ትእምርተ ንስሐ – የንስሐ ምልክት

Published by

on

ትእምርተ ንስሐ – የንስሐ ምልክት 

አንድ ተነሳሒ ንስሐ ለመግባት ዝግጅት ማድረጉ የሚታወቅበትንና በንስሐ ሕይወት ውስጥ መኖሩን የሚያሳዩ ከሚባሉት መሠረታዊ ነጥቦች የሚከተሉትን እናያለን 

መግቢያ ጥቅስ፦ 

መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ስለ ንስሐና ተነሳሕያን ባስተማረበት አንቀጽ እንዲህ አለ “ለንስሐ የሚያበቃችሁን በጎ ሥራ ሥሩ” ማቴ 3፡8፤ 

በጎ ሥራ ብለን የምንረዳውም ሊያድነን ከሰማያት በወረደውና ከድንግል ማርያም በተወለው ማመንን ነው። “የእግዚአብሔር ሥራ እስሩ በላከው እንድታምኑ ነው” እንዲል ዮሐ 6፡29፤ 

የትምህርቱ ጭብጥ መልእክትና ማገናዘቢያ ጥቅስ፦ 

የሰማነውን በመናገርና ባልሆነ ተስፋ ውስጥ መኖር ብቻ በራሱ የንስሐ ሕይወት ወይም የተነሳሒ ምእመን መለያ ምልክት አይደለም። የሚከተሉት ጥቅሶች ይህንን ያስረዳሉ። 

“አብርሃም አባት አለን በማለት የምታመልጡ አይምሰላችሁ” ማቴ 3፡9፤ 

“እናንተ በአባታችሁ ያያችሁትን ታደርጋላችሁ አላቸው እነርሱም መልሰው የእኛ አባታችን አብርሃም ነው አሉት ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አላቸው የአብርሃም ልጆች ብትሆኑስ የአብርሃምን ሥራ በሠራችሁ ነበር” ዮሐ 8፡38፤ 

ከዚህ ቀጥለን ለንስሐ ምልክት የሚሆኑ ሦስት ነጥቦችን በቅደም ተከተል እናያለን

1 ኃጢአትን መናዘዝ 

ይህም ኃጢአትን ለራስ ሕሊና ከመንገር ይጀምራል፤ ውስጣችን ያላመነበትን ነገር መናገር ከተውኔት የተለየ ስለማይሆን የምንናገረው የምናምንበትን መሆን አለበት። “አመንኩ በዘነበብኩ – በተናገርሁት አመንሁ” እንዲል መዝ 115፡1፤  

“ስለ ኃጢአቴ ወደ እግዚአብሔር ራሴን እከሳለሁ አንተም የልቤን ሽንገላ ተውልኝ” እንዲል መዝ 31፡5፤

“በራሳችን ብንፈርድ ባልተፈረደብን ነበር” 1ቆሮ 11፡31፤ 

ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት አጽንዖት በመስጠት እንዲህ ይላል። 

እስመ ለልየ አአምር ጌጋየ ወኃጢአትየኒ ቅድሜየ ውእቱ በኵሉ ጊዜ ለከ ለባሕቲትከ አበስኩ ወእኩየኒ በቅድሜከ ገበርኩ – እኔ በደሌን አውቃለሁ ኃጢአቴም ሁልጊዜ በፊቴ ነውና አንተን ብቻ በደልኩ በፊትህ ክፋትን አደረግሁ መዝ 50፡3

ይህንን ማድረግ ስንችል ከካህኑ ፊት ቆመን በደላችንን ስንናዘዝ መንፈሳዊ ድፍረት ይኖረናል

“ኢያሱም አካንን ልጄ ሆይ፥ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ክብር ስጥ፥ ለእርሱም ተናዘዝ፤ ያደረግኸውንም ንገረኝ፤ አትሸሽገኝ አለው አካንም መልሶ ኢያሱን በእውነት የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን በድያለሁ እንዲህና እንዲህም አድርጌአለሁ በዘረፋ መካከል አንድ ያማረ የሰናዖር ካባ፥ ሁለት መቶም ሰቅል ብር፥ ሚዛኑም አምሳ ሰቅል የሆነ ወርቅ አይቼ ተመኘኋቸው፥ ወሰድኋቸውም፤ እነሆም፥ በድንኳኔ ውስጥ በመሬት ተሸሽገዋል፥ ብሩም ከሁሉ በታች ነው አለው” ኢያ 7፡19 

2 ከበደሉት ሰው እርቅ ማድረግ 

“መባህን በመሠዊያው በምታቀርብበት ጊዜ በዚያም ሳለህ የታጣላህ እንዳለ ብታስብ መባህን ከዚያ በመሠዊያው ፊት ትተህ ሂድና አስቀድመህ ከወንድምህ ጋር ታረቅ ከዚህ በኋላ ተመልሰህ መባህን አቅርብ” ማቴ 5፡23፤ 

3 የበደሉትን መካስ 

“የበደልሁትም ቢኖር ስለ አንድ ፈንታ አራት እጥፍ እከፍለዋለሁ ጌታችን ኢየሱስም እንዲህ አለው ዛሬ ለዚህ ቤት ሕይወት ሆነ እርሱ የአብርሃም ልጅ ነውና የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቷልና” ሉቃ 19፡8 

ቅዱስ ጳውሎስ አናሲሞስን በተመለከተ ለፊልሞና ሲጽፍ እንዲህ አለ “የበደለህ በደል ቢኖር ወይም የሚከፍልህ ዕዳ ቢኖር በእኔ ላይ ቊጠረው እኔ ጳውሎስ ስለ እርሱ እከፍላለሁ ብዬ በእጄ ጽፌአለሁ” ፊል 1፡18፤ 

ይቆየን 

Leave a Reply

Discover more from በመካነ ራማ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ኤላም የትምህርት ማዕከል

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading