– ሰይጣን ያቆሰለህን ቊስል አሳይ ማለት ሰይጣን ያሠራህን ኃጢአት ለመምህረ ንስሐህ ንገር ብትሸሽገው ግን ቊስልህ ይመግላል ይሸታል።
እስመ ኢይትፌሣህ በእንተ ምንትኒ ከመ ዘየኀብኡ ኅሊናቲሆሙ እምአበዊሆሙ ወኢይሬእይዋ ሎሙ – ያሰቡትን ከአባቶቻቸው እንደመሠወራቸውና ገልጠው እንዳለመናገራቸው ሰይጣንን ሌላ ደስ የሚያሰኘው የለምና።
ፊልክስዩስ ተስእሎ ፻፸
ራስን ለካህን ማሳየት መቻል የመንፈሳዊ ጥብዓትና ጥበብ ውጤት ነው። ጥብዓት ማለት መጨከን ወይም አንድን ነገር ያለመሰቀቅ ለማድረግና የሚመጣውን ሁሉ በጸጋ ለመቀበል መወሰን ማለት ነው።
ተደብቀን የሠራነውን ኃጢአት ካህኑን ታዛቢ አድርገን ራሳችንን በእግዚአብሔር ፊት እናካስሳለን። ነቢዩ “ራሴን ስለኃጢአቴ በእግዚአብሔር ፊት አካስሳለሁ” እንዳለ።
ኃጢአት ሠርቶ ለመደበቅ መሞከር ወይም በምክንያት ወደኋላ ለመሸሽ መሞከር ቊስልን ከሐኪም እንደመደበቅ ነው። ሕክምና ካላገኘ ቊስሉ ያመረቅዛል ስር ይሰዳል ይሰፋል። በዚሁ ከቀጠለም ለኅልፈተ ሕይወት ሊዳርግ ይችላል።
ኃጢአትም በመንፈሳዊ ሕክምና ካልተወገደ ለሞተ ነፍስ ይዳርጋል። “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነው” እንዳለ ሐዋርያው።
ሰይጣን ኃጢአት እንድንሠራ የሚያበረታታንና የሚገፋፋንን ያህል ከመምህረ ንስሐችን ጋር ስለበደላችን እንዳንወያይና ራሳችንን በንስሐ ሕይወት እንዳንመራ በማዝገየት የበቀል በትሩን ያሳርፍብናል።
ሊቁ እንደነገረን በኃጢአታችን አፍረን ወይም ፈርተን ወደኋላ በሸሸንና ምንም እንዳላጠፋ ሰው በድፍረት በተመላልስን መጠን የሰይጣን የደስታ መጠንም ይጨምራል። ምክንያቱ ደግሞ ቢያንስ በሁለቱ ነጥቦች ሊገለጥ ይችላል።
፩ ባለፈው ስሕተታችን የአጥፊነት ስሜት ስላልተሰማን ተደጋጋሚ የኃጢአት ሥራ ለመሥራት ራሳችንን እናዘጋጃለን።
፪ ከመንፈሳዊ ነገሮች መራቅን ምርጫችን ወደማደረግ እንመጣለን። ይህ ደግሞ እንደጠፋን እንድንቀርና ምንም የመመለስ እድል እንዳይኖረን ሊያደርግ ይችላል።
ስለዚህ ሰይጣን ቊስላችንን በደበቅን ቁጥር የበለጠ እንድንቈስል ምቹ ጊዜ እያገኘ ስለሆነ ደስታው ይጨምራል።
አሁን ይህን መልእክት የሚያነቡ አንባቢ ሆይ የቈሰሉት ቊስል ካለ እባክዎ ከመምህረ ንስሐዎ ጋር ለመነጋገር አይዘግዩ። በዘገዩ መጠን የቊስሉ መጠንና ክፉ ሽታው እየጨመረ ይሄዳልና።
ሕፃን ልጅ ከሚወደዱለት ጠባይዓት አንዱ ጉዳት የደረሰበትን አካሉ ለእናቱ ማሳየት መቻሉ ነው። በቃል መግለጥ ባይችል እንኳ በምልክት ሊያሳይ ይጥራል።
ስለሆነም ሰይጣን ያቈሰለንን የኃጢአት ቊስል ከመደበቅ ይልቅ “ራስህን ለካህን አሳይ” በሚለው መሪ የወንጌል ቃል መሠረት ራሳችንን ለካህናት አባቶቻችን እያሳየን ከቊስለ ኃጢአት እንፈወስ።
“ወፈውሰኒ እስመ ተሀውካ አዕፅምትየ – አጥንቶቼ ታውከዋልና እባክህ ፈውሰኛ”



Leave a Reply