደዌው ድኗል፤ ኢዮብ የአዳም፣ ከነሕፃናቱ፣ ደዌ የመርገመ ሥጋ የመርገመ ነፍስ፣ ዮርዳኖስ የጥምቀት ምሳሌ።
ቦ እስራኤል ዮርዳኖስን ተሻግረው ምድረ ርስት ገብተዋል ምእመናንም ተጠምቀው ገነት መንግሥተ ሰማያት ገብተዋልና።
ኤልያስ ዮርዳኖስ ተሻግሮ ገነት ገብቷል ምእመናንም አምነው ተጠምቀው ገነት መንግሥተ ሰማያት ለመግባታቸው ምሳሌ፤
የኤልሳዕ ደቀ መዛሙርት ጸበበነ ማኅደር ንዑ ንግዝም ዕፀ ወንሕንጽ ካልአ ማኅደረ ብለው ሄዱ እሱም መምህረ ትሕትና ነውና አብሯቸው ሄደ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ ሲቆርጥ ምሳሩ ከዛቢያው ወልቆ ከባሕር ገባበት ዝኒ ኅቡይ እግዚእየ ጌታዬ ጥንቱን የተውሶ ያውም ጠፋ ተጨርሶ አለው የገባበትን አሳየኝ አለው አሳየው ቅርፍተ ዕፅ ቀርፎ አመሳቅሎ ቢመታው መዝቀጥ የማይቻለው ቅርፍተ ዕፅ ዘቅጦ መዝቀጥ የሚገባውን ብረት ይዞት ወጥቷል።
እንደዚሁም ሞት የማይገባው መለኮት ሞቶ ሞት የሚገባውን አዳምን ለማዳኑ ምሳሌ።
ጥምቀቱንም ሽቶ አላደረገውም በመጠመቁም ጸጋ ያገኘበት አይደለም።
ለምን በዮርዳኖስ ተጠመቀ ቢሉ ዮርዳኖስን ብርህት ማኅፀን ለማድረግ፤ ለጥምቀት ኃይልን ለመስጠት ነው።
- ዮርዳኖስ በበጋ የማይጎድል በክረምት የማይተርፍ ማዕከላዊ ውኃ ነው፤
የጌታም ጥምቀቱ እኛን ከመጥቀም በላይ እሱን ከመጥቀም በታች ነውና።
- ዮርዳኖስ በባሕረ ጥብርያዶስ ላይ የሚሄድ ነው ዐባይ በጣና ላይ እንዲሄድ፤
የጌታም ጥምቀት ከእኛ ጥምቀት በላይ ነውና።
- ብዙ ንዑሳን አንቅዕት ይገቡበታል እሱ ያበረታቸዋል እንጂ እነሱ አያበረቱትም የጌታም ጥምቀት ለእኛ ጥምቀት ኃይል ጽንዕ ይሆናል እንጂ የእኛ ጥምቀት ለጌታ ጥምቀት ኃይል ጽንዕ አይሆንምና።
- ንዕማን በዮርዳኖስ ተጠምቆ ከደዌው ተፈውሷል ንዕማን የአዳም ከነሕፃናቱ፣ ደዌ የመርገመ ሥጋ የመርገመ ነፍስ፣ ዮርዳኖስ የጥምቀት፤
ምሥጢሩ እንደምን ነው ቢሉ?
ዲያብሎስ የጨለማ መጋረጃ ጋርዶ በአዳምና በሔዋን ሥቃይ አጸናባቸው ስመ ግብርናታችሁን ጽፋችሁ ብትሰጡኝ ባቀለልሁላችሁ ነበር አላቸው አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ ሔዋን አመቱ ለዲያብሎስ ብለው ጽፈው ሰጡት መጻፍስ የለም ብሎ ይሁንብን ማለታቸውን መናገር ነው፤
በሁለት ዕብነ ሩካም ጽፎ አንዱን በዮርዳኖስ አንዱን በሲኦል ጥሎታል በዮርዳኖስ የጣለውን ሲጠመቅ እንደሰውነቱ ተረግጦ እንደ አምላክነቱ አቅልጦ አጥፍቶልናል፤
በሲኦል የጣለውን በዕለተ ዓርብ በአካለ ነፍስ ሲኦል ወርዶ ነፍሳትን ሲያወጣ አጥፍቶልን ወጥቷል።
“ጌታችን ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኃው ወጣ እነሆ ሰማያት ተከፈቱ የእግዚአብሔር መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱም ላይ ሲመጣ አየ እነሆም ድምፅ ከሰማያት መጥቶ በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ”
ጥምቀቱን በውኃ ያደረገው ስለምን ነው ቢሉ?
ትንቢቱ ምሳሌው ይፈጸም ዘንድ ነው።
ትንቢት፦
እነዝኃክሙ በማይ ንጹሕ ከመ ትንጽሑ እምርኵስክሙ ተብሎ ተነግሯል
ምሳሌ፦
ለታውጽእ ባሕር ዘቦ መንፈሰ ሕይወት ወዘይትሐወስ ውስቴታ ባለ ጊዜ በልብ የሚሳቡ በእግር የሚሽከረከሩ በክንፍ የሚበሩ በደመ ነፍስ ሕያዋን ሆነው የሚኖሩ ፍጥረታት ተገኝተዋል፤ ከዚያው የቀሩ አሉ በረው በረው የሄዱ አሉ፤ ከዚያው የቀሩ የጥሙቃን በረው የሄዱ የኢጥሙቃን ምሳሌ፤ ይህስ እንዳይሆን ወባረኮሙ ለክልኤሆሙ በአሐቲ በረከት ይላል ብሎ ሁሉም የጥሙቃን ምሳሌ፤
በልብ የሚሳቡ የሰብአ ዓለም፤ በእግር የሚሽከረከሩ ከትሩፋት ወደትሩፋት የሚሉ የባሕታውያን ምሳሌ፤ በክንፍ የሚበሩ የጻድቃን የሰማዕታት ምሳሌ፤ ጻድቃን ሰማዕታት ተመስጦ አላቸውና።
ምሥጢሩ እንደምን ነው ቢሉ?
- ውኃ በዙፋን ካለ ንጉሥ በአደባባይ እስካለ ጽኑስ ለሁሉም ርኩብ ነው፤ ጥምቀትም የተሠራው ለሁሉ ነውና።
- ውኃ ጽንፍ እስከ ጽንፍ ይፈሳል፤ ጥምቀትም ጽንፍ እስከ ጽንፍ ይደረጋልና።
- ውኃ ያነጻል፤ ጥምቀትም ያነጻልና።
- ውኃ ለወሰደው ፍለጋ የለውም፤ በጥምቀት የተሠረየ ኃጢአትም በፍዳ አይመረመርምና።
- ውኃ መልክ ያሳያል፤ መልክ ያለመልማል ጥምቀትም መልክአ ነፍስ ያሳያል፤ መልክአ ነፍስ ያለመልማልና።
- በውኃ የታጠበ ልብስ ኃይል ጽንዕ ግዘፍ እየነሣ ይሄዳል፤ ምእመናንም ተጠምቀው ገድል ትሩፋት እያከሉ ይሄዳሉና።
- ሥጋዊ ተፍኅሮ የነርብቃ የነሲፓራ በውኃ ምክንያት ሆኗል፤ መንፈሳዊ ተፍኅሮንም በውኃ ለማድረግ፤
- ሸክላ ሠሪ ሠርታ ስትጨርስ የቃባት እንደሆነ ከስክሳ በውኃ ለውሳ ታድሰዋለች፤ ጥምቀትም አዲስ ያደርጋልና።
- ቀድሞ ሰብአ ትካትን ኋላ ግብጻውያንን በውኃ አጥፍቷል ለመዓት እንጂ ለምሕረት አልተፈጠረም እንዳይሉ ለምሕረት እንደተፈጠረ ለማጠየቅ።
የወዲያኛው ቀስቱን እያጋለ መርዝ እየቀባ እያተባ ይመጣል፤ የወዲህኛውም እግዚአብሔር ጥበቡን ገልጦለት ጀባውን ከውኃ ነክሮ ለጋሻው አልብሶ ይሄዳል፤ መርዙን ጀባው ይጠርግለታል ግለቱን ውኃው ያቀዘቅዝለታል፤ ስለቱን ጋሻው ይመልስለታል፤ እንደዚሁም ሁሉ ምእመናን በጥምቀት ባገኙት ኃይል ድል ይነሣሉና።


Leave a Reply